>
5:21 pm - Tuesday July 20, 3002

ለእውነት መታገል መጀመሪያ ይጎዳል- ኋላ ያስከብራል፡፡ (ብርቱየ እንኳን ደስ አለሽ) - ታምራት ታረቀኝ 

ለእውነት መታገል መጀመሪያ ይጎዳል- ኋላ ያስከብራል፡፡ (ብርቱየ እንኳን ደስ አለሽ)
  ታምራት ታረቀኝ  
“ለእነርሱ ያስፈገጋቸው፣ ያስገረማቸው ጉዳይ ግን እኔን ሁሌም የምኖርለት፣ የምቆምለት፣ እንዳንዴም የምታሰርበት እና የምፈታለት ታላቅ ቁም ነገር ነው። የሕግ የበላይነት ወይም ሕገመንግሥታዊነት። ”     ብርቱካን ሚደቅሳ ታኀሣሥ 18/2001 ዓ.ም በየእለቱ አዳዲስ ነገር እያመጡ መሽቶ መንጋቱን በጉግት አንድንጠብቅ ያደረጉን፤በሰሞኑ የአሜሪካ ጉብኝታቸው ደግሞ በሰአት ልዩነት ምክንያት በቀጥታ ስርጭት ካልተከታተልን  የማንረካ ሆነን ቁጭ ብሎ ለማደር ያበቁን ጠቅላይ ምኒስትር አብይ  አህመድ በየቦታው መጋረጃዎችን እየከፈቱ በጥሩም በመጥፎም አጀኢብ የሚያሰኙ ነገሮች እያሳዩን እያሰሙን ነው፡፡
በሁሉ ነገሮች ደስተኛ ስሆን አንዱ ግን በውስጤ ለአመታት ተሸፍኖ የተቀመጠንና በቅርቡ ጥቂቶች  ሚጢሚጣ ነስንሰውበት በጣሙን ሲያቃጥለኝ የሰነበተ ቁስሌን የነካ በመሆኑ እጅግ በጣም ተደስቻለሁ፡፡
 በዋሽንግተን ከተከናወኑ ፕሮግራሞች በአንዱ ወደ መድረክ ወጥተው ገና ንግግራቸውን ሲጀምሩ  በመጀመሪያ አሉ፣ “ በመጀመሪያ  በኢትዮጵያ የሴቶች ትግል ውስጥ ደማቅ ቀለም ቀብታ ያለፈች ጀግና ሴት በዚህ አዳራሽ በእኛ መካከል እንዳለች ስለሰማሁ ብርቱካን ሚደቅሳን እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ፤ ብርቱካን ሚደቅሳ የፖለቲካ ነጋዴ ሳትሆን የነጻነት ታጋይ ስለሆነች፡ ”አሉ፡፡ሰማሁ፤ ማመን አቀተኝ መልሼ ከልሼ አዳማጥሁት፡፡
ትልቅ ሰው የሚከብረው በትልቅ ሰው ነውና በእጅጉ ደስ አለኝ፡፡በጣም ብዙ ሰዎች እንደተደሰቱም እገምታለሁ፡፡የእኔ ግን ከሁሉም ይለያል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያት ብትሉኝ ብርቱካንን ከፖለቲካ ውጪ ለማድረግ  ከከይሲው መለስ ዜናዊ ባልተናነሰ የትግል አጋሮቼ ፤የእምነት ተጋሪዎቼ ባለችን በእኛ የተፈጸመባትን በደል ስለማውቅ፡፡ ይህ ውስጤ ተቀምጦ የሚያደማኝ ጽፌም ተናግሬም ሊሽርልኝ ያልቻለ ቁስል ነው ዛሬ  በአብይ አህመድ ንግግር ፈውስ ያገኘው፡፡ለሁሉም ግዜ አለው፤ ክብር ምስጋና ለአንድየ የማሪያም ልጅ ይሁን፡፡ ከአስር አመት በላይ የዘለቀ ቁስሌ ላይ ሚጢሚጣ የመነስነስ ያህል ሆኖ ከአንድ ወር በላይ ሲያቃጥለኝ የከረመው ጉዳይም በዚሁ ንግግር ታከመ፡፡
ብርቱካን ጋር ለመጀመሪያ ግዜ በግንባር ተገናኝንተን የተዋወቅነው በምርጫ 92 ዋዜማ ነው፡ ከግል ተወዳዳሪነት ወደ ኢደፓ ተወዳዳሪነት ለመቀየር ልናግባባት፡፡ እሷ ግን ገና በወጣትነቷ ወደ አመቸበት እየተገላበጡ መነገዱ የማይሆንላት የእምነት ሰው ነበረችና የለም ትናት የተናገርኩትን ዛሬ ማጠፍ አይቻለኝም ብላን ተለያየን፡፡ ከዛ በኋላ ቅንጅት፣ እስር ቤት አለና አንድነት በጣም አቀራረበን፤የብርቱካንን ማንነትና ምንነት በቅጡ ለመገንዘብ የቻልኩትም በዚህ ወቅት ነበር፡፡በተለይ ደግሞ ዳግም ወደ ወህኒ ከመላኳ ቀደም ብለው የነበሩት ሀያ ቀናት ምንግዜም የሚረሱኝ አይደሉም፡፡  በዛን ወቅት የነበረው ነገር እኔን ይህን ያህል ካቆሰለኝ ብርቱካንን እንዴት አድርጓት ይሆን ብዬ ሳስብ የህመም ስሜቴ ይጨምራል፡፡
አሁን የነጻነት ጮራ ፈንጥቋልና ሰዎችን በመብራት የሚፈልግ መሪም አግኝተናልና ብርቱካን የሰራችውንም የተሰራባትንም ለመጻፍ እሞክራለሁ፡፡ በቅርቡ ስለ ብርቱካን ጽፌ  አናወጣ ብለው ቁስሌን እዳባባሱት  ባለ ድረ ገጾች አታሚዎችና አሳታሚዎችም የፖለቲካ ነጋዴ ሆነው  አናትምም ካላሉኝ በቀር፡፡
ሰው ጨራሽ የነበረውን የኤድስ በሽታ ለመግታት የተቻለው ማለባበስ ይቅር በመባሉና በእኛ ይብቃ ትውልድ ይዳን ያሉ የቫይረሱ ተጠቂዎች አደባባይ ወጥተው መናገር በመጀመራቸው ነው፡፡ ፖለቲካችንም ይሄው ያስፈልገዋል፡፡ መቼም ይሁን እንዴት የአስከፊውና አስቀያሚው  የፖለቲካ ቫይረስ ተጠቂ የሆን ወይንም የነበርን ሰዎች ጎመን በጤና ማለቱንም ሆነ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን የሚሉ ለ 21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥኑ ብሂሎችን ወደ ጎን ብለን የነበርንበትን፤ ያለፍንበትን የሰራነውንና የተሰራብንን በድፍረት ግን በሀቅና በማስረጃ ለትውልዱ መማሪያነት ማቅረብ የሚጠበቅብን ይመስለኛል፡፡ደፍረው ንስሀ ሊገቡ ኃጢአታቸውን በይቅርታ ሊያጸዱ ያልፈለጉና ዛሬም ያለ እኔ እያሉ ትናንት ያበላሹት ዛሬን አጨልሞብን ነጋችንንም ለማበላሸት የሚታትሩና አደብ አልገዛ ያሉትን ማንነታቸውን አላወቁት ከሆነ ማሳወቅና አረፍ በሉ ማለት ይገባል፡፡አስር ጣትን ወደሌላኛው ጎራ በመቀሰር ብቻውን ምንም እንዳልመጣ አይተናል፡ ደግሞስ የራስን ቤት ሳያጸዱ የሌላውን ቆሻሻ መናገርስ እንደምን ይቻላል፡፡
በቁስሌ ላይ ሚጢሚጣ መነስነስ ያልኩት ሰሞነኛ ጉዳይ፡
ወያኔንና ደደቢቶችን ስናወግዝ የኖርንበትን ነገር ሁሉ ለአፍታ ቆም ብለን ብንፈትሽ ከምንቃወመው ነገር የጸዳን ነን ብለን ለመናር የሚያስችል ነገር የምናገኝ አይመስለኝም ፡፡ ከዚህ አንዱንና ከአሁኑ ጉዳዬ ጋር የሚዛመደውን ላንሳ፡፡ ወያኔ የመናገርና የመጻፍ በጥቅሉ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነትን ያፍናል ብለን ጮኸናል፤ በመንግስት ተቀጥረው የሚሰሩ ጋዜጠኞችን ያላልናቸው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በተቃውሞው ጎራ ያሉ ራዲዮ ይሁን ቴሌቭዥን ፣ ጋዜጣ ይሁን ድረ-ገጽ ሁሉም ወያኔን ከተቃወንበትና የመንግስት ጋዜጠኞችን ስናወግዝ ከነበረበት ጉዳይ የነጹ ናቸው ብሎ መናገር ይቻል ይሆን? የእኔ መልስ አይደለም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም ሰሞነኛውንና በቁስሌ ላይ ሚጢሚጣ የመነስነስ ያህል የሆነብኝን ጉዳይ በማስረጃነት ላቅርብ፡፡
ከሰኔ 16 የመስቀል አደባባ ሰልፍ ማግስት ወትሮ ከማላውቀውና ከዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ዋዜማ ጀምሮ ደምበኛ ወደ ሆንኩት እና  በውሸት ነግዶ ለማትረፍ የሚደረግ ህሊና ቢስነት እያሳዘነኝም ቢሆን የምጎበኘውን ዩ-ቲዩብ ስቃኝ  አዲስ አበባ ፒያሳ ሙሀሙድ ሙዚቃ ቤት አጠገብ እርጋታ ወስደው በተለያየ መንገድ ስሜታቸውን የሚገልጹ ወጣቶች አየሁና በአተኩሮ ስከታተላቸው ብርቱካን ሚደቅሳ የሴት አንበሳ ሲሉ ሰማሁ፡፡  በዚህ ወቅት  ከመቅጽበት ብርቱካን ከፊቴ መጥታ ግጥም አለች፡፡ይሄኛው ያኛው ብየ አሁን እዚህ ልገልጸው የማልችለው ትውስታ በአይነ ልቦናዬ ድቅን እያለ እንደ በድን አደረገኝ፡፡ ትንሽ ስረጋጋ ዩ-ቲዩቡን ዘግቼ ጣቶቼን ኪ-ቦርድ ላይ ማሳረፍ ጀምርሁ፡፡
እንዲህ ተዜመ በፒያሳ ብርቱካን ሚደቅሳ የሴት አንበሳ የሚል ርዕስ የሰጠሁትንና ስሜቴን የገለጽኩበትን ጽሁፍ ወደ ሰባት ለሚሆኑ ድረ-ገጾች ላኩት፡፡ከፊሎቹ ከመቅጽበት ለንባብ ሲያበቁት ከፊሎቹ ተዉት፣ሁለት ቀን ሶስት ቀን ሳምንት አየኋቸው የለም፡፡አዘንኩ፣ለምን ይህን ሊያደርጉ ቻሉ፣ እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው ብዬ ራሴን ጠየቅሁ፡፡ቢሆንም መልስ አላገኘሁም ነበር አሁን ግን መልሱን ከጠቅላይ ምኒስትር ዶ/ር አብይ አገኘሁ፡፡
ነገሩን ከማሳዘን አልፎ አናዳጅ ያደረገው ስለ ብርቱካን የተጻፈ ጽሁፍን ለማስነበብ ያልፈቀዱት ወገኖች የእኔ ለሚሉዋቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች መድረክ ሆነው ከማገልገል አልፎ እነዚሁኑ ሰዎችን አይነኬ አድርገው አትንኩብን የሚሉ መሆናቸው ነው፡፡እነዚህ አይነኬ ሰዎቻቸው ላይ የቱንም ያህል በመረጃና ማስረጃ የዳበረ ጽሁፍ ብትልኩ አያስተናግዱም፡፡ ምክንያት ሰዎቹ ለእነርሱና በእነርሱ አይነኬ ናቸውና፤ ከዚህ የሚብሰው ደግሞ እነርሱ በማይፈልጉት ሰው ላይ ተራ አሉባልታ ተራ ስም ማጥፋት ያዘለ ጽሁፍ ያስተናግዳሉ፡፡
ይህም ብቻ አይደለም ዘረኝነት የሚያቀነቅኑ ጥላቻ የሚሰብኩ አንድነትን የሚሸረሽሩ ጽሁፎች በእነዚሁ ገጻቸውን ስለ ብርቱካን ለተጻፈ ጽሁፍ በነፈጉ ድረ ገጾች ይስተናገዳሉ፡፡ የእነዚህን እነማንነት መዘርዘር የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም ምክንያት ለቃባሪው ማርዳት ስለሆነ፡፡ጎመን በጤና በማለት አይናገረው እንጂ ድረ-ገጾችን የሚጎበኝ ሰው ሁሉ ትናንትም የታዘበው ዛሬም የሚታዘበው ነው፡፡ለበለጠ ማረጋጋጫ ደግሞ ይህንንም ጽሁፍ ለሁሉም ስለምልከው ታውቁዋቸዋላችሁ ትለዩዋቸዋላችሁ፡፡ከፍሬአቸው ታውቁዋቸዋላችሁ አይደል የሚለው መጽኃፉ፡፡
በመጨረሻ ለእነዚህ ወገኖቼ ምክር ልትሆን ከቻለች የአቤ ጉበኛን አባባል ላስታውስ፡፡
“ለመሆኑ እነ ግርማዊ ጭጭ በሉና እነ አፈንጉስ አይተንፍሱ እንደዲመኙት ሁሉ ሥልጣን የእነሱ ቢሆን ኖሮ ምን ሊሰሩ ኖሯል፤ ለነጻነት ለእኩልነትና ለፍትህ ስንታገል ኖርን የሚሉ ሰዎች ለምን ሀሳብን በመጨቆን ያምናሉ ጥቅምን ሲያሳድዱ ሊደርስ የሚችለውን የማይጠገን አደጋ እያዩስ እነሱም ለምን ይታወራሉ እኔ ግን ማንም ዋሾ ይጥላኝ እንጂ ያየሁትን መግለጼን መተው እንደ ከፍተኛ ሀገርን መካድ ስለምቆጥረው ያየሁትን እውነት በቀልድ መልክ አቅርቤለችኋለሁ  ” አቤ ጉበኛ 1969 ዓ ም
Filed in: Amharic