>
5:18 pm - Wednesday June 14, 8361

"...አታስጨርሱን አስታጥቁን" ህዝባዊ ጥያቄ ታሪክ እንዳይደገም! (ደረጄ ገረፋ ቱሉ)

“…አታስጨርሱን አስታጥቁን” ህዝባዊ ጥያቄ
ታሪክ እንዳይደገም!! 
ደረጄ ገረፋ ቱሉ
በዚህን ጊዜ የ1966ቱ ስህተት እንዳይደገም ሚዲያዎቻችን በወቅቱ ተሳታፊ የነበሩ አካላትን በተደጋጋሚ ቢያወያዩ እና ከዚያ ብንማማር ጥሩ ይመስለኛል ።
የ1966ቱን ለውጥ ተከትሎ መጀመሪያ መስቀል አደባባይ ላይ የመኢሶኑ ዶር ፍቅሬ መርዕድ ተገደለ።እዚያው መስቀል አደባባይ አከባቢ በመንግስቱ ኃይለማሪያም ላይ የመግደል ሙከራ ተደረገ።በኃላ ላይ ሲጣራ ይህንን ሁሉ ድርጊት የፈፀመቱ የኢህአፓ ቡድኖች ናቸው።
ከዚያ ህዝቡ አታስጨርሱን አስታጥቁን እያለ መፈክር ማሰማት ጀመረ።ሰልፍም ወጣ።መንግስቱም በጠርሙስ የተሞላ ቀይ ቀለም በአቢዮት አደባባይ እየደፋ ተቃራኒ ኃይሎችን እንዴት እንደሚደፋ በሺዎች ፊት ደነፋ ።
እንደፎከረውም መንግስቱ ውሎ አድሮ መግደሉን በስፋት ተያያዘው።ይህ ግዲያ ስፈፀም የነበረው በተቃራኒው ኃይል ላይ ብቻ አልነበረም ። ኢህአፓ እና ደርግ ሰላም ይውረድ ያሉትን ወይም ከተቃራኒ ኃይል ጋር እንነጋገር ያሉትን አመራሮቻቸውን ጭምር በሰርጎ ገብ ፈርጀው ፈጁአቸው።
ኢህአፓዎች እነ ጌታቸው ማሩን የገደሉት ከደርግ ጋር በተወሰነ ነጥብ ላይ አብሮ መስራት ይቻላል ስላለ ብቻ ነው።
ደርግ እነ ጄነራል ተፈሪ በንቲን ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረግናቸው ያለው በኢህአፓነት ጠርጥሮአቸው ነው።
የደርጉን አርክቴክት ኮነሬል አጥነፉ በመንግስቱ ትዕዛዝ ከስብሰባ ወጥቶ እንዲገደል የተደረገው ለኢትዮጵያ ሶሻልዝም እንደወረደ ሳይሆን ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ይዛመድ በማለቱ ነው።
ጄነራል አማን አምዶም የኤርትራን ጉዳይ በሰላም እንቋጨው በማለቱ በደርግ ተገደለ።
ኃይሌ ፊዳ ጠዋት ጠዋት መንግስቱ ጋር ለውይይት ሲሄድ ዛሬ ቁርስ ያደርገኝ ይሆን እያለ በስጋት እንደኖረ ተስሮ እና ተሰቃይቶ ቁርስ ሆነ።መንግስቱ ኃይሌን ለምን ቁርስ እንዳደረገው ግልፅ አይደለም።
ይህ ሁሉ ሲሆን ህዝቡ መግደልን ተዛምዶ የፍየልወጣጤን በሬዲዮ እንደ ህዝብ መዝሙር ጠዋት ጠዋት ማዳመጥ ይናፍቀው ነበር።በወቅቱ መግደል አሰቃቂ ወንጀል ሳይሆን ልክ እንደ ቁርስ እና ምሳ ተራ ነገር ነበር።የጅምላ እብደት እዲህ ነው የሚያደርገው ። አመሉ ነው።
በአጭሩ በቀይ እና ነጭ ሽብር ብዙ ወጣት በአደባባይ ተቆላ።
ዛሬስ ?
ዛሬም የሆነ አካል የመግደል ሙከራ እና መግደልን እያካደ ይመስላል። ገና መጣራት ቢኖርበትም ያው በመስቀል አደባባይ ታሪክ እየተደገመ ነው።
በየቦታው ሰልፎችም አሉ።በፍቅር ሀገር አይመራም የሚሉ መፈክሮች በየቦታው እየተሰሙ ነው።ያው መልዕክታቸው ግልፅ ነው።መግደል እና ማሰር መንግስት ይጀምር የሚሉ ናቸው።መንግስት አይልፈስፈስ የሚሉ ድምፆች ዛሬ ማራክ ቅላፄ እያገኙ ነው።ለጆሮ የሚጥሙ ሆነዋል።ተለምደዋል።
እናም በለኮከብ እና የልሙጥ ሽብር እንዳንጀምር ሁሉም ይረጋጋ።ታሪክ እራሱን እንዳይደግም ከ1966ቱ አቢዮት ትምህርት እንውሰድ።ሚዲያዎቻችን ወደ ኃላ እየሄዱ ነገር መጎልጎል ብቻም ሳይሆን ህዝቡን ወደ ፊት ይውሰዱት።ወደ ኃላ መሄድ ከፈለጉ ደግሞ በደንብ ወደ ኃላ ሄደው ከውድቀታችን ጭምር ያስተምሩን።
የመንግስትን የፖለቲካ ዘርፍ የሚመሩ ወገኖች አቢዮት መጨረሻ ላይ ማንን እንደምትበላ ወደ ዓለም አቢዮቶች ሄድ ብለው ይከልሱ።
አቢዮትን መስቆም አቢዮት ከመቀስቀስም በላይ ከባድ መሆኑን በመረዳት ህዝቡን በማስከን ወደ መደበኛ ህይዎቱ ይመልሱት።
የፈረንሳይ አቢዮት 60 ዓመት አከባቢ ለምን ፈጀበት የሚለውን ትንሽም ቢሆን ይተንትኑ።ኢትዮጵያ 60 አይደለም 6 ዓመት አቢዮት ውስጥ መቆየት እንደማትችል መረዳት ጥሩ ይመስለኛል ።
አሁን እየገደለ ያለው አካል ካለም ማንበብ ባይችል እንኳን ታሪክን ጠይቆ ይረዳ።
አያዋጣውም።በመጨረሻ ያው ዋናውን ስልጣን የጨበጠው አካል ይደፍቀዋል።
Filed in: Amharic