>

በምጥ የተያዘችውን ሴት የገደሉ የክልል ፖሊሶች ለፍርድ አልቀረቡም!!! (ውብሸት ታዬ)

በምጥ የተያዘችውን ሴት የገደሉ የክልል ፖሊሶች ለፍርድ አልቀረቡም!!!
ውብሸት ታዬ
ሆን ተብሎ ሕዝቡን ወደቁጣ ለመምራት 
ካሳ በመስጠት ለመሸፋፈን እየተሞከረ ነው!!
 
   ሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ‘በምጥ ለተያዘች ነፍስ ጥይት?!’ በሚል ርዕስ በዚሁ ማሕበራዊ ገጽ ያጋራሁዋችሁ መረጃ ነበር።
  ጉዳዩ በአጭሩ በተጠቀሰው ዕለት ምጥ የጠናባት ወ/ሮ ብርሃኔ ማሞ ከሜጢ ከተማ ወደደምቢ ዶሎ ሆስፒታል ሪፈር ተብላ ደምቢዶሎ ከተማ ከምሽቱ 5:30 ላይ ስትደርስ በክልሉ ፖሊስ ልዩ ሃይል በጥይት ተገድላለች። አብረዋት የነበሩ የቤተሰቦቿ አባላት የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዚህ ግፍ ጋር በተያያዘ በቀጣዩ ቀን ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞ በከተማዋ ተቀስቅሶ የነበረ ሲሆን በግድያው ተሳትፈዋል የተባሉ ሶስት የፖሊስ አባላት:-
    ማለትም 1ኛ ኮንስታብል አብርሃም ስዩም፣ 2ኛ ኮንስታብል በቀለ በዳዳ(Badhaadhaa)፣ 3ኛ ኮንስታብል መልካሙ ነጋሳ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እንደተጀመረ ጠቁሜ ነበር። እውነታው ግን ከዚያ የተለየና አስደንጋጭ የማናለብኝ የፍትሕ ጥሰት እየተፈፀመ መሆኑን ዛሬ ያነበብኩት የረዥም እስር አጋሬና ጓደኛዬ   የ Lammii Beenyaa  መረጃ አረጋግጦልኛል። ተጠርጣሪዎቹ እስከዛሬ ለፍርድ አልቀረቡም! ያሳዝናል፤ ልብ ይሰብራል!
  በደምቢዶሎ ከሚገኙ ጓደኞቼ ደውዬ እንዳረጋገጥኩትም ሁኔታው ሆን ተብሎ ሕዝቡን ወደቁጣ ለመምራት በሚመስል መንገድ የፍትሕ መበየንን ወደጎን በማድረግ ጉዳዩን ለተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ በመስጠት ለመሸፋፈን እየተሞከረ ነው ብለውኛል። በቁጥጥር ስር ዋሉ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ያሉበት ወታደራዊ ካምፕም በቀላሉ ለማምለጥ አመቺ መሆኑ ሕዝቡን ቁጭት ውስጥ እንደከተተው ነግረውኛል።
   በምጥ ስትቃትት በጥይት ናዳ ያለፈችው የወ/ሮ ብርሃኔ ደምና ይህችን ምድር እንዳይቀላቀል በግፍ የተቀጨው ህፃን ነፍስ ይጮሃሉ። ይህን ግፍ አቅልሎ ማለፍ የህሊናም፣ የመንፈስም፣ የነፍስም፣ በአጠቃላይም የሰው መሆን ዕዳችን ነው። ደጋግመን እንላለን፤ ፍትሕ በአስቸኳይ! ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ!
(የፎቶ መግለጫ የግፍ ግድያውን በመቃወም በደምዶሎ የተደረገ ትዕይንተ ሕዝብ)
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic