>

ኢትዮጵያ ምን ኣይነት ሽማግሌ ያስፈልጋታል? (እንዳለ ጌታ ከበደ)

ኢትዮጵያ ምን ኣይነት ሽማግሌ ያስፈልጋታል?
እንዳለ ጌታ ከበደ
ሳናውቅ የሰበርናቸው ድልድዮች ብዙ ናቸው፡፡… ይኼ ድልድይ እግዜር ካደለን ነገ እኛም የምንሄድበት ይሆናል፡፡ የ60ዎቹ ትውልድ አውቆ ይሁን ሳያውቅ ከሰበራቸው ድልድዮች አንዱ በሽምግልና ሥርዓት ማመን ይመስለኝ ጀምሯል፡፡ የበቀልንበትን ስር መርሳት፣ ተኮትኩተን ያደግንበትን ሥርዓት መዘንጋት…
ድልድዩ ተሰብሯል ያልኩት በድልድዩ የሚመላለሱ ሰዎችን በማጣቴ ነው፡፡ ድልድዩ ስለተሰበረ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ክፍተት በየጊዜው እየሰፋ ነው፡፡ ጥቂቶቹ ድልድዩን ተሻግረው ወደዚያኛው ዓለም ለመቀላቀል ሲዘሉ ይሳካላቸዋል፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ ተሰናክለው ይወድቃሉ፤ ወንዙም ይወስዳቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ግን አትድረስብኝ አልደርስብህም ተባብለው ያሉ ናቸው፡፡ …
በዚህም የተነሳ ብዙ ነገር አጥተናል፡፡ ሕዝቡም መንግሥቱም ጎድሎበታል፡፡ ወደኋላ ለመቅረታችንም የራሱ የሆነ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ምነው ቢሉ ሕዝብ በአንዳች ነገር ቅያሜ ሲገባው አቤት የሚልበት መድረክ የለውምና፡፡ እናንተ እያላችሁ እንዴት እንዲህ እንሆናለን? ብሎ ብሶቱን የሚያሳስብበት ምኩራብ የለውም፡፡
ያም ሆኖ ሕዝብም መንግሥትም ሊያውቀው የሚገባ አንድ እውነት አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች የሚሰባሰቡበት አንድ ጉባኤ ቢኖር፣ አባላቱ ለሹመትና ለሽልማት ሳይሆን፣ ወድቆ ለተነሳው ባንዲራ ክብር ሲሉ እውቀታቸውንና ቀሪ እድሜያቸውን ለመክፈል ዝግጁ ሆነው ቢገኙ፣ ብዙ ቀዳዳ ይደፈናል፤ ብዙ ጉድለት ይከደናል፤ ልክ እንደ ሦስተኛ ዐይን ይሆኑልናል፤ በቸልተኝነት ወይም በዝንጋዔ ብዛት ወይም በሥራ ውጥረት ምክንያት ያላየናቸውን እንድናይ ያደርጉናል፡፡የማንበብ ባህል ባልተንሰራፋበት፣ የግል ፕሬሶች በመዋከብ፣ በመታሰርና በመሰደድ እድሜያችንን ፈጀነው በሚሉበት በአሁኑ ዘመን፣ ሽማግሌዎች በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ገደል በደለል እንዲሞላ አድርገው ዐይን ሆነው ያዩናል፤ ያዩልናል፤ ያስተያዩናል፡፡
…በደርግ ዘመን የአብዮት ችቦ ተቀጣጥሎ፣ እራሱንም ሌሎችንም መፍጀት ሳይጀምር በፊት፣ በአንዳንድ መኮንኖች … በንጉሡ የስልጣን መዋቅር ውስጥ ከነበሩና ገለል የተደረጉ ግን አሁንም መለስተኛ ተደማጭነት ያላቸውን ለማነጋገር ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሃዋርያት ናቸው፡፡ ደጃዝማቹ አርአያ በተሰኘ ልቦለድ መጽሐፋቸውና ቴዎድሮስ  ታሪካዊ ድራማ በተሰኘ ተውኔታቸው እውቅና ያተረፉ ናቸው፤ ትምሕርታቸውን ያጠናቀቁት ፈረንሣይ አገር ነው ፤ በእርሻና በማስታወቂያ ሚኒስትርነት ማዕረግ ሲሰሩ ቆይተው፣ በዘውድ አማካሪነት ማገልገል በጀመሩበት ዘመን ሁለት መኮንኖች ወደ ቤታቸው አመሩ፡፡
ከመኮንኖቹ አንዱ የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣ ከግራዝማቹ ጋር ስላሳለፉት ቆይታ ምስክርነት ሲሰጡ፣ ‘… በጥንቃቄ ካዳመጡን በኋላ – የጭን ገረድ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? አሉን፤ በአገራችን ባህል ሲያስፈልግ እንደሚስት፣ ሲያሻም እንደ ሠራተኛ የምታገለግል ናት፤ ያ ማለት እኔ ነኝ፡፡ አንድ ጊዜ ሚኒስትር ነበርኩ፤ አሁን ደግሞ ችላ ተብዬ በአማካሪነት አለሁ፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ሥራ የለኝም፡፡ የሚያዳምጠኝም የለ፣ ንጉሱንም አልፎ አልፎ ነው የማገኛቸው – በማለት ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ረዘም ያለ ንግግር ካደረጉልን በኋላ – እኔ በአዝጋሚ ለውጥ እንጂ በአብዮት አላምንም፤ ለእናንተ ለወጣት መኮንኖች የምሰጣችሁ ምክር፤ በስሜት እንዳትገፋፉና ረጋ እንድትሉ ነው!’ ማለታቸውን የደም ዕንባ በተሰኘ መጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡
መኮንኖቹ ምክር ጥየቃና መፍትሔ ፍለጋ ሽማግሌ ዘንድ ማቅናታቸው ደግ ነው፡፡ የሽማግሌውን ምክር ሰምተው ለመተግበር የነበራቸው ሞራል ግን የቀዘቀዘ ነበር፤ እናም ሽማግሌው የፈሩት አልቀረም፡፡ በስሜት ተገፋፍተው ማንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ እንዲሆን የማይመኘው ሁሉ ሆነ፡፡ ምክር አቋዳሽ የሆኑት እኚህ ሰውም በዘውዱ ሥርዓት በነበራቸው ስልጣን ምክንያት ለሰባት ዓመታት ያህል ታሰሩ፤ ደም ፈሰሰ፤ ያለፍርድ መገደል፣ ማስገደልና መገዳደል የአብዮቱ መለኪያና መታወቂያ ሆነ፡፡ ቤተክርስቲያኑም ቤተ ሙስሊሙም እራሱን ለማዳን ይሯሯጥ ገባ፤ ተቋማት በዝምታ ተዋጡ፤ አልበዛም እንዴ ለማለት አቅም አነሳቸው፤ እና ያ እንዳይደገም የምንለው ነገር ሁሉ ሆነ …
ሽማግሌ የለንም!
Filed in: Amharic