>
5:21 pm - Monday July 20, 7142

በኢህአዴግ ውስጥ የህወሃት የበላይነት ተከርክሟል ፣..... (አበጋዝ ወንድሙ)

በኢህአዴግ ውስጥ የህወሃት የበላይነት ተከርክሟል ፣

አሁንም ግን ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ኢህአዴግ ነው፣

ከፊታችን የተጋረጠው አደጋም ሙሉ በሙሉ አልተቀረፈም! !

አበጋዝ ወንድሙ

ባለፉት ዓመታት የነበሩት ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች መጋጋል ሀገራችንን ወዳልታወቀ፣ ግን በጎ ወዳልሆነ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል የሚል ፍራቻ ነግሶ በነበረበት ወቅት፣ጫናው የገዥውንም ጎራ  አስደንብሮ የወቅቱ / ሃይለማርያም ስልጣኑን የለቀቀበት ሁኔታ ፈጥሮ ነበር። ይሁንና የሱ ስልጣን መልቀቅ በራሱ ሃገራዊ  እፎይታንና መረጋጋትን ሊፈጥር አልቻለም ነበር።

ሆኖም፣ ሃይለማርያምን በመተካት የኢህአዴግ ሊቀ መንበርና ቀጥሎም / ተብሎ የተሰየመው አብይ አህመድ ስልጣኑን ሲረከብ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባደረገው የመጀመሪያ ንግግርና ከዛ በመቀጠል ባለፉት አራት ወራት የስልጣን ዘመን የወሰዳቸው አርምጃዎች፣ በሀገር ደረጃ በሚባል መልኩ ትልቅ ተስፋን የጫረ ለመሆን በቅቷል።

ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ፣የወደፊት ሃገራዊ ጉዟችን በታላቅ ተስፋ የተሞላበት የመሆኑን ያህል ግን፣ ይሄ አዲስ ሃገራዊ ተስፋና መነሳሳት የቀድሞ የበላይነታቸውን ያሳጣቸው ቡድኖችና በነበረው ሁኔታ ተጠቃሚ የነበሩ ወገኖችን  ስላላስደሰታቸው ማናቸውንም መንገድ በመጠቀም ለመቀልበስና ወደ ቀድሞው ሁኔታ ሊመልሱን መውተርትራቸውን መዘንጋትም ሆነ አቅሎ መመልከት ትልቅ ስህተት ስለሆነ፣ ነቅቶ አየተከታተሉ አደጋውን ማምከን ያስፈልጋል።

ህወሃት 1983 ኢህአዴግ የሚል ጭምብል ለብሶ አዲስ አበባን፣ ብሎም ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር፣ ከሱ ውጭ ሌላ አድራጊ ፈጣሪ ድርጅት እንዳልነበር የማያውቅ ( አውቀው አይናቸውን ሸብበው ከነበሩ ፈረንጆች ውጭ) ማንም አልነበረም። ህወሃት ውስጥ ከኤርትራ ጋር ከተደረገው ጦርነት በዃላ ክፍፍል ተፈጥሮ፣ አሸናፊው የመለስ ቡድን አጋዥ ፈልጎ ከብአዴን ጋር እስኪወግን ድረስ፣ የህወሃት ብቸኛ አሽከርካሪነትም ጥያቄ ውስጥ ገብቶ አያውቅም።  

እንዲያውም  በሽግግሩ ወቅት ከነበረውና ዓመት ሳይሞላው ከሰመ ከተባለውየኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መኮንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ’ (ምርኮኛ ወታደሮች)  ኢዴመአን) ውጭ ሌሎቹ፣ ህወሃት በመደበላቸው  ሞግዚቶች  የመጀመሪያውን አስር አመታት ዘልቀዋል።

ህወሃት በድርጅቱ ውስጥ ያሉትን ተቀናቃኞች አስወግዶ መለስ በብቸኝነት እስከ አለተ ሞቱ ድረስ  በመራቸው አመታት ውስጥም የኢህአዴግ አድራጊና ፈጣሪ ህውሃት እንደነበር የታወቀ ነው።

1997 ዓም በተደረገው ምርጫ ሽንፈት ገጥሞት የነበረው ኢህአዴግ ተቃዋሚዎቹን ከደፈጠጠ በዃላ እድሜ ቀጥል አድርጎ የወሰደው ሚሊዮኖችን በአባልነት ስም ማግበስበስ ነበር። በየድርጅቱ ተመልምሎ የነበረው ይሄ ሃይል ነው ዛሬ፣ ወቅቱን ጠብቆና ራሱን አደራጅቶና አቀናጅቶ በኢህዴግ ውስጥ የህወሃትን የበላይነት ሽርሽሮ በቁመቱ የከረከመው።

ከመለስ ሞት በዃላና በተለይም ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ስልጣን ከጁ ማፈትለክ መጀመሯን የተረዳው የህወሃት አመራር ሂደቱን  ለማስቆም በደህንነትና ወታደራዊ ተቋሞቹ ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ሊሳካለት አልቻለም።  

የዛሬ ስምንት ወር ገደማ የህወሃት መሃከላዊ ኮሚቴ ረጅም ጊዜ ወስዶ ባካሄደው ስብሰባ በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነቱን የሚያሳጣው ሂደት መፋጠንን በመመልከት፣ ሂደቱን አጓቶ በበላይነት የመቀጠል ህልሙን እውን ሊይደርግልኝ ይችላል በሚል፣ በውስጡ መሸጋሸግ ለማድረግ ቢሞክርም ዳግም ሳይሳካለት ቀርቷል

የህወሃት ስብሰባና ይዞት የወጣው መግለጫ እንደታሰበው የበላይነቱን ሊያሳጣው የሚችለውን ሂደት ማጓተት ሳይሆን፣በመርህ አልባ ግንኙነትየከሰሳቸው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች  በተለይም ኦህዴድና ብአዴን የበለጠ ተቀናጅተው፣ህወሃትን በቁመቱ ልክ በማድረግ፣  ምናልባት በኢህአዴግ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል የአባል ድርጅቶች እኩልነት የታየበት ወቅት አንዲሆን  አድርገዋል።

ይሄ ውስጣዊ አደረጃጀታቸውን የሚመለከት ሲሆን፣ከዚህ ቀደም ባቀረብኩት አጭር ጽሁፍ ጠቁሜ እንደነበረው በሀገር ደረጃ ከነበረው አጠቃላይ ህዝባዊ አመጽና ትግል አንጻር፣ የኢህአዴግ በስልጣን የመቆየት ብቸኛ የተስፋ ገመድ የለማ ቡድን እንደነበረና፣የአብይ አህመድ /ምኒስቴር መሆን ደግሞ አማራጭ እንዳልነበረው አመላክቼ ነበር።

ህወሃት የአብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ብሎም /ምኒስቴር መሆን ሊዋጥለት ባለመቻሉ ሂደቱን ለማደናቀፍ ብዙ ቢጥርም ሳይሳካለት በመቅረቱ፣ አብዛኞቹ የቀድሞ አመራር አባላት አየመረራቸውም ቢሆን ለጊዜውም ቢሆን መቀበል ተገደዋል።

አሁን በሂደት በመታየት ላይ እንዳለውም፣ የዚህ አዲሱን ሁኔታ መቀበል የቸገረውና አንዳንድ የአኩራፊ ቡድን አባላት፣ ግማሹ በጡረታ ግማሹ በገዛ ፍቃድ ስልጣንን በመልቀቅ ከየቦታው ተጠራርተው  መቀሌ በመክተም  ለመዶለት ቢሞክሩም በትግራይ ክልልም ቢሆን ቅቡልነቱ ውሱን በመሆኑ፣እንቅፋት ለመሆን የሚያደርገው ጥረት በስፋት ሊሳካለት ይችላል የሚል ግምት የለም

በተቃራኒው፣ከዚህ በፊት በህወሃት አመራር አባላት ተሰምቶ በማያውቅ መልኩ፣ ደብረ ጽዮን በቅርቡ ባደረገው አንድ መግለጫ ፣ትግራይ ውስጥ ካሉ ዓረናን ከመሰሉ ድርጅቶች ጋርም በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ አብረን እንሰራለን ማለቱና፣ሽፋኑ የምሁራን ጉባኤ ቢሆንም አረጋዊ በርሄ፣ ግደይ ዘራጽዮን፣ አብርሃ ደስታ አበበ /ሃይማኖትና ሌሎችም በተገኙበት፣ ነባርና ያሁኑ የህወሃት አመራር አባላት በአንድነት የታደሙበት ስብሰባ መካሄዱ በራሱ፣የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ተጠሪ አኔ ብቻ ነኝ’ በሚል ሌሎችን ሲያስርና ሲያሳድድ ለነበረው ህወሃት እብሪት መተንፈስና በቁመቱ  መከርከም አመላካች አድርገን መውሰድ እንችላለን።

በህወሃት ውስጥ፣ ኦህዴድም ሆነ ብአዴን ውስጥ ፈንቅሎ የወጣውን አይነት የለውጥ ሃይል መኖሩ አጠራጣሪ ባይሆንም ባንጻራዊ ሁኔታ ሀወሃት  ውስጥ ባለው አፈናና ቁጥጥር ለጊዜው ጎልቶ መታየት  ባይችልም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር እህት ድርጅቶቹ ውስጥ ባሉት ሃይሎች ከተደገፈና ከተበረታታ ፈንቅሎ መውጣቱ የማይቀር ነው።

ይሄ ሳይሆን ቀርቶ ድርጅቱን አስመልክቶ ጅምላ ፍረጃና ውግዘት ከቀጠለ ግን በህወሃት ውስጥ ያለው የለውጥ ሃይል እንዲደፈጠጥ ማገዝና፣ በኢህአዴግ ውስጥ  የተፈጠረውን  ለውጥ መቀበል የማይፈልገውን ሃይል በማጠናከር ሃገራዊ ትርምስ እንዲፈጥር በር ስለሚከፍት መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነት የተቀዳጀው የነአብይ ቡድን ይሄን ሁኔታ በቅጡ በማጤን አግላይ ከሚመስሉ እርምጃዎች በመጠንቀቅ፣ እህት ድርጅቱ ውስጥ ያሉትን በማቀፍ መንቀሳቀሱ ለድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ለሀገር የሚበጅም በመሆኑ በቅጡ ሊያስቡበት ይገባል።

አሁን በተወሰነ ደረጃ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚካሄድ የርስ በርስ መናቆርና የሚያመጣው መዘዝም ሆነ፣ በተወሰነ ደረጃ የሚታየው በመንጋ የሚካሄድ ስርዓተ አልበኝነት የሚዳዳው ግድያና ትርምስና አደገኛ አካሄዱ  በጊዜ እንዲቆም ካልተደረገ፣አንጻራዊ ሰላማችንን ማናጋት ብቻ ሳይሆን አገራዊ ትርምስ ሊፈጥር ስለሚችል፣ መንግስት ችላ ሳይል በአጣዳፊ አትኩሮት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ለነዚህ ሁኔታዎች ማቆጥቆጥ የተወሰነውን ድርሻ የሚወስዱት፣ በኢህአዴግ ውስጥ በተደረገው የአሰላለፍ ለውጥ ከሁሉም የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች የተገፉ ወገኖች ቢሆኑም፣ ለውጡ የፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም የመንግስት ክንድ ላልቷል በሚል ስሌትና ወቅቱን በመጠቀም፣ ግርግር ፈጣሪዎች እንዳሉም የሚታወቅ ነው።     

የዛሬ አራት ወር ግድም በኢህአዴግ   /ምኒስቴር ሆኖ የተመረጠው አብይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በወሰዳቸው በርካታ አውንታዊ እርምጃዎች  በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያነሳው ከመሆኑም በላይ፣ ህዝብ ለወደፊቱ ተስፋን እንዲሰንቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎች መታየት በመጀመራቸው ሀገራችን በተሻለ ሁኔታ ላይ ትገኛለች

ይሄ ተስፋ ሰጭ  ህኔታ እየጎለበተ በመሄድ የህዝብን ጥያቄ በመጠኑም ቢሆን ያስተናግድ ዘንድና፣ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸሻገር የሚያስፈልገው ጉዞ እንዳይደናቀፍና አላስፈላጊ እክል እንዳይገጥመው  በመላ ሀገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት የሚታወቅ ነው።

ይሄም በመሆኑ ኢትዮጵያን በማስተዳድር ላይ ያለው ኢህአዴግን በበላይነት የሚመራው የአብይ ቡድን፣ ውስጣዊ አንድነቱን በቶሎ አጠናክሮ ፣ነገሮች ስር ሰደው ለመፍትሄ አስቸጋሪ ከመሆናቸው በፊት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግና በተገኘው ጊዜያዊ ድጋፍ ሳይሳከር ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።

 

Filed in: Amharic