ዘመድኩን በቀለ
አዲስ አበባ ~ ጉዳዩ ስለ ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ በድብቅ ስለሚነገረው ሹክሹክታ ይፋ እንዲደረግልኝ ስለመጠየቅ ይሆናል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከአሜሪካ ከተመለሱ በኋላ ከሚዲያም ከህዝብ ዐይንም እንደተሰወሩ ይታወቃል። ለተከታታይ ወራት እረፍት አልባ ሥራ እንደሠሩና ከባድ ጊዜ እንዳሳለፉ አውቀን እረፍት ላይ ይሆናሉ ብለን ብናስብም ነገሩ ግን ቀኑ እየገፋ፣ ድምጻቸውም እየጠፋ ሲመጣ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ወይም እየጠየቀ ያለ አካል ግን እስከአሁን አልተገኘም። ሹክሽታው ማረጋገጫ ይፈልጋል እንጂ። ሹክሹክታዎች ግን አሉ።
ለዚህ ሹክሹክታ ከአሜሪካው ጉብኝት መልስ ከጠ/ሚ ዶኮ ዐቢይ አህመድ ጋር በአንድ አውሮፕላን ተሳፍራችሁ የመጣችሁ ዜጎች እውነቱን ብትነግሩን ነፃ ታወጡናላችሁ ብዬ አስባለሁ። በተለይ በ VIP ጠሚው ጋር የነበራችሁ ሰዎች ትለመናላችሁ። ሆስተሶችና ፓይለቶችም ብትሆኑ በአውሮፕላኑ ውስጥ ተከስቶ ነበር ብትሆኑ ስለሚባለው ስለተሞከረው የግድያ ሙከራ ብትነግሩን እንዴት ሸጋ ነበር መሰላችሁ።
እንደሚባለው ከሆነ ጠሚዶኮ በዕለቱ ከአሜሪካን ሲመለሱ በራሳቸው ጠባቂ አማካኝነት በአውሮፕላኑ ውስጥ የመግደል ሙከራ ተደርጎባቸው ነበር። እናም በእግዚአብሔር ኃይልና በሌሎቹ ጠባቂዎች ንቃት ከተቃጣባቸው አደጋ ሊተርፉ ችለዋል።
በዚህም የተነሳ አውሮፕላኑ ውስጥ በነበረው ከፍተኛ የሆነ ግርግር ምክንያት አደጋ ለማድረስ ሞካሪው በቁጥጥር ስር እስኪውልና ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ አውሮፕላኑ አዲስ አበባ እስኪገባም ሆነ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ እንዲዘገይ መደረጉም ተነግሯል። ጠሚው ከአውሮፕላኑ እንደወረዱ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ በቀጥታ ወደ ማረፊያቸው መሔዳቸው ተነግሯል።
እናም አሁን ጠሚዶኮ በሁኔታው ተደናግጠው በጠና ታመው አልጋ ላይ ውለዋል የሚሉም አሉ። አደጋ ለማድረስ የሞከረው ጠባቂያቸውም በቁጥጥር ስር መዋሉም ተነግሯል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ መረጃ አቀባይ የሆኑት አቶ ፍጹም አረጋ ዛሬ ጠሚዶኮ ለድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ተማሪዎች በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት ስልጠና ሲሰጡ እንደዋሉ በገጻቸው ላይ በመለጠፍ የሚታወቁት ሰው ዛሬ ሲለጥፉ ባይታዩም #EBC የለጠፈው ፎቶ ግን በዛሬው ዕለት የተነሳ ፎቶ ሳይሆን ጠሚዶኮ ዐቢይ ባለፈው ጊዜ መምህራንን ሰብስበው ባናገሩ ጊዜ የተነሱትን ፎቶ እንደሆነ መምህር ስዩም ተሾመ በፌስቡክ ገፁ ላይ አስተባብሎ እውነቱን አውጥቷል።
ጠሚዶኮ የሁለቱን ሲኖዶሶች እርቅ አስመልክቶ ባለፈው ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገ ዝግጅት ላይ ይገኛሉ ተብሎ ብዙ ከተጠበቁ በኋላ በመጨረሻ እንደማይገኙ መነገሩና ከዳላስ ምእመናን የተበረከተላቸውን የአልማዝ ስጦታም በተወካያቸው አማካኝነት እንደወሰዱ ታውቋል።
በሌላም በኩል ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ የሀገር መሪ ያህል የሚቆጠረው የህዳሴ ግድቡ ታላቁ አንጂነር ስመኘው በግፍ በአደባባይ መታረዱ ይታወቃል። እናም ጠሚዶኮ አዲስአበባ እነደገቡ ስለ ኢንጅነሩም መግለጫ ይሰጣሉ፣ የሟች ልጆችንም ያጽናናሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስከአሁን በዚያ ጉዳይ ላይ ትንፍሽ አለማለታቸውም ሲታይ የሆነ ከበድ ያለ ነገር አለ ብሎ መጠርጠርም ክፋት የለውም።
ሰሞኑን ደግሞ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የዘር ማጥፋትና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውድመት ሲካሄድ እያዩ፣ እየሰሙም ዝምታን መምረጣቸው የጤና አይመስልም። በአጭር ወራት ውስጥ በየዕለቱ አዳዲስ አጀንዳዎችን በማቅረብ ዓለሙን ሲያስደምሙ፣ ተቃዋሚውን ሁሉ ሳይቀር በፈቃዱ የኢህአዴግ አባል ሲያደርጉት የነበሩ የሀገር መሪ ድንገት ከሳምንት በላይ ሲሰወሩ እያየን የት ደረሱ፤ ብለን ያለመጠየቅ ነውርም፣ ኃጢአትም፣ ወንጀልም ነው።
ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ በዛሬው ዕለት ከጀዋር አህመድ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ የነበራቸው ቢሆንም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ጃዋር ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የነበረው ቀጠሮ ተሰርዞ በምትኩ ከፕሬዘዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር እንዲነጋገር ተደርጓል ተብሏል።
እናም እኔ በበኩሌ እጠይቃለሁ። ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ የት ናቸው? ማስመሰሉ ይቅርና እውነታውን ንገሩን። ከሐሜትና ከሽኩሹኩታም አድኑን። እውነታውን ሳትነግሩን ነገሮችን ለማስቀየስ አንዴ አስመራ፣ አንዴ ጅቡቲ የምታደርጉትን ግርግር አቁሙና እውነቷን ንገሩን።
ባለፈው ጊዜ ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር ሐምሌ አርፈው ነሐሴ እንደተረዳነው መደባበቅ አያስፈልግም። ከድንጋጤ በስተቀር በጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ ላይ የከፋ አደጋ እንዳልደረሰባቸው አሾክሻኪዎቹ ሲናገሩም ተደምጧል። እናም አንድ ጊዜ ብቅ ብለው መኖራቸውን ቢናገሩ እንኳ መልካም ይመስለኛል።
እንዲያውም ጅቡቲ የሆነ የደረሳት መረጃ ስላለ ዜጎቿን ከድሬደዋና ከሶማሌ ክልል በአውሮፕላን፣ በመኪናና፣ በባቡር እያስወጣች ነውም የሚል ዜና ቢቢሲ ትግሪኛ በምስል አስደግፎ ምሽቱን መረጃውን ለቋል። ጅቡቲ ከዚህ በፊት አድርጋ የማታውቀውን ነገር ነው አሁን ያደረገችው።
እናም ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድን የበላ ጅብ ይጩኽልን። አከተመ።
ሻሎም ! ሰላም !
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ነሐሴ 1/2010 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።