>

"ኢጆሌ" ባሌዎች "የኢጆሌ" ባሌነታችሁን እሴት አትልቀቁ! (ብርሐነ መስቀል አበበ - ዶ/ር)

“ኢጆሌ” ባሌዎች “የኢጆሌ” ባሌነታችሁን እሴት አትልቀቁ!
ብርሐነ መስቀል አበበ (ዶ/ር)
የባሌ ዞን የቱርስት መስብ ከሆኑት የተፈጥሮ ሃብቶች አንዱ የባሌ ብሄራዊ ፓርክ ነው። የባሌ ብሄራዊ ፓርክ ደግሞ በውስጡ ከያዛቸው እንሰሳት ውስጥ በአለም በባሌ ተራራ ላይ ብቻ የሚገኙት ቀይ ቀበሮዎች ይገኙበታል።
የእነዚህን የባሌ ቀይ ቀበሮዎች የቱሪስት መስብ ሚና ለማጉላትና ለከተማዋ ውበት ሲባል በጎባ ከተማ አንዱ አደባባይ በኢህዲግ መንግስት (መች እንደሆነ አመቱን አላወኩም) ሃውልት ተሰርቷል። ይህ እጅግ በጎና መልካም ነገር ነው።
ይታያቹሁ እንግዲህ፣ አሁን በባሌ ጎባ ለተፈጠረው ችግር ባሌ ብቻ ለሚገኙት ለነዚህ ቀይ ቀበሮዎች ለቱርስት መስብ የተሰራ ሃውልት የህዝብ ግጭት ምክንያት ይሆናል ብሎ የሚያስብ አንድም ጤናኛ አእምሮ ያለው ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም።
ነገር ግን ህዝባችንን ከማባላት ውጭ ምንም አገራዊም ሆነ ህዝባዊ አጃንዳ ያሌላቸው ኃይሎች ማድረግ የቻሉት ይህን ነው።
የኦሮሞ ህዝብን የሰላም፣ የእኩልነትና የዲሞክራሲ አጃንዳ የማይፈልጉ ነገር ግን በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚነግዱ ኃይሎች የቀይ ቀበሮዎቹን ኃውልት አፍርሰን የጄኔራል ታደሰ ብሩ እና የሃጂ አደም ሳዶን ሃውልቶች በቦታው ላይ እንሰራለን ብለው ህዝብ ይቀሰቅሳሉ።
ተሳካላቸው። ህዝብ ቀስቅሰው የቀይ ቀበሮዎቹን ኃውልት አፍርሰው የኦነግ ባንዲራ በቦታው ላይ ተከሉ። ይታያቹ። ለታደሰ ብሩና ለአደም ሳዶ ሃውልት መስራት ከፈለጉ ለምን ሌላ ሃውልት አይሰሩም? ለምን በባሌ ብቻ የምትገኘውን ቀይ ቀበሮ ሃውልት ማፍረስ አስፈለገ? ለምን የኦነግ ባንድራስ ተከሉበት?
እነዚህ ቡድኖች የቀይ ቀበሮዎቹን ኃውልት አፍርሰው የኦነግ ባንድራ ሲተክሉ የኦነግን ባንዲራ አውርዶ የኢትዮጵያን ባንድራ የሚሰቅል ሰው እንደሚኖር ጠንቅቀው ያውቃሉ። በዚያ ሂደት ደግሞ ግጭት እንደሚፈጠር ያውቃሉ። የግጭቱ መስመርም ኃይማኖታዊ እንደሚሆን ይረዳሉ። አላማቸውም ያ እንዲሆን ነው።
ጫወታው ያለው እዚህ ጋ ነው። ግጭት ቀስቃሾቹ የሚያደርጉትን ያውቃሉ።   በዚህች የኦነግ ባንድራ ስም የብዙ ሺህ የኦሮሞ ልጆች ደም ባለፉት 40 ዓመታት ስለፈሰሰ የኦሮሞ ህዝብ ለዚህች ባንድራ ሩሩ ልብና በትንሹ እንደሚቀሰቀስ የሚያውቁት ሁሉ የሚጠቀመት ይቺን ባንድራ ነው። ነገር ግን እነዚህ ሰዋች ባንድራዋንም ሆነ የባንዲራዎን አለማ አይወክሉም።
ለማስታወስ ያህል ኦነግ  የኦሮሞ ህዝብ ማንነት እንዲከበር እና የኦሮሞ ህዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ለመታገል የተቋቋመ ድርጅት ነበር። በዚህ ድርጅት ስም እና ለዚህ ዓላማ የኦሮሞ ህዝብ በርካታ ውድ ልጆቹን በሞት፣በእስራት እና በስደት አጥቷል። ላለፉት 27 ዓመታት ብቻ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ንግዳቸውን፣ስራቸውን እና ንብረታቸውን ያጡት ኦነግ ናችሁ ተብለው ነው። ብዙ ሺህ ኦሮሞ የተሰደደው ኦነግ ነህ ተብሎ ነው። እኔ ከስራዬ የወጣሁት ኦነግ ነህ ተብዬ ነው። ብቻ፣ ለኦሮሞ ህዝብ የሚናገር ሁሉ ኦነግ ነህ ተብሎ ተጠቅቷል። በነገራችን ላይ ጄኔራል ታደሰ ብሩም ሆኑ ሃጂ አደም ሳዶ የኦነግ አባል አልነበሩም።
ነገር ግን የኦሮሞን ህዝብ ስነልቦና የሚያውቁት እነዚህ ግጭት ፈጣሪ ቡድኖች የኦነግ ባንድራ እና የእነ ታደሰ ብሩን ስም የሚጠቀሙት ለእኩይ ተግባራቸው ጥሩ የህዝብ መቀስቀሻ ስለሚሆናቸው እንጂ የሁለቱንም አላማ አይጋሩም።  ጄኔራል ታደሰ ብሩ ለኦሮሞ ህዝብ አንድነትና እኩልነት ታግሎ የሞተ ጀግና ነው። እነዚህ ቡድኖች ግን ዋናው አላማቸው የኦሮሞን ህዝብ ከፋፍሎ ማባላት ነው።
በባሌ ጎባ የሆነውም ይኸው ነው። የኦሮሞ ህዝብ የፍትህ፣ የእኩልነት እና ዲሞክራሲ ጥያቄ አንሶ የምልክትና የሃውልት እንዲሆን ለማድረግ ጥረዋል።ህዝቡን  በኃይማኖት ከፋፍለው ህዝብ የመጠቃትና የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማው ለማድረግ ሞክረዋል።
በዚህ ሁኔታ በባሌ ህዝብ ላይ በተሰራው ወንጀልና ለጠፋው የሰው ህይወት እጅግ አዝኛለሁ። አማራ፣ኦሮሞ፣ ክስቲያን፣እስላም ሳይል በአብዲ ኢሌ ታጣቂዎች የተፈናቀለውን ህዝብ መንግስት ዞር ብሎ ባላየበት ጊዜ ከለው አካፍሎ ህዝባችንን ከሞት ያዳነ ህዝብን ዛሬ በኃይማኖትና በፓላቲካ ከፋፍለው ሲያባሉት ማየት ልብ ያቆስላል።
ሃይማኖትና ብሄር ሳይለዩ “እጆሌ ባሌ”  ብለው ከአውሮፓ፣ ከኤሲያ፣ ከአውስትራሊያ እና ከአሜርካ ተጠራርተው ገንዛብ አዋቶ በጋራ የተጎዳ ወገኑን የሚረዳ ትልቅ ህዝብ በኃይማኖትና በብሄር ለይቶ ወንድም፣ ወንድሙን እንዲያጠቃ ማድረግ የወንጀልም ወንጀል ነው።
አንድ ነገር በግልፅ መታወቅ አለበት። ኦሮሞን ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ደም እንዲፋሰሰ እና ኦሮሞን በሃይማኖትና በፓላቲካ አስተሳሰብ ከፋፍሎ ለማባላት የሚሰሩ ቡድኖች የኦሮሞ ህዝብ ጠላት እንጂ የኦሮሞ ህዝብ መብት ታጋዮች አይደሉም።
የኦሮሞ ህዝብ ለኦሮሞ እንታገላለን እያሉ ወደ ጥፋት ከሚመሩት የበግ ለምድ ከለበሱ የውስጥ ጠላቶች እና የቀን ጅቦች ራሱን መጠበቅ አለበት። የኦሮሞ ህዝብ የስረዓት እንጂ የህዝብም ሆነ የኃይማኖት ጠላት የለውም።
 አሁን በጎባ የተፈጠረውንም ችግር በሰላም እንዲፈታ ህዝቡ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን አሳትፎ ለሰላም፣ለፍቅር እና ለአንድነት እንዲሰራ መድረግ ያስፋልጋል።”ኢጆሌ” ባሌዎች “የኢጆሌ” ባሌነታችሁን እሴት አትልቀቁ
Filed in: Amharic