>
5:28 pm - Tuesday October 9, 8660

ሰማያዊ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር   የ“ተዋህደን አብረን እንስራ” ጥያቄ አቅርቧል!!! (አለማየሁ አምበሴ)

ሰማያዊ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር   የ“ተዋህደን አብረን እንስራ” ጥያቄ አቅርቧል!!!፡፡
አለማየሁ አምበሴ

    “ሰማያዊ” ፓርቲ በቅርቡ ወደ ሃገር ውስጥ እንደሚገባ ከተነገረለት “አርበኞች ግንቦት 7” የፖለቲካ ድርጅት ጋር ለመዋሃድ ማቀዱን አስታውቋል፡፡
ፓርቲው ቀደም ብሎ “ተዋህደን አብረን እንስራ” የሚለውን ጥያቄውን ለአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ማቅረቡን አስታውሶ፣ የድርጅቱን አመራሮች ይሁንታ እየተጠባበቀ መሆኑንም ለአዲስ አድማስ ገልጧል፡፡
“ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር የፕሮግራምና የዓላማ ልዩነት የለንም” ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ፤ ”ከድርጅቱ አመራሮች ጋር በውህደቱ ዙሪያ የሚደረግ ውይይት ይኖራል፤ ለዚያም ዝግጅት እያደረግን ነው” ብለዋል፡፡
በአሜሪካና ካናዳ ቆይታ አድርገው ሰሞኑን ወደ ሃገር ቤት የተመለሱት አቶ የሸዋስ፤ ከአርበኞች ግንቦት 7 በተጨማሪ በአሜሪካ ከሚገኙና ወደ ሃገር ቤት ተመልሰው በፖለቲካው ለመሳተፍ ከሚፈልጉ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም ጋር ፓርቲያቸው ለመዋሃድ መዘጋጀቱንና ይህንንም ሲያስገነዝብ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
“ተቃዋሚዎች ሰብሰብ ብለን ተጠናክረን መውጣት አለብን” ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ ቀደም ሲል ከመኢአድ ጋር የተጀመረው የመዋሃድ እንቅስቃሴም እየተጠናከረ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ላለፉት 10 ዓመታት የትጥቅ ትግልን ጨምሮ ሁለገብ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየውና በኢትዮጵያ መንግስት የተጣለበት የሽብርተኛነት ፍረጃ በቅርቡ የተነሣለት አርበኞች ግንቦት 7፣ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

Filed in: Amharic