>
5:28 pm - Wednesday October 10, 2627

ግድያዎች እና የሽብር ተግባራት በማጣራት ስም እያዳፈኑ መጓዙ ዋጋ ያስከፍላል!?!  (ዘመድኩን በቀለ)

ግድያዎች እና የሽብር ተግባራት በማጣራት ስም እያዳፈኑ መጓዙ ዋጋ ያስከፍላል!?!
 ዘመድኩን በቀለ
~ የኢንጅነር ስመኘው አሰቃቂ የግድያ ድራማ ላይ እየታየ ያለው የማድፈን አዝማሚያ ባየሁ ጊዜ፣
 
~ የዳንጎቴ ሥራ አስኪያጅ፣ ሾፌርና ፀሐፊያቸው ገዳዮችጉዳይ ተዳፍኖ እንደቀረ ባየሁ ጊዜ፣
 
~ የኤፍ ቢ አይ መርማሪዎች ጭምር ተሳትፈውበታል የተባለው የሰኔ 16ተ የመስቀል አደባባይ ፍንዳታም ተደፋፍኖ እንደቀረ ባየሁ ጊዜ፣
 
~ የአርቲስት ታምራት ደስታ አሟሟትም ጉዳይ እንዲሁ እንደዋዛ ተደፋፍኖና ተሸፋፍኖ እንደቀረ ባየሁ ጊዜ
~ የኦሮሞ ከሱማሌ መፈናቀል፣ የጌዴኦ ከጉጂ ዞን መፈናቀል፣ የዐማራ ከኦሮሚያና ከቤኒሻንጉል መፈናቀል። እነዚህ ሁሉ ተመርምረው በቅርቡ ለህዝብ ይፋ ይደረጋሉ ተብለው የነበሩት የመንግሥቴ ቃል የውኃ ሽታ ሆነው እንደቀሩ በተሰማኝ ጊዜ፣ አንዳቸውምም እስከ አሁን ለህዝብ ይፋ እንዳልተደረጉና ዝም ብሎ ብቻ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ” የቀን ጅቦች ” ሥራ ነው፣ ገዳይ የተሸነፈ ነው ማለቱን መስማት በሰለቸኝ ጊዜና ለገዳዮች የልብ ልብ መስጠቱ እረፍት በነሳኝ ጊዜ ይሄ ነገር  እስከመቼ ድረስ ያዛልቃል? የቀን ጅቦቹስ እነማናቸው? ለማለት ያህል ይኼን ጦማር ጻፍኩላችሁ።
~ ደርግ በግርማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት፣ ኢህአዴግ በደርግ፣ በአልሸባብ፣ በሻአቢያ፣ በግብጽ ፣ በኒዎሊብራል፣ በአልቃይዳ፣ በነፍጠኛው ወዘተ እንደሚያሳብበው ሁሉ የጠሚዶኮ መንግሥትም ” የቀን ጅብ ” የሚል የማይታይ ጭራቅ ፈጥሮ ኃጢአቱን ሁሉ የሚደፈድፍ እየመሰለኝም በመቸገር ላይ እገኛለሁ። የለውጡ ተቃዋሚ ባልሆንም እጄ እስኪላጥ ግን አጨብጫቢ አይደለሁም። ካላስ።
 ~ በዚህ ወቅት ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድን መወቀስ፣ መምከርና የቀናውን መንገድ ለማሳየት መመኮር  ማለት የጋለ ብረት ምጣድ ላይ እንደመቆም፣ ደግሞም በጀማውና በመንጋው ዘንድ እንደሚያስቀስፍ ባውቅ ብረዳም እኔ ግን ቢጠቅምም ባይጠቅምም እነ አንድ ዜጋ በሰለለና በቀጭን ድምጼ በጋለው የድጋፍ ጭብጨባ መሃል ሆኜ የእኔ እውነት የምለውን ምክረ ሃሳቤን ለጠሚዶኮዬ ከመስጠት አልቦዝንም። ለጠሚዶኮም የሚጠቅማቸው የእኔ የታናሻቸው ያልተቀባባ ጥሬ ሃቅ የሆነ ወንድማዊ ምክርም ነው ባይም ነኝ። እናም ዛሬም ምክሬን እንደ አንድ ዜጋ ለጠሚዶኮ ያለስስት በድፍረት እለግሳቸዋለሁ።
~ ወዳጆቼ ሰውየው የረቀቁ የአመራር ጥበብ የተካኑ ብቻ ሳይሆኑ የቅርብ አማካሪዎቻቸው የኢትዮጵያን ህዝብ እንዴት ማንበርከክ፣ በፍቅርም መግዛት እንደሚቻል ጭምር በሚገባ እንዳስቀጸሏቸው እያየሁም ያለሁበት ሁኔታ ነው ያለው። ጠሚው ለታማኝ በየነ፣ ለብርቱካን ሚደቅሳ፣ ለአበበ በለውና ለአበበ ገላው፣ ለሲሳይ አጌናና ለሌሎችም ያሳዩት አክብሮትና ፍቅር በስለትም በምክርም የማይቻል አስደናቂ ጥበብ ነው። ይኼን በህይወት ዘመኑ ሁሉ አንድ ሆኖ የማያውቀውን፣ መሆንም የማይፈልገውን ዲያስፖራ አንድ አድርጎ የመግዣውን የቡዳ መድኃኒትም በደንብ ያገኙ መሆናቸውም የሚታይ እውነት ነው። እናም በዚህ የሞቀ ስካር ውስጥ በሃይለኛው የጭብጨባ ግለትም ውስጥ ለጠሚዶው ምክር መለገስ “ካበደ ሰው ” እንደሚያስቆጥር ባውቅም እኔ ግን እንደምንም ብዬ ብሰማም ባልሰማም በትኅትናም ደግሞም ትንሽ በመወብረትም ጭምር የተለመደውን ነጭነጩን ምክሬን እለግሳቸዋለሁ። ምንአልባትም ከጠሚዶኮ አጠገብ ያሉ አንዳንድ ወዳጆቻችን ይሄ እብድ እንዲህም እያለ ነው እኮ ብለው ቢያሳዩዋቸው በማለትም ጭምር ነው ይህን መጻፌ።
~ የጻፍኩት ለእኔም መሪዬ ለሆኑት ንጉሤም ጭምር ስለሆነ ለንጉሤ በጻፍኩት የግል ሃሳቤ ምክንያት ወዶ ገብ ደጋፊዎች ባትንበጫበጩብኝ ደስ ይለኛል። ከፖፑ ባላይ ፖፕ የምትሆኑ ምእመናን ትንሽ አደብ ግዙ፣ ተረጋጉም ለማለት እወዳለሁ። ይኸው ነው። ደግሞ ለውበትም ቢሆን አንድ የእኔ አይነቱን ዕብድ ምክር መስማትም ብዙ አያስከፋም። እናም አጨብጫቢዎቹ ትንሽ ጮጋ በሉ ለማለት ነው።
ክቡር ጠሚዶኮ ሆይ!  ወደ ጉዳዬ ልግባ።
ያው እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ ምርጫን ያህል ነገር አጭበርብረህ ስታበቃ ያውም በ99.6% አሸነፍኩ ብለህ ባወጅክ ማግስት፤ ዓለም በሙሉ በድርጊቱ በመገረም እንዴት ተደርጎ ሲልህ? የተቃዋሚዎች በቁጣ፣ ህዝቡም ሁሉ በብስጭት አይደረግም፣ ይሄማ ግልጽ ዘረፋ ነው። እልም ያለም ሌብነት ነው። እንዴት ተደርጎ ነው 100 በ100 ልታሸንፍ የምትችለው በማለት ሊጠይቅህ፤ ደግሞም ድምጼን ውለድ ብሎ ሊያስጨንቅህ መሆኑን ስታውቅ ወዲያው ማስቀየሻ ትፈጥራለህ፣ [ በአንድ ጀንበርም፣ በአንዲት ምሽት ፕሮጀክት ነድፈህ ይፋ ታወጣለህ። መጀመሪያ ሚሊንየም ግድብ ትልና ስሙ የእንግልጣር ሆኖ ለሀገሬው አልያዝ እንዳለው ስታይ ደግሞ “ህዳሴ” ግድብ ትለውና ወዲያው በፍጥነት ስሙን ትቀይርና አዳሜን በዓባይ አይጨክንም ብለህ መንጋውን ሁሉ ዓባይ ዓባይ ዓባይ ፣ የሀገር ሲሳይ እያልክ አቅሉን አስተህ አደባባይ በማዋል ታስጨፍረዋለህ።
ታዲያ በዚህ መሃል የምርጫውን ውጤት የሚጠይቅ ሰው ከተገኘ አለቀለት። እንደሀገር መካድ ይቆጠርበትና ፀረ ልማት፣ ፀረ እድገት፣ ፀረ ዲሞክራሲ፣ ፀረ ተባይ፣ ፀረ አረም ፀረ ህዝብ ብቻ ፀረ፣ ፀረ የሻአቢያ ተላላኪ፣ የግብጽ ዶላር ናፋቂ፣ የአልሸባብና የአልቃይዳ ወዳጅ፣ የአልኢትሃድ አፍቃሪ፣ ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ የድሮ ሥርዓት ነፋቂ፣ የደርግ ትራፊ፣ የአጼው ሥርዓት ናፋቂ፣ ጠባብ፣ ነፍጠኛ፣ ወዘተ የሚል በኢህአዴግ መዝገብ ውስጥ የሚገኙ ስያሜዎችን ተከናንቦ ዋጋውን ያገኛታል። ብልቱ ይኮላሻል፣ ጥፍሩ ይነቀላል፣ የዘር ፍሬው እንዲፈስ ይደረጋል፣ እግሩም ወገቡም ይቆረጠሰል፣ ኩላሊቱም ይፈርሳል። ቅጣቱ ይኽቺ ብቻ ናት። እናም በዚህ የማስቀየሻ ጨዋታ ወቅት የምርጫ ውጤት መጠየቅ ዋጋ ያስከፍላል። መፍትሄውም የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን ተብሎ የምርጫውን ጉዳይ ጮጋ ማለት ብቻ ነው። አራዳው መንግሥቴም በጨበጣ በ99.6% የምርጫ ውጤት ሀገርን በሌብነት ማስተዳደር ይጀምራል። ይኽ የመንግሥቴ የማስቀየሻ ስልት ነው።
ደግሞ በሌላ ጊዜ በህዝብ ድምጽ በዝራራ ያሸነፉትን የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ሰብሰበህ ቃሊቲ አስገብተህ ትከረችምባቸውና ዓለሙም የኢትዮጵያ ህዝብም ሊበላህ ሲነሳ ማስቀየሻ ካርታህን ትመዝዛለህ። እዚሁ ሶደሬ አምጥተህ ጠፍጥፈህ የፈጠርከውንና ያደራጀኸውን “#አልሸባብ ” የተባለ የዳቦ ስም ያወጣህለትን የሶማልያ ወጣቶች ቡድን መሣሪያ ሰጥተህ ታስታጥቅና “የሀገር ሉአላዊነት ተደፍሯል” ምናምን ቅብጥርስዬ የሚል አጀንዳ ከች ታደርግና፤ ፒፕሉን አፉን ታስይዝልኛለህ። ቅድሚያ ለሀገር ሉዓላዊነት፣ የቅንጅት እስረኞች ጉዳይ ከሀገር ሉዓላዊነት በኋላ ይታያል፣ አሁን ምንም የሚያስቸኩል ነገር የለም። ትልና አዳሜን ዝም፣ ጭጭ፣ ጮጋም አሰኝተህ ትሸበለላታለህ። ከዚያም ነገሩ ሲረሳሳ አጥፍቻለሁ ይቅር በለኝ ብለህ አስፈርመህ ነፃ የሆኑትን ዜጎች አንገት አስደፍተህ አንቀጥቅጠህ ትገዛቸዋለህ።
የሆነ ጊዜም ችግር የተፈጠረ በመሰለህ ጊዜም የእነ ኃይሌ ገብረሥላሴን የለንደን የማራቶን ሩጫ ለ2 ሰዓትም ቢሆን ስንት ነገር እንዲያስተነፍስልህ አየር ላይ አውለህ ህዝቤን ታደነዝዘዋለህ። የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚሠራቸው ወንጀሎች #ምቹ ጊዜ በመጠቀም ማስቀየሻ በመፍጠር በኩል በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የማይገኝለት አገዛዝ ነው። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ፣ በሌላም በሌላም ጊዜ አይተነዋል፣ ዳስሰነዋል፣ ቀምሰነዋል። ከምር እነደ መንግሥታችን ህዝቡን ሿሿ የሚሠራ እልም ያለ አስቀያሽ አጭቤ መንግሥት በዚህች ምድር ላይ ያለ አይመስለኝም።
አሁንም የጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ መንግሥትም ወደ ቀልቡ ቢመለስ መልካም ነው። ሀገር በህግም በፍቅርም መግዛት አለበት። በስብከት ብቻ የሚገዛ ሀገር በምድር ላይ ፈጽሞ የለም። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የተረሸነው ኢንጅነር አንድ ተራ ግለሰብ ብቻ አይደለም። ሓላፊነቱ ከዶክተር ዐቢይና ከኦቦ ለማ ከአቶ ገዱም ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም። እነሱ ፖለቲከኞችና የኦሮሞ፣ የዐማራ፣ የትግሬና የደቡብ ወኪሎች ናቸው። ኢንጂነሩ ግን በብሔር ውክልና የተሾመ አይደለም። ኢትዮጵያ ለምትባለው ሀገርና በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ ልጆቿ መብራት ለማብራት፣ ከጨለማ ለማውጣት፣ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ሲጣደፍ በግፍ የተገደለ የ100 ሚልየን ህዝብ ግምት የሆነ የሀገር ዋልታ የሆነ ሰው ነው የሞተው።
ፖለቲከኞቹ በጉልበትም በብልጠትም በግድም የኢትዮጵያ መሪ ነን ማለት ልማዳችሁ ነው። ሳንመርጣችሁ የምትሾሙብን ማፍያዎች መሆናችሁም የታወቀ ነው። እንዲያም ሆኖ እኮ በሁሉም ዜጋ ዘንድ አትወደዱም። የህውሓት ሰዎች የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ስም መስማት አይፈልጉም። የዐማራ ስም ሲነሳ ያጥወለውላቸዋል። ይነስራቸዋልም። የዐማራን ጤፉን እየበሉ። በመብራቱ እየደመቁ፣ እንጨቱን እያነደዱም ቢሆን ዐማራውን ሲጠሉት ለጉድ ነው። የህውሓት ደጋፊ የሆነው የትግራይ ህዝብም እንደዚያው እንደህውሓት ነው።
ዶር ደብረ ጽዮን በአብዛኛው የዐማራና የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የሚጠሉ መሪ ናቸው። ዶር ዐቢይም በትግራይ ህዝብ ዘንድ ቁጥር 1 ጠላት ከተደረገ ውሎ አድሯል። ለዚህ ምስክሩ በትናንቱ የመቀሌ ሰልፍ ላይ የዐቢይን ስም፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ፣ የዐቢይንም ፎቶ ይዞ የተገኘ ይረሸናል የተባለ ይመስል ስለመደመር፣ ስለ ዐቢይ ትንፍሽ ሳይሏት ነው እንደጨፈሩ፣ ኤርትራን እንደተለማመጡ ሰልፋቸውን ያጠናቀቁት። ስለዚህ ትግሬ ከዶር ዐቢይ መንግሥት ጋር በግድ እንዲፋታ እየተደረገ ነው ማለት ይቻላል። ዶሩ ብቻ ነው ስለ እነሱ እሪሪሪሪ የሚለው እንጂ እነሱ አፍንጫቸውን ይዘውበታል።
ዶር ዐቢይም አጸፋውን በትናንትናው ዕለት ለትግሬዎቹ የህውሓት ኤሊቶች አስረግጦ ነግሯቸዋል። ሚልየኖች በሚከታተሉት ዝግጅት ላይ ህውሓት የምትጠላቸውን፣ ስማቸው ሲጠራ የሚነስራትን በሙሉ በስም እየጠራ አብግኗቸዋል። ታማኝ በየነን በህዝብ ሁሉ ፊት አክብሮ ህውሓትን አንገቷን አስደፍቷታል። አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃንን በመድረኩ ላይ፣ አክቲቪስት አሉላን በአዳራሹ ውስጥ፣ ሚልየን የህውሓት ደጋፊዎችን በያሉበት ቀርቅሮላቸዋል።
ዶር ዐቢይ ለማ መገርሳን፣ ወርቅነህ ገበየሁን ከኦህዴን፣ ደጉ አንዳርጋቸው፣ ደመቀ መኮንን፣ አምባቸው መኮንን፣ ሟቹን አቶ ተስፋዬን በግልጽ አመስግኖ ሲያበቃ ደብረ ጽዮንና ሽፈራው ሽጉጤን ባላየ ባልሰማ ጮጋ ብሎአቸዋል። ህውሓት ያሰቃያቸውን እነ ብርቱካን ሚደቅሳን አመስግኖ፣ ሲሳይ አጌናን አወድሶ፣ አበበ በለውን ጋብዞ ህውሓትን አብግኗታል። ከሁሉ ከሁሉ የህውሓት ፈጣሪ ተደርጎ የሚታየውን መለስ ዜናዊን እንደገደለባቸው የሚቆጥሩትን ጋዜጠኛ አበበ ገላውን አቅፎ ስሞ፣ አብሮም ፎቶ ተነስቶ ለልብ ድካምና ለደም ብዛት ዳርጓቸዋል። ከሁሉ ከሁሉ የመለስን ስም ላለመጥራት ” ያለፈው ሰውዬ ” በማለት ቆሽታቸውን ልጦታል። አራት ነጥብ።
እናም ፖለቲከኞች ራሳችሁ ተጠላልፋችሁ ስታበቁ የምትመሩትን ህዝብም በራሳችሁ መረብ አጥምዳችሁ የክፉ ኃሳባችሁ ማኅበርተኛ በማድረግ የጽዋ ቀማሽ ታደርጉታላችሁ። ዶር ዐቢይ ስም ሳይጠቅስ የቀን ጅብ እያለ በመጣራቱ ሰው ሁሉ ህውሓቶችን የቀን ጅብ እንዲላቸው አስደረገ። የቀን ጅቦች የተባሉትን ግን ከበጎቹ በረት በመለየት መንጋውን ከመበላት ሲያተርፍ አልታየም። አሁን እንደቀን ጅቦቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃነት ያለው ማን አለ። አንድ ወንጀለኛ የትግራይ ሰው ወንጀል ሠርቶ መቀሌ ከገባ ማን አባቱ ከዚያ ሊያመጣው? የቤተ ክህነቱ ጎይቶም እንኳ ባቅሙ ለአጣሪ ኮሚቴው ቃልህን ናና ስጥ ሲባል ” አልችልም መቀሌ ነው ያለሁት፣ አልመጣም ብሏቸው አርፏል። መቀሌ የወንጀለኞች መደበቂያ ምሽግ ሆናለች ማለት ነው። ለዚህ ነው ጠሚዶኮ ” ከህዝቡ እንዳንቀያየም ብለን ነው ወንጀለኞቹን ዝም ያልናቸው እስከማለት የደረሱት።
አሁንም እደገምዋለሁ። የኢንጅነር ስመኘው በቀለን ጉዳይ ለማድበስበስ ባትሞክሩ ይመረጣል። ትግሬዎቹ ካልጠፋ ቀን ኢንጅነሩ በአደባባይ በቀን ብርሃን ከተረሸኑ በኋላ የኢንጅነሩን ፎቶ ይዛችሁ ” እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን ” ብላችሁ ትናንት በመቀለ ያለ ለቅሶ ከበሮ እየደለቃችሁ መዝለላችሁን አልወደድኩትም። የምን ማረሳሳት ነው። ዶር ዐቢይም ቢሆን በእኔ ዕይታ ልክ አይደለም። እንደሚናገረው ለኢትዮጵያ የሚያስብ ቢሆን ይህ የኢትዮጵያን ብርሃን ለመፈንጠቅ የሚታትርን ሰው መረሸን ሰምቶ ” አዝኛለሁ ” በምትል አጭር ቃል መግለጫ ሰጥቶ ነገሩን አድበስብሶ ማለፍ የለበትም ነበር ባይ ነኝ። የሌሎች ሀገር መሪዎች ቢሆኑ ኖሮ እንዲህ ያለ የመቶ ሚልዮን ሰው ግምት በግፍ በተገደለ ጊዜ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ይመለሱ ነበር። ነገር ግን ይኼን አላደረጉም።
በጥጋባቸው የተለያዩ ጎጠኛ የሃይማኖት መሪዎችን አስታርቄ ይዤ በመምጣት የኢንጂነር ስመኘው በቀለን ጉዳይ አዳፍነዋለሁ ተብሎ በድሮ እስታይል ህዝብ ለማደንዘዝ ታስቦም ከሆነ ይኼኛው ጉዳይ በቀላሉ የሚፈታ አይመስለኝም። በጠራራ ፀሐይ ያውም በመስቀል አደባባይ የ100 ሚልየን ህዝብ ግምት የሆነ ሰው እየተገደለ እያየ የኢትዮጵያን ህዝብ እነ አባ መርቆሬዎስን ይዞ በመምጣት ማስቀየስ የሚቻልም አይመስለኝም። እነሱስ ቢሆን እንዲሁ ከመሬት ተነስተው እሺ ብለው እንዴት ይመጣሉ? እኮ እንዴት ይመጣሉ? ስብከት እንጂ ህግ ወደማያስተዳድራት ሀገር እንዴት አምነው ይመጣሉ?
ጎንደርና ትግራይን በአንድ ካምፕ፣ በአንድ ማዕድ በዚህ ሰዓት እንዴት አብሮ ማስቀመጥ ይቻላል?  ሌላ የ3 ተኛው የዓለም ጦርነት ለማስነሳት ካልሆነ በቀር እንዴት ይሆናል። የድርድሩ አካሄድ እስከአሁን ለህዝብ ግልጽ ባይሆንም መታረቃቸው ግን እስየው። ግዝት መፍታታቸውም እሰየው። ነገር ግን መሠረታዊው የሃይማኖት ልዩነት ሳይፈታ የሀገርቤት ጠላና እንጀራ ስለናፈቃቸው ብቻ እሺ፣ እሺ፣ በጄ ይሁን ይሁን ብለው ታረቅን ያሉት ነገር ውኃ የሚቋጥር አይመስለኝም። እናም በደንብ ቢታሰብበት መልካም ነው።  ሲጀመር መጀመሪያም ቢሆን እንደኔ ተንቦቅቡቀውና ፈርተው መስሎች እግሬ አውጪኝ ብለው መለስ ዜናዊን ፈርተው የነኩት። እና ታዲያ አሁን በምን ሂሳብ ይመጣሉ? ቤተክህነቱም፣ ቤተመንግሥቱም እኮ አሁንም ፀረ ዐማራ ነው። ፋርጣዎች ነግሬያችኋለሁ። በደንብ አስቡበት። እንደሰማሁት ከሆነ እናንተም ጠርጥራችኋል፣ መስከረም 8/2011 እንመጣለን ብላችሁታል ተብሎ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም በብዙ ጉትጎታ ከጠሚዶኮ ጋር አብራችሁ ለመመለስ መወሰናችሁ ተሰምቷል። አዎ ዋል አደር ብላችሁ አስቡበት። እኔ ተናግሬያለሁ።
ያው እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ የውጪው ሲኖዶስ ጳጳሳት በእምነታቸው በኩል ፀረ ማርያም እንደሆኑ ይታወቃል። በቤተሰብ ፍቅር ተጠምደው ቤተክርስቲያንን በዘመዳ ዘመድ እንደሞሉ ከሚነገርላቸው ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ እና አሁን በሚታየው የጆፍ ጆፍ እርቅ ተሳታፊ ያልሆኑት የካናዳው ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ብቻ ናቸው በሃይማኖት የማይታሙት። ፓትሪያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እንዲያውም በግድ እየጎተቱ እያመጧቸው እንጂ በአርምሞ ላይ እንደሆኑ ነው የሚነገረው። በፓትሪያርኩ የሚነግዱት ሌሎቹ ናቸው እንጂ ፓትሪያርኩ አንዳች ሲናገሩ እስከአሁን አልተደመጡም። በሃይማኖታቸውም እንደማይታሙ ይነገራል።
እናም ሌሎቹ ጳጳሳት በሃይማኖት ከጠሚዶኮ ሃይማኖት ጋር ተቀራራቢ ብቻ ሰይሆን አንድም ናቸው። አንዳንዶቹ እንዲያውም ታቦት አያስፈልግም፣ ኢየሱስ አማላጅ ነው። ገድልና ድርሳናት ከቤተክርስቲያን ይውጡ የሚሉት እኮ ናቸው አሁን እርቅ ብለው በፈጣጣ ከች ያሉት። ፒያኖና ጃዝ፣ ኦርጋንም በመቅደስ ካልገባ ባዮቹ እኮ ናቸው አሁን የዕርቁ ቀንደኛ ደጋፊ የሆኑት። አቡነ መርቆሬዎስ ከድሮ ጀምሮም ቢሆን ስልጣኑን እንደማይፈልጉ በብዙ የቅርብ ሰዎቻቸው ተነግሯል። የውጪው ሲኖዶስ በእነ አባ ወልደትንሳኤ ምንፍቅና፣ በእነ አባ ሚካኤል ምንፍቅና፣ በእነ አባ ገብረ ሥላሴ ምንፍቅና በመታመሷ ምእመናኖቿንም ገቢዋንም አጥቷ ለመሞት አንድ ሳምንት የቀራት እንደነበረች ይታወቃል። እናም እሷን የማዳን ሥራ ነው አሁን የተሠራው።
አባ ገብረ ሥላሴና አባወልደትንሣኤ በአውስትራሊያ ከመናፍቁ በጋሻው ደሳለኝ ጋር የሠሩትን ፀያፍ ሥራ ሁሉም ያውቀዋል። በአትላንታ ማርያም እነ አባ ሚካኤል በፍርድቤት ድረስ ተካሰው የደረሰባቸውን ውርደት ያውቃሉ። እነ ልዑለ ቃል፣ እነ ፓስተር መላኩ በመደመር ሂሳብ ከች ሊሉ እኮ ነው የተፈለገው። እናም ዶር ዐቢይ እነዚህን የተሃድሶ አራማጆች ነው ከሞት የታደጋቸው። ከመጥፋትም ያዳናቸው። እና እንዲህ ያለው የእምነት ችግር ሳይጠራ በስመ “መደመር” በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መርመስመስ አይታሰብም። አሁን አባ መዓዛም ሊደመር ነው ማለት ነው። በእመቤታችን ላይ የተሳለቁት፣ ” ጥንተአብሶ አለባት ” ብለው በግልጽ መጽሐፍ የጻፉት አባ መልከ ጸዴቅም በፈጣጣ ዝም ተብለው ሊደመሩ ነው ማለት ነው? አልገባኝም። ያዋከቡት ነገር…  ሆኖ ነው የሚታየው።
አሁን እናት ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁለት ባል ሊኖራት ነው ማለት እኮ ነው። በ8 ተኛው መቶ ሺ በመጨረሻው ዘመን እምዬ ተዋሕዶ ቅድስት ቤተክርስቲያን የሁለት ወንዶች ሚስት ልትሆንልን ነው ማለት እኮ ነው። ሁለቱም ባሎቿ ደግሞ ዲያስፖራ የነበሩ መሆናቸው ነው የሚገርመው። አቡነ ማትያስና አቡነ መርቆሬዎስ። ይሄ ከምር ጸያፍ ነው። በመደመር ሂሳብ ወደ ቤተክርስቲያን የሚገባ የርኩሰት ትምህርት ነው። ከሆነም አንዱን ሽሮ አንዱን ማስቀጠል እንጂ ሁለት ፓትሪያርክ ለጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን ፈጽሞ አይገባትም። ከተቻለ አንዳቸው ሥልጣኑን በገዛ ፈቃዳቸው ይልቀቁ እንጂ እናቴን ለሁለት ወንዶች ስትዳር እንደማየት አፀያፊ ነገር የለም። እርግጠኛ ነኝ አቡነ መርቆሬዎስ ቢጠየቁ ፈቃዳቸው እንጦጦ ኪዳነምህረት ገዳም ገብቶ መቀመጥ ብቻ ነው። ፓትሪያርኩ እንዳይናገሩ ግን ለጎሙዋቸዋል። በ12 ቁጥር ሚስማር ነው የጠረቀሙዋቸው። አሁን እኔ የምፈራው ከሁለት አንዳቸው ፓትሪያርኮች የተፈጥሮ ሞት ቢሞቱ እንኳን የሚፈጠረው የዘር ፖለቲካ ፍጅት ነው። እናም አረጋግታችሁ። ነገሩን በደንብ መርምራችሁ። የበሰለ አካሄድ ብትሄዱ ለእኔ ፈቃዴ ነው። አዲስ አበባ ያለው ሲኖዶስ ገና ከታጋይ ጳጳሳት ቁጥጥር ነፃ አልወጣም። ይኸው ነው።
እናም ጠሚዶኮዬ የአሜሪካ ግርግሩን ተወት አድርገህ ፊትህን ወደ ሀገር ብታዞር መልካም ነው። ስማ ልንገርህ ደመቀ መኮንን ጓዱ ሞቶበት ለቀብር ባህርዳር ነው ያለው። ለማ መገርሳ ከአጠገብህ የማይለይ ጓድህና አለቃህ መሆኑን ትናንትም ስለነገርከን ከአጠገብህ ነው ያለው።  ውጭ ጉዳይህ ተቆጣጣሪም ጠርናፊህም ስለሆነ አይለይህም መቼ ሥራውን እንደሚሠራ እግዜር ይወቀው እየተባለም መሆኑን ልነግርህ እወዳለሁ። ገበየሁ ከጋርዶችህ እንደአንዱም እየተቆጠረም ነው። የቀን ጅቦች ያልካቸውም የአንተን ከአዲስ አበባ መውጣት አይተው ምንም ባይፈይዱም እንኳ አሁን አዲስ አበባ ናቸው ያሉት እየተባለ ነው። እናም 4 ኪሎን እንዲህ ወለል አድርገህ ከፍተህ ትተህ በአሜሪካ ከ60 ዎቹ አዛውንቶች ጋር መሟገት፣ ከአርቲስቶች ጋር ፎቶ መነሳት፣ ካለው ሁኔታ አንጻር ተገቢ አይደለም። እኔ ተናግሬያለሁ። ስበከቱን ትተህ ሀገሪቷን በህግ አስተዳድራት። ኢየሱስም ከፍቅር ስበከት በተጨማሪ ጅራፍ ሰርቶ እየዠለጠና እየገረፈ ከቤተመቅደሱ ሥርዓት፣ ህግና ደንብም ውጪ የነበሩትን ሲያስወግድ እንደነበር ለአንተ አይነገርህም። ስበከት ብቻውን 100 ሚልዮን ህዝብ አይመራም።
እስላሞቹን በዓረብኛ ቁራን እየቀራህ። ኦርቶዶክሶቹንም እንዲሁ በሚረዱትና በሚገባቸው ቋንቋ ስላወራሃቸው በቃ ሰሙህ ተቀበሉህ ማለትም አይደመም። እናም ዳይ ወደ ሥራ ተመለስ። ዙረቱ ይብቃ። አሁን ዜጎች እየጠየቁ ያሉት በጠራራ ፀሐይ፣ በመስቀል አደባባይ፣ የተገደለውን የሀገር አደራን በጫንቃው የተሸከመ ብሔራዊ ጀግና ገዳዮቹን መንግሥትህ ለፍርድ እንዲያቀርብ ነው።
ህዝብ እየጠረጠረ ነው። እንዲህ እያለ እየጠየቀም፣ እየጠረጠረም ነው። እስቲ ለመልሱም ተዘጋጁበት።
፩ኛ፦ በግብጽ ጉብኝትዎ ወቅት አልሲሲ ወላሂ፣ ወላሂ ብሎ ያስማሎት ለምንድነው?  ከመጋረጃው በስተጀርባ የሚገኘው የመሃላው ምስጢር ምንድነው? ከእርስዎ የግብጽና የኤምሬት የኤርትራም ጉብኝት በኋላ ኢንጂነሩ በግፍ ሲገደል ይህን ያለመጠየቅ አይቻልምና እንዲህም የሚጠይቁ አሉ። እናም የእርስዎ ምላሽ ምን ይሆን?
፪ኛ፦ የተረሸኑትን ኢንጂነርን ጠርቶ ማብራሪያ መጠየቅ ሲቻል ምሑራንን ሰብስበው “የህዳሴው ግድብ ከእንግዲህ ወዲህ በአስር ዓመት ውስጥም አያልቅም” ብለው መናገርዎ ተሰምቷል። ሌላ ጊዜ ቃል በገቡት መሠረት እያንዳንዱ ስብሰባዎ፣ ጉብኝትዎ፣ ደም ሲሰጡ ጭምር በቴሌቭዥን ይተላለፋል። ይኼኛው ግን ለምን ተዋጠና በእነ መምህር ስዩም ተሾመ በኩል ብቻ እንዲተላለፍ ፈለጉ?
መቸም ይህ ንግግርዎ ዝም ተብሎ የተነገረ ተራ ንግግር እንዳይደለም የፖለቲካ ትርፍና ኪሳራውን በደንብ አስልተውና ጨምቀው የተናገሩት መሆኑም ግልጽ ነው። እናም የህዳሴው ግድብ ችግር ኢንጅነሩ ነው ወይስ የሜቴክ?  ገልጸው ይንገሩን ጌታው። ብዙዎች ምንአልባትም የእርስዎ ይኽን ቃል ተናግረዋል መባልን የሰሙት ” የቀን ጅቦች ” የሚሏቸው ሰዎች ነገሩን ከእርስዎ መንግሥት ጋር ለማያያዝ እና ለማስጠየቅ ሲሉ ባላቸው ኔትወርክ አማካኝነት ይኼን ፈጽመው ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬም አለኝ። እናም መልስዎን በቶሎ ለህዝብ ይፋ ቢያደርጉ።
፫ኛ፦ ኢንጅነሩ ከመረሸኑ በፊት የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የኢንጅነሩን የግል ሾፌር በሌላ እንቀይርልሃለን በማለት ከሥራ ካስወገዳችሁት በኋላ ኢንጂነሩ ብቻቸውን መኪናቸውን እንዲያሽከረክሩ አድርጋችኋል ይባላል። እናም ይኼ ነገር ምን ያኽል እውነት ነው? መልስ የሚሻው ጥያቄ ነው።
፬ኛ፦ ኢንጂነሩ ከመገደሉ ከሁለት ቀን በፊት በእርስዎ እዝ ስር የሚታዘዘው የመከላከያና የደኅንነት ተቋም በመስቀል አደባባይ ያሉትን ካሜራዎች እንዲነሱ አድርጓል ተብሏል።ኢንጂነሩ ከተረሸኑ በኋላ ግን በትናንትናው ዕለት ሐምሌ 20/2010 እንደገና ካሜራዎቹ እየተገጠሙ መሆናቸውም ታይቷል። እና ይኼ ነገር እንደምን ይታያል ክቡርነትዎ?
፭ኛ፦ እርስዎ ከግብጽ ጉብኝትዎና ወላሂ ወላሂ ብለው ከማሉ በኋላ ወደ ሀገርዎ ሲመለሱ በግብፅ የነበሩ የኦነግ ወታደራዊ አመራሮችን በአውሮፕላንዎ ጭነው መመልስዎ ይታወቃል። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ለግብጽ መንግሥት በግልጽ በአደባባይ ግብጽ ትርዳን እንጂ የህዳሴውን ግድብ እናስቆምላታለን ብለው ቃል የገቡ ሰዎች ናቸው። እናም ክቡር ሆይ ነገሩ እንዴት ነው?
፮ኛ፦ ኢንጂነሩን በቶሎ ናና ጋዜጣዊ መግለጫ ስጥ ብሎ ጠርቶ ሲያበቃ ጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጥበት አዳራሽ እየጠበቁት ሳለ ኢንጂነር ስመኘው ሞተ እኮ ብሎ ጋዜጠኞቹን ወደ ኢንጂነሩ ወደ ተረሸነበት መስቀል አደባባይ መላክስ እንደምን ያለ ቀልድ ነው?
ከዚያ ደግሞ እርስዎ ወደ አሜሪካ ሽው ብለው ሄዱ። የኢንጅነሩንም ሞት በሰሙ ጊዜ ” ስመኘው የሚባል ሰው ሞተ ” ብለው ነገሩን አቅልለው ተናገሩ። እደግመዋለሁ ኢንጂነሩ ሁላችሁንም ይቦንሳችኋል። አብዛኛዎቻችሁ ለኢትዮጵያ ጤፍ የሚቆላ ምላስ ተሸክማችሁ የምትዞሩ ውስጣችሁ ግልጽ የልሆነ አፈ ቅቤዎች ናችሁ። ኢንጂነሩ ግን ንፍሮ በሚቀቅል፣ ዳቦ በሚጋግር በረሃ ውስጥ ከቤተሰብ ተለይቶ መከራውን ሲበላ የነበረ ጀግና የሆነ ዜጋ ነው። እናም የዚህ ብሔራዊ ጀግና አሟሟት የፋርጣዎቹን መናፍቃን ንስሀ ሳይገቡ፣ በአደባባይ የጻፉትን መጽሐፍ ሳያቃጥሉ፣ የሰበኩበትን ሲዲ ቪሲዲ ሳያስወግዱ፣ እናት ቤተክርስቲያንንም ይቅርታ ሳይጠይቁ ሰተት ብለው ዘው ብለው በቤተክርስቲያን ይሰየማሉ ብለው አይጠብቁ። እነሱን ይዤ መጥቼ የኢንጂነሩን አሟሟት አፈር አልብሼ አልፋለሁ ብለውም አያስቡ። የተገደለችው ኢትዮጵያ ናት ይሄን አስረግጠው ይወቁ።
በተረፈ ” እርስዎ የቀን ጅቦች የሚሏቸውም ገድለዋቸው ከሆነ ” መደመር፣ ፍቅር ቅብጥርሴ የሚሉትን ይተዉትና ሃቁን ቁጭ ያድርጉልን? እርግጠኛ ነኝ ገዳዮቹ አይደለም ትግራይ አፍጋኒስታን ቢደበቁ የሚለቃቸው የለም። ዝም ብሎ በቃ ሊገድሉ፣ ሊዘርፉ፣ ሊያፍኑ የሚችሉት የህውሓት ሰዎች ናቸው በሚል ሂሳብ ነገሩን አለባብሶ ማለፍ የሚቻል አይመስለኝም። በዚህ ጉዳይ ህውሓትም ራሷን ማጥፋት አትፈልግም። እናም ዜጎች በሙሉ ባልተጣራ ነገር አንድ ህዝብ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማድረግም አግባብ አይመስለኝም።
እናም ክቡር ሆይ ከእነ አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ ጋር ፎቶ መነሳትዎን ገታ ያድርጉና በአስቸኳይ ወደ መንበርዎ ይመለሱልን። ንጉሥ ሆይ ወደ ዙፋንዎ በመመለስ ፍትህን ለኢትዮጵያችን ያሰጡልን። ፍትህ ለኢንጅነር ስመኘው በቀለ ያሰጡ።
አክባሪዎና በዕድሜ ታላቅዎ በሙያና በሥልጣን በእውቀትም ከእግርዎ ትቢያ በታች ታናሽዎ የምሆን ስደተኛና ከርታታ ወንድምዎ ነኝ።
በመጨረሻም  |~ ብሔራዊው ጀግናና በአደባባይ የተረሸነው ኢትዮጵያዊው ኢንጂነር የማክሰኚቱ ልጅ ዛሬ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ሥርዓቱ ይፈጸማል። መልካም የዘላላማዊ እረፍት ለጀግናችን። ኢትዮጵያ ሆይ እግዚአብሔር ያፅናናሽ።
ሻሎም  ! ሰላም !
ሐምሌ 22/2010 ዓም
ከራየን ወንዝ አጠገብ።
Filed in: Amharic