>

የግንቦት 7 ሚና  ቢሆን ብዬ የማስበው! (አቻምየለህ ታምሩ)

የግንቦት 7 ሚና  ቢሆን ብዬ የማስበው!
አቻምየለህ ታምሩ
ግንቦት 7 የዜግነት ፖለቲካ ለማራመድ  በአንድ ወር ጊዜ  ውስጥ ወደ ሀገር ቤት ሊያመራ እንደሆነ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  ነግሮናል። በአመራሮቹ የተሰጠውን ጋዜጣዊ  መግለጫ ተከትሎ በማኅበራዊ ሜዲያ  የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ሰንብተዋል።
2. ድርጅቱ በተለያየ ጊዜ ሲያራምዳቸው የነበራቸው  ጸረ አማራ አቋሞቹ  [ለምሳሌ በግንቦት 7 ልሳን ቁጥር 25 ጥቅምት 27 2001 ዓ.ም. በርዕሰ አንቀጹ የወጣው የድርጅቱ አቋም]፤
2. አመራሮቹ  ከ ያ ትውልድ የግራ ፖለቲካ  ትርክት የተላቀቀ የኢትዮጵያ ታሪክ አረዳድ  አለመያዛቸው [ለምሳሌ  አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኢሳት ለንዶን ስቲዲዮ ቀርቦ በሰጠው ቃለ ምልልስ  «የሸዋ መንግሥት» ሲል የጠራውን   የኢትዮጵያ መንግሥት የአማራ መንግሥት አድርጎ  በማቅረብ  ወያኔዎች በትግሬነት ተደራችጀት ከመሰረቱት  የሕወሓት  አገዛዝ  ጋር አንድ አይነት አድርጎ  ያቀረበበርትን  ትክርት ልብ ይሏል]፤
3. ድርጅቱ  በገሀድ የሚታወቅን ሀቅ  ለማስመሰል  የማይገደውና ውሸት ደፋር መሆኑ [ለምሳሌ  ያህል «ሰሜን እዝ» እያለ ሲያወራው የከረመውና  በባለፈው ጋዜጣዊ መግለጫውም  ጭምር  ትጥቅ እንዳስፈታ  አድርጎ ያቀረበው  ዲስኩር ነጭ ውሸት መሆኑ]፤ ወዘተ ከተሰጡት የተቃውሞ አስተያየቶች መካከል ይገኙበታል።
የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ለሚያውቅ ሰው   የዛሬው የአገራችን ፖለቲካ የጦፈ የጎሳ ፖለቲካ ፍልሚያ የሚካሄድበት መስክ  ሆኗል። በሌላ አነጋገር  የፖለቲካ ገበያው የዜግነት ፖለቲካ ለሚያራምድ  ፓርቲ እዚህ ግባ የሚባል ሕበረ ነገዳዊዊ  ገበያ የለውም። ይህ ጠጣር እውነታ በሆነበት  ያገራችን እውነታ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜግነት ፖለቲካ ማራመድ ማለት  የጎሳ ፖለቲካ አራማጆችን  እጥፍ ድርብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ  የሚያደርግ፤ የዜግነት ፖለቲካ የሚካሄድበትን  አካባቢ  ደግሞ  የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን  የዜግነት ፖለቲካ የሚካሄድበትን አካባቢ ድርሻ  የጎሳ ፖለቲከኞች  ድጋሜ እንዲያጫርቱ በማድረግ  አድሎ እንዲፈጸም  ማገዝ ጭምር ነው።
አገሩ የጎሳ ፖለቲካ በመሆነበት አኳኋን የዜግነት ፖለቲካ ማካሄድ ዜግነት ፖለቲካ የሚካሄድበትን አካባቢ ድርሻ ለጎሳ ፖለቲከኞች ማጫረትና እጥፍ ድርብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን በምሳሌ ማስረዳት እፈልጋለሁ።
ኢትዮጵያ ውስጥ በነገድ  መመዘኛ  አማራና ኦሮሞ  በጋራ ሰባ ከመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ይሸፍናሉ። የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምድ የፖለቲካ ፓርቲ  የሚታገለው ስልጣን ለመያዝ ከሆነ የግድ አማራና ኦሮሞን ነገዶችን ማዕከል አድርጎ  ፖለቲካውን ሊዘረጋ ይገባል።   በሌላ አነጋገር ግንቦት 7 አገር ቤት ገብቶ የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምድ ከሆነ  ፖለቲካውን  የአማራና የኦሮሞን ነገዶችን ማዕከል አድርጎ  ሊዘረጋ ይገባል ማለት ነው። ምናልባት ለግንቦት 7 ይህን ማድረግ ላይከብደው ይችላል።
ሆኖም ግን ግንቦት ሰባት በኦሮሞ መካከል ገብቶ ከኦሕዴድና ኦፌኮ ጋር ተወዳድሮ የኦሮሞን ድምጽ ሊያገኝ ይቻላል ወይ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ አሉታዊ ነው። ራሳችንን ማሞኘት ካልፈለግን በስተቀር ግንቦት ሰባት ዛሬ ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ ከኦሕዴድ [ዐቢይና ለማ] እና ኦፌኮ [ በቀለ ገርባና ዶክተር መረራ ጉዲና] ጋር ተወዳድሮ የኦሮሞን ድምጽ ሊያገኝ አይችልም። ይህንን ጠጣር እውነት ልንክደው የማንችለው ሀቅ ነው።
ዛሬ ላይ መሬት የረገጠው  እውነታ ይህን ከመሰለ ግንቦት 7 በሚያራምደው  የዜግነት ፖለቲካ ዋና ገበያው አማራው ብቻ ነው ማለት ነው። ግንቦት 7  ውስጥ የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱ የኦሮሞ ተወላጆች ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም ግን እነዚህ ሰዎች ዛሬ ባለው ነባራዊ እውነታ  ከዐቢይና ለማ፤ ከበቀለ ገርባና ዶክተር መረራ ጋር ተወዳድረው  አሸናፊ ሆነው በመውጣት  የግንቦት 7ን የዜግነት ፖለቲካ ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ  ሊሸጡለት አይችሉም።
እነዚህ የኦሮሞ ተወላጅ ፖለቲከኞች  የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ በመሆናቸው የሚያገኙት ጥቅምና  ሊጫረቱት የሚችሉት ድርሻ  ቢኖር ግንቦት 7  የዜግነት ፖለቲካ እያራመደ ከሚያገኝው  ከአማራው  ድርሻ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር ግንቦት 7 የዜግነት ፖለቲካ በማራመዱ የአማራውን ድርሻ ሙሉ ድርሻውን አሟጦ ለነ ዐቢይና ለማ እንዲሁም ለነ በቀለ ገርባና ዶክተር መረራ የሰጠውን  ኦሮሞን እንወክላለን ለሚሉ እያጫረተ አማራውን እየጎዳ ነው ማለት ነው። ይህ አማራን የሚጎዳና ኦሮሞን ከድርሻው በላይ ከአማራ እንዲጫረት የሚያደርግ ፖለቲካ ትክክል አይደለም።
ዋናው ፖለቲካ የጎሳ በሆነበት የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ  የዜግነት ፖለቲካ ማራመድ የአማራን ድርሻ ለሌላው በማጫረት አማራንው የሚጎዳ ከሆነ  አማራን ማዕከል አድርጎ የዜግነት ፖለቲካ አራምዳለሁ የሚል አካል  የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አድሎ እንዲፈጸም  እያደረገ  ፖለሪካ  ሊሰራ አይቻልም። ዝምም መባል የለበትም።
በዚህ  ነባራዊ  ያገራችን ሁኔታ እንደ  ግንቦት 7  አይነት  የዜግነት ፖለቲካ ማራመድ የሚፈልግ ፓርቲ በሚያደርገው ፖለቲካ  እንቅስቃሴ [ኢትዮጵያውያንን በእኩል  የመጥቀም ፍላጎት ካለው ማለቴ ነው] ማድረግ የሚችለው አንድ ነገር  ይታየኛል። የአንዱን ድርሻ ለሌላው የሚያጫርትበትን የዜግነት ፖለቲካ ፓርቲነት ትቶ ንቅናቄ በመሆን  በምርጫ ሳይሳተፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካው  ከጎሰኛነት ወደ ዜግነት ደረጃ እንዲያድግ የዜግነት ፖለቲካ ኅልዮትን ማዳበር፣ በሕዝቡ ዘንድ  እንዲሰርጽና ተቋማዊ እንዲሆን በማድረግ ድርሻውን ሊወጣ ይችላል።
ስለዚህ  ግንቦት 7  የዜግነት ፖለቲካ አራምዳለሁ ብሎ አገሩ በሙሉ  የጎሳ ፖለቲካ በሆነበት ሁኔታ የአማራውን ድርሻ ለሌላው ለማጫረት ወደ ምርጫ ፖለቲካ ከሚገባ ምርጫ የማይሳተፍ ንቅናቄ ሆኖ ዛሬ ተቋማዊ የሆነው  የኢትዮጵያ የጎሰኛነት  ፖለቲካ ወደ የዜግነት  ፖለቲካ ደረጃ እንዲያድግ  ለማገዝ  የዜግነት ፖለቲካን ኅልዮት ቢያዳብርና  ፋይዳው ላልገባቸው ቢያስተምር፤  የዜግነት ፖለቲካ በሕዝቡ ዘንድ  ተቀባይነት እንዲኖረው ቢሰራና  ተቋማዊም  እንዲሆን  ቢሰራ  ሚናውን በመወጣት ለኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic