>

የነ አቦይ ማትያስና የመለካውያኑ ዕዳና በደል!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የነ አቦይ ማትያስና የመለካውያኑ ዕዳና በደል!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ መርቆሬዎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በመለካውያኑ ላይ አስፈረዱባቸው!!!
 
ወዮ ለነ አቦይ ማትያስና በአጠቃላይ ለመለካውያን “ጳጳሳት” ተብየዎች ወዮ!!!
መቸም ሥጋውያን ናቸውና እነ አቦይ ማትያስና መለካውያኑ ጳጳሳት ነን ባዮች አቦይ ማትያስ ከሕገ ቤተክርስቲያን ውጭ የያዙትንና ቤተክርስቲያን የማታውቅላቸውን ፕትርክና ሳይለቁ ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ ሀገር ቤት ለመግባት ተስማምተው በመግባታቸው “አሸነፍን!” ብለው እየፈነደቁ ይገኛሉ፡፡ አየ አላዋቂነት!!! እውነቱ ግን እነኝህ ሰዎች ክፉኛ የተሸነፉ መሆናቸው ነው፡፡
ወያኔና እነ አቦይ ማትያስ አወናብደውም፣ አምታትተውም፣ አዋክበውም “ቀኖና ቤተክርስቲያን መልሶ ካልተከበረ ካልተጠበቀ በስተቀር አልገባም!” እያለ እምቢ ብሎ በስደት የኖረውን የቤተክርስቲያኗን ሲኖዶስ ዋጋ የከፈለለትን ቀኖና አሽረው ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ አድርገዋል፡፡
እርግጥ ነው በስደት የኖሩት ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አባቶች በአቋማቸው ባለመጽናታቸውና ቀኖናው እንደተሻረ ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ በመስማማታቸው ተስማምተውም በመግባታቸው ከቀኖና ሻሪዎቹና አፍራሾቹ ጋር እንደመተባበር ተቆጥሮባቸው በደል ጥፋት ኃጢአት አይሆንባቸውም፡፡ ምንክያቱን ወደኋላ እገልጽላቹሀለሁ፡፡ ተጠያቂ የሚሆኑትና ቅጣት የሚጠብቃቸው “ጉልበት አለን!” ብለው ለቤተክርስቲያን ጠላት ለወያኔ ሲባል ሕገ ቤተክርስቲያንን የሻሩትና ያሻሩት እነ አቦይ ጳውሎስ፣ እነ አቦይ ማትያስና ባጠቃላይ መለካውያኑ ወይም የወያኔ አገልጋይ ጳጳሳትን ነው፡፡
ቀኖና ቤተክርስቲያንን የሻሩት እነ አቦይ ማትያስና ተባባሪ ጳጳሳት አባትነቱ ቀርቶ ተራ ክርስቲያንነቱ እንኳ የሚሰማቸው ቢሆኑ ኖሮ በሕገ ወጥ መንገድ ከመንበራቸው ያፈናቀሏቸውን ቅዱስ ፓትርያርኩን፣ ቀኖናዋን የሻሩባትን ቤተክርስቲያንን፣ የቤተክርስቲያን ራስ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስንና ሕዝበ ክርስቲያኑን ይቅርታ በመጠየቅ የሻሩትን፣ የጣሱትን፣ ያፈረሱትን ቀኖና መልሰው አቅንተው ማስተካከልና ሕገ ቤተክርስቲያን በሚያዘው መሠረትም መንበረ ፕትርክናውን መልሰው ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ ማስረከብ ነበረባቸው እንጅ ከቀኖና ውጭ በደባልነት ለማስቀመጥ እንዲስማሙ ባላደረጉ ነበረ፡፡
ቀኖና ቤተክርስቲያን “ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ፓትርያርክ አይሾምም!” ይልባቸዋልና፡፡ ፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 4 ቁጥር 68-70፡፡
እንዲሁም “የፓትርያርክ ሥልጣን በአንድ ዘመንና በአንድ ሀገር ለ2 ሰዎች ልትሆን አይገባም! በአጋጣሚ በተለያየ ምክንያት ተፈጽሞ ከተገኘ ግን መንበሩ ወይም ሥልጣኑ ቀድሞ ለተሾመው ትጽናለት!” ይልባቸዋልና፡፡ ፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 4 ቁ.70
ይሄንን ሕገ ቤተክርስቲያን እንኳንና ለፀረ ቤተክርስቲያን አላዊ አገዛዝ ለወያኔ ሲባል ይቅርና ለአማኒና ለቤተክርስቲያን መከታ ለሆነ ደገኛ መንግሥት ጥቅም ሲባል እንኳ የሚሻሻል የሚቀየር አይደለም፡፡ መለካውያኑ የወያኔ ቅጥረኛ ጳጳሳት የሕዝበ ክርስቲያኑን ሱታፌ (አንድነት) የቤተክርስቲያኗን አሐዳዊነት የሚፃረር የሁለት ፓትርያርክ በአንድ መንበር የማስቀመጥ ውሳኔ ወስነው ለፀረ ቤተክርስቲያን አገዛዝ ሲሉ ቀኖና መሻራቸው ነው ዕዳ በደላቸውን የሚያከፋባቸው፡፡
ቀኖና የመሻራቸው ምክንያት ይሄ መሆኑ በግልጽ እየታወቀ ለቤተክርስቲያን ጥቅም ሲሉ እንዳደረጉት ሁሉ “ቀኖና የማሻሻል ሥልጣን አለን!” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እንዲያ ከሆነ አንድ አንገብጋቢ ጥያቄ አብሮ ይነሣል “ስለዚህ ከዚህ በኋላ ቤተክርስቲያን ሁለትና ከዚያ በላይ ፓትርያርክ በአንድ መንበር ይኖራታል ማለት ነው ወይ?” የሚል፡፡ ሕገ ቤተክርስቲያንን አፍራሽ መለካውያኑን እንዲህ ብላቹህ ስትጠይቋቸው “አይ አይደለም እንደሱ አይሆንም ለአሁኑ ብቻ ነው!” ብለው እጅግ አሳፋሪ፣ የደነቆረና ነውረኛ የቅጥረኝነት መልሳቸውን ይሰጣሉ፡፡ ጠንቀኛ ሥርዓትና መጥፎ ትምህርት በቤተክርስቲያን ላይ እየተከሉ እንደሆነ አይገባቸውም፡፡
እንዲህ ከሆነ ታዲያ ምኑ ላይ ነው ቀኖና የተሻሻለው??? ሲጀመር ቀኖና የተባለ ድንጋጌ ሁሉ ይሻሻላል ማለት ነው ወይ??? እንደ ዶግማ ሕግጋት ሁሉ ከቀኖና ሕግጋትም ፈጽሞ የማይሻሻሉና እንደ ዶግማ የሚቆጠሩ ሕግጋትም አሉና፡፡ ለምሳሌ ጫማ አድርጎ ወደቤተክርስቲያን ወይም ወደ ቤተመቅደስ መግባት፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ይሄም የፓትርያርክ ቀኖና የሚሻሻል አይደለም፡፡ ሲጀመር እነኝህ ወንበዴ፣ ቅጥረኛና ከሐዲ ጳጳሳት ማን ሆነው ነው ቅዱሳኑ ሠለስቱ ምዕት በመንፈስቅዱስ ተቀኝተው የደነገጉትን ሕገ ቤተክርስቲያን ማሻሻል የሚችሉት??? ለምንስ ዓላማ??? ይሄ እጅግ የበዛ በደል ክህደትና ድፍረት አይደለም ወይ???
እነኝህ የወያኔ ቅጥረኛ ጳጳሳት እንዲህ ብለው ያበቁና ዞር ይሉና ደግሞ ምን ይላሉ “ቤተክርስቲያን ቀኖና ሲሻር ዝም ብላ መመልከት የጀመረችው ከአቡነ ቴዎፍሎስ ጀምሮ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ መገደላቸው ሳይታወቅ አቡነ ተክለሃይማኖትን በፓትርያርክነት ከሾመችበት ጊዜ ጀምሮ ነውና ከዚያ ጀምሮ ለተፈጸመው ስሕተት ቤተክርስቲያን ይቅርታ እንድትጠይቅ ይደረጋል!” ይላሉ፡፡
አንደኛ ነገር ስሕተትነቱን ካመኑ ስሕተቱን በማስተካከል በአንድ መንበር አንድ ፓትርያርክ ነው ማስቀመጥ ያለባቸው፡፡ ስሕተት ሳይታረም ለስሕተት ይቅርታ አይጠየቅም፡፡ ይሄ ተራ የማወናበድ ተግባር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ቀኖናውን የመለወጥ መብት አለን ብለው እያደረጉት ባለበት ሁኔታ እንደገና ደግሞ “ስሕተት ነው!” በማለት “ቤተክርስቲያን ይቅርታ እንድትጠይቅ ይደረጋል!” ማለቱ ፈጽሞ የጤነኛ ሰዎች አስተሳሰብና ተግባር አይደለም፡፡
ሲጀመር ቅዱስ ፓትርያርኩን ከመንበራቸው ያፈናቀሏቸው የአላውያኑ ሎሌዎች ወንበዴ ጳጳሳት ናቸው እንጅ ቤተክርስቲያን አይደለችምና ግፉን ያልፈጸመችው ቤተክርስቲያን አይደለችም ይቅርታ መጠየቅ ያለባት፡፡ ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ሕብረት ማለት ነውና፡፡ በመሆኑም ከወያኔ ደጋፊ ካህናትና ምዕመናን በስተቀር ይሄንን አረማዊ ተግባር የደገፈ የለምና በየበረሃው፣ በየዋሻው፣ በየፍርኩታው፣ በየገዳማቱ ያሉ ቅዱሳን አባቶችና ሰፊው ምዕመናን ሲቃወመውና ሲያዝኑበት የባጁበት ጉዳይ ነውና ቤተክርስቲያንማ ለ26 ዓመታት ሙሉ “ቀኖና ተሻረ ሕግ ፈረሰ!” እያለች ስትጮህ፣ ስታለቅስ፣ ስትጸልይ ወደፈጣሪዋ ስትከስ፣ ስታመለክት ነው የከረመችው፡፡
በመሆኑም ቤተክርስቲያንን ያለ በደሏ ያለ ኃጢአቷ በደለኛ ኃጢአተኛ ያደረገው የጋራ መግለጫ መታረም አለበት፡፡ እነሱም ለዚህ ቤተክርስቲያንን ያለ ኃጢአቷ ኃጢአተኛ ላደረገ በደላቸው ብቻ ከባድ ንስሐ አለባቸው፡፡ ኃላፊነታቸውን ተጠያቂነታቸውን ከራሳቸው ማሸሹን ትተውና ጥፋቱ፣ በደሉ፣ ኃጢአቱ የራሳቸው የጥፋት ቡድኑ መሆኑን አምነው ቢታረሙ ንስሐ ቢገቡ ነው የሚሻላቸው፡፡ ሰውን ማወናበድ እንደቻሉት ፈጣሪን ማወናበድ አይችሉምና፡፡ እረኞች ነን፣ አባቶች ነን የሚሉ ሰዎች ፈጣሪን ጨርሰው እረስተው በእንዲህ ዓይነት ውንብድናና ክህደት መነከራቸው ግን እጅግ እጅግ የሚያሳዝን፣ የሚያስለቅስ፣ የሚያስመንን ነገር ነው፡፡ ነገረ ሥራቸውን ስናይ እግዚአብሔርንም ማወናበድ ማምታታት እንደሚችሉ የሚያምኑ የሚያስቡ ነውና የሚመስሉት፡፡
እናም እነኝህ ጳጳሳት ነን ባይ የወያኔ ታጋዮች ኃላፊነት ተሰምቷቸው፣ የክርስቶስና የቤተክርስቲያን አደራ ገዷቸው የቤተክርስቲያን ጥቅም በማስቀደም እስከሞት ድረስ ታምነው እንደ ሐዋርያት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” ሐዋ. 5፤29 በማለት
ቤተክርስቲያንን ማገልገል ሲጠበቅባቸው እነሱ ግን ይሄንን የሚጠበቅባቸውን ከማድረግ ይልቅ ሥጋዊ ጥቅማቸውን ብቻ በማሰብ፣ ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአላዊው አገዛዝ በመታዘዝና በማደር፣ እግዚአብሔርን፣ ቤተክርስቲያንንና ሕዝበክርስቲያኑን በመናቅ ፈጽሞ ሊያደርጉት የማይጠበቅባቸውንና ሥልጣነ ክህነታቸውንም የሚያሽር ተግባር በመፈጸም አሁንም የአላዊውንና የቤተክርስቲያኗን ጠላት የወያኔን ጥቅም በምታዩት መልኩ ለማስጠበቅ ችለዋል፡፡
ለዚህ እጅግ ሲበዛ ድፍረት ለተሞላበት ተደጋጋሚ ጥፋታቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የከፋ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፣ በክህነታቸውም ተሽረዋል፡፡ ምክንያቱም ሕገ ቤተክርስቲያንን መሻር ከሥልጣነ ክህነት እንደሚያሽር የቤተክርስቲያኗ የሕግ መጽሐፍ ፍ/ነ/ፍ/መ አንቀጽ 5 ግልጽ አድርጎ ደንግጓልና ነው፡፡
እንግዲህ እናንተ የውሸት ፓትርያርክ፣ ጳጳሳትና ካህናት ተብየዎች “የኦርቶዶክስን አከርካሪ እንዳያንሠራራ አድርጌ ሰብሬዋለሁ!” እያለ የሚፎክረው የፀረ ቤተክርስቲያን የወያኔ አገልጋዮች ከነፍስ መከራ ይልቅ የሥጋ መከራ ከከበደባቹህ፣ ከዘለዓለማዊው መከራ ይልቅ ጊዜአዊው መከራ ከበለጠባቹህና “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሔድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ!” ሐዋ. 20፤28-30 ሲል የጣለባቹህን አደራ ጥላቹህ፣ እግዚአብሔርን ንቃቹህ ለአላዊ ፀረ ቤተክርስቲያን አገዛዝ ካደራቹህ ፈጣሪ ምርጫቹህን በሚገባ ያከብርላቹሃል፡፡ ዋጋቹህንም አዘጋጅቶም ይጠብቃቹሃል፡፡
ለመንጋው የማይራሩት ጨካኞችና ምንደኞች መለካውያኑ የወያኔ ቅጥረኛ ጳጳሳት እንዲያው ዝምብለው በሌላቸው ወይም በተሻረ ጵጵስና ወይም ሥልጣነ ክህነት ነው “ፓትርያርክ ሾምን፣ ሲኖዶስ ነን! ምንትስ እያሉ ሲቀልዱ የባጁት፡፡ በአንድ ቤተክርስቲያን ሁለት ሲኖዶስ ሁለት ፓትርያርክ የለም! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስና ፓትርያርክ በስደት ላይ የነበረው ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ትገናኝ የነበረውና እግዚአብሔርም የሚያውቀው ይሄንን ሕጋዊውን ተሰዶ የነበረውን ሲኖዶስና ፓትርያርክ እንጅ ቀኖና ቤተክርስቲያን የማያውቃቸውንና ቀኖና አፍራሾችን ሕግ ጣሾችን ሕገወጥ የወያኔ አገልጋዮች ወንበዴ የጳጳሳት ቡድንን አይደለም፡፡ ይሄንን የምለው እኔ አይደለሁም ቀኖና ቤተክርስቲያን እንጅ፡፡ ጵጵስና ፕትርክናና መንፈሳዊ ሥልጣን በሕግ፣ በቀኖና፣ በምግባር፣ በሃይማኖትና ሥርዓት እንጅ በጉልበት፣ በልብስ፣ በአስኬማ ወይም በቆብ፣ ዘርፋፋ ቀሚስ በማጥለቅ፣ በሽበታማ ጢም…. አይደለም!!!
እንግዲህ ያለው ነገር ይሄ በሆነበት ሁኔታ ነው ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ለ26 ዓመታት መለካውያኑ ወይም የእግዚአብሔር ሳይሆን የወያኔ አገልጋዮች የሆኑቱ ጳጳሳት ይጸጸቱና ይስተካከሉ ይታረሙ ይመለሱ እንደሆነ ተመልክተው ጨርሶ የማይመለሱና የማይታረሙ መሆናቸውን በመመልከታቸው “እንደተሰደድኩ ባርፍ ቤተክርስቲያን እንደተከፈለች መቅረቷ ነው!” ብለው በእጅጉ በመሥጋታቸውና ይህ እንዲሆንም ፈጽሞ ባለመፈለጋቸው ካላቸው ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት በመነሣት ነው ሕገ ቤተክርስቲያን እየደገፋቸውና ሙሉ መብቱን የሰጣቸው ለእሳቸው ሆኖ እያለ በመለካውያኑ ላይ በእግዚአብሔር ዘንድ ሊያስፈርዱባቸው መብት እንደሌላቸው መብታቸውን አሳልፈው ሰጥተው ወደሀገር ሊገቡ የቻሉት፡፡ በመሆኑም ቀኖና ቤተክርስቲያን እንደተሻረ ሳይቀና ሳይስተካከል መግባታቸው ቅዱስ ፓትርያርኩንና ብፁዓት አባቶችን ዋጋ ቢያሰጣቸው እንጅ በደለኛ አያደርጋቸውም፡፡ ምክንያቱም ለቅድስት ቤተክርስቲያን ህልውና፣ ደኅንነት፣ አንድነት በማሰብ ያደረጉት ነውና፡፡
እናም እያንዳንድህ በዚህ ግፍ ላይ እጅህ ያለበትና ከመለካውያኑ የወያኔ አገልጋዮች የተሻሩ ጳጳሳት ጎን ቆመህ ስታገበግብ የከረምክ ከጳጳስ እስከ ተራ ምእመን ያለህ ሁሉ ወዮልህ ወዮታ አለብህ!!! አመንክም አላመንክም ከእግዚአብሔር ዘንድ ጽኑ ፍርድ ይጠብቅሃል!!! እግዚአብሔር ቀላል ያድርግልንና ፍርዱ ቅጣቱ ለሀገርም መትረፉ አይቀርም!!!
እንኳን ደኅና አመጣቹህ ቅዱስ አባታችን እንዲሁም ብፁዓን አባቶች!!!
ድል ለቤተክርስቲያን!!! 
Filed in: Amharic