>
5:21 pm - Monday July 20, 8809

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የክፍፍል እና የውህደት ጉዞ

ቢቢሲ አማርኛ

በመጀመሪያ በቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ፣ ከእርሳቸው ኅልፈተ ህይወት በኋላ ደግሞ በብፁዕ አቡነ ማቲያስ በሚመራው እና መቀመጫውን አገር ውስጥ ባደረገው ሲኖዶስ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስም ፓትርያርኩ አድርጎ በሚቆጥረውና ሰርክ ‘ስደተኛው’ እየተባለ በሚጠራው ሲኖዶስ መካከል ሰላም አውርዶ እርቅ ለመፍጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎች መደረጋቸው ባይቀርም እስካሁን ድረስ ስኬት ሲናፍቃቸው ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አንዲት ቤተ ክርስትያንን እና አማኞቿን እንወክላለን የሚሉትን ሁለቱን የእምነት አስተዳዳር መዋቅሮች ዓይን ለዓይን ከመተያየት ሲከለክል የቆየው ቁርሾ ተወግዶ ወደአንድነት እንዲመጡ ፍላጎታቸውን ከገለፁ በኋላ የተጀመረው እንቅስቃሴ ግን ፍሬ የያዘለት ይመስላል።

ከትናንት አመሻሹ አንስቶ ሲኖዶሶች እርቀ ሰላም ይዘገብ ይዟል። ውህደቱ ምን ፋይዳ እና ትርጉም አለው? ቀጣይ እርምጃዎችስ ምን ይሆናሉ ስንል የእምነቱን ሊቃውንት አነጋገረናል።

የቤተ ክርስትያኗ አመራር እንዴት ለሁለት ተከፈለ?

በ1983 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የደርግን ስርዓት ጥሎ ስልጣን ላይ ሲወጣ፣በአራተኛው ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ደስተኛ እንዳልነበር በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ማኅበረ ካህናት ሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ ይናገራሉ።

“በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ ልዩነት መፈጠር የተጀመረው ብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ተደርጎ ብፅዕ አቡነ ጳውሎስ በስፍራቸው እንዲተኩ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ነው፤” ይላሉ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

ቀሲስ ኤፍሬም እንደሚሉት አዲሱ መንግሥት የፖለቲካ ጉልበቱን በመጠቀም ፓትርያርኩ ከመንበራቸው እንዲነሱ በጉምቱ ባለስልጣናቱ ሳይቀር ጥረት አድርጓል።

በዚህ አስተያየታቸው የሚስማሙት የቀድሞው የማኅበረ ቅዱሳን አመራር ዲያቆን ዳንዔል ክብረት ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት በወቅቱ ብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስ መንግስታዊውን ጫና መቋቋም ካለመቻላቸውም ባሻገር፤ አንዳንድ የኃይማኖት አባቶች የእርሳቸው መንበራቸውን መልቀቅ ብቸኛው መፍትሄ ነው ማመናቸው አልቀረም።

የፓትርያሪኩን ከአገር መውጣት ተከትሎም ሌላ ምርጫ ተካሄደና ሌላ ፓትርያሪክ ተሾመ፤ አንዳንድ ጳጳሳት ስደተኛውን ፓትርያሪክ መከተልን መረጡ፤ ከጥቂት ዓመታት በኋላም በአገረ አሜሪካ ሌላ ሲኖዶስ መሰረቱ፤ ሌሎቹ ደግሞ አገር ውስጥ በነበረው ሲኖዶስ ለመቀጠል ወሰኑ።

“ከዚህም የተነሳ ቤተ ክርስትያኒቷ በሁለት ሲኖዶስ፣ በሁለት ፓትርያሪክ የምትመራ ሆነች” ይላሉ ዲያቆን ዳንዔል።

ለእርሳቸው ይህ ሂደት ሁለት የቤተ ክርስትያኒቷን አስተምህሮዎች የጣሰ ነው እንደሆነ ዲያቆን ዳንኤል ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው አባባልም በመጀመሪያ “አንድ አባት ልጆቹን ትቶ መሄድ ተገቢ አይደለም፤” በመቀጠል “እኝህ አባት ከአገር ቢወጡም እርሳቸውን እና ሌሎቹን ከስደት ለመመለስ ጥረት መድረግ ሲገባው ሌላ አባት ተሾመ። ከበፊትም የሚመዘዝ ችግር ቢኖርም ይህንን ችግር በትዕግስት እና በብልሃት ማለፍ ቢቻል ኖሮ ይ. ነገር አይፈጠርም ነበር። የቤተክርስያኒቱ ስርዓት አንድ አባት በህይወት እያለ ሌላ አባት መሾም አይፈቅድምና።”

ክፍፍሉ ምን ዳፋ አስከተለ?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን አሁንም ትልቋ የአገሪቱ የእምነት ተቋም ትሁን እንጅ የአማኞቿ ቁጥር ከአጠቃላዩ ምዕመን ያለው የመቶኛ ድርሻ እያሽቆለቆለ ነው የሚገኘው።

ለመጨረሻ ጊዜ በ1999 ዓ.ም በተደረገው የህዝብና ቤት ቆጠራ መሰረት ከአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ ከአርባ ሦስት በመቶ ከፍ የሚለው የእምነቱ ተከታይ ሲሆን፤ ቤተ ክርስትያኗ በ1977 ዓ.ም ቆጠራ ወቅት ከነበራት አገር አቀፍ የምዕመናን ድርሻ ግን ሃምሳ አራት በመቶ ገደማ ነበር።

ዲያቆን ዳንዔል ለዚህ አብዩ ተጠያቂ “የቤተ ክህነቱ መዳከም ነው” ይላሉ።

“ቤተ ክህነቱ ቤተ ክርስትያንዋን መሸከም ከሚችልበት አቅም በታች ነው። አሁን ላለው ቤተ ክህነት፣ አሁን ላለችው ኢትዮጵያ እና አሁን ላለው ትውልድ የሚመጥን አይደለም። ሁለቱም ቦታ፤ አሜሪካም ያለው እዚህም ያለው። ለዚህ የሚመጥን አቅም የለውም” ሲል ያብራራል።

ለቤተ ክህነቱ መዳከም ደግሞ የሲኖዶስ፣ የኃይማኖት መሪዎችን እና የአማኞችን መከፋፈል ተወቃሽ ያደርጋሉ።

ቤት ክህነቶች ዋና ተግባራቸውን “ውጊያ” ላይ በማድረጋቸው ምክንያት ተቀዳሚ ሥራቸው ሊሆን ይገባው የነበረው “ወንጌልን የማዳረስ ስራ፣ የሐዋርያዊነትን ስራና ምዕመናንን የመጠበቅን ስራ ተረስቷል” ይላሉ።

ቀሲስ ኤፍሬም በበኩላቸው የሁለት የተኮራርፉ አስተዳደሮች መኖር፣አንድ እምነት እና አንድ ስርዓት ያላቸው ምዕመናን እና ካህናት ለመራራቃቸው ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር ይህም በፋንታው በርካታ ችግሮችን ወልዷል ይላሉ።

“ቤተ ክርስትያኗ በአጠቃላይ አሁን ላለባት ድክመት፣ ለምዕመናኗ ቁጥር መቀነስ፣ ለአስተዳደሯ መበላሸት፣ ሙስና እና ዝርፊያ [በጓዳዋ] ለመሰልጠናቸው፣ ሙያው እና ስነ ምግባሩ የሌላቸው ሰዎች በልዩ ልዩ መዋቅሮች ለመሰግሰጋቸው ሁሉ በር የከፈተው ይህ በአባቶች መካከል ያለው ልዩነት ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእምነት ልዑካን ጋርImage copyrightFITSUM AREGA TWITTER

አሁንስ ከቤተ እምነት ላይ የቤተ መንግሥት ጥላ ተገፏል?

ሲኖዶሶቹ አንዳቸው ሌላኛቸውን የእምነቱን ህግ እንደጣሱ ወይንም ኃይማኖታዊ ቅቡልነት እንደሌላቸው ያዩዋቸው የነበረ ለመሆኑ አንደኛው መገለጫ እርስ በራሳቸው መወጋገዛቸው ነው።

አሁን ይካሄድ በያዘው ሽምግልና ላይ በጋራ ሲፀልዩ መስተዋላቸው ይሄንን ውግዘት በይፋዊ ባይሆን በተግባር ቀድመው ለማንሳታቸው ምስክር ነው የሚሉት ቀሲስ ኤፍሬም ናቸው።

እርስ በእርስ የሚተያዩባቸው መንገዶች ምናልባትም በተደጋጋሚ የተደረጉትን የእርቅ ሙከራዎች የማክሰም ድርሻ ቢኖራቸውም፤ የአገሪቱ ፖለቲካዊ መልክ ጉልህ ሚና እንደነበረው ግን ሁለቱም ይስማማሉ።

የአሁኑ እርቀ ሰላም ስኬትንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደር አቋም ጋር የሚያያይዙት ብዙ ናቸው።

ቀሲስ ኤፍሬም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን በሌሎች የዓለም ክፍሎች ካሉ የክርስትና እምነቶች በተለየ መንግስታዊ ትስስር ከምስረታዋ አንስቶ እንዳላት ያስረዳሉ።

“በሌሎች አገራት በአብዛኛው እምነቱ በህዝቡ ዘንድ ከሰረፀ በኋላ መንግስታት እንደተቀበሉት ታሪክ የሚያስረዳ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ግን የሆነው በተቃራኒው መንግስት እምነቱን ተቀብሎ ነው ከዚያ ወደሕዝቡ ያሰረፀው። ስለዚህም ከዚያ የሚመዘዝ መንግስታዊ ቁርኝት አለ” ይላሉ።

በየዘመኑ የመጡ መንግስታት ቤተ ክርስትያኒቷን ዓላማቸውን ለማስፈፀሚያ ተጠቅመውባታል የሚሉት ቀሲስ እሸቴ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር መንግስት እና እምነትን ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚለያይ እርምጃ እንደሚወስድ ተስፋቸውን ይገልፃሉ።

ከዚህ በኋላስ?

ዲያቆን ዳንዔል የፖለቲካዊ ፍላጎት መጥፋት እንጅ ሲኖዶሶቹን በእርቅ ማጨባበጥ እስካሁንም የሚከብድ ነገር ሆኖ እንዳልነበር ያምናሉ።

ከዚህ ቀደም የተደረጉ የእርቅ ጥረቶች “ላለመሳካታቸው አንዱ እንቅፋት የአገሪቱ ፖለቲካ ነው” ይላሉ አክለው “ምክንያቱም ሁለቱም በየራሳቸው የሚደግፏቸው የፖለቲካ አዝማሚያዎች አሏቸው። የአገር ቤቱ ሲኖዶስ የአገር ቤቱን ፖለቲካ፣ የውጭው ሲኖዶስ ደግሞ የውጭውን ፖለቲካ ስለሚደግፉ እና በፖለቲካው ጫና ውስጥ በመውደቃቸው ነው።”

በውጭ አገር ያለው ሲኖዶስ በአማኞች ቁጥር ከተመዘነ ያለው አቅም በጣም ትንሽ ይሁን እንጅ በሚያንቀሳቅሰው የገንዘብ መጠን እና ባለው ተፅዕኖ ትከሻው የደረጀ ነው እንደ ዲያቆን ዳንዔል አስተያየት።

ከሁለቱ ፓትርያሪኮች መካከል የስልጣን መንበሩ ላይ መቀመጥ ያለበት የሚለው ጥያቄ ሌላኛው ማነቆ ሆኖ የቆየ ቢሆንም እርሱን አሁን መፍታት ብዙም አይገድም ይላሉ።

ብፁዕ አቡነ ማቲያስ የአስተዳደሩን ስራ እየሰሩ፤ አቡነ መርቆሪዮስን ደግሞ በመንበራቸው ሆነው ከአስተዳደሩ ስራ ግን ገለል እንዲሉ ስማቸውም በቅዳሴ እየተጠራ በሲኖዶሱም እየተገኙ እንዲቀጥሉ ማድረግ አማራጭ ሆኖ እንደሚታያቸው ይናገራሉ።

“አቡነ መርቆሪዮስን የአስተዳደር ስራ ላይ እንዲሳተፉ ቢደረግ ከጤናም ከዕድሜም፣ከአገሪቱ ከሃያ ዓመት በላይ ርቀው ከመቆየታቸውም አንፃር ሊቸገሩ ይችላሉ።” ይላሉ።

ቀሲስ ኤፍሬም በበኩላቸው በውጭ አገር ያሉት ፓትርያርክ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም አባቶችና ካህናት ወደአገር ቤት ተመለሰው በየአገር ስብከቱ እንዲመደቡና የአገልግሎት መዋሃድ እንዲፈጠር ይጠብቃሉ።

ከዚህም ባለፈ ተመሳሳይ ክፍፍል እንዳይፈጠር “ህጎች ይወጣሉ፣መመሪያዎች ይወጣሉ፤ በተለይ ከመንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት ቤተ ክርስትያን ህግ ታወጣለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን።” ብለዋል

Filed in: Amharic