>

“እንበታተናለን” ወይስ “እንገነጠላለን?” ሁለቱንስ ምን አመጣቸው?" (በቴዎድሮስ ተ/አረጋይ)

“እንበታተናለን” ወይስ “እንገነጠላለን?” ሁለቱንስ ምን አመጣቸው?”
በቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
* “እንበታተናለን” በፍጹም የታረመ የመሪ ንግግር አይደለም!
 
መለያየታችን ካልቀረ፣ እናንተም እንደ ሀገር አትቀጥሉም’ ነው ወይስ…??
አንድ ሰው ትዳር ሲመሠርት ያለው አማራጭ ከሚስቱ ጋር ተከባብሮ መኖር ወይም መፋታት ነው፡፡ አንድ ሰው ጥሬ ስጋ ቢያምረው፣ ገንዘብ ካለውና ከፈለገ ገዝቶ መብላት ወይም እንዳማረው መቅረት ነው፡፡ የትም ቢሆን ምርጫህ ሁለት ነው፤ ማድረግ ወይም አለማድረግ፣ መሆን ወይም አለመሆን ነው፡፡ ትናንት ዶ/ር ደብረፅዮን ለመቀሌ ከተማ ሕዝብ የተናገሩት የዚህኑ ዓይነት ነው፡፡ “ያለን አማራጭ ተከባብረን መኖር፣ ወይም መበታተን ነው” በማለት በፍጹም የትግራይን ሕዝብ የማይመጥን ንግግር ተናገረዋል፡፡
“እንበታተናለን” በፍጹም የታረመ የመሪ ንግግር አይደለም፡፡ ሕዝብ ነው የሚበተነው፤ ፈንዲሻ አይደለም፡፡ ይሁንስ ቢባል ተከባብሮ መኖር ቢያቅት፣ ዶ/ር ደብረፅዮን ማለት የነበረባቸው “እንለያያለን/እንገነጠላለን” ነው ወይስ “እንበታተናለን”? ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተለያዩ (ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገነጠለች) እንጂ ማንም አልተበተነም፡፡ ነው ወይስ ‘መለያየታችን ካልቀረ፣ እናንተም እንደ ሀገር አትቀጥሉም’ የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ነው የፈለጉት? ይህ ደግሞ ጨዋነት አይደለም፡፡ በፍጹም የትግራይን ሕዝብ የሚያክል ንግግር አይደለም፡፡ ንግግሩ ያን ጨዋ፣ ያን በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ሕዝብ አይመጥነውም፡፡
አብዛኛው ሕዝብ ለ27 ዓመት የተቃወመውን የሕወሓት/ኢሕአዴግ የበረሀ ጭምር መዝሙር የሆነው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ድሮም እዚያ ቦታ የተቀመጠው ለዚህ ቀን መጠባበቂያ ነው፡፡ ሀገር ለ27 ዓመት እንደመራ ፖርቲ 4 ወር እንኳ ሳይሞላ ለዚህ የሚያደርስ ምን ውርጅብኝ ወረደ? ደግሞስ ኤርትራን ያየ፣ ያውም በዚህ ዘመን እንዴት በመገንጠል ይጫወታል? መገንጠል ለኤርትራ ከውድቀት ውጭ ምን ጠቀማት? መገንጠል ለኢትዮጵያስ ከኪሳራ ውጭ ምን አመጣላት?
በየትኛውም የሰው ልጅ ላይ የሚደርስ ጉዳትን እቃወማለሁ፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ በትግራይ ተወላጆች ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ማንነታቸውን መሰረት ያደረገ አደጋ መድረሱን እቃወማለሁ፡፡ ሰው ቁጥር አይደለም፤ ግን ደግሞ በቁጥር ይገለጻል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ከደረሱ ብሔር ተኮር ግጭቶች፣ ሞቶች፣ መፈናቀሎች አንጻር በትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰው ቁጥር ውስጥ የሚገባና “ለመበታተን” ፉከራ የሚያበቃ ነው አልልም፡፡ እንደ አማራው ለ27 ዓመት የግጭትና የመፈናቀል መሞከሪያ፣ የተፈናቃዩ ቁጥርም እንደ ኦሮሚያው 600,000 ወይም እንደ ጌድኦው ከ800,000 በላይ ይድረስ ማለትም አይደለም፡፡ የእውነት ዶ/ር ደብረፅዮን ንግግርዎት ደስ አይልም፡፡ ደስ አይልም!
ሕወሓት ዶ/ር አብይን ያልተቀበለችው ዛሬ ሳይሆን ገና ምርጫው ሳይካሄድ ነው፡፡ አንዴ አቶ ሽፈራው፣ ቀጥሎ ደግሞ አቶ ደመቀ ተብለው አሁን በሀገሪቱ እየሆነ እንዳለው ሁሉ ሰውየው እንደ አልአዛር የፖለቲካውን መቃብር ፈንቅለው ብቅ አሉ፡፡ እንዴት ሊሆን ቻለ? እንዴት ሴራውን በጥሰው ወጡ? አላውቅም፡፡ ዶ/ር አብይ ምርጫውን አሸንፈው (በ27 ዓመት ብቸኛው ያልተጭበረበረ ምርጫ ይመስለኛል) የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላም በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን ባሉበት ምድር ሁሉ በግልፅ አመራራቸውን ያልተቀበለው ሕወሓት ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮ ኤርትራን የሰላም ግንኙነትን የተገበሩት ዶ/ር አብይ ሆነው ሳለ፣ በትዕዛዝ በሚመስል መልኩ የዶ/ር አብይ ምስል በምንም እንዳይታይ አድርጎ በሕዝቦቹ ግንኙነት ምንም ድርሻ የሌላቸውን የአቶ መለስን ፎቶ ይዞ መውጣት መልዕክቱ ግልጽ ነው፡፡
ለማጠቃለል ያህል እዚህም እዚያም ያለው የብሽሽቅና ሴራ ፖለቲካ ማንችንም አይጠቅመንም፡፡ ሀገሪቱን ሳይሆን “መበተን” የሚለውን ቃል መበተን ያስፈልጋል፡፡ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ስለ አንድነት እያወሩ ሕወሓት ብቻውን (ከትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ውጭ) ስለ መበተን ማሰቡ ራሱ ትዝብት ውስጥ ይጥለዋል፤ ጥሎታልም፡፡
Filed in: Amharic