>

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ" ነገር!! ፕሬዝዳንት ኢሳያስን እንደምሳሌ 

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ” ነገር!!
ፕሬዝዳንት ኢሳያስን እንደምሳሌ 
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስካያጅ መሀል አዲስ አበባ ላይ ተገድለው ተገኝተዋል።ዛሬ ላይ የኒህ ሰው በዚህ ሰአት ባየነውና በሰማነው ሁኔታ ተገድለው መገኘት ብዙ ነገር አያይዘን እንድናስብ ያስገድደናል።ብዙ ሰው ከዚህ በፊት በሀገሩ ላይ ሲፈፀም የነበረውን የፖለቲካ ሸፍጥና ሴራ ከግምት ውስጥ በማስገባት የግድያ ወንጀሉን “የቀን ጅቦች”ወደሚባሉት እያስጠጋ ማስብ ይፈልጋል።ይህ መላምት እንደአንድ ግምት ሊወሰድ የሚችል ቢሆንም የአባይ ወንዝ ጉዳይ የብዙ ፍላጎቶች ግጭት የሚስተናገድበት ማእከል በመሆኑ ጉዳዩን ከተራ ሌብነትና መረጃ ማጥፋት በላይ ያሉ መላምቶችንም ማየት ያስፈልጋል ብየ አምናለሁ።ይህንን ፕሮጀክት በተመለከተ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ (“Oromia Media Network (OMN)”) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “መለስ ዜናዊ በስልጣኑ የመጀመሪያ አመት አካባቢ ከሳቸው ጋር ግብፅ ለስራ ጉዳይ በሄዱበት ወቅት “ስለ አባይ ወንዝ ከግብፅ ባለስልጣናት ጋር መነጋገር ስለምፈልግ ሁኔታወችን አመቻችልኝ” ብሎ እንደጠየቃቸውና ፕሬዝዳንት ኢሳያስም “ይህ ጉዳይ አሁን አጀንዳ መሆን እንደሌለበት መክረውት እንደነበር ነገር ግን መለስ በጣም ግፊት ስላደረገባቸው አቶ ኢሳያስ ከባለስልጣናቱ ጋር እንዳገናኙት ገልፀው መለስን የግብፅ ባለስልጣናት “ማነህ አንተ ይህን ጥያቄ የምታነሳ” ብለው መለስን በንቀት እንዳዩትና እንዳናናቁት መለስም በሁኔታው በጣም እንደተናደደና ግብፆችን “ምን ማድረግ እንደምችል አሳያቸዋለሁ” እያለ በዝቅተኝነት ስሜት ተሰቃይቶ እንደነበር” አቶ ኢሳያስ በቃለምልልሳቸው ገልፀው ነበር። የንግግራቸው ማጠንጠኛና ማጠቃላያም “መለስ የአባይን ግድብ የጀመረው ግብፆች ባሳደሩበት የዝቅተኝነት ስሜት ተነሳስቶ ነው” የሚል ነው።አቶ ኢሳያስ ደግሞ ባሁኑ ሰአት በታላቅ ወንድምነት ማእረግ የዶ/ር አብይ አማካሪ ለመሆን እንደወሰኑ ኢትዮጵያን በጎበኙ ጊዜ አዋሳ ላይ ቃል ገብተዋል።ይህንን ካልኩ ዘንዳ አቶ ኢሳያስ ከድሀ ጉሮሮ እየተነጠቀ የተጀመረውን የአባይ ግድብ በተመለከተ ለዶ/ር አብይ ምን አይነት ምክር  እንደሚለግሱ ወደፊት የምናየው ይሆናል።
Filed in: Amharic