>

በአገራችን አንድነት አንደራደርም!!! አንዱዓለም ቦኪቶ)

በአገራችን አንድነት አንደራደርም!!!
አንዱዓለም ቦኪቶ
ሁልህም ትኖራለህ ትኖራለህ! ..ወንድምህ ነኝ !ወንድሜ ነህ! …ትንሽ በተኳረፍን ቁጥር የእናታችንን ቤት ጥለን እየሮጥን የአባታችንን ቤት ካላፈረስን የምንል ከሆነማ ..እንዴት ይሆናል ወገን?! እረ እየተስተዋለ!!!
 
በትላንትናው እለት መከላከያችን ጅጅጋ ውስጥ ባደረገው ኦፕሬሽን አብዲ ኢሌ አስቦት የነበረውን ሴራ አክሽፎ ተልእኮውን በድል በመወጣት ከተማውን ለቆ ወጥቷል፡፡ይህንን ነገር አንዳንዶች በተለያየ መንገድ በመረዳት እዚህም እዛም የሚለጥፉትን እያየን እያዘንን ነው፡፡..የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ሌክቸረር ነው የተባለ በስሱ ፊደል የቆጠረ ልጅ ሳይቀር “ጀግናው የሶማሌ ጦር የኢትዮጲያን መከላከያ ሰራዊት ቂጡን ብሎ አባረረው” አይነት ይዘት ያለው ፖስት ሲፖስት ስታዩ ምንም እንኳን ባንዳነትን ብርቅ ባይንም ይሄን ያህል የወገኑ መከላከያ ሰራዊት በወሮበሎች መጠቃት ወይም “መሸነፍ” የሚያስፈነድቀው ጭንጋፍ በዚህ እድሜዬ ያውም በመጠኑ ፊደል ከቆጠረ ሰው ስላልጠበኩ በጣም መደንገጤም አልቀረም፡፡
ከኤርትራ ስንታረቅ “አማራ ወደብህን ፡የትግራይ ህዝብ ፍቅርህን ነው የሚፈልገው” ብሎ ወደቡን ብቻችንን የምንጠቀምበት ይመስል የሾካካ መፈክር ይዞ የሚወጣ ተጋሩ ወጣት ስታዩ …ሶማሌን “ነዳጅህን ፈልገው ነው አትስማቸው በላቸው” የሚል ወጣት ተጋሩ ስታዩ …በአንድ ወቅት የኢትዮጲያ ማእከል የነበረችው ትግራይ…እና ያ በአገር ፍቅር የማይታማው ኩሩ  እና ታላቅ ህዝብ እንዴት ዛሬ ላይ እጃችንን አፋችን ላይ የሚያስጭኑን ወጣቶች እንዳፈራ ስታስቡት የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሚሯሯጡና  በታላላቆቹ ሌቦች ስፖንሰር የሚደረጉ ግልገል አሳማ ፌስቡከሮች  አእምሮውን ለመጠምዘዝ ያደረጉት ስራ ምን ያህል መሬት እንደያዘ ስትረዱ ትደነግጣላችሁ!
በኢትዮጲያ ሶማሌ የሚደረገው ፊር ፊር በአጭር ግዜ ውስጥ እልባት ያገኛል…እሱ አያሳስበኝም፡፡ማንም አገሩን የጠላ ባንዳ የባንዳ ልጅ ባረቀቀው ህገመንግስት መነሻ ሚሊዮኖች የወደቁላት አገር የማንም መንደሬ በከፋው ቁጥር ጥዬ እሄዳለው ስላለ ተቦጫጭቃ አትቀርም፡፡ ሁልህም ትኖራለህ ትኖራለህ! ..ወንድምህ ነኝ !ወንድሜ ነህ! …ትንሽ በተኳረፍን ቁጥር የእናታችንን ቤት ጥለን እየሮጥን የአባታችንን ቤት ካላፈረስን የምንል ከሆነማ ..እንዴት ይሆናል ወገን?! …አብሮን መኖር የማይችል  ትእግስቱ ያለቀበት ወንድም ካለም ለጊዜው የእናቱን ቤት ለቆ (መሬቱን ለቆ)  በመውጣት ጎረቤት አገር ስደተኛ ሆኖ መኖር ይችላል፡፡ ካላስ! ሲበርድት ይመለሳል እንጂ ማንም ጤነኛ ህዝብ “አብረን እንኖራለን ሲከፋን ደግሞ እስከመገንጠል መብት አለን” ብሎ በአዋጅ  ጽፎ አገር አይመሰርትም!፡፡  እኔ ኢትዮጰያው የባሌ ኦሮሞው አባቴ በሶማሌ ጦርነት ተዋግቶ አስፈላጊውን መስዋትነት ከፍሎ ድንበሩን እንዳስረከበኝ ነው የማውቀው …፡፡ በእኔ ግዜም  የሀገርን አንድነት አስጠብቆ ለማቆየት አስፈላጊ ከሆነ የትኛውንም መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ፡፡
ሁላችንም እንዲያው “ፖለቲካሊ ኮሬክት” ለመሆን  ብለን በአገራችን የአንድነት ጉዳይ ላይ ባንመጻደቅ ጥሩ ነው፡፡
ጠ/ሚ አብይ አህመድ አሁን ኳሷ በእግሮ ስር ነች ….በደንብ አጥቅተው ይጫወቱ… የአገሮን አንድነት አስጠብቀው ታሪክ ሰርተው ይለፉ!…በእርስዎ ግዜ አንዲትም ስንዝር መሬት ከኢትዮጲያችን እንዳትጎል የማንንም ባንዳ ወሬ ሳይሰሙ ስራዎትን ይስሩ .፡፡ ለዚህም ሃያሉ ፈጣሪ ይርዳዎት!
ይህ የእኔ ሃሳብ ነው ፡፡
በኢትዮጲያ አንድነት የሚደራደር ሰው ስለሚከረፋኝ ትንሽ ለሚሞክረኝ ክፉ መልስ ነው ያለኝ ፡፡ ቢ ማይ ገስት፡፡
ኢትዮጲያ ለዘላለም ከነሙሉ አካሏ እና ክብሯ ትኑር፡፡
Filed in: Amharic