>

የሟች መለያየት ለገዳይ እንጅ ለሟች አይጠቅመው!!! (ፋሲል የኔዓለም)

የሟች መለያየት ለገዳይ እንጅ ለሟች አይጠቅመው!!!
ፋሲል የኔዓለም

አብዲ ኢሌ ስልጣኑን ለማቆየት ከ3 ሺ በላይ የሌሎች ብሄር ተወላጆችን እንደ ከለላ (human shield) እየተጠቀመባቸው መሆኑን ስፍራው ላይ ያሉ ሰዎች እየተናገሩ ነው። ከ10 ሺ በላይ የራሱን ወገኖች ሲገድል የኖረ  ጨካኝ ፍጡር፣ በእነዚህ ዜጎች ላይ እርምጃ አይወስድም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም። ከቅዳሜ እስከ ዛሬ ብዙ ወገኖቻችን አልቀዋል፤ አብዲ ኢሌ ከ40 ሚሊዮን በላይ ደጋፊ ያላትን ኦሮቶዶክስ ቤ/ክርስቲያንን ነክቷል፤ በብሄራቸው ምክንያት ብዙ መስሊሞችም ተጎድተዋል።

 በአብዲ ኢሌ ድርጊት ያልተበሳጩ ወገኖች ቢኖሩ ሰውዬውን ወደ ስልጣን ያመጡት እና በስልጣን ላይ እያለ የጠቀማቸው  ብቻ ናቸው። አብዲ ኢሌ ከእንግዲህ በመንግስት ስልጣን ላይ መቆየት ቀርቶ፣ ተገቢውን ፍርድ ሳያገኝ በሰላም በኢትዮጵያ ምድር እንዲኖር የሚፈቅድ ዜጋ የሚኖር አይመስለኝም። ሰውየው የትም ይግባ የት  ተይዞ ለፍርድ እስኪቀርብ ትግላችንን መቀጠል አለብን፤ አብዲ ኢሌ የጨካኝ አምባገነኖች መጨረሻ ምን እንደሚመስል ማስተማሪያ ሊሆን ይገባል።
በሌላ በኩል ህዝቡ የፌደራሉ መንግስት ምን እያሰበ እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል። በግሌ አብይ በድካም ብዛት ታሞ ካልሆነ ወይም ቀደም ብሎ ለእረፍት ወጥቶ ካልሆነ ፣ እንዲህ አይነት አንገብጋቢ ነገር ሲያጋጥም ዝም ብሎ ይቀመጣል ብዬ አላስብም፤ አብይን የምንወደው ግልጽነትን ስላሳየን ነው፤ ዛሬም ያንን ግልጽነት እንፈልጋለን።
ትክክለኛ መፍትሄ ማመንጨት የምንችለው ትክክለኛ መረጃ ሲኖረን ነውና አብይ ከቻለ ራሱ ካልቻለ ደግሞ ወኪሉ ቀርቦ ያስረዳን። መከላከያ ለምን ገባ? የአብዲ ኢሌ ባህሪ እየታወቀ ለምን የሌሎች ብሄር ተወላጆች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አልተነገራቸውም? አብዲ ኢሌን ሳይዘጋጅ ለመያዝ ታቅዶ ከነበረ ለምን ከሸፈ? ከፌደራል መንግስት በኩል መረጃ ለአብዲ ኢሌ ያቀበለ ነበር? የዚህ እንቅስቃሴ መጨረሻስ  ምን ይሆናል? መመለስ ያለባቸው አንድ ሺ አንድ ጥያቄዎች አሉ። ሁሉም ነገር ይነገረን ብለን ባንጠይቅም፣ ቢያንስ መከላከያ ለምን እንደገባና ለምን እንደወጣ ሊነገረን ይገባል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እምነቱን ያሳረፈው በአብዛኛው በፌደራል መንግስቱ ላይ እንጅ በክልል መንግስታት ላይ ባለመሆኑ፣ የፌደራል መንግስቱ ለህዝቡ ጥያቄ ሳይውል ሳያድር መልስ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን።  ጊዜው ለአገራችን አንድነትና ለህዝባችን ደህንነት ስንል በጋራ የምንቆምበት እንጅ አቃቂር እያወጣን የምንለያይበት ባለመሆኑ፣ እኛም በአንድነት ቆመን ዜጎቻንን መታደግ ብቻ ሳይሆን አገራችንን ከገዳይ አምባገነኖች ነጻ ማውጣት አለብን። የሟች መለያየት ለገዳይ እንጅ ለሟች አይጠቅመውምና በአንድነት ጸንተን ገዳዮችን እንታገል።
Filed in: Amharic