>

የኢትዮጵያ ሮያል የባህር ኃይል! (አሰፋ ሀይሉ)

የኢትዮጵያ ሮያል የባህር ኃይል !
አሰፋ ሀይሉ
ይህ የኢትዮጵያ ሮያል የባህር ኃይሎች መለዮ ላይ የሚደረግ አርማ (‹‹ኢንሲግኒያ››) ነበር፡፡ በመጀመሪያ አሜሪካኖች የቃኘውን ባህር ኃይል የጦር ሠፈር ለራሳቸው ባህር ሠርጓጆች መናገሻነት ከኢጣልያ ወረራ በፊት እንዳቋቋሙት ይነገራል፡፡ በ1947 ዓ.ም. ደግሞ – የኢትዮጵያ ሮያል የባህር ኃይል – “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የባህር ኃይል” የሚል ኦፊሴላዊ ስም ተሰጥቶት – ቋሚ የጦር ሠፈሩን – በምፅዋ ወደብ ላይ አቋቋመ፡፡
በ1950 ዓ.ም. ላይ – ሦስት ተከታታይ ዓመታትን የፈጀው – ታላቅ የግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅ – ይህ የኢትዮጵያ ሮያል የባህር ኃይል – ከንጉሠ ነገሥቱ የምድር ጦር እና ከንጉሠ ነገሥቱ የአየር ኃይል በመቀጠል – በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ መምሪያ ሥር – በሦስተኛነት ተደመረ፡፡
የኢትዮጵያ ሮያል የባህር ኃይል ታሪክ እንደሚያስረዳው – ሲቋቋም ጀምሮ ዋና ግዳጁ የነበረው – በቀይ ባህር ጠረፎች ላይ ቁጥጥርና አሰሣ የማድረግ – ቋሚ የቅኝት ግዳጅ ሲሆን – ዋና ማዘዣውን አዲስ አበባ እና ምፅዋ ላይ አድርጎ፣ በመጀመሪያ በክብር ዘበኛና የምድር ጦር ምክትል ዋና አዛዥ ሥር፣ በመቀጠልም የጦር ኃይሎች ሁሉ ጠቅላይ አዛዥ በሆኑት በግርማዊነታቸው በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘ ኢትዮጵያ ዋና የጦር አዛዥነት ሥር እንዲመራ ተደረገ፡፡
የኢትዮጵያ ሮያል የባህር ኃይል በቆይታው ዘመን – የናቫል ኦፊሰሮች ማሰልጠኛ ኮሌጅ በአስመራ፣ የዳይቪንግ ማሰልጠኛ ኮሌጅ በምፅዋ፣ የስፔሻል ኮማንዶ ዩኒት ማሠልጠኛ ኮሌጅ በምፅዋ፣ በአሰብና በአስመራ፣ እና የባህር ኃይል የመገናኛና ጥገና ኮሌጅ በቀይ ባህር ዳህላክ ደሴት ላይ፣ እንዲቋቋሙ ከማድረጉም በላይ – በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድና ያላሠለሠ ጥረት – በዓለም ሥመ ጥር በሆኑት የሮያል ኖርዌጂያን የባህር ኃይል ኮሌጅ፣ የብሪትሽ ሮያል ባህር ኃይል ኮሌጅ፣  የኢታሊያን ናቫል አካዳሚ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ናቫል አካዳሚ፣ የሶቭየት ናቫል አቪዬሽን፣ እና በሌሎችም ታዋቂ የባህር ኃይል መኮንኖች አካዳሚዎች የኢትዮጵያና የኤርትራ ተወላጆች በከፍተኛ ቁጥር እየተላኩ ትምህርት ቀስመው እንዲመለሱና በአማካሪነት እና በአሠልጣኝነት ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ አድርጓል፡፡
በ1983 ዓ.ም. ሕዝባዊ ግንባርና ኢህአዴግ የምድር ጦር ሠራዊቶች በጋራ የደርግን የባህር ኃይል ሠራዊት – በምፅዋና አሰብ ከነነበሩት የጦር መርከቦችና የጦር ጀልባዎች ጋር ደምስሰው – አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ በኋላ – የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ – እንዲፈርስ ስለተደረገ  – ከዚያ ወዲህ ህልውናው አክትሞ – በታሪክ ማህደር ብቻ የሚገኝ – ያለፈና የማይመለስ የታሪክ ግብዓት ብቻ ሆኖ ቀርቷል፡፡
በአሁኑ ሠዓት በአዲስ አበባ የሚገኘው የቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት የባህር ኃይል ዋና የጦር ሠፈር – የኢሥፍ (ማለትም የምሥራቅ አፈፍሪካ ተጠባባቂ ጦር) ዋና መቀመጫ ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን – ብዙዎቹ መርከቦች እንደወደሙ – የቀሩትም ለሌሎች ሀገሮች እንደተሸጡ – ሌሎቹም ባሉበት በስብሰው እንደቀሩ ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ ሮያል የባህር ኃይል በስም ተለይተው የሚታወቁ በርካታ የጦር መርከቦችና ጀልባዎች የነበሩት ሲሆን – ለኢትዮጵያ በህይወት የተረፈቻት አንዲት ጂቢ-21 የተሰኘች – ለእናቷ ብቸኛ የቅኝት የጦር ጀልባ – በአሁኑ ሰዓት – በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለቤትነት – ሀገራችን በቀራት ብቸኛው ታላቁ የውሀ አካል ላይ – ማለትም በጣና ኃይቅ ላይ –  በሠላም እየተንሸራሸረች እንደሆነ ይታመናል፡፡ በበኩሌ ‹‹ዘርዓይ ድረስ›› ትባል የነበች መርከብ እንደነበረች ሰሜቼያለሁ – ለምን እንደሆነ አላውቅም ይህቺን መርኬ ዝም ብዬ እ ወ ዳ ታ ለ ሁ ! ! !
ወደፊት – አንድ ቀን – የኢትዮጵያና የኤርትራ ወንድማማች እህትማማች ሕዝቦች – ለዘመናት ህብረትና ጥንካሬያችንን በማይፈልጉ ቅኝ ገዢዎች – እንዲሁም ብሶት (አሊያም ስር-የሰደደ ሸር) በፈነቀላቸው ኃይሎች በተፈጠረው የሀበሾች ሕዝቦች የእርስ በእርስ ፍጅት የተነሣ – ማንንም ላይጠቅም – ወደኋላ ያስቀረንን – ተመልሶ ቁልቁል የተምዘገዘገውን – ጎረቤቶቻችንን ብቻ አጠንክሮ – እኛን እርስ በእርስ አፋጭቶ የቆየውን – ያን ታላቅ የፀብ ግድግዳ አፍርሰን – ያን ታላቅ ጥቁር የጥላቻና የፀብ ፅልመት አስወግደን – አንድ የታላቅ ሕዝቦች የተደመረ የፍቅር፣ የተደመረ የታላቅ የሀበሻ ሕዝቦች ማንነት፣ እና አንድ የተደመረ ሊመጣ ያለውን ማንም ሊገረስሰው የማይችለውን በፍቅርና በፈቃደኝነት ላይ መሠረቱን ያቆመውን – የታላቆቹ የኤትርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ የባህር ኃይል፣ የጋራ የባህር ኃይል ኮሌጅ፣ የጋራ የባህር ኃይል የክብር ሜዳሊያ፣ የጋራ የባህር ኃይል ብሔራዊ አገልግሎት ኖሯቸው – በተባበረ የሀበሻ ልጆች ክንድ – በተባበረ የሀበሻ ልጆች ወደር የማይገኝለት አቅም – ሀገሩን፣ ሠማዩን፣ ባህሩን፣ አድማሱን ሁሉ በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደምንሞላው – እንደምናጥለቀልቀው – አንድ ቀን ያ እንደማይቀር – በፍፁም ልቤ፣ በፍፁም ነፍሴ፣ በፍፁም ሁሉ ነገሬ አምናለሁ፡፡
ለእኔ የሚታየኝ – ብዙዎች እንደሚሉት ኦና የሆነና ያረጀ ያፈጀ የባህር ፍቅር – ወይ የባህር በር ፍቅር – ወይ የድንበር ፍቅር አይደለም፡፡ ለእኔ የሚታየኝ በሸርና በተንኮል በስልት ተጎንጉኖ ባጭሩ እንዲሰነጣጠቅ፣ እንዲቆማመጥ የተደረገው ታላቁ የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን ታላቅ ሕዝባዊ ማዕበል ነው፡፡ የሀበሻ ልጆች – ከነልጆቻችን – ከነልጅ ልጆቻችን – ከነዘርማንዘሮቻችን – በፍቅር ስንደመር – ምድር የማትበቃን – ታላቅ የአፍሪካ ሕዝቦች እንሆናለን፡፡ ታላቅ ኃይልን የምንላበስ – በተባበረ ጥረታችን፣ አብሮነታችንና ክንዳችን – ታላቅ የብልፅግና ማማ ላይ ህዝባችንን ማድረስ የምንችል – ታላቅ ሕዝቦች እንደምንሆን አንዳችም ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህ የእኔ የፍቅር ሕልም ነው፡፡ ይህ የአንድ፣ የሁለት፣ የሶስት፣ የአራት ሰው – ወይም የጥቂት ሺህዎች ሀበሾች ቅዠት ብቻ እንዳልሆነ፣ ሆኖም እንደማይቀር – በቅርብ ያየናቸው ሀበሻዊ የፍቅር ማዕበሎች በዓይናችን በብረቱ አሳይተውናል፡፡ እኛ አሁን ላይ በሕይወት የምንገኝ የኢትዮጵያና የኤርትራ ትውልዶች ለዚህ ሊመጣ ላለው ታላቁ ህብረታችን – ህያው ምስክር ነን፡፡ ይህ የእኔ ብቻ ሳይሆን – የብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሕልም እንደሆነም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አምናለሁ፡፡
አምላክ – የሀበሻ ልጆችን ሁሉ – አንድም ሣያስቀር – ከነልጅ ልጅ ልጆቻቸው – እስከመጪዎቹ አስር ሺኅ ታላላቅ ሀበሻዊ ትውልዶቻቸው ድረስ – አብዝቶ አብዝቶ ይባርክ ዘንድ ከልብ ተመኘሁ፡፡ እምዬ ኢትዮጵያ – በልጆቿ ፍቅር ተሞልታ – ለዘለዓለም ትኑር፡፡ አበቃሁ፡፡
‹‹The Ethiopian Navy, known as the Imperial Ethiopian Navy until 1974, was a branch of the Ethiopian National Defense Force founded in 1955. It was disestablished in 1996 after the independence of Eritrea in 1991 that left Ethiopia landlocked.››
— Ethiopian Navy, From Wikipedia, the free encyclopedia.
Filed in: Amharic