FBC
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 30 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈጸመውን ድርጊት አወገዘች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ በተፈጸመ ድርጊት ሳቢያ የሰው ህይዎት በመጥፋቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው ሰባት አብያተ ክርስትያናት ሙሉ በሙሉ ተቃጥለው የካህናት ህይዎት ማለፉንም ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም የሰላማዊ ሰዎች ህይዎት ማለፉንና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውን ጠቅሰው፥ በሁኔታው የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።
አሁን ላይ አብረው በኖሩ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተጸመው ድርጊት በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባም ጠይቀዋል።
ቤተ ክርስቲያኒቱም አሁን ላይ የተፈጠረው ችግር እንዲቆምና ሰላም እንዲሰፍን እንደ ወትሮው ሁሉ ድጋፏን ታደርጋለች ብለዋል።
ለተቸገሩ ወገኖችም ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመው፥ ህይዎታቸውን ላጡ ወገኖችም በሁሉም አድባራትና ገዳማት ፍትሃት ይደረጋልም ነው ያሉት።
ከዚህም በተጨማሪም ነገ የሚጀምረው የፍልሰታ ጾም በሁሉም አድባራት እና ገዳማት በምህላ እና በጸሎት እንደሚታሰብም አንስተዋል።