>

ከተቃጠለው ሕዝብ ይልቅ የአቃጣዩ አያያዝ በሚያስጨንቃቸው ሰዎች ሥር መኖር ከባድ ነው!!! (ዳንኤል ክብረት)

ከተቃጠለው ሕዝብ ይልቅ የአቃጣዩ አያያዝ በሚያስጨንቃቸው ሰዎች ሥር መኖር ከባድ ነው!!!
ዳንኤል ክብረት
ኢትዮ-ሶማሊ ክልል የተሠራው ዘግናኝና አረመኔያዊ ሥራ ነው፡፡ ሰውን በቁሙ ማቃጠል፡፡ ሴቶችን መድፈር፡፡ መኪና ይዞ በየቤቱ እየዞሩ የሰው ንብረት መዝረፍ፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል፡፡ ለመሆኑ መንግሥት የለም? አንድ ክልልስ ሥልጣኑ የሰው ዘርን እስከማጥፋት ድረስ ነው?  ይህን መሰሉ ግፍ ዚያድባሬ ኢትዮጵያን የወረረ ጊዜ ነበር በምሥራቁ ክፍል የተፈጸመው፡፡ ዚያድባሬ አለ ማለት ነው? የክልሉ ፕሬዚዳንት የልቡን ከሠራ በኀላ ትናንት ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መጥቶ እንመካከር ሲል ነበር፡፡ ሰው ከተቃጠለ፡ ንብረት ከተዘረፈ፡ ቤተ ክርስቲያን ከተቃጠለ በኀላ የምን ምከከር ነው? አሁን በዚያ ክልል ስላለው ሕዝብ እንደ አዲስ ማሰብ አለብን፡፡ ሌላ መፍትሔም ማምጣት አለብን፡፡ ከተቃጠለው ሕዝብ ይልቅ የአቃጣዩ አያያዝ በሚያስጨንቃቸው ሰዎች ሥር መኖር ከባድ ነው፡፡
በሰሞኑ ግጭት የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናትና ካህናት
1. የዋርዴር  ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል ቄስ  ያሬድ ኅቡዕ ተገደሉ፣
2. ቀብሪ  ደኃር  ደብረ መድኃኒት  ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን  ተቃጥላለች፡፡
3. ደጋሐቡር መካነ  ሰማዕት ቅዱስ  ጊዮርጊስ  ቤተክርስቲያን ሲቃጠል ቄስ ኪዳነ ማርያም ንብረቱ ተገድለዋል፡፡
4. በጅጅጋ የምሥራቀ  ፀሐይ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል እና የደብረ ሰዋስው ገዳም የተቃጠሉ ሲሆን
 አባ ገብረ  ማርያም  አስፋው፣ መ/ር አብርሃም ጽጋቡ ተገድለው አስከሬናቸው ተቃጥሏል፡፡
***
የኢትዮጵያ መንግስት በጅጅጋ እየተፈጸመ ላለው ዘግኛኝ እልቂት አፋጣኝ መፍትሔ ይስጥ!!
መ/ር ታሪኩ አበራ
«ሰይፍን የሚያነሱ ሁሉ  በሰይፍ ይጠፋሉ»ማቴ 26፥52
እናንተ የሰው ደም የጠማችሁ፣የዲያብሎስ መንፈስ በልባችሁ የነገሠ  አሕዛብ እፈሩ እኛ ክርስቲያኖች ስንሞት እንበዛለን እንጂ አንቀነስም፤ሲመቱን እንደ ሚስማር እንጠብቃለን እንጂ አናፈገፍግም፣ሞት ይፈራናል እንጂ እኛስ ሞትን አንፈራም፤ የምናመልከው ጌታ በሲዖልና በመቃብር ላይ ድልን የተቀዳጀውን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።እስከሞት ድረስ  እንታመናለን አክሊልንም በአባቱ ዙፋን ፊት እንቀዳጃለን።
እናንተ የክፋት መርዝ በልባችሁ የሞላ የእፉኝት ልጆች ይህንን እወቁ በመሞት እንጂ በመግደል ጽድቅ የለም፤አባታችሁ መግደልን በሰይፍ አስተምሯችኋል፤ እኛ ደግሞ አባታችን  እየሞቱ መክበርን በመስቀል ላይ አስተምሮናል።እግዚአብሔር ጻድቅ ፈራጅ ነው ያፈሰሳችሁትን ደም በሰባት እጥፍ በቅርቡ ይበቀላችኋል። እግዚአብሔር እግዚአብሔር ነው፤ የማንም ደም ባለ ዕዳ አይደለም፣ ደማቸው በግፍ  የፈሰሰውን የንጹሐን ክርስቲያኖችን ሕይወት በእናንተና በቤታችሁ ላይ ይበቀላል።
 በጅጅጋ የፈሰሰው የሰማዕታቱ ደም በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ጌታ ሆይ ፍረድልን እያለ ይጮኻል።እውነት እውነት እላችኋለው እናንተ እጃችሁ በሰው ደም የጨቀየ አማሌቃውያን ከእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ አታመልጡም።
ክርስትና በክርስቶስ ሞት ተመስርታ በሰማዕታት ደም የጸናች ቅድስት እምነት ነች። ከጥንት እስከ አሁን ሰይጣን ቀስቱን ወረወረ፣ዝናሩንም ፈታ ቤተክርስቲያንን ግን ከቶውን ሊያጠፋት አልቻለም።ዮዲት ጉዲት ቤተክርስቲያንን አቃጠለች፣ ካህናትን ገደለች፤ ነገር ግን   እርስዋ ጠፋች እንጂ  ቤተክርስቲያን እስካሁን በክብር  አለች።ግራኝ መሐመድ አብያተ ክርስቲያናትን አቃጠለ፣ ካህናትን አርዶ ገደለ እርሱም አሟሟቱ  ከፍቶ ጠፋ ቤተክርስቲያን ግን እስካሁን ከነሙሉ ክብሯ አለች።በአረመኔው ንጉሥ በዲዮቅልጢያኖስ ሰይፍ ያልጠፋች ቤተክርስቲያን መቼም አትጠፋም ፡ ጠላቶችዋ ግን እንደ ቅጠል ይረግፋሉ፣እንደ አክርማም ይሰነጠቃሉ፣እሳት እንዳየው የሸማኔ ፈትል በመለኮታዊ የቁጣ በትር ከምድረ ገጽ ይጠፋሉ።  ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ላይ ስለተመሰረተች ወጅብም ቢነሳ ነፋስም ቢነፍስ ከቶውንም  አትወድቅም። ከቤተክርስቲያን ጋር የሚጋፉ ሰዎች ሁሉ የሚታገሉት ሰማይና ምድርን በቃሉ ካጸናው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ጋር ነውና ፍጻሜያቸው እጀግ የከፋ ነው። ፈርዖንና ሠራዊቱን የቀጣ የእግዚአብሔር ክንድ በእነርሱም ላይ ይወድቃል፤ መጨረሻቸውም ከባድ ጉስቅልናና ጥፋት ነው።ከዓለቱ ጋር ለሚታገል ለእርሱ ወዮለት! ዓለቱ በወደቀበት ጊዜ ያደቀዋል፤ ፈውስም አያገኝም።ዓለቱ እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።
በጅጅጋ ሰማዕታት የሆናችሁ  የክርስቶስ ሙሽሮች በረከታችሁ ይደርብን።
በጅጅጋ ያላችሁ  ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ ጽናትና ብርታት ይስጣችሁ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን አንዳችም ኃይል የለም፣መካራም ሰይፍም ያልፋል ቤተክርስቲያን ግን ለዘለዓለም ጸንታ ትኖራለች።በርቱ ፣በሃይማኖት ቁሙ የቅዱሳን አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን።ልባችን ከእናንተ ጋር ነው።
እባካችሁ ክርስቲያኖች በጸሎት እናስቧቸው።
Filed in: Amharic