>
5:18 pm - Thursday June 15, 9397

ከላቁት ሁሉ የበቃው ምሁር  ፕ/ር መሳይ ከበደ!!!  (ሙሉ አለም ገ/መድህን)

ከላቁት ሁሉ የበቃው ምሁር  ፕ/ር መሳይ ከበደ!!!
ሙሉ አለም ገ/መድህን
ህላዌውና ቀጣይነቱ አጠራጣሪ ቢሆንም ምሁር ጠል የሆነውን ኢህአዴግን በሊቀመንበርነት እየመራ ያለው ጠ/ር አብይ አህመድ የአገሪቱን ቀጣይ የታሪክ ምዕራፍ የሚወስኑ አቅጣጫዎችን መስመር በማሰያዝ ላይ ይገኛል፡፡የትላንቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን መድረክ በግንባሩ መቃብር ላይ ካልሆነ በስተቀር ያን የመሰለ ነፃ መድረክና ሰዋዊ አመራር የሚታሰብ እንዳልነበረ የብዙዎች እምነት ነው፡፡ራሱን ለታላቅ ታሪክ ያጨው ጠ/ሩ የቀደመውን የማህበራዊ ሳይንስ ዕውቀታችንን ፈትኖታል፡፡ አዲስ ምልከታ ለማምጣት የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን መዘገባቸውን ማገላበጥ ግድ ብሏል፡፡‹ የብራ መብረቅ›  የሆነው ጠ/ር አብይ አህመድ በ‹‹ወዳጅ Vs ጣላት›› አሰላለፍ ራሱን የበየነውን አብዮታዊ ዴሞክራሲን አፈር ከቶታል፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር የተካሄደው ውይይት ብዙ ሊባልልት የሚገባና በቀጣይም ደርዝ ያላቸው ትንታኔዎች ከተለያዮ አቅጣጫዎች ሊወጡ እንደሚገባ የመድረኩ ታዳሚዎች እምነት ነው፡፡በተለይም በምሁር ጠሉ ሟቹ ጠ/ር  በአሳፋሪ ሁኔታ ከስራቸው የተሰናበቱ 42ቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን  መንግሥት ራሱ ‹‹ይቅርታ ጠይቋቸው›› ወደሥራ ገበታቸው እንደሚመለሱ በጠ/ሩ የተገለጸበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ከራሷ ጋር እንድትታረቅ ብሎም የታሪክ ፈተናዋን እንድትሻገር  ተስፋ ሰጪ ዕድል አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡ከሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ ኢትዮጵያ በታሪኳ የምሁር ችግር ነበረባት ለማለት ይቸግራል፡፡ችግሩ የነበረው ገዥዎቹ ከአገዛዝ ባህሪያቸው ጋር የሚስማማ መደባዊ ምሁር የሚፈልጉ መሆናቸውና ምሁራኑም መደባቸውን ለመሸጥ ፍቃደኛ ሆነው አለመገኘታቸው  ብሎም የገዥው መደብ አወዳሽ ሆነው መገኘታቸው ነበር፡፡ያም ሆኖ ‹አዳሽ ምሁራን› አልጠፉም ነበር፡፡ድህነትና ኃላቀርነት በተጫነው ማህበረሰብ ውስጥ ለዛውም የገዥው ኃይል ፍላጎት ሳይታከልበት ማህበረሰባዊ ንቃት ላይ የሚያተኩሩ ምሁራን ህልማቸውን እንደታቀፉ ማሸለባቸው ከዚህና መሰል ሁነቶች ጋር የሚዛመድ ይመስለኛል፡፡ ከግዛት አንድነት ያልተሸገረው የአገር ግንባታ ሂደቱ መጨናገፍና ባለበት መርገጥም ራሱን የቻለ የምሁራን  ፈተና ነበር፡፡ዛሬም ድረስ የአደባባይ ምሁራን ቁጥር መሳሳት ምንጩ ይሄው ነው (ምሁሩ ከራስ ባላይ የሚል እሳቤ ይጎድለዋል የሚለውን ትችት ሳንዘነጋ)፡፡
የሆነው ሆኖ አፈሩ ይክበደውና በሟቹ ጠ/ር ምሁር ጠል ባህሪ በግፍ ከተባረሩ 42 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ውስጥ ዛሬ ላይ በህይወት የሌሉ ይገኙበታል፡፡ይህን ጊዜ አይተው ቢያልፉ ምንኛ መልካም ነበር!? በደረሰባቸው በደል የተነሳ ብስጭቱ በጊዜ ሂደት  በስኳር  እና በደም ግፊት ህመም እየተሰቃዮ በቤታቸው ውስጥ አይነ-ስውር እና ግማሽ አካላቸው ሽባ ሆኖ ያሉ ከተሰናባቾች ውስጥ ይገኙበታል፡፡እኔ እንኳን ሁለት ምሁራንን አውቃለሁ፡፡ዝርዘሩ ብዙ ነው፡፡ መለስ  ዜናዊ ክፉ ዘረኛ ነበር፡፡ እርሱና የዘመን ተጋሪ የታሪክ አተላዎች ተክለውብን የሄዱት መርዝ እያደር ሲጠዘጥዘን ይኖራል፡፡እንዴት እንደምንነቅላቸው በቅጡ ካላሰብንበትም የታሪክ ፈተናችን አካል የሚሆኑ መርዞችን ረጭተዋልና ሲያባሉን መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡
የሆነው ሆኖ፤ከዚህ ውሳኔ ጋር በተያያ በወቅቱ ተሰናባች ከሆኑት 42 የዮኒቨርሲቲው ምሁራን መካከል በርካቶች  በምዕራቡ ዓለም ዮኒቨርሲዎችና የምርምር ማዕከላት ውስጥ እየሰሩ በህይወት አሉ፡፡ብዙዎቹን በርቀት እያየናቸው በዕውቀታቸው ተደምመን፣ ስራቸውን ለማግኘትና ለማንበብ  ዕቁብ ገብተናል፣ ለዱቤ እጃችን ዘርግተናል፣ዲያስፖራ ወዳጅ አፍርተን ተለማምጠናል…(አኔና የቅርብ ጓዶቼ ይህን አድርገናል)፡፡ አሁን የትውልድ ትግል ፈቅዶ በሩ እየተከፈተ ነው፡፡ እነዚህ ምሁራን ወደአገራቸው ይገቡ ዘንድ በጉጉት እየጠበቀን ነው፡፡ከተሰናባች ምሁራኑ ውስጥ  የዳይተን ዮኒቨርሲቲው የፍልስፍና መምህር ፕ/ር መሳይ ከበደ ይገኝበታል፡፡ ሌሎች ምሁራን እንዳሉ ሆነው በልዮነት ውስጥ ይህን የኢትዮጵያ ዕንቁ በጉጉት እንጠብቀዋለን፡፡እርሱ በሚሰጠው ፐብሊክ ሌክቸር አዳራሽ ውስጥ መታደም ምንኛ መታደል ይሆን? የአገሪቱን የታሪክ ፈተናና የትውልዱን ስንጥቀት በቅጡ ከተረዱት ጥቂት የአደባባይ ምሁራን አንዱ የሆነው ፕ/ር መሳይ ከበደ፤ በቀጣይ አገር ቤት ገብቶ ከአቻዎቹ ጋር በሚያቋቁመው ‹ቲንክ ታንክ› ውስጥ በጥበቃና በጽዳት ሰራተኝነት መቀጠር በራሱ ለሀገር ግንባታው ራሱን የቻለ ተዋጽኦ አለው፡፡ ግነት አይደለም፡፡ አንድ ደገኛ ወዳጅ አለኝ፡፡ ከእንቅልፉ ሲነቃ የሰርክ ጥያቄው ‹መሳይ ምን አለ!? ነው፡፡ ይሄ የብዙዎች የሰውየው አድናቂዎችና አንባቢዎች የሰርክ ጥያቄ ነው፡፡ የፕ/ር መሳይ ከበደን ሥራዎች እንዳነብ የገፋፋኝን ይሄን ደገኛ ወዳጄን በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡ በነገራችን ላይ የፕ/ሩ መጽሃፍት በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቤተመጽሃፍት ውስጥ እንዳይቀመጡ እስከ መከልከል ደርሶ ነበር፡፡ ሰውየው በሁሉም አክራሪ ዘውጌ ብሔርተኞች  በተለየ መልኩ ደግሞ በትግራይና በኦሮሞ ጽንፈኞች ሳይቀር ‹የላቀ አቅም ባለቤት› አንደሆነ ጥላቻቸው ሳይገድባቸው ይመሰክሩለታል፡፡ኢትዮጵያ ከራሷ ጋር እንድትታረቅና በራሷ እምቅ ኃይል ወደፊት እንድትራመድ የሚያስችል የትምህርት ሥርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁነኛ  መሃንዲስ ከሚሆኑት አንዱ ፕ/ር መሳይ ከበደ ለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡ የመሳይን ስራዎች በተለይም የጥናት ውጤቶቹን መዘርዘር የሚቻል አይደለም፡፡እንኳን እኔ ደካማው የመሳይ አቻዎች ራሱ በዝርዝር የሚያስታውሱት አይመሰልም፡፡
ከመጽሃፍቱ ውስጥ፤
1. Ideology and Elite conflicts፡ Autopsy of the  Ethiopian Revolution (2011)
2. Radicalism and Cultural Dislocation in Ethiopia 1960-1974 (philosophy faculty publications 2008)
3. Survival and modernization, Ethiopia’s Enigmatic present; A philosophical Discourse
4. Africa’s Quest for a philosophy of Decolonization (philosophy faculty publications 2004)
5. Meaning and Development (philosophy faculty publications 1994)
ቁጥራቸው ከላቀው አርቲክሎቹ ውስጥ ሦስት እጅግ የሚገርሙኝ አርቲክሎች አሉት
1. The Ethiopian Conception of Time and Modernity
2. The Roots and  fall outs of Haleselassie’s Educational policy
3. Directing Ethnicity Toward Modernity
በእውነት ይሄን የለውጥ ሂደት አብዝተን ልንጠነቀቅለት የሚገባው የአገሪቱን ተንከባላይ የትውልድ ዕዳና የዘመናት ህመም ፈውስ የሚሆኑ ድንቅ ምሁራን ወደአገር ቤት እንዲገቡና የአካዳሚክ ነፃነት ከማብሰሩ ጋርም በተያያዘ ነው፡፡ ከእንግዲህ የምሁራን የጥናት ውጤት ሸልፍ ማሞቂያ መሆኑ የሚያበቃበት ጊዜ የቀረበ ይመስላል፡፡ምሁራኑም ቢሆን ለተግባራዊ ጥናትና ምርምር፣ ለሃሳብ  መተጋገል ራሳቸውን ያዘጋጁ፡
ለሁሉም ግን ፕ/ር መሳይ ከበደ ይለያል!!
Filed in: Amharic