>
5:18 pm - Sunday June 16, 9135

‘ቻይና ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?’፡ በፓርቲና ግለሰብ ደረጃ የወረደው የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት

‘ቻይና ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?’ ብዬ ልፃፍ እስኪ

By Mulugeta B. Teferi

በቅርቡ በሃገራችን የተደረገውን ለውጥ ተከተሎ ብዙ ሀገራት እንደየጥቅማቸው ደግፈዋል፡፡ አንዳንዶች ድግሞ ፍዘት ይዟችዋል፡፡ የ’ልማቱ’ ሁሉ የበላይ መሀንዲስ የነበሩት ቻይኖች ምናልባት በይፋ በሚያራምዱት ‘በሀገራት የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ ያለመግባት’ ፖሊሲ ምክንያት ሊሆን ይችላል ፍዘት ይታይባቸዋል፡፡ ምንም ባለማድረግ ለውጡን የጎሪጥ እንደሚያዩት አስተውለናል፡፡

የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት መሰረት

የሁለቱን ሀገራት ግንኑነት የሚያሳልጠው ምክንያታዊ ነገር ቻይና የሰፊ የተፍጥሮ ሀብት እና ገብያ ጥማቷ ነው፡፡ ለዚህ ድሞ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አፍሪካ ላይ እንድታትኩር ማድርጉ ነው፡፡ አፍሪካ ላይ ለመግባት ባነጣጠረችባቸው አመታት ደግሞ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ምቹ በር ሆና ተገኝታለች፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል፣ በታሪክ እና በሌሎች ምክንያቶች የጥቁር አፍሪካ ኢ-መደበኛ መሪ ነች፡፡ ይህች አገር ባጋጣሚ ሆኖ በኮሚኒዝም የተጠመቀ አብዮታዊ ፓርቲ በበላይነት የተቆጣጠራት ነበረች፡፡ ከሌላው አገር ይልቅ የማኦ ደቀ መዝሙሮች የሚመሯት አገር ጋር እስከ ግለሰብ የደረሰ ግንኙነት መመስረት ቀላል ነበር፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ላይ ከሚያገኙት ጥቅም ይልቅ ወደ አፍሪካ እንደመግቢያ በር በመጠቀም የሚያገኙት ስለሚበልጥ ቻይኖች በመጀመሪያዎቹ የግንኙነት አመታት በጣም ለጋሶች ነበሩ፡፡ መንገድ እንዴት እንደሚሰራ፣ ትምህርት እንዴት እንደሚስፋፋ፣ ጤና ለሁሉም እዴት እንደሚዳረስ፣ ፍትህ እንዴት እንደሚሰፍን ከሚደሰኩሩ ምዕራባዊያን ልቀው መንገዱን ራሳቸው ሰርተው አሳዩን፣ ትምህርት ለማስፋፈት በግንባታ ረዱን፡፡ ቆየት ብለውም የኤሌክትሪክ ሃይል፣ ስኳር ፋብሪካ፣ የመዳበሪያ ፋብሪካ እና ባቡር የምንገነባበት ብር አበድረው እራሳቸው በዚያው የግንባታ ኮንትራቱን መውሰድ ጀመሩ፡፡

ከሀገራት ወደ ፓርቲና ግለሰብ ደረጃ የወረደው ግንኙነት

እየቆየ ቻይና በአፍሪካ አምባገንንን መሪዎች ስር የሚተዳደሩ ሀገራት የምታገኘው ከገብያ ውጭ የሆነ ተጠቃሚነት ሳባት፡፡ ይህ ማለት እንደ ዝምባብዌ ባሉ ሀገራት የሚታፈሰው የአልማዝ ማዕድን በቀላሉ ከተቋማዊ ቁጥጥር ውጭ ወደ ሀገሯ ማጓዝ ችላለች፣ ደቡብ ሱዳን ነዳጀ፣… ኢትዮጵያ ውስጥ እኛ ዘይት እየተቸገርን እርሷ ሰሊጡን ታጉዘ ነበር፡፡ አንዴም ፕሬዝዳንት ሙጋቤ 5 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ከዘመባብቄ አልማዝ ገቢ መጥፋቱን በይፋ አንስተው ሲነጫነጩ ነበር፡፡ ይህም በቻይኖች እና በዝምባብዌ መንግስት መካከል ለተወሰነ ጊዜ ከፍኛ ችግር ፈጥሮ ነበር፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ግንኙነትም በዚህ ምክንያት ከመርህ ውጭ በሁለቱ ምሪ ፓርቲ(የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲና የኢትዮጵያ ኮሙኒስት ፓርቲ… ይቅረታ ኢሕዴግ) ሰዎች የሚዘዎር ሆነ፡፡ የብድር ስምምነት ሲደረግ የኢኮኖሚ ባሙያዎች ሳይመክሩበት እንዲሁ በከፍተኛ አመራሮች እየተዎሰነ ብቻ ከፍተኛ ብድሮች በከፍተኛ ወለድ ከቻይና ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ መበደር ብክፍተኛ ሁኔታ ቀጠለ፡፡ በተለይም በቅርብ አመታት የኢትዮጵያ መንግስት የሚያድርገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየጨመረ ሲሄድ ምዕራባውያን በተለያየ መልኩ የሚደርጉት ድጋፍ ቀነሰ፡፡ ኢህአዴግም የውጭ ምንዛሪ ጉድለቱን ለመሸፈን ከፍተኛ ወለድ ያለውን ብድር መውሰዱን ቀጠለ፡፡ ይህ ብድር የሚሳዝነው በይፋ በመንግስት በዋቅር ሪፖርት የማይደረግ መሆኑ ነው፡፡

እንድማስታውሰው በፍርንጆች 2015 የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ብድር 16 ቢሊዮን ዶላር (1 ቢሊዮን ዩሮ ቦንድ ከሸጥን በኋላ) ብቻ ነበር፡፡ ይህ አሃዝ በሶስት አመት ውስጥ (2018) ውድ 27 ቢሊን ዶላር ተመነደገ፡፡ የሀገር ውስጥ ብድር ደግሞ 22 ቢሊዮን ዶላር ጠጨማሪ አለ፤ በአጠጋላይ ውድ 46 ቢሊዮን ዶላር ብድር አለባት፡፡

ምንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች ቻይናዎቹ መስረተ ልማት በመገንባታቸው ቢያመሰግኗቸውም፤ ከቻይና ጋር የሚደረግ ግንኙነት በመስረታዊነት በዝባዥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተፍጥሯ ምክንያት ስላለው ነው፡፡ የቻይና ህዝብ እና ኢኮኖሚ የጥሬ እቃ እና የገብያ ፍላጎት እኳ ኢትዮጵያን አሜሪካን ያራቁታል፡፡ ወንዞቻቸውን ወደ ድም ወንዝነት፣ አየራቸውን ወደ ጭስ የቀየረ ስልጣኔ ነው እንዳስመዘገቡ መርሳት የለብንም፡፡ በመሆኑም በአግባቡ ከተያዘ ከቻይና ጋር የሚደረግ ግንኙነት ትንሽ ጥቅም ይኖርዋል፤ በተለይም ለአጭር ጊዜ፡፡ ነገር ግን በቅጡ በመርህ ተመስርቶ ከልተያዘ ከቻይና ጋር የሚደረግ ግንኑነት እጅግ አክሳሪ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ከቻይና ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ 447 ሚሊዮን ዶላር ተበድረን የሰራነውን የአዲስ አባባ ቀላል (አጥሩ ከባድ) ባቡር ብድሩን ሲሰጡን ውል ውስጥ የነርሱ ድርጅት ባቡሩን እንዲገነባ፣ ፍርጎና ሌሎች ቁሶች ከቻይና እንዲመጡ በማድረጋቸው እነርሱ ሁለት ነገር ኤክስፖርት አድርገዋ፡፡ አንድ የግንባታ አገልግሎት ሁለት ደግሞ የተለያዩ የባቡር ክፍሎች፡፡ በዚህ ምክንያት ከተበደርነው ዶላር ውስጥ አብዛኛው ተመልሶ ለነርሱ የሚሄድ ነው፡፡ ምናልባት ያስቀረናት ዶላር ካለች ባቡሩ ሲገነባ ኮንትራክተሩ መንዝሮ ለሰራተኞች የቀን ምንዳ የከፈላት ዶላር ብቻ ናት፡፡ ባቡሩ ተገንብቶ ያስገኘው ጥቅም እና የአገልግሎት ቀጣይነቱ፣ ከዚህ በኋላ ምን ያክል የጥገና ወጪ እንደሚያስፈልገው እያደር እናያለን፡፡ በባቡሩ ምክንያት ህዝቡ እያገኘ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም፣ እየከፈለ ያለው ዋጋ (በአጭሩ መዞር ባለመቻል በመኪና ነዳጅ…) እንዲሁም ለአንዳድ ማህበራዊ እክሎች ተዳርጎ የሚከፍለው ማህበራዊ ዋጋ በአጠቃላይ ቢጠኑ ደግሞ ሌላ ታሪክ ነው፡፡

በአጭሩ “የቻይና መንግስት ማፍያዊ የሆነ አሰራር ይመቸዋል” ብል ብዙም አልሳሳትኩም፡፡ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት በሚል መርህ ሰበብ ህዝብን ገለል አድርጎ ከአምባገንኖች ጋር መሻረክ ይቀናዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የነበርው ግንኙነትም ከተቋማዊ መዋቅር ይልቅ በፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተንጠለጠለ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል ቻይናዎች አሁን ባለው ለውጥ ግራ ተጋብተው የፈዝዙት፡፡

በቅርቡ የቻይናው ፕሬዝዳንት ጂ ፒንግ የምዕራብ አፍሪካ አገራትን አዳርሰው እዚህ ጎርቤት ሩዋንዳ ሄደው ፖል ካጋሜን መጎብኘታቸውን ሰማን፡፡ ብዙ ጊዜ የሀያላኑ መሪዎች የአፍሪካ ጉብኝት ሲያደርጉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የተለምደ ተግባራቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደ አንድ ትልቅ የአፍሪካ ሀገር ካላት ተፅዕኖ በተጨማሪ 54ቱን የአፍሪካ ሀገራት እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ባለስልጣናትን ለማግኘት አዲስ አበባ ምቹ ነች፡፡ ከዚህ ይልቅ ፕረዚዳንት ጂ ፒንግ በቅርቡ በተደረገው ጉብኝት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሆኑትን አምባገነን ‘ልማታዊ’ መሪ መጎብኘትን መርጠዋል፡፡

Rwanda’s President Paul Kagame & China’s President Xi Jinping

ይህ ሁሉ እግዲህ አንድ ያሚያሳየን ነገር አለ፡፡ ቻይና ተጠያቂነት የሰፈነበት እና ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማት ያላቸው ሀገራት ጋር የምታደርገው ግንኙነት በአጭር ጊዜ ያለባትን የጥሬ እቃ ርሃብ አያረካም፡፡ ስራ አጥ የሆኑ ዜጎቿን በአፍካ መሰረተ ልማት ግንባታ ሰበብ መሰግሰግ ይከብዳታል፡፡ በ’ልማታዊነት’ ሰበብ ከጨረታ ውጭ የሚሰጥ የስራ ኮንትራት፣ ከገብያ ይልቅ በፖለቲከኞች የሚወሰን የሽርክና ውል የበለጠ ለቻይናዎች አሰራር አመቺ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው ኢትዮ-ቻይና ግንኙነት መፋዘዝም ከዚህ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ከግለሰቦች የድለላ ሚና አላቃ ተቋማዊ ግንኙነት መመስረት ግድ ይላታል፡፡ እንደሚታዎቀው ምዕራባውያን ሊያደርጉት የማይችሉ ስራዎችን በመስራት የቻይና ሚና በአጭር ጊዝ የሚተካ አይደለም፡፡ በረዥም ጊዜ ቻይናዎች የሚሰሩት ሙያዊ ስራ በሀገር ውስጥ ባለሞያዎች ሲተካ በ’ኮምፓራቲቭ አድቫንቴጅ’ ላይ የተመሰረተ የንግድ ግንኙነት ከቻይና ጋር መመስረት ይቻላል፡፡ ለጊዜው ግን ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ቻይናዎችን እንደገና መቅረብ እና የፈዘዘውን ግንኑነት መርህን መሰረት አድርጎ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡ አሁንም አፍሪካ ላይ ባለን የምሪነት ሚና ቻይናዎች ይፈልጉናል፡፡ ሩዋንዳ የኢትዮጵያን የመሪነት ሚና ለመተካት በፍፁም አትችልም፡፡ የኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች መሪነት ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ነውና፡፡

By Mulugeta B. Teferi

Email: mule8001@gmail.com

Filed in: Amharic