>
5:13 pm - Thursday April 19, 9404

ለጉድ የጎለተው ‹‹ቤተ ክህነት›› (ከይኄይስ እውነቱ)

ለጉድ የጎለተው ‹‹ቤተ ክህነት››

ከይኄይስ እውነቱ

በቅርቡ ‹‹ተካክሎ መበደል » በሚል ርእስ ባቀረብኹት አስተያየት የኢኦተቤ/ክርስቲያንን እንወክላለን በሚሉ፣ ባገር ውስጥና በውጭ በስደት በሚገኙ ‹‹አባቶች›› መካከል የተድበሰበሰ/የማስመሰል ‹‹ዕርቅ›› ስለመፈጸሙ እና የዕውነትና የምሕረት አደባባይ በሆነች ቤ/ክ ስም ዕውነትን ወደ ጎን አድርጎና ሕገ ቤ/ክርስቲያንን ተላልፎ ‹‹ሁለት ፓትርያርኮች›› ባንድ መንበር እንዲቀመጡ፤ በሁለቱም ወገኖች በኩል መሠረተ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤ/ክ በመተላለፍ የተሰጡ የጵጵስና ሹመቶች እንዲፀኑ፤ወዘተ የተላለፈው ውሳኔ በየትኛውም የእምነቱ መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረግጬ ገልጫለኹ፡፡ ይህ ዓይነቱ ‹‹ዕርቅ›› ለጊዜው ለፖለቲካው ሥርዓት እንደሚጠቅም ቢገመትም ዘለቄታ አይኖረውም፡፡ ዕውነትን ያልደፈሩ ‹የሃይማኖት አባቶች› ተሰሚነት ኖሯቸው አገራዊውን አለመረጋጋት በዕርቅ በሽምግልና ያረጋጋሉ ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው፡፡ በቅድሚያ የራስን የውስጥ ችግር ማጥራት ይቀድማል፡፡

እላይ የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የኢኦተቤ/ክ እወክላለኹ የሚል ተቋማዊ አካል ካለ፣ ስምንት አብያተ ክርስቲያናት ላይ አደጋ ሲደርስ፣ አገልጋዮች ሲሞቱና ሲጎዱ ምን እያደረጉ ነው? ከቤተ መንግሥቱ ፈቃድ እየጠበቁ ይሆን? ‹ጅብ ከሄደ..› ዓይነት መልእክት ለማስተላለፉ በማሰብ ነው? በቂ የፋይናንስ አቅም ያላት ቤ/ክ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክ/ሃገር በተፈጠረው የሽብር ተግባር ቤት ንብረታቸውን ጥለው፣ ሸሽተው ወደ ጎረቤት አገር ስለተጠለሉት ምእመናን ባጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት የለባትም? የሚያስደነግጠው ዝምታ ትርጕሙ ምንድን ነው? እንዴት እስከመጨረሻው እንዳሳፈራችሁን ትዘልቃላችሁ? መቼ ይሆን የመንፈሳዊ አባትነት ወግ የምታሳዩን?

Filed in: Amharic