>
5:14 pm - Friday April 20, 0142

የህወሃት የመጨረሻ ርግጫዎች!! (ያሬድ ደምሴ)

የህወሃት የመጨረሻ ርግጫዎች!!

ያሬድ ደምሴ

The last kick of the dying buffalo is dangerous!!!

ህቅታ ላይ ያለ በሬ ርግጫ በጣም አደገኛ ነዉ፡፡ነብሱ ከስጋዉ በምትለይበት የመጨረሻ ወቅት ላይ የሚሰነዝረዉ ርግጫ በሬዉ በህይወት በነበረበት ዘመን በቀንዱ ወግቶ ከሚያስከትለዉ ጉዳት በእጥፍ የከፋ ነዉ፡፡

ህወሃትም በዚህ በመጨረሻዉ የህቅታዉ ወቅት ላይ የሚራገጠዉ ርግጫ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ከተራገጠዉ በላይ እንደሚከፋ ምንም ጥርጥር አልነበረዉም!! ርግጫዉ ከተጀመረ ከረምረም ቢልም አሁን ግን ከመቼዉም ጊዜ በበለጠ ተባብሶ ቀጥሏል!! እርግጫቸዉ የበለጠ አደገኛ የሚያደርገዉ ደግሞ ሃግ ባይ ማጣታቸዉ ነዉ፡፡ እስከአሁን የቆነጠጣቸዉ አካል ባለመኖሩ ደረታቸዉን ነፍተዉ በየሄዱበት ሁሉ የእልቂት ነጋሪታቸዉን ይሄዉ እየጎሰሙ አሉ፡፡

ደ/ር አብይም የዚችን ሃገር ወቅታዊ በሽታ ለይቶ ከማወቅና መፍትሄ ለመፈለግ ከመጣር ይልቅ የበሽታዉ ምልክቶቹን በመፈወስ ስራ ላይ መጠመድን የመረጡ ይመስላሉ፡፡እሳት እንዳይለኮስ ከማድረግና ሳይቃጠል በቅጠል ከማለት ይልቅ እሳት በየተነሳበት ቦታ እየሄዱ እሳቱን ለማጥፋት ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡

በዚህ 3 ወር ዉስጥ የተከናወኑ ጥቂት የተስፋ መቁረጥ ርግጫዎችን ማየት ብቻ በቀን ጅቦች ላይ እርምጃ ለመዉሰድ በቂ ናቸዉ፡፡ ዶ/ር አብይ ላይ የተቃጣዉ የግድያ ሙከራ በነማን እንደተቀናበረ በግልጽ እየታወቀ ጥቂት የፖሊስ አባላትን በማሰር አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ አይነት ስራ ተሰራ፡፡ደቡብ ክልል ዉስጥ በሲዳማና ወላይታ መሃል የብሄር ግጭት ተነሳና ዜጎች ተጎዱ፡፡ቤኒሻንጉል ክልል ዉስጥ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተከፍቶ በርካቶች ለሞትና ለከባድ ጉዳት ተዳረጉ፡፡ በመተማ በኩል ሱዳን ወረረችን ተባለ፡፡ባሌ ዉስጥ ብጥብጥ ተከሰተ፡፡ደሴ ሸዋበር መስጊድ ዉስጥ ጸጉረ ልዉጥ ሰዎች ገብተዉ አማኞች ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፡፡የሆኑ ግለሰቦች ለመሳሪያ ግዥ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለማሸሽ ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ወደ አገር ዉስጥ ሲገቡ ተያዘ፡፡ይሄ ሁሉ እንገዲህ ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚንስቴር ከሆኑ በኋላ ከተከሰቱ የህወሃት የመጨረሻ ርግጫዎች መሃል በጣም ጥቂቶቹ ናቸዉ፡፡

የዶ/ር አብይ አስተዳደር ዝምታዉና ትዕግስቱን ስላበዛዉ እነሆ ዛሬ ደግሞ የህዳሴዉ ግድብ ስራ አስኪያጂ በአደባባይ ተገሎ ተገኘ፡፡ ይሄ እንግዲህ እያጣጠረ ያለዉ የዱር በሬ ሌላኛዉ አስከፊ እርግጫ መሆኑ ነዉ፡፡ዛሬም እጃችንን አጣጥፈን “የሚቀጥለዉ የደወል ድምጽ የሚጠራዉ”ን ሰዉ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡

የአብይ መንግስት እነዚህን 20 የማይሞሉ የእልቂቱን ዘዋሪዎች ለቅሞ ማሰር ተስኖት በቀን ጅቦች የመጨረሻ የህቅታ ርግጫ እያጋለጠን ነዉ፡፡ በዚህም ሰበብ ይቺ ሀገር ልትወጣዉ ከማትችለዉ አዘቅት ዉስጥ እየገባች ትገኛለች፡፡ ይሄ ነፃነት የራበዉ ህዝብ እንዳይጎዳ ዶ/ር አብይ አፋጣኝ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ህዝቡ በደም ፍላት ግብታዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ ቢነሳ ይህቺ ሃገር የከፋ ሁከትና ብጥብጥ ዉስጥ መግባቷ ሳይታለም የተፈታ ነዉ፡፡ ለአብነት በቅርቡ አማራ ክልል ዉስጥ በረከት ስምኦን ደብረ ማርቆስ ዉስጥ ታዬ ተብሎ ህዝቡ በደም ፍላት የወሰደዉን እርምጃ ማየት ብቻ የጉዳዩን አሳሳቢነት መገመት ይቻላል፡፡

ዛሬ ከህወሃት አብራክ የተፈለፈሉት “የቀን ጅቦች” ለመሸፈት ደደቢት ጫካ  ለመግባት የሚያበቃ ሃሞት የላቸዉም፡፡ ነገር ግን የትግራይ ህዝብን እንደ ጫካ ሊጠቀሙበት ቆርጠዉ ተነስተዋል፡፡ለዚህም ህወሃትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነዉ እያሉ የትግራይ ህዝብን ለማሳመን ቀን ከሌሊት ላይ ታች ሲባክኑ ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የትግራይ ህዝብ አይደለም ይችን አይነት የጅል ጨዋታ ቀርቶ ቱባ እንቆቅልሽ መፍታት የሚችል ህዝብ ነዉ፡፡በጥቂት ድንጋይ ራሶች አይታለልም፡፡እናም እነዚህን የቀን ጅቦች በቁጥጥር ስር አዉሎ ለህግ ማቅረብ ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚያገናኘዉ አንዳችም ነገር እንደሌለ ነጋሪ አያስፈልገዉም፡፡   

ስለዚህ ዶር አብይ ከዛሬ ጀምሮ ስለፍቅርና ይቅርታ ማዉራታቸዉን ትተዉ ወደ እርምጃ ሊገቡ ግድ የሚልባቸዉ ወቅት ላይ ደርሰዋል፡፡የኢንጅነር ስመኝ ግድያ ለ አብይ አስተዳደር የማንቂያ ደዉል ነዉ፡፡ ከይቅርታ በላይ ለሆኑ ሰዎች ስለይቅርታ ማዉራት ጊዜ ማጥፋት ነዉ፡፡ እንዲህ ላሉ አዉሬዎች 70 ጊዜ 7 ጊዜ ይቅር ቢሏቸዉ አይገባቸዉም፡፡ ለነርሱ የበዛ ትዕግስት ጅልነት ነዉ፡፡ ግድየሌሽነት ነዉ፡፡በሚገባቸዉ ቋንቋ ካላናገሯቸዉ እነዚህን አዉሬዎች ማስቆም ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ፍትህን ለማስፈን ተብሎ ህዝቡ አምኖበት የሚወሰድ እርምጃ ደግሞ እንደ አምባገነናዊ እርምጃ ሊቆጠር ፈጽሞ አይችልም፡፡የሆነ አካል ያኮርፋል ተብሎ የህዝብ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ያለመዉሰድ ልፍስፍስነት እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይቻልም፡፡

ስለሆነም ለግለሰብ ብሎም በአጠቃላይ ለህዝቡ ደህንነት ሲባል እነዚህ በህቅታቸዉ ዋዜማ የሞት ሽረታቸዉን እየተፈራገጡ ህዝብን በመጨረሱ ያሉ የቀን ጅቦች በቁጥጥር ስር ዉለዉ ከህዝቡ ገለል እንዲሉ ማድረግ አማራጭ የሌለዉ መፍትሄ ነዉ፡፡ያለበለዚያ በርካቶች የጥቃቱ ሰለባ መሆናችን ስለማይቀር ከዚህ በኋላ መንግስት ከመርዶ ነጋሪነት የዘለለ ኃላፊነት ሊኖረዉ አይችልም!!! ምክንያቱም the last kick of the dying buffalo is always dangerous!!!

Filed in: Amharic