>
5:18 pm - Saturday June 14, 5980

አልፎ ሄዶም እንኳ ለትዝታ በልብህ የምታስቀምጠው ሰው!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

አልፎ ሄዶም እንኳ ለትዝታ በልብህ የምታስቀምጠው ሰው!!
ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ
አንዳንድ ግዜ የሆኑ በድብቅ የኖሩ ቁልፍ ሰዎች በድንገት ህይወታቸው ሲያልፍ <እንኳንም አላወኩት!> ትላለህ። ሌላ ጊዜ ደግሞ <እንኳንም አወቅኩት!> በማለት ውስጥህን ትነግረዋለህ። እንደ መጽናኛም
ትወስደዋለህ። አልፎ ሄዶም ለትዝታ ታስቀምጠዋለህ። ዛሬ እንኳንም አወቅኩት ብዬ ለራሴና የቅርብ ጓደኞቼ የነገርኩት ሰው የቀብር ስነ ስርአት እየተፈፀመ ነው። ተስፋዬ ጌታቸው ይባላል። በምክትል ፕሬዝዳንት ማእረግ
የብአዴን ድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ነበር።
.
ከተስፋዬ ጋር ሁለት የተለያዩ ቀናት ለረጅም ሰአታት ተገናኝተን ተነጋግረናል። የመጀመሪያው አጋጣሚ በቅርብ የማውቀው ዴንቨር የሚገኝ ታናሽ ወንድሙ ስልክ ደውሎ ” ተስፋዬ ሊያገኝህ ይፈልጋል?” በማለቱ ከብዙ ማንገራገር በኃላ ነበር የተገናኘነው። ለማግኘት ያንገራገርኩት ተስፋዬ ለውጡን ከሚመሩት የብአዴን አመራሮች አንዱ መሆኑን የቀደመ መረጃ ስላለኝ ከእኛ ጋር መገናኘቱ ለአደጋ ያጋልጠዋል በሚል ነበር። ስንገናኝም ስጋቴን
ገለጥኩለት። ተስፋዬ ከት ብሎ እየሳቀ <እየተካሄደ ያለው ለውጥ እንዲህ አይነት ጥቃቅን ጉዳዮች ከተሻገረው አመታት አለፈ> በማለት ምላሽ ሰጠኝ።
አብራው የመጣችው የትዳር ጓደኛው የህዝቡ የለውጥ ስሜትና የደረሰበት ደረጃ በሚጣፍጥ አማርኛ አጫወተችን። ብዙም ሳይቆይ በአሜሪካን የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ሲደውልለት በድጋሚ እየሳቀ “እናንተ አሸባሪ ካላችኃቸው ሰዎች ጋር ሻይ ቡና እየጠጣሁ ነው!” በማለት አሾፈበት። ከዚህ በኃላ በተረጋጋ መንፈስ ተነጋገርን። ወጋችን ባለማለቁ ሌላ ቀን በሰፊው ለመጫወት ወስነን ተለያየን።
.
በሁለተኛው ቀን ግንኙነታችን ሀብታሙ አያሌው፣ ተወልደ በየነና ጄኔራል መላኩ አብረውን ነበሩ። አጋጣሚው ጠለቅ ያለ ውይይት እንድናደርግ እድል ፈጥሮ ነበር። በኢትየጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ብአዴን እንዴት
እንደሚገልጠው፣ የለውጥ እና ፀረ -ለውጥ ሃይሉ ፍልሚያ የደረሰበት ደረጃ፣ ለውጡን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ኃይሎች ማንነት እና የሀይል ሚዛናቸው፣ ፀረ ለውጥ ሀይሉ በየጊዜው የሚጠነስሰውን ሴራ ተቋማዊ በሆነ
መንገድ ለማክሸፍ ምን እያደረጉ እንደሆነ፣ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚደረገውን የሽግግር ሂደት በምን መልኩ እየመሩት እንደሆነ፣ በብአዴን እና ኦህዴድ ውስጥ ያለው የለውጥ አመራር መደጋገፍ ወደ ሌሎች የለውጥ ሀይሎች ለማሸጋገር ምን አይነት ስትራቴጂና ስልት ነድፈው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ፣ ኢሳት በሚያቀርባቸው ፕሮግራሞች ላይ ብአዴንም ሆነ ሌሎች ለውጥ ፈላጊ አመራሮች ያላቸውን ምልከታ…ወዘተ የውይይታች ማዕከላዊ ነጥቦች ነበሩ። (ሌላ ጊዜ በዝርዝር እመጣበታለሁ።)
.
እንደ እውነቱ ከሆነ ከተስፋዬ ጋር የነበረን ቆይታ ወቅታዊ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ነበር። እርግጥ ተስፋዬ ያጋጠመው ህመም ከባድ መሆኑ ገፅታው ቢያሳብቅም በፍፁም እርጋታና የራስ መተማመን በመረጃና ማስረጃ ተደግፎ የሚያቀርበው ሃሳብ ከለውጡ መሀንዲሶች አንዱ መሆኑን የሚገልጡ ናቸው።
.
(በነገራችን ላይ ከተስፋዬ ጋር በነበረን ቆይታ የብአዴን ሊቀመንበር ለሆነው አቶ ደመቀ መኮንን ያለኝ አክብሮት እንዲጨምር አድርጓል። #ደመቀ_መኮንን በወሳኝ ሰአት ቆራጥ ውሳኔ ባይሰጥ ኖሮ ዛሬ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ
ከነቤተሰቦቹ በህይወት አናገኘውም ነበር። የተረጋጋ ጊዜ ሲገኝ <<ደመቀን ደመቀ አዳነው!>> በሚል ርዕስ እመለሳለሁ።)
.
ነፍስ ይማር
Filed in: Amharic