ያለመታመን እዳ!!
የሽሀሳብ አበራ
መንግስት የሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ በጥርጣሬ እየታዮ እየወደሙ ነው፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ይሄ ተከስቷል፡፡ ኩርፊያ እና ጥርጣሬ በመንግስት ላይ ከፍ ብሏል፡፡ በእርግጥ በ 27 ዓመቱ ውስጥ እንኳን የሚታመን መንግስት መንግስታዊ መዋቅር እንኳን እንዳልነበር በእስረኞች ላይ የደረሰውን ግፍ እና የነ መላኩ ፈንታን እንዲሁም የታምራት ላይኔን ቃለመጠይቅ የሰማ ይረዳል፡፡
ጠሚዶ አብይ አህመድም መንግስታዊ አሸባሪነት ከመኖሩም በላይ ያለፉት 27 ዓመታት ቆሻሻ ተግባራት የተፈፀመባቸው እንደሆነ መስክረዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት የተፈፀሙ ወንጀሎች በቀጣይም መንግስትን በጥርጣሬ ህዝቡ እንዲመለከተው ይገፋሉ፡፡
…
አቶ መላኩ ፈንታ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጠው ቃለመጠይቅ ሲታሰር ብአዴን አልሰማም፡፡ያሰረው ማፍያ ቡድኑ ነው፡፡ ብአዴን ከንፈሩን ከመምጠጥ ያለፈ ሚና አልነበረውም፡፡ ብአዴን፣በድርጅት ግምገማ ከሙስና ንፁህ በመሆን ከፍተኛ ሰጥቶ ፣ በሳምንቱ በከባድ ሙስና ሲታሰር ቤተሰቦቹን እንኳ ብአዴን ለመጠየቅ ፈራ፡፡ እንደ ህዝቡ ከንፈሩን መጦ ዝም አለ፡፡ አቶ መላኩ አቶ በረከት እና የህወሓት ሰዎች እንዳሰሰራቸው አብራርተዋል፡፡የሚገርመው አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከጎንህ ነኝ ሲሏቸው ቆይተው አቶ መላኩን ፈርመው አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል፡፡ ከአቶ ታምራት ላይኔ ልምድ በመነሳት አቶ ሃይለማርያምም የእስር፣የድብደባ፣የዛቻ ቅጣቶች በማፍያ ቡድኑ እንደሚደርስባቸው መጠርጠር ቀላል ነው፡፡ አቶ ሃይለማርያም በስልጣን እያሉም የሃገሪቱን መረጃ እኔ አላውቅም ብለው በግላጭ ተናግረዋል፡፡ ሃገሪቱ የምትመራው ውስኪ ቤት በሚወሰን ውሳኔ እንጂ በምክርቤት አይደለም፡፡የምክር ቤት አባልትም የሃሳብ ደሃዎች፣መሞገት ነውር የሚመስላቸው፣ከሰውነት ክብር ወርደው እሺ እሺ ብለው ሲያጎነብሱ፣ሲጫኑ የኖሩ ወንበር አሟቂዎች ነበሩ፡፡ ከጫካ እንደሚኖሩ አንድ ቀንም የወጡበትን ማህበረሰብ ችግር አውጥተው አያውቁም፡፡
…
…
የሶማሌው አብዲ ኢሊ፣ ጌታቸው አሰፋ ከአዲስ አበባ ሰው ሹሞ እንደሚልክ በግልፅ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ጁነዱን ሳዶ ” ርዕሰ መስተዳድር ብሆንም፣የኦሮሚያን ክልል አንድ ቀንም መርቸው አላውቅም” ብለዋል፡፡
አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ካሁን በኃላ እንጂ ከዚህ ቀደም ርዕሰመስተዳድር ቢሆኑም ክልሉን ሙሉ በሙሉ እንዳልመሩ ተናግረዋል፡፡
…
ባህርዳር ላይ ካለው እስር ቤት የሚሰቃያ ታሳሪዎችን በተመለከተ በ 2004 አካባቢ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አያሌው ጎበዜ ተጠይቀው ” ስለሚታሰሩ ሰዎችም ሆነ ስለሚታሰሩበት ቦታ መረጃ እንደሌላቸው” ለታሳሪ ቤተሰቦች ተናግረዋል፡፡ብአዴን ባህርዳርን አልመራም፡፡ነገሩ በግለሰብ ደረጃ እንኳን የብአዴን ሰዎች ነፃ አልነበሩም፡፡ታምራት ላይኔ፣መላኩ ፈንታ፣ጀኔራል አሳምነው ፅጌ ወዘተ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ነበሩ፡፡ግን ብአዴን እንኳን ህዝቡን የራሱን አመራሮች ሊያድን አልቻለም፡፡
..
በ 27 ዓመት የነበረው ማፍያ ቡድን በብዛት ወደ ሃላፊነት የሚያመጣቸው የእውቀት ደሃ የሆኑትን ፣ ስነ ልቦናዊ ስብራት ያለባቸውን እና በልተው ለመኖር ብቻ የሚኖሩ ከእንስሳት ከፍ ከሰው ዝቅ ያሉ ሰዎችን ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚመሩት ህዝብ ሁሉ እንደ እንስሳ እየተጫነ እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡ ነፃነት ወይም ሞት ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ እንዳይፈራ አሳቢያንን ወደ እስር እየማገዱ ያስገርፋሉ፡፡
…
የ27 ዓመቱ የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ታሪክ ጥቁር ሆኖ ይመዘገብ ዘንድ ባለታሪኮች ፈቅደዋል፡፡ያውም በህይዎት እያሉ፡፡
…
የመንግስትን የ 27 ዓመት ባህሪውን የተረዳ ህዝብ ወርቅ ቢያነጥፍለትም እሾህ ይመስለዋል፡፡መድሃኒት ቢያቀርብለትም መርዝ ይመስለዋል፡፡ ፀጥታ ሊያስከብርለት ቢፈልግም ራሱ መንግስት አሸባሪ ይመስለዋል፡፡ ስለነበርም፡፡ እንዲህ ከሆነ የህዝብ ቁጣዎች መቀጠላቸው ተፈጥሮአዊ ነው፡፡
…
ብአዴን በ 27 ዓመቱ ካስመዘገበው የውርደት ታሪኩ ተምሮ መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ ወቅቱ ያስገድደዋል፡፡ እስካሁን የሰየማቸው የካቢኔ አባላት እና ልዮ ልዮ ሹመቶች ግን ብአዴን አድሮ ቃሪያነቱን ማሳያ ናቸው፡፡በቀጣይ ጉባዔው ካላስተካከለ እስካሁን የሰጣቸው ሹመቶች የባለፈውን 27 ዓመት ግብዝነት ለመድገም እንዳቀደ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
…
አልማን ጨምሮ ጥረት እና የመሳሰሉት የልማት ድርጅቶች በብዛት የካቢኔ ሚስቶች እና የደከማቸው በጡረታ የሚደጎሙበት ሰዎች በሃላፊነት የሚሾሙበት ቦታ ነው፡፡ እነ ጥረት ያረጁ ካቢኔዎች እንደ መቆዶኒያ የአዛውንቶች ማዕከል ይሰባሰቡና የሚበሉበት፣እንደ ህፃን የሚጫዎቱበት አትራፊ ድርጅት ነው፡፡ ነገር ግን አልማ ሆነ ጥረት የአማራነት ስነ ልቦና ያላቸው ሰዎችን አቅፈው አያውቁም፡፡የአማራ ልማት ማህበር ተብሎ ብሄርተኛ አይደለም፡፡አልማ ብሄርተኛ ካልሆነ የገንዘብ ምንጩ ካሁን በኃሏ ይነጥፋል፡፡
..
ባጠቃላይ ከኢኮኖሚው እስከ ፓለቲካው ጥገናዊ ሳይሆን መሰረታዊ ለውጥ ካልተደረገ ለውጥ ፈላጊ ህዝብ መሪውን መብላቱ የነበረ፣የሚኖር ሃቅ ነው፡፡ዛሬ በየቦታው የሚነሱ ግጭቶች እና ኩርፊያዎች መንግስትን ካለማመን የሚመነጩ በመሆናቸው፣የሚታመን አመራር እና መዋቅር መዘርጋት እንጂ ማውገዝ፣ማሰር መፍትሄ ሆኖም አያውቅም፡፡ሊሆንም አይችልም፡፡ የዛሬ ትንንሽ ቁጣዎች ተደምረው ወደ ግዙፍ አመፅ ሳይቀየሩ በ 27 ዓመት እንኳን መንቃት ካልተቻለ ዙሪያ መለስ ውድመት ይከተላል፡፡