>

ይድረስ ለህወኃቶችና ደጋፊዎቻቸው!!! (ሳምሶን ጌታቸው) 

ይድረስ ለህወኃቶችና ደጋፊዎቻቸው!!!
ሳምሶን ጌታቸው 
እናንተም አስተሳሰባችሁም አርጅታችኋልና ዕድል ቢሰጣችሁም መምራት አትችሉም!!!
 
ይኼ ሀሳብ በንቀት የተጻፈ ሳይሆን፣ በፍፁም ዕውነትና ቅንነት እንዲሁም በብስጭት የተሰነዘረ ኮስታራ ግን ወንድማዊ ማስታወሻ መሆኑ ይታወቅ።
ህወኃቶች እኮ “ሰው” የላችሁም። ዘመኑ የሚጠይቀውን ጀግና ሰው የላችሁም። በዙሪያችሁ ስትሰበስቡ የኖራችሁት ኮልኮሌ በሙሉ መስማት የምትፈልጉትን የራሳችሁን ዲስኩር የሚያስተጋቡ ሆድ አደር በቀቀኖችን ነው። ካድሬዎቻችሁ ማሲንቆ አይዙም እንጂ እንደ የመሸታ ቤት አዝማሪዎች ያሉ አስመሳዮች ናቸው። ያልሆናችሁትን ናችሁ እያሉ እያወደሱ፣ እያስደሰቱ ገንዘብ የጨበጣችሁበትን እጃችሁን በዘዴ መፈልቀቅ ብቻ ህልማቸው የሆነ።
በእርግጥ የሕዝቡን ፍላጎት አጢኖ “ኧረ ተሳስታችኋል፣ ይኼን አስተካክሉ” የሚላችሁ ወጣት ጭራሽ እንደማትስጠጉም የታወቀ ነው። ምክር መስማት ሞታችን ነው ብላችሁ ተፈፅማችኋል። በዚህም ምክንያት ያስጠጋችኋቸው ወጣቶቻችሁ በሙሉ፣ ፖለቲካን በዕለት ጉርስነትና በጠባብ ራዕይ የሚመዝኑ እንጂ ሀገር አቀፍ ጀግናና ተራማጅ መሆን የማይችሉ መሆናቸው ተረጋግጧል።
ሁሌም ሕዝብ ከሚወደው በተቃራኒ በመጓዝ፣ ሆን ብላችሁ ታበሳጫላችሁ፣ በብሔር ማንነቱ ላይ ቅጥያ በመደረብ በየሚዲያው ስራዬ ብላችሁ ትዘልፋላችሁ፣ ብሔርን ከብሔር ታናክሳላችሁ፣ የአንዱ ብሔር ጥቅም በሌላኛው ብሔር ኪሳራ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ታደርጋላችሁ። በአጠቃላይ ሕዝብን ከሕዝብ ማናከስ፣ ማናናቅ፣ ማለያየት ዋነኛው የፖለቲካ መርኃችሁ እንደነበር እናንተም የማትክዱት ሀቅ ነው።
እግዚአብሔር በሚያውቀው የመጨረሻ የክፉ ሰዎች ስብስብ ናችሁ። እሺ አሁን ቅንነትና አቅም ያልፈጠረባችሁን እኛ ምን እናድርግ? ዘመኑ የሚፈልገው አንድ ጎበዝ ቢኖራችሁ ኖሮ፣ ጠ/ሚ አብይ የፈፀሟቸውን ግማሹን እንኳን የሚፈፅም፣ ሕዝብ ሊታረቃችሁ ይችል ነበር። ግን ያ ጀግና የላችሁም፣ ዕድሉም አምልጧችኋል።
አስቡት እስኪ አንድ ትንታግ ጎበዝ ጀግና አባል ኖሯችሁ፤ “እስከ ዛሬ የተጓዝንበት መንገድ የተሳሳተ ነበር። በአማራ፣ በኦሮሞ በደቡብ ወንድሞቻችንና በመላው የሀገራች ሕዝብ ላይ የተፈፀመው ብሔር ተኮር ጥላቻ ስህተት ነበር። አላግባብ የታሰሩ እስረኞችን እንፈታለን። በኃይማኖት ተቋማት ላይ የነበረን ሕገወጥ ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ ስህተት ስለነበር እናርማለን፣ በአጠቃላይ ለሕግ የበላይነት እንሰራለን።” ቢልና በተግባርም ቢፈፅም መገመት ትችላላችሁ ውጤቱን?
በኢኮኖሚው ላይ የተፈጠረው የለየለት ዘረፋና ውንብድና እንዲታረምና ወንጀለኞችም በሕግ እንዲዳኙ ብታደርጉ፣ በመላው ሀገሪቱ የተፈጠረው ቀውስ የትግራይን ሕዝብ ያሳዘነ መሆኑን ብትገልፁና ብትችሉ ጀግናው የጎንደር ሕዝብ እንዳደረገው “የኦሮሞ፣ የአማራና በጥቅሉ የሌሎች ወንድሞቻችን ደም ደማችን ነው” በሚሉ አይነት መሪ ቃሎች የተኳሹ ሕዝባዊ የፍቅርና የሠላም ሠልፎችን በመላው ትግራይ ብትጠሩ፣ የሚመዘገበውን ታላቅ ሀገራዊ ውጤት አስባችሁታል? እንዲያ ያለው ጎበዝ ጀግና መሪ ቢኖራችሁ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያን መሪ፣ “ትግሬ ስለሆነ አንፈልገውም” የሚል ይመስላችኋል? በእርግጥ እናንተ የምታስቡት እንደዚያ ነው። ግን ተሳስታችኋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ ጠ/ሚ ዐብይንና አቶ ለማ መገርሳን ከጥቂት ወራት በፊት ከነመፈጠራቸውም አያውቃቸውም ነበር። በአነጋገራቸው፣ በተገራ አንደበታቸው፣ የሕዝብን ፍላጎት በሚያውቅ ንግግራቸውና ትህትናቸው፣ ከሁሉ በላይ ሀገራችን ኢትዮጵያን ባስቀደመ አቋማቸው ነው የልጅ የአዋቂውን፣ የሙስሊም ክርስቲያኑን ልብ ማሸነፍ የቻሉት። ማንም ጤነኛ ሰው፣ ስለ ብሔር ማንነታቸው፣ ስለሚከተሉት ኃይማኖታቸው፣ ስለ ኢሕአዴግነታቸው ግድ የሰጠው አልነበረም። ስለዚህ ያ የሀገር ጀግና ከህወኃት አብራክ የወጣ ቢሆን ኖሮ ምስሉን በቲሸርቶቻችን አትመን አደባባይ ለድጋፍ እንወጣለት ነበር።
ይኼን ዕውነት እንኳ ዐይታችሁ፣ ለካ ይህ ነበር ስህተታችን የማለት አቅምና ማስተዋሉን አልፈጠረባችሁም። ለማንኛውም ክፉዎች ናችሁና እኛ እንደናንተ ባንጠላችሁም፣ አንወዳችሁም። ባላችሁ የተበለሻሸ የፖለቲካ አቋማችሁ የተነሳ አንፈልጋችሁም። ግን ደግሞ ወንድሞቻችን ናችሁና ክፉአችሁን አንመኝም። ብትችሉ አንድ ነገር ግን ለማድረግ ሞክሩ። ከደም ከሥጋ ወንድሞቻችን የትግራይ ሕዝብ ራስ ውረዱ።
እስኪ አሁን እኛ ያልነው ካልሆነ ሀገሪቱን እንበተናለን ማለት ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ቀርቶ ከአንድ ጤነኛ ሰው ይጠበቃል? ለኤርትራ ሕዝብ እኛ የበለጠ ቅርብ ነን ምናምን እያሉ ነባራዊውን ዕውነታና የቅርብ ጊዜ ታሪክ የዘነጋ፣ የሀገርና የክልልን ሥልጣን የረሳ መፈክር ማሰማት፣ መሳቂያ መሳለቂያ ከመሆን ሌላ ምን ይፈይዳል? አያችሁ አስቦ ለመንቀሳቀስ የሚችል አመራር ይቅርና አንድ ደህና መካሪ እንኳን የላችሁም። ህወኃት በሙሉ አንድ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰነፍ ሰዎች ስብስብ ሆኖ ቀርቷል የሚባለው ለዚህ ነው።
ለማንኛውም ቢያንስ ከአብራኩ ለወጣችሁት ሕዝብ አስቡ። የሰው ጀግና የለውም። ጊዜ ነው ጀግና። አሁን ጊዜ አሸንፏችኋል። እናንተም አስተሳሰባችሁም አርጅታችኋልና ዕድል ቢሰጣችሁም መምራት አትችሉም። ይልቅ የተፈጠረውን የዕርቅና የምህረት መርኅን የሚከተለውን አዲሱን አመራር በመተባበር ብዙ ጥቅማችሁን ማስጠበቅ በሚያስችላችሁ መንገድ ነገሮችን ለማበጃጀት አስቡበት።
ለጀግንነት፣ ጊዜው አይረፍድም። ጀግንነት ደግሞ የጊዜን ነገር ከማየት ይጀምራል። መበለጥንም በጊዜው ማወቅ ጀግንነት ነው። በአልሞት ባይ ተጋዳይነት በተንኮል የትግራይን ሕዝብ ከወንድሞቹ ለመነጠልና ሀገራችንን ለመረበሽ እየሞከራችሁ ያለውን ድርጊታችሁን ተዉትና ከሕዝብ ጋር ለመታረቅ ጣሩ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን እናንተን አቶ ኢሳያስንም ይቅር ያለ ሕዝብ ነውና፣ ለይቅርታና ለሠላም ራሳችሁን አዘጋጁ።
Filed in: Amharic