>

የፌደራል መንግስት እርምጃ ትክክለኛ ነው! (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም)

የፌደራል መንግስት እርምጃ ትክክለኛ ነው!
ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም
መለስ ዜናዊ አብዲ ኢሌን ሲሾም፣ ከጋንቤላ እስከ አፋር የክልል መሪዎችን በአንድ ትዕዛዝ ሲያወጣና ሲያወርድ የህግ ጥያቄ አልተነሳም።አብዲ ኢሌ በ10 ዓመታት ውስጥ አስር ሺዎችን ሲገድልና ሲያስገድል፣ መቶሺዎችን ሲያሰደድ የህግ ጥያቄ አልተነሳም። አምባገነኖች ዜጎችን ሲገደሉ የገዳዩ ወገኖች ህግ ተጣሰ አይሉም፣ ዜጎችን ለመታገድ እርምጃ ሲወሰድ ግን ህግ ተጣሰ እያሉ ያላዝናሉ። በህግ ስም መግደል ወንጀል ሳይባል፣ ግድያን ለማስቀረት የሚወሰድ እርምጃ ወንጀል ተደርጎ ሲወሰድ ከማየት በላይ የሚያሳፍር ነገር የለም።  የህዝብን ህልውና የማይታደግ ህግ እንዴት ህግ ሊባል ይችላል? ዶ/ር አብይ የወሰደው እርምጃ ህጋዊና ትክክለኛ ነው። እንደ ቀኖና በየጊዜው የሚጠቀሰው ህገመንግስት መግደለን፣ ማሰርንና ማሳደድን አይፈቅድም፣ ግድያ ተፈጽሞ ሲገኝ ግን አስፈላጊው እርምጃ ተወስዶ ግድያው እንዲቆም ይፈቅዳል።
የዶ/ር አብይን እርምጃ የሚቃወም ሰው የዜጎች ሞትና ስደት የማያሳስበው፣ በህግ ስም እየገደለ ለመኖር የሚያስብ፣ በጥቅም የታወረ እና ሰብአዊ ርህራሄ ያልፈጠረበት ሰው ነው። ገዳዮች ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ሊኖሩ አይፈቀድላቸውም፤ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዜጎች በነጻነት ይኖሩ ዘንድ አምባገነኖች ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ተጠራርገው መውጣት አለባቸው።
 የሶማሊ ወገናችን ስቃይ የእያንዳንዳችን ስቃይ ነው። የሶማሊ ክልል ህዝብ  ሲስቅና ሲደሰት እንጅ ሲያለቅስን ሲተክዝ ማየት አንሻም። ዶ/ር አብይ ህገ መንግስቱንም አለማቀፍ ህጉም በሚፈቅድላቸው መሰረት ሰቆቃቀን ለማስቆም የወሰዱትን ቆራጥ እርምጃ፣ ለሰው ልጆች መብት መከበር የሚታገሉ ሁሉ ሊደግፉት ይገባል።
Filed in: Amharic