>
5:26 pm - Wednesday September 17, 1147

እያየሁት ያደግኩት የህወሀት መርዝ - የጀግኖች አምባ!!! (መባ ዘውዴ)

እያየሁት ያደግኩት የህወሀት መርዝ – የጀግኖች አምባ!!!
መባ ዘውዴ
የግዜ መገላበጥ ይገርማል:: በ1960ዎቹ መጨረሻ ሶማሌ የአሜሪካን ወዳጅ ነበረች:: የኢትዮጵያ መሪዎች ወደ ኮሚኒዝም እያዘመሙ በመምጣታቸው አሜሪካ ደስተኛ አልሆነችም:: ስለዚህ የሶማሌ ወዳጅ ሆነች:: የዲፕሎማሲና የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ ተሰጣትና ሶማሌ ልቧ አብጦ ኢትዮጵያን ወረረች:: አሜሪካ ደግሞ ለኢትዮጵያ መሳርያ አልሸጥም ብላ አሻፈረኝ አለች:: የተከፈለባቸውን መሳርያዎችም ለመላክ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች:: በዛ ላይ አብዮቱ ፈንድቶ በርካታ ጀነራሎችን  በልቷቸዋል:: የንጉሱ ክቡር ዘበኛ የሚባለውም የሰለጠነ ጦር ተበትኗል::
ሶማሌን ሊያስታግሳት የቻለው ብቸኛ ኃይል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ብቻ ነበር:: በዚህ ወቅት ኮሎኔል መንግስቱ ክተት አውጀው የዘመቻ ምልመላ ተጀመረ:: በአጭር ግዜ ውስጥ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ምልምል ሚሊሻዎች ታጠቅ ከተቱ:: በሶስት ወራት ስልጠናም ውጊያ ተላኩ::
ለዚህ ሚሊሻ አስኳል የነበረው የኢትዮጵያ እግረኛ ጦር ነበር:: በተለይ ነበልባል: ናደው ; አስረኛ : አራተኛ : አየር ወለድ ወዘተ:: የኩባና የራሻ ወታደሮች ውለታም እንዳለ ሆኖ:: እነዚህ ቁጥራቸው ጥቂትም ቢሆኑ እጅግ የሰለጠኑ ወታደሮች ነበሩ:: ሚሊሻውና ወታደሩ ተሰባቅረው የመልሶ ማጥቃቱ ውጊያ ተካሄደ::
የኢትዮጵያ ጦር የሶማሌን ወራሪ ድምጥማጡን አጥፍቶ ሶማሌ ድንበር ደረሰና ድል ታወጀ::ጦርነቱ ላይ የተፈጸሙ ጀብዱዎች ለሰሚ የሚገርሙ ነበሩ:: የጅብ ቦንብ ይዘው ታንክ የሰበሩ : ከፓራሹት ወርደው የጠላት ምሽግን ያፈረሱ : ፈንጂ ረግጠው ለሌላው መንገድ የጠረጉ ወዘተ ወዘተ
እነዚህ ጀግኖች አካላቸው የተቆረጡት ተመርጠው ስለ ውለታቸው ” የጀግኖች አምባ” እንዲጦሩ-   በጀግንነት ከጠላት ጋር ሲዋጉና ጀብዱ ፈጽመው አካላቸውን ላጡ ጀግኖች መንከባከብያና ውለታቸውን ለማሰብያ ” የጀግኖች አምባ” ተቋቋመላቸው::
ጀግኖች አምባ ደብረዘይት ውስጥ ከሞዴል ትምህርት ቤት አጠገብ ይገኝ የነበረ ትልቅ የአርበኞችና የጀግኖች መጦርያና መታከምያ ነበር:: በርካታ የሶማሌ የጦር ጉዳተኞች ይጦሩበትና ይታከሙበት ነበር::
ህወሀት አዲስ አበባን ስትቆጣጠር ግን ከስራዎቿ አንዱ  ጀግኖች አምባን ማፍረስ ነበር:: አለምንም ርህራሄ ጀግኖች አምባን አፍርሳ በሺዎች የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞችን ሜዳ ላይ በተነቻቸው::
ያኔ ልጅ ነበርኩ:: አንዱ ጀግና አስታውሰዋለሁ ( የአካል ጉዳተኛ ) ሁሌ ቅዳሴ አይቀርም ነበር:: በክራንችም : በዊል ቸርም እየታገለ ቅዳሴ አይቀርም ነበር:: አንዳንዴ መንገድ ላይ ሳገኘው :ስለሚያሳዝነኝ ያቅሜን ያህል ዊል ቸሩን እገፋለት ነበር::
አንድ ቀን ዝክር ስለነበረው ቤቱ ጠራንና እኔና ታዬ በላቸው ( ዶክተር ታዬን ነፍሱን ይማረውና) ቤቱ ሄድን:: ኑሮው ያሳዝናል:: ከዛችም ኑሮው ግን ሚካኤልን ይዘክር ነበር:: የጀብዱ ሜዳዪን : ፎቶዎቹን ሰርተፊኬቱን ማየት ጀመርን::ስለ ጦርነቱ ቁጭ አድርጎ ያጫውተን ነበር:: ግድግዳው ላይ ትልቅ ሰንደቅ ዓላማና የኢትዮጵያ ካርታ ነበር:: በኩራት ሁሌ እሷን እያየ ነበር የሚተርክልን::
ያኔ ብዙም ትርጉሙ አይገባኝም ነበር:: አሁን ሳስበው ግን ልቤ ይደማል:: ይሄ ሰው በሶማሌ ጦርነት ግዜ ከፍተኛ ጀብዱ የፈጸመና ያንድ ክፍለጦር ምክትል አዛዥ ነበር::
ከጀግኖች አምባ ተባሮ: የሚያስታውሰው አጥቶ አንድ ቀን ሞቶ ተገኘ:: ጦር ሜዳ የሚያውቁት ጓደኞቹ ተንሰቅስቀው አልቅሰው ቀበሩት:: ቀብሩ ላይ እስካሁን ትዝ የሚለኝ – ቀብሩ ላይ ታሪኩን ሲያነብ የነበረው ወታደር ንግግር ነበር ” ኢትዮጵያዬ ውለታችን ይህ ነበር”:: ሰዉ ሁሉ ሲያለቅስ ሁለት ሰዎች ግን “ከት “ብለው ይስቁ ነበር:: ደስታቸው ወሰን አልነበረውም::
በግዜው ደብረዘይት ላይ የነገሱት ሃባርና ወድ ራያ ( የትግል ስሙ ከሆነ አላቅም) የሚባሉ ሁለት ወያኔዎች ነበሩ:: ለምን ቀብሩ ላይ እንደተገኙ የገባኝ በኋላ ወሰን ባጣው ሳቃቸው ነው:: ሁሌም ግን የዚህችን ወንበዴ ፍጻሜ ማየት እጓጓለሁ:: ይሄ ሁሉ ሀገር ክህደት : መርዝ: ጥላቻና እብሪት ፍጻሜው ምን እንደሚሆን አንድ ቀን እናየዋለን:: አይቀርም:;
Filed in: Amharic