>

እዉን ዶ/ር አብይ ኢህአዴግ ነዉን? የሽግግር መንግስት አሁን ያስፈልገናል? (ያሬድ ደምሴ መኮንን)

እዉን ዶ/ር አብይ ኢህአዴግ ነዉን?

(የሽግግር መንግስት አሁን ያስፈልገናል?)

ያሬድ ደምሴ መኮንን

አንዳንድ ጸሃፍት ዶ/ር አብይን መደገፍ ኢህአዴግን መደገፍ ነዉና የሽግግር መንግስት እስካልተቋቋመ ድረስ ይሄ ጉዞ የትም አያደርስም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡አሁን እነ ዶ/ር አብይ እያከናወኑት ያሉት እጅን አፍ ላይ የሚያስጭኑ ተግባራት የተለመደዉ ኢህአዴጋዊ ድራማ እንጂ ሃቀኛ ለዉጥ ለማምጣት የታሰበ አይደለምና ከወዲሁ ንቁ እያሉ ሊያስጠነቅቁን ይሞክራሉ፡፡ የባህዳሩ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ጀግናዋ እማዋይሽ አለሙ ያነሱትን የሽግግር መንግስት ይመስረት ጥያቄ ተከትሎ በዚሁ አሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሠአሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋዉ የተባሉ ጸሃፊ በአንድ ወቅት በዚሁ ethioreference ላይ የሽግግር መንግስት አስፈላጊነትና ጠቀሜታዉ በሚል ርዕስ ያቀረቡት መጣጥፍ ለአብነት ይጠቀሳል፡፡ይሄዉ ጥያቄ ዛሬም በዶ/ር አብይ የአሜሪካ ቆይታ ወቅትም ተደግሞ ሰምቼዋለሁ፡፡   

እንደ ሠዓሊ አምሳሉና መሰሎቻቸዉ፣ ዶ/ር አብይ ከኢህአዴግ አብራክ ስለወጣ ብቻ አሁን እያደረገ ያለዉ መሰረታዊና መዋቅራዊ ለዉጦች እንደ ጥገናዊ ለዉጥ ወይም ከጥቂት ወራት በፊት የነበሩት መሪዎች ሲያደነቁሩን እንደነበረዉ እንደ ጥልቅ ተሃድሶ መቁጠር ያለብን አይመስለኝም፡፡ አሁን ጊዜዉ ስላልደረሰ ኢህአዴግ በስም ደረጃ ህያዉ ይሁን እንጂ የህወሃቱ ጄኔራል ተክለብርሃን ከዚህ ቀደም እንደተናገረዉ የአብይ አስተዳደር ፈጽሞ የኢህአዴግ ሽታ እንደሌለዉ እርግጥ ነዉ፡፡ እኔ በበኩሌ ዶ/ር አብይ በኢህአዴግ እቅፍ ውስጥ ስላደጉ ብቻ አፌን ሞልቼ ኢህአዴግ ነዉ ለማለት አልደፍርም፡፡ዶ/ር አብይን መደገፍም ኢህአዴግን መደገፍ ነዉ ብዬ አላምንም፡፡

ለምን?

አንድ ግለሰብ የአንድ ድርጅት አባል ወይም ኃይማኖት ተከታይ ነዉ የሚባለዉ የድርጅቱን መርህ ወይም የሃይማኖቱን አስተምህሮ ወዶና ፈቅዶ አምኖ ሲቀበል ብቻ ነዉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰዉ በእየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት ሳያምን ክርስቲያን ሊባል ይችላልን? የአላህ አንድነትንና የመሃመድ መላክተኝነትን (ረሱልነት) አምኖ ያልተቀበለን ሰዉ በምን መስፈርት ነዉ ሙስሊም ብለን ልንጠራዉ የምንችለዉ?

ዶ/ር አብይ ከበአለ ሲመታቸዉ ጀምሮ ኢህአዴግ በመቃብሬ ካልሆነ አይታሰቡም ያላቸዉን የኢህአዴግ “ወርቃማ” መርሆችንና አስተምህሮቶችን ምትሃት በሚመስል ሁኔታ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ድንጋይነት ሲቀይሯቸዉ እያየን ዶ/ር አብይን እንዴት ነዉ የኢህአዴግ ድራማ መሪ ተዋናይ ነዉ ብለን ለማመን አይደለም ለመጠርጠር የምንችለዉ?(የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና)፡፡የኢህአዴግን የጠባብ ብሄርተኝኘት ሽታ አጥፍቶ የኢትዮጵያዊነትንና ያንድነት መአዛ ባገር በምድሩ እንዲያዉድ ያረገን ጀግና እኔ በበኩሌ ከኢህአዴግ ተርታ አሰልፌ አላሳንሰዉም፡፡ለዚያም ነዉ ህዝቡ ደ/ር አብይን እንጂ ኢህአዴግን ደግፎ ሰልፍ ያልወጣዉ፡፡ ይሄ እዉነታ ደግሞ ለዶ/ር አብይ ብዙ ሩቅ አይደለም፡፡

በፖለቲካ ዉስጥ እያንዳንዱ ዉሳኔ ላይ ጊዜን (timing) መጠበቅ ብልህነት መሆኑ የሚያውቁ ያውቁታል፡፡ ሁሉም ነገር በቅደም ተከተልና በጊዜዉ ሲሰራ የሚፈለገዉ ግብ ላይ ያደርሳል፡፡ እንዲሁ ስልጣን አገኘሁ ተብሎ የሚወሰዱ ግብታዊ እርምጃዎች ግን የኀላ ኀላ ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡

እነ አብይና ጓደኞቹ ላለፉት 27 ዓመታት እንደ ተራራ ገዝፎ የታየንን ጎልያዱን ኢህአዴግ ገንድሰዉ የጣሉት የራሱን የኢህአዴግ ወንጭፍና ድንጋይ ከእጁ ላይ ቀምተዉ ነዉ፡፡ህዝቡ ከዉጭ ሆኖ ከሚወነጭፈዉ ድንጋይ ጋ ተባበረና ኢህአዴግ በዝረራ ለመሸነፍ በቃ፡፡ይህን ለዉጥ ያመጡት የኢህአዴግን ማሊያ ለብሰዉ ስለሆነ አሁንም መጫወት ያለባቸዉ ይሄኑ ማሊያ ለብሰዉ መሆን አለበት ብዬ አጥብቄ አምናለሁ፡፡

ዶ/ር አብይ ስልጣን በያዘ ማግስት ወንበሩ ላይ ሳይደላደል “የቀን ጅብ” ብሎ ስም ያወጣላቸዉን ጎምቱ ባለስልጣናት ለማሰር ቢሞክር የሚገጥመዉ ፖለቲካዊ ኪሳራ የከፋ እንደሚሆን ለማወቅ የፖለቲካል ሳይንስ ሊቅ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ ነገር ግን መጀመሪያ የዉጩንና የዉስጡንም ድጋፍ ማግኘትና ወያኔ ለራሷ ብቻ እንዲመች አድርጋ የዘረጋችዉን ስርአትና መዋቅር ማፈራረስ ያስፈልገዉ ነበር፡፡፡፡በ27 ዓመት የተገነባን መዋቅር በ 3 ወር ለማፈራረስ መሞከር ደግሞ ከጥቅሙ በላይ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ለአንድ ወገን ብቻ እንዲበጅ ተደርጎ የተበጀዉን ስርአትና መዋቅር አፈራርሶ ለሃገር የሚበጅ መዋቅር መዘርጋቱ ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ተግባር ስለነበር ጠቅላይ ሚንስተራችን ይህንንም በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ላለፋት 27 አመታት ሲገነባ የነበረን መዋቅር በአንድ ጀምበር ንዶ የሽግግር መንግስት ይመስረት ጥያቄ ማቅረብ፣ ስተት ነዉ ባይባልም እንኳ፣ ሁኔታዎችን ያላገናዘበና ጊዜዉን የጠበቀ ባለመሆኑ ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም፡፡ደግሞም አሁንም ድረስ መሳሪያዉና ገንዘቡ በነማን እጅ እንዳለ መዘንጋት የለበትም፡፡

ይህ ስልጣን የተገኘዉ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ቢሆን ኖሮ የነበረዉን ሁሉ ባንድ ጀምበር ንዶ አዲስ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ባልከበደ ነበር፡፡ይሄ ከዜሮ መጀመር እንዳላዋጣን ባለፋት ሁለት መንግስታት ስላየነዉ የአንዱዓለም አራጌን “ያልተሄደበት መንገድ” ለመሄድ መድፈር አለብን፡፡ነገሩ ሁሉ ሾላ በድፍን በሆነበት ባሁኑ ጊዜ የሽግግር መንግስት ምስረታ ማሰብ የበራችልንን ቁራጭ የነጻነት ሻማ አስነጥቀን እንደገና በጭቆና ጨለማ ዉስጥ ለመደነባበር መቸኮል ይመስለኛል፡፡

እንደምናዉቀዉ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን የመጣዉ የኢህአዴግ ሞተር የሆነዉን ህወሃት ይሁንታ አግኝቶ አይደለም፡፡ አሁንም በነዚህ ኃይሎች ክፉኛ እየተፈተነ መሆኑ የምናዬዉ ሃቅ ነዉ፡፡ እናም “እኛ ኢህአዴጎች…..” እያለ በየስብሰባዉ ላይ ስለመሠከረ ብቻ፣ ዶ/ር አብይ የኢህአዴግን ቀኖና አምኖ የተጠመቀ ካድሬ ነዉ ብሎ መናገር በየእሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ያላመነን ሰዉ ክርስቲያን ብሎ እንደ መጥራት ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ዶ/ሩ እንዳሉት አስቀድሞ ስም ቀይሮ በግብር እዚያዉ ከመሆን አስቀድሞ ግብሩን መቀየሩ ላይ አጥብቆ መስራቱ ሳይሻል ይቀራልን? ቆይቶ ግብሩ ስሙን ይቀይረዋልና!!

ያሁኑ የመሪዎቻችን ጥረት በተቻለ መጠን ያለምንም ደም መፋሰስና እልቂት፣ኢህአዴግ የተባለዉ አገዛዝ ቀስ በቀስ ሟሙቶ እንዲጠፋ ማድረግና ከሁለት አመት በኀላ በነጻ ምርጫ በህዝብ ድምጽ ያሸነፈዉ/ያሸነፉት ፓርቲ/ፓርቲዎች መንግስት እንዲመሰርቱ ማስቻል መሆን አለበት፡፡ያኔ ወደድንም ጠላንም ኢህአዴግ የሚባል ግንባር እንደማይኖር በርግጠኝነት ለመናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ የሚለዉ ስያሜ ከነዶ/ር አብይ የአመራር ፍልስፍና በልክ የተሰፋ መጠሪያ ሊሆነዉ አይችልም፡፡ይህንን ለማወቅ እዚያም እዚህም ተበጣጥቀዉ ያሉ በተለያዩ ወቅቶች ያደረጓቸዉን የዶ/ር አብይ ንግግሮችን ሰፍቶ ማጤንና ማስተንተንን ብቻ ይበቃል፡፡ያኔ ዶ/ር አብይ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የመያዝ ዕቅድ እንደሌላቸዉ ይገባናል፡፡

ኢህአዴግ የሚለዉን መጠሪያ ካዋቀሩት ቃላት መሃል “አብዮታዊ” እና “ግንባር” በሚሉት በነዚህ ሁለት ቃላት ብቻ ኢህአዴግ የሚለዉ ስያሜ እንደሚቀየር ዶ/ር አብይን ሳንጠይቅ ማወቅ ይቻላል፡፡

ራሱን ሪፎርሚሰት ብሎ የሚጠራዉ ዶ/ር አብይ አብዮተኛ ነን ለሚሉ ድርጅቶች ብዙም ስሜት ያላቸዉ አይመስልም፡፡ቀድሞ ነገር አብዮትና ዴሞክራሲ አብረዉ ለመዝለቅ የሚሳናቸዉ ሃራምባና ቆቦ ሃሳቦች ናቸዉና፡፡ በሃገራችን የተከሰቱት ሁለት አብዮቶች የሃገሪቱን ጅምር ልማቶች አዉድመዉ ከዜሮ የጀመሩና ብዙ ደም ያፋሰሱ በመሆናቸዉ ከአብዮት ይልቅ ለሪፎርም ቅደሚያ ይሰጣሉና፡፡በዚህም ሰበብ እነዶ/ር አብይ የሚመሩት የወደፊቱ ፓርቲ አብዮታዊ ከሚለዉ ተቀጽላ የጸዳ ይሆናል ብሎ ማለት ይቻላል፡፡

ሌላኛዉ ግምባር የሚለዉ ቃልም ለጦረኞችና ለገዳዮች ስብስብ የሚሰጥ መጠሪያ እንጂ ፍቅር፣ይቅርታንና ሠላምን ለሚሰብክ ድርጅት የሚመጥን መጠሪያ ሊሆን አይችልም፡፡ስለሆነም ግንባር የሚለዉም ቃል ኢህአዴግ ከሚለዉ ስያሜ መወገዱ ሳይታለም የተፈታ ነዉ፡፡ ምን ቀረ? ኢህዴ ብቻ!!  ስለዚህ ይቺ ሃገር የሚያስፈልጋት ግንባር ሳይሆን አመለካከትን መሰረት ያረገ ፓርቲ ነዉና ግንባር ለቴስታ ብቻ ሆኖ ይቀራል ማለት ነዉ፡፡

ይሄዉ ዶ/ር አብይ መስራት ያለበትን ፈርጀ ብዙ ስራዎችን ለመስራት ሌት ተቀን እየለፋ እንደሚገኝ እየታዘብን ነዉ፡፡ወዴት እንደሚወስደንና በየትኛዉ መንገድ እንደሚወስደን በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳዉቆናል፡፡ አታሞ በሰዉ እጅ ያምር…ነዉና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዶ/ር አብይ እጅ ያለዉን ከበሮ ለመቀበል ከመቋመጥ በፊት፣ አታሞዉ ነገ በእነሱ እጅ ላይ ሲሆንም እንዲያምር ከወዲሁ መስራት ያለባቸዉን ነገር መስራት ላይ ቢያተኩሩ ዉጤታማ ለመሆን ያግዛቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡እንደቀደመዉ ትዉልድ በ”እናሸንፋለን” እና በ”እናቸንፋለን” እየተጣሉ መቶ ግልገል ፓርቲዎችን አቋቁሞ  አገር ለመምራት ማሰብ ቅዠት ነዉ፡፡በአዲሱ የመደመር ፍልስፍና የተበጣጠቁት ፓርቲዎችም መደመር አለባቸዉ፡፡ዶ/ር አብይ እንዳለዉ ለዚች ሃገር ሁለት ወይም ሶስት ጠንካራ አገራዊ ፓርቲዎች ይበቋታል፡፡ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ለስልጣን መቋመጡንና በረባ ባልረባዉ አንጃግራንጃዉን አቁመዉ በቀጣዩ ምርጫ ቢያንስ ቢያንስ የጥምር መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ ለማግኘት ከወዲሁ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡

እስከዚያዉ ግን የዶ/ር አብይ አስተዳደር በዚህ አያያዙ ከቀጠለ እንደ ሽግግር መንግስት ቆጥረነዉ ወደቀጣዩ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲያሻግረን እድል ልንሰጠዉ ይገባል፡፡ያለበለዚያ ዶ/ር አብይ ያለበትን የዉስጥ ፍትጊና ጦርነት ረስተን ወቅቱን ያልጠበቀ ግብታዊ ጥያቄ እያቀረብን ለተጀመረዉ ለዉጥ ሳንካ እየፈጠርን ለለዉጡ እንቅፋት ባንሆን መልካም ይመስለኛል፡፡ስለዚህ ለነዶ/ር አብይ በሙሉ ልብ የምናደርገዉን ድጋፍ እንዳይሸረሽሩት እንደነ ሠዓሊ አምሳሉ አይነት ፀኃፊዎችን  ሃሳብ ልንሞግት ግድ ይለናል፡፡ላለፉት 27 ዓመታት በጭቆና ዉስጥ ሆነን ብሩህ ቀን እንዲመጣ የታገስን ህዝቦች ለዶ/ር አቢይ 2 ዓመት መስጠት ከከበደን “እዉር ነገ ዓይንህ ይበራልሃል ቢሉት ዛሬን እንዴት አድሬ?” እንዳለዉ መሆናችን አይደል?ትግስቱን ይስጠን!!

Filed in: Amharic