>

ስለመቀሌዉ ሰልፍ እዉነት እንነጋገር! (ታዬ ደንደአ)

ስለመቀሌዉ ሰልፍ እዉነት እንነጋገር!
ታዬ ደንደአ
ዛሬ መቀሌ ላይ ሠላማዊ ሠልፍ ተደርጓል። አስተባባሪዉ ህወሀት እንደሆነ ይታወቃል። የሰልፉ  ዓላማ ደግሞ የኢትዮ-ኤርትራን የሠላም ስምምነት መደገፍ እንደሆነ ተነግሯል። በሠልፉ ላይ የመለስ ዜናዊ እና የኢንጂነር ሰመኘዉ በቀለ ፎቶ ደምቆ ታይቷል። መለስ ለሠላም ህደቱ ትልቅ ሚና እንደነበረዉ ሲገለፅ ለክቡር እንጂነር ስመኘዉ ሀዘን ተገልፇል። ህገ-መንግስቱም ይከበር ተብሏል። ይህ ብቻዉን ስለሰልፉ አጠቃላይ እዉነታ ይነግረናል። የማስመሳያ ሰልፍ!
ኢትዮጵያና ኤርትራ ሲጣሉ መለስ የኢትዮጵያ ጠሚ ነበር። ጦርነቱ በማይሆን ምክንያት ተቀስቅሶ የብዙ ሺ ዜጎችን ህይወት ቀጠፈ። መለስ ዜናዊ የዓለም አቀፍ ፍ/ቤት የሰጠዉን ዉሳኔ ባለመቀበል የሠላም ህደቱን አደናቀፈዉ። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አለመግባባቱን ለመፍታት በተደጋጋሚ ደብደቤ ፅፈዉ ከመለስ መልስ ማጣታቸዉ ተረጋግጧል። ለ20 ዓመታት የቆየዉን የጥላቻና የጥርጣሬ  ቋጠሮ በመፍታት ሁለቱን ሀገሮች ያስታረቀዉ ዶር አብይ አህመድ ነዉ። መቀሌ ላይ ግን የመለስ እንጂ የዶር አብይ ፎቶ አልታየም። ህያዉ አብይ በፈፀመዉ ጀብዱ ሟቹ መለስ መወደሱ ያ ድጋፍ የይስሙላ መሆኑን በግልፅ ያሳያል። ሠላም ያመጣዉ ተርስቶ ጦርነት የቀሰቀሰዉና ለእርቅ እንቅፋት የነበረዉ ተከበረ። ደግሞም መጀመሪያ ላይ ዶር አብይ የፍ/ቤቱን ዉሳኔ በመቀበላቸዉ እነዝሁ ሰዎች ጠንከር ያለ ተቃዉሞ ሲያሰሙ ነበር። ትግራይ ላይ በተለያዩ ከተሞች የተቃዉሞ ሠልፍ ሲደረግ ነበር። አዲስ አበባ ላይ ራሱ ሠልፍ ተጠርቶ መሠረዙ ይታወሳል። ታዲያ ዛሬ የታየዉ “ጉሮ ወሸባዬ” ከየት መጣ?  ማንን ለማታለል አስበዉ ነዉ? የኢትዮጵያ ህዝብ 2010 ላይ ሲደርስ እነሱ በ1983 ላይ ቀርቷል። መግባባት ያቃተን ለዝህ ይመስለኛል!
ስለህገ-መንግስት ደግሞ ባያወሩ ይሻል ነበር። ምክንያቱም ህገ-መንግስቱን በመጣስ የአፓርታይድ ስርዓት የዘረጉት እነሱ ናቸዉ። ዜጎችን በመግደል እና በማሰቃየት ለሰሚ የሚዘገንን ኢሰበአዊ ወንጀል ሲፈፅሙና ሲያስፈፅሙ የነበሩት እነሱ ናቸዉ። ራሳቸዉ ፀረ-ህገመንግስት ሆነዉ ሲያበቁ የህገ-መንግስቱ ጠበቃ ሆነዉ ብቅ አሉ!
ከላይ ያየናቸዉ ሁለት እዉነታዎች ስለክቡሩ ኢንጂነራችን ግድያ ፍንጭ ይሰጠናል። ኢንጂነሩን ማን ገደለዉ? እስከ አሁን አልተረጋገጠም። ነገር ግን ፀረ-ሰላም እና ፀረ-ሰዉ የነበረዉን “የሠላም አባት” ካሉ እና እራሳቸዉ ቀዳደዉ የጣሉትን ህገ-መንግስት “ይከር” ካሉ በኀላ ለኢንጂነር ስመኘዉ “ከልብ አዝነናል!” ማለታቸዉ ምን ማለት እንደሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅ ነዉ። እዉነት አይፈጠርም! ማስመሰል ደግሞ በዛሬ ጊዜ የትም አያደርስም! እዉነት እንነጋገር!
Filed in: Amharic