>

ኧረ  ተዉ እናንተ ሰዎች በእሳት አትጫወቱ!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ኧረ  ተዉ እናንተ ሰዎች በእሳት አትጫወቱ!!!
አሰፋ ሀይሉ
ከሰሜን ኢትዮጵያ በኩል የሚሰሙ ደስ የማይሉ ወሬዎች አሉ፡፡ በጋዜጣም በማህበራዊ ድረገፆችም፡፡ እንደወሬው ከሆነ የፌዴራል መንግሥቱ የፖሊስ ሠራዊት ባልደረቦች ከፌዴራሉ የልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት የተቆረጠ የእሥር ትዕዛዝ ይዘው ተጠርጣሪዎቹ ይገኙበታል ወደተባለው ወደ ትግራይ ብሔራዊ ክልል ያቀናሉ፡፡ ያን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አልቀበልም ያለው የትግራይ ክልል ፖሊስ ሠራዊት ደግሞ የእሥር ትዕዛዙን ይዘው ወደ ክልሉ የመጡትን የፌዴራል ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል፡፡ ወይም ቃሉ አግባብ አይሆንም እንጂ በአንዳንድ ሰዎች አባባል ‹‹አግቷቸዋል››፡፡ የአንድ ሀገር ፌዴራል ፖሊስ ፤ በዚያው ሀገር ክልላዊ ፖሊስ ሲታገት ይታየን እስቲ?! ወይም በተቃራኒው አገላብጠን… በአንድ ሀገር ውስጥ ያለ ክልል የፖሊስ ሠራዊት አባላት ፤ ሥራቸውን በማከናወን ላይ እያሉ ፤ በፌዴራል ፖሊስ አባላት ተከበው ቢታገቱ እንደማለት አይደል???!!
በአንድ ሥርዓት ውስጥ እየኖርን እንዳለን ኢትዮጵያውያን ዜጎች – ወይም እንደ አንደ ዜጋ – ከዚህ በላይ ጆሮን ሊያም የሚችል – እጅግ አስገራሚ፣ አሳዛኝና ማፈሪያ የሆነ ሌላ ጉድ ምን ሊሰማ ይችላል??!! ኧረ ተዉ – ሀገርን ማስተዳደር እንደ ዕቃ-ዕቃ ጨዋታ የሚታይ ነገር አይደለም?! ኧረ ተዉ ወደየት እየሄድን እንደሆነ እያስተዋላችሁ ተጓዙ?!  ይሄ የሥርዓት አልበኝነት ነገር እኮ በቃ – ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ እየተባባሰ መጣ እኮ!! ማን ህግ አክባሪ፣ ማን አስከባሪ፣ ማን ህግ አፍራሽ፣ ማን ህግ አስፈጻሚ፣ ማን ህግ አውጪ፣ ማን ህግ ተርጓሚ እንደሆነ መለየት ያልተቻለበት አሳሳቢ ጊዜ ላይ .. እንደቀልድ ደረስን ማለት ነው???!! በፌዴራሉ የወንጀል ህግ ‹‹ወንጀል ናቸው ተብለው በተጠቀሱ ጉዳዮች ላይ ሕገመንግሥታዊ ሥልጣን ያለው ማን ነው?? – ግልጽ አይደለም እንዴ ይሄ??!! እና የምን ሥርዓት አልበኝነት ነው???!!! እንዴ?!! ኧረ ተዉ ይሄ ነገር ወደየት ሊሄድ እንደሚችል ረጋ ብላችሁ አስቡ??!!
ለነገሩ እኮ – በመሬት ላይ ተከሰተ የሚባለው እውነት ከሆነ እኮ – ለነገሩ – ይህ አሁን በትግራይ ክልል እየተደረገ እንደሆነ የምንሰማው ዓይነቱ ዓይን-ያወጣ ሥርዓት ዓልበኝነት – የመጀመሪያችን እኮ አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቷ – ለፌዴራሉ መንግሥት አንገዛም የሚል – በክልል ምሽግ የመመሸግና የማስመሸግ – እና እስቲ ልብ ያለሽ ነይና የምታስሪውን ውሰጂ እስቲ? – የመባባል ሥርዓት አልበኝነት የተጀመረችው ገና ያኔ ነው፡፡ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን – ከሶማሌ ክልል እንዲፈናቀሉ መደረጋቸውን ተከትሎ – የፌዴራሉ መንግሥት – በጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሚና አላቸው ያላቸውን በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ባለሥልጣናትና የሠራዊት አባላትን ታሥረው – ወደ ፌዴራሉ መንግሥት ማረፊያ ቤት እንዲወሰዱ ትዕዛዝ ሲሰጥ እኮ – ያኔም – ልክ እንዳሁኑ – ሁለቱም ክልሎች – ባለስልጣኖቻችንን አንሰጥም! እኮ እንዳሉ – በግልጽ አደባባይ እኮ ነው እንደቀልድ እንድንሰማው የታወጀልን!!! እንዴ!! ምን ማለት ነበር ያ??? ምን ማለትስ ነው ይሄስ?!!!
ይሄ እኮ የመንግሥታዊ ሥርዓቱን ቅቡልነት ማጣት እያመላከተን ያለ – እጅግ አደገኛ ምልክት እኮ ነው፡፡ ባለፈውስ ጊዜ – የሠራዊቱ አባል የነበረውን ኮሎኔል ደመቀን ክልሉ ሣያውቀው – በፌዴራሉ መንግሥት ሠራዊት አባላት ለማሠር የተደረገው ሙከራ?? እሱስ ምን ማለት ነበር?? እንዴ! በዚያን ወቅት እኮ – ህግን ፈርተው፣ ትዕዛዝን ተቀብለው፣ በህግ የተጣለባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት እየተጉ የነበሩ የአንድ ሀገር ሠራዊት አባላት እኮ ነፍስ ነው እንዲጠፋ – እንዲጠፋፉ የተደረገው?!!! እንዴ?!! እሺ ያስ ይሁን?? ‹‹በፌዴራል መንግሥቱ ፍ/ቤቶች በሌላ ወንጀል ተፈልጎ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶበታልና ወደ አዲስአበባ ላኩት!›› የሚለው በወቅቱ የአማራ ክልል እያስተዳደረው ለሚገኘው ማረሚያ ቤት የተላከውስ መልዕክት??!! እና የተሰጠውስ ምላሽ??? በትክክል የሀገሪቱ ህግና ሥርዓት – ከለየለት ሥርዓት አልበኝነት እና መንግሥታዊ አሸባሪነት ተላቅቆ – በስክነት ነገሮች መረጋጋትና በቁጥጥር ሥር መዋል እስኪችሉ ድረስ ያን ጊዜ – በዚህ ትርምስ ሰበብ – ስንት ቤተሰብን የሚያስተዳድር ምስኪን ዜጋ ነፍሱን አጣ??!! ማነው ለእነዚህ ሽፍታዊ ቁማሮችና ይዋጣልኖች ተጠያቂ የሆነው እና የሚሆነው??!!! ከዚያስ ወዲህ በዚህች ሀገር ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሠፈነ፣ ተከበረ ማለት ነው – ማለት ነው????!!!
ብቻ ግን እዚህች ሀገር ላይ ‹‹ጥጋብ›› በዝቷል፡፡ ጥጋብ ሊያሰማማንም ፤ ሊያስማማንም አልቻለም፡፡ ልክ የመዲናችን አሽከርካሪ አንዱ አንዱን ንቆ እንደሚንቀሳቀሰው ሁሉ – ልክ በመንገድ ስንተላለፍ አንዱ ለአንዱ መንገደኛ ዘወር እንደማይለው ሁሉ – በሀገሪቱ ያሉ ጥጋብ የተጸናወታቸው የክልልና ክልል፣ የፌዴራልና ክልል ኃይሎችም – እርስ በእርስ ሲተላለፉ – በጥጋብ አንዱ አንዱን ገፍቶ፣ ትከሻውን አሳይቶ – ኮቴውን ተለካክቶ – ተገፋፍቶ – ተደማምቶ እንዲሆን የሚፈልጉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ማለት ነው ወይ???? እንዲህስ ያሉት – በትልቅ ሀገራዊ የእሳት ዲፖ አጠገብ ለከት የሌለው ቤንዚን እየተራጩ ዕቃ-ዕቃ እንደመጫወት ያሉት ነገሮች – ወደየት እንደሚያመሩ በሰከነ አዕምሮ መረዳት የሚችል ሰውስ ከዚህች ሀገር ተጋፊ እና ተገፋፊዎች (እንደ አህያ??) መሐል አልፈጠረልንም እዝጌሩ ማለት ነው??!!! አወይ ኢትዮጵያዊ መሆን??!!!
መስከን አቅቷችሁ – እንዲህ በዕብሪታችሁ – የሀገራችንን ምስኪን ህዝብ ወደ እሳት ልትማግዱ ያቆበቆባችሁ – አይናችንን አናሽም ያላችሁ – እናንት ችኩል ጠብ-ነጂዎች – እባካችሁ!!! ኧረ እባካችሁ!!! ተዉ እባካችሁ!!! ረጋ ብላችሁ እስቲ አስቡ ለሀገር ለትውልድ እባካችሁ!!! ኧረ እያንዳንዱን ውሳኔያችሁን – እና እርምጃችሁን – በትውልድ ህይወት ላይ ቆማችሁ እየፈረዳችሁ እንደሆነ ይታሰባችሁ ላፍታ???!!! ኧረ ተዉ ተመከሩ! ተዉ! ተዉ! ተዉ – ከእዝጌር ተታረቁ???!!! ኧረ ተዉ…. ትውልድን የሚያህል ማሣ ላይ ተቀምጣችሁ . . . ተዉ በእሣት አትጫወቱ ?!!!!!!
/በመደምደሚያዬ … ‹‹እምቢ ካላችሁ – እዝጌር ሌላውን ሳታነካኩ – እንደ ተልባ እግር – ንቅል ያርጋችሁ !!›› የሚል የእርግማን መዓት አምሮኝ ነበር…፡፡ ግን የነሱ ጥጋብ መች አነሰና – ደሞ ደርሶ ከጥጋብ አምባ አጉል ልደባለቅ ማለት?? – ብዬ – በሠላም – ወደጎጆዬ – ውልቅ – ወይም – ጥልቅ!!!!!/
ዜጎችን ማናከስና ደም ማፋሰስ ባለፈው ይብቃ!!! ሠላምን እና ስክነትን እና መከባበርን እና የዜጎችን ደህንነትን እና ፍቅርን አጥብቀው የሚሹ ዜጎችን እግዜር ያብዛልን፡፡ አሊያ ግን – ወደፊት የባሰ ወሬ ስላለመስማታችን – ወይም ከዚህስ የባሰ ስላለመኖሩ – ምን ዋስትና አለን????!! ኧረ ተዉ አታሸብሩን ተዉ???!!! ልቦናውን ይስጣችሁ!! እኔ ግን በቃኝ አቦ!!! ቅ ጥ ል ል ል…. አልን እኮ!!! ‹‹በስንቱ ልቃጠል?!!›› አለች ብረት ምጣድ!!!!!
ኡፍፍፍፍፍፍ…………………………………………………!!!!!!!!!!!
ፎቶው (ከምስጋና ጋር)፡-
‹‹በእሣት መጫወት›› ፡፡ ‹‹Playing with Fire by Nick356 …›› ፡፡
Filed in: Amharic