>
5:09 pm - Sunday March 2, 5727

ያቃጠሏት ሁሉ አንድ በአንድ ጠፍተዋል - ቅድስቲት ቤተክርስቲያን ግን ይኸው አለች!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ያቃጠሏት ሁሉ አንድ በአንድ ጠፍተዋል – ቅድስቲት ቤተክርስቲያን ግን ይኸው አለች!
አሰፋ ሀይሉ
 
“አምላክ ልቦናውን ይስጣችሁ፡፡ የምታደርጉትን አታውቁምና ይቅር ይበላችሁ፡፡ በእናንተ ኃጢያት ትውልዳችሁ እንዳይጠፋ መዳኛውን ይስጣችሁ፡፡ እምነት ተስፋ ፍቅር ይደርባችሁ፡፡ ፍቅርን አስበልጡ፡፡ ክብሪታችሁን አስቀምጡ፡፡ በሠላም ግቡ፣ በሠላም ውጡ፡፡ ትድኑ ዘንድ፡፡” 
             
ሰዎች ግፍ ሠሩ እኮ አይባልም፡፡ ግፍ አቆዩ ነው፡፡ ግፍ ግፍን ትወልዳለች፡፡ እነዚህም መናፍቃን ገና ሊመጣባቸው ያለውን ግፍ አበዙ፡፡ ግፍን ለራሳቸው አቆዩ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤተክርስትያንን ያቃጠሉ ሁሉ ፈጥነውም ዘግይተው ባቆዩት ሥራቸው ልክ ሣይከፈላቸው የቀሩ የሉም፡፡
ዮዲት ጉዲት ቤተክርስቲያናትንና መንፈሣዊ አገልጋዮችን፣ አድባራትን፣ ገዳማትን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ቅዱሰ ንዋያትን ሁሉ አቃጠለች፣ ፈጀች፣ አወደመች፡፡ ግራኝ አህመድም መጣ፡፡ ግራኝ አህመድም በረገጠው ሥፍራ ሁሉ ያሉ ቤተመቅደሶችን በእሣት አጋየ፣ የቻለውን ሁሉ ጥፋትን አደረሰ፡፡
አፄ ዮሐንስ ቃላቸውን አፍርሰው በማህዲስቶች የታገቱትን እንግሊዞች የማርያም መንገድ ሰጥተው በኢትዮጵያ ምድር ተሻግረው እንዲያመልጡ መርዳታቸውን ተከትሎ ደግሞ – ደርቪሾች ከመተማ እስከ ጎንደር እየገሰገሱ – በመንገዳቸው ያገኙትን ቤተመቅደስና ክርስቲያን የሆነችውን ሁሉ ነገር በእሣት እያጋዩ፣ አመድ እያረጉ፣ እየፈጁ ጎንደር ገቡ፡፡ በተዓምራቱ የተረፉ ሁለት ቤተመቅደሶች ብቻ ሲቀሩ – ቤተክርስቲያን የተባለን፣ ንዋየ ቅድሳትን፣ ፅላቱን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ ነዳያንን፣ መነኮሳትን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናትን፣ እና በየቤተስኪያኑ የተጠለሉ ምዕመናንን ሁሉ በላያቸው የበቀል እሣትን ለቀቁባቸው፡፡ አመዳቸው እስኪወጣም ከጎንደር ሊወጡ አልፈለጉም፡፡ አመዱን ከተመለከቱ በኋላ ነበረ ሱዳኖቹ ባደረሱት ጥፋት እየጨፈሩ ወደመጡበት በጥፋት የከሰለ ሃገራቸው የተመለሱት፡፡
/ለየት የሚለው፣ እና የሚገርመው ግን – ለዛሬዋ ዘመናዊት ኢትዮጵያ የመሠረት ድንጋይ ያኖሩት – እና እጅግ የምናከብራቸው የኛው አፄ ቴዎድሮስ እንኳ – ከጎጃም ወደ ጎንደር ሲመለሱ – ቀሳውስት አመፅ አቀጣጥለው ህይወታቸውን ሊያስቀጥፉ አሲረዋል የሚልን ወሬ ሰምተው – ሊቀበሏቸው እስከጉዛራ የወጡ ክርስቲያን ሴቶችን ሳይቀር – ሁሉንም አጥፍተው – ከተማዋን ሁሉ ከነጠረጠሯቸው ቤተክርስቲያኖቿ እንዳጋይዋት ታሪክ ያወሳናል፡፡ ያሣዝናል እልህም እንዲህ ሀገር ሲያጠፋ፤ እና ራሱን ሲያጠፋ!/
ቀጠሉና ደግሞ – የፈረደባትን ቤተክርስቲያን ሊያጠፉ ፋሺስቶች መጡ፡፡ ክርስቲያን ነን ብለው በአንገታቸው ክታብ አስረው ኢትዮጵያውያንን በባርነት ሊገዙ በቀልን ለብሰው፣ እሳት ጎርሰው፣ ጉድጓድ ምሰው፣ ለጥፋትና ለጥፋት እየተንቀለቀሉ ወዳገራችን የመጡት – የኢጣልያ የተራቡ በቀለኛ ተኩሎች – እና መላ የፋሺስት ሠራዊታቸው – በያገራችን አጥቢያ ያሉ ቤተክርስቲያናትን አቃጠሉ፣ ንዋየ ቅድሳትን፣ ቅድሳት መጻሕፍትንና ፅላቶችን ሁሉ ዘረፉ፡፡ ክርስቲያን ነን እያሉ – ሌላ ቀርቶ አቅመ-ቢስ አረጋውያን መነኮሳትና ባህታውያንን – ወንድ ከሴት ሳይሉ – ከነነፍሳቸው አቃጠሏቸው፡፡ ገደሏቸው፡፡ እሳት ለቀቁባቸው፡፡ አነደዷቸው፡፡
ቤተክርስቲያናችን – ስለኢትዮጵያ ሕዝብ በመቆሟ – ስለአርበኝነቷ – ስለአኩሪ ተጋድሎዋ – ስለብርታቷ፣ ፀሎት ፍታቷ – በኢትዮጵያዊነቷ የማትደራደር በመሆኗ – የአኩሪ ሥልጣኔያችን እምብርት እና ማህፀን በመሆኗ – ልጆቿን፣ አረጋውያኗን፣ ሊቃውንቶቿን፣ አባቶቿን፣ ቅዱሳት መጻሕፍቷን፣ ጥበቧን፣ ጥበባችንን፣ መንፈሳዊነታችንን፣ ፅናታችንን ሁሉ በጉያዋ እቅፍ አድርጋ – በሠላም በጦርነት ሳትል ስብስብ አድርጋ – እንደ እናት በበረከቷ አስጠልላ በመኖሯ – ብዙ ብዙ ተነግሮ የማያልቅ እጅግ ብዙ መስዋዕትነት ተቀብላለች ውድ ቤተክርስቲያን፡፡ ብዙ ብዙ ተነግሮ የማያልቅ የከፋ መስዋዕትነትን ተቀብለዋል ውድ አባቶቻችን፡፡ እንዲያም ሆነው ግን አልጠፉም፡፡
እንዲያም በእሣት መካከል ሆናም – በአስከፊ የእሣት ጎዳናዎች ላይ እየተረማመደችም ግን – ይህች ቅድስቲት የኢትዮጵያ ዋልታ – ቅድስቲት የማትበጠስ ማተባችን – እናት ዓለም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘ ኢትዮጵያ – ከዮዲት ጉዲት እስከ ግራኝ አህመድ – ከደርቡሽ እስከ ፋሺስት – ከአሊ አብዶ እስከ አብዲ ኢሌ ድረስ – የተቃጣባትን መቅሰፍት ሁሉ – የተለኮሰባትን እሳት ሁሉ በተዓምራቱ ተቋቁማ – ይኸው እስከዛሬም ለልጆቿ፣ ለሕዝቦቿ፣ ለፃድቃን ለሰማዕታት፣ ለፈጣሪ ለመላዕክታት ፀሎቷን፣ ፆሟን፣ ቡራኬዋን፣ ፍታቷን ሱባኤዋን ሳታስተጓጉል – በቅዱስ ያሬድ ዜማ – በድቅድቅ ሌት ፅልመት ያለእንቅልፍ – እንደማለዳ ወፍ በጧት መዓልት – ለህዝቦቿ፣ ለኢትዮጵያ፣ ለሌሎች ቤተ ዕምነቶች ተከታዮች ሁሉ አብሮ መኖርን ተቀብላ እያቀበለች፣ መንፈሳዊነትን እየሰበከች – ባህላችንን፣ ጥበባችንን፣ መንፈሳዊ ኢትዮጵያዊነታችንን በጉያዋ እምቅ አድርጋ ከጅቦች እየተከላከለች – ይኸው እንዳለች አለች፡፡
የምትወዱ ስሙ እውነቱን፡፡ እውነትን የማትወዱ እንደሬት እየተናነቃችሁ ዋጡት፡፡ ቤተክርስቲያኒት ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ኢትዮጵያ – አለች፡፡ በእሣቱ ሁሉ ውስጥ ጋይታም ነበረች፡፡ አሁንም እየተለኮሰባት ባለው እሣት እየተንገበገበችም አለች፡፡ ወደፊትም እንደ ሚሳቅ፣ ሲድራቅና አብደናጎም – በእሣት እቶን ውስጥ እንኳ ብትጣል – በእሣት መካከል በክብር እየተመላለሰች ትኖራለች፡፡ ከአመዷ ውስጥ ጥፋትን በቤዛ ትንሣዔ ነስታ – በህይወት እየተመላለሰች ትቀጥላለች፡፡ የጥበብ መንፈሷን በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እያሣረገች ትኖራለች፡፡ ቀስተደመናዋን በሰማይ በምድር እያለበሰች በክብር ትኖራለች፡፡ ሕዝቦቿን በመንፈስ ትባርካለች፡፡ ለፈጣሪዋ ትቀድሳለች፡፡ የዘመን ጥበብን ትዘምራለች፡፡ በመንፈስ፣ በውሃ፣ በእምነት እያጠመቀች ትጓዛለች፡፡
ትናንት በቅድስቲት ቤተክርስቲያናችን ላይ እሣትን የለኮሱ እጆች ሁሉ – እሣቱ ለራሳቸው እየሆነ – በራሳቸው የግፍ እሣት ጠፍተዋል፡፡ ወደፊትም እሣትን የሚለኩሱ ሁሉ ባቆዩት ግፍ ይጠፋሉ፡፡ የየዋሃን መናኸሪያ – ቅድስቲት ታሪካዊት ኢትዮጵያዊት ቤተክርስቲያናችን ግን – እሣቱን በአምላክ ቸርነት እያጠፋች – በእምነት – በተስፋ – በፍቅር – እስከ ወዲያኛው የምድሪቱ ፍፃሜ ድረስ – በመንፈሳዊ የቃልኪዳን ጉዞዋ ትቀጥላለች፡፡
እሣትን የምትለኩሱ – በለኮሣችሁት እሣት ትጠፋላችሁ፡፡ ቤተክርስቲያናችን ግን በስመ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስቅዱስ – በመስቀለ እየሱስ ሕዝቦቿን እየባረከች – እያጠየመቀች – አሁን እንደሚለኩሱት ያሉትን በድን መንፈስ ያላቸውን ሁሉ – ሞትን ከሚጠራ የሙታን ህይወታቸው በጥምቀቱ እያስነሳች – በመንፈስ ፀንታ – በኢትዮጵያ ሠማይ ምድር – በኢትዮጵያ ኮረብታ ላይ – የክብር ቀስተደመናዋን ዘርግታ – እስከዘለዓለሙ ትኖራለች፡፡ እንደግመዋለን – ቤተክርስቲያንን ያቃጠሉ – በግፋቸው እንደተቃጠሉ – ቃል ለምድር ለሠማይ – ታሪክ ምስክራችን ነው፡፡ እሣትን የለኮሱ ሁሉ በራሳቸው ዲን ይጠፋሉ፡፡ ቤተክርስቲያናችን ግን – እሣትን ድል ነስታ – በልጆቿ፣ ለልጆቿ፣ ስለልጆቿ፣ ስለአንዲት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች፡፡
ቅድስቲት ቤተክርስቲያናችንን – ለሕዝቦቿ በፀለየች፣ በባረከች፣ ባዳነች፣ ፅሞናን ባስተማረች፣ ፈጣሪን በለመነች – ምን አደረገች?? ተጎናብሰው እየለመኑ እየዘከሩ የሚኖሩ ምስኪን አገልጋዮቿስ ምን አደረጉ? ፈሪሃ እግዜርን ተላብሰው የሚኖሩ ምዕመኖቿስ ምን አደረጉ?? እና . . . እባካችሁ – እባካችሁ – እናንት የእርኩሳን ጋኔን መንፈስ የተጠጋችሁ አረመኔዎች – እናንት የሌጊዮን መንፈስ ያደረባችሁ ድውዮች – እናንት የአጋንንት አለቃ የብሔል ዜቡል መንፈስ ያደረባችሁ የእሣት ልጆች ሆይ – እባካችሁ – ቤተክርስቲያናችንን አትንኩ፡፡ ትናንት የነኩት ዛሬ የሉም፡፡ ዛሬ እናንት የምትለኩሱት እሣትም – ለነገ ፍም ሆኖ እንደሚጠብቃችሁ – እንደ ወንጌላዊ ዮሐንስ ራዕይን ማየት አያስፈልገውምና – ተዉ ለራሳችሁ፣ ለትውልዳችሁ፣ ለሕዝባችሁ፣ ላገራችሁ ድነት ስትሉ ቤተክርስቲያናችንን ተዉ፡፡
አምላክ ልቦናውን ይስጣችሁ፡፡ የምታደርጉትን አታውቁምና ይቅር ይበላችሁ፡፡ በእናንተ ኃጢያት ትውልዳችሁ እንዳይጠፋ መዳኛውን ይስጣችሁ፡፡ እምነት ተስፋ ፍቅር ይደርባችሁ፡፡ ፍቅርን አስበልጡ፡፡ ክብሪታችሁን አስቀምጡ፡፡ በሠላም ግቡ፣ በሠላም ውጡ፡፡ ትድኑ ዘንድ፡፡ አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ አምላክ ኢትዮጵያንና የቁርጥ ቀን ልጆቿን ሁሉ አብዝቶ በበረከቱ፣ በፅናቱ፣ በማዳኑ ይጎብኝልን፡፡ ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም – በፍቅር – ትኑር፡፡
† ቅድስት ቤተክርስቲያን በጂጂጋ ስትቃጠል የሚያሣየው ምስል (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
“ጉዛራ ጎርጎራ ጎንደር – Guzara Gorgora Gondar @ Facebook Timeline – Aug. 6, 2018”
Filed in: Amharic