>

ህዝቡን ወደ ጥፋት እሽክርክሪት ለመመለስ በስሜት እየተወራጩ  የልዩነት ዘር መዝራት አደገኛ ነው!!! (ፋሲል የኔአለም)

ህዝቡን ወደ ጥፋት እሽክርክሪት ለመመለስ በስሜት እየተወራጩ  የልዩነት ዘር መዝራት አደገኛ ነው!!!
ፋሲል የኔአለም
 
የስሜት ሰዎች ከበሮ ባለበት መጨፈር፣ ጽናጽል ባለበት መቀደስ፣ ድንኳን በተዘረጋበት ማልቀስ፣ ጠመንጃ ባለበት መፎከር፣ የሰላም ጉባኤ ባለበት ሃዋርያ መሆን የሚያምራቸው፣ ዛሬ ኢትዮጵያዊ፣ ነገ ቀበሌያዊ ኢህአዴጎች ለ27 ዓመታት የተከተሉት መንገድ አገሪቱን መቀመቅ ውስጥ እንደከተታት ተረድተው መንገዳቸውን ለማስተካከል እንቅስቃሴ በጀመሩበት በዚህ ወቅት፣ ትናንት የእነሱን መንገድ ሲያወግዙ የነበሩት ሰዎች፣ ዛሬ በዚያ የቁልቁለት መንገድ  ለመጓዝ ሲሽቀዳደሙ ስናይ ፖለቲካችንን ምክንያት ሳይሆን ስሜት እየነዳው መሆኑን እንገነዘባለን።  በስሜት የሚነዱ ሰዎችን ለማወቅ ቀላሉ ዘዴ ጠዋት የተናገሩትን ማታ የማይደግሙት መሆናቸው ነው፤ የስሜት ሰዎች ከበሮ ባለበት መጨፈር፣ ጽናጽል ባለበት መቀደስ፣ ድንኳን በተዘረጋበት ማልቀስ፣ ጠመንጃ ባለበት መፎከር፣ የሰላም ጉባኤ ባለበት ሃዋርያ መሆን የሚያምራቸው፣ ዛሬ ኢትዮጵያዊ፣ ነገ ቀበሌያዊ እየሆኑ  እንዲህ ሲልዋቸው እንዲያ፣ እዚህ ሲሏቸው እዛ የሚገኙ፣ የውሃ ልካቸው የማይታወቅ፣ ተደናግረው የሚያደናግሩ ናቸው።
የሰው ልጅ በሰውነቱ ወደሚከበርበት የዜጋ ፖለቲካ ለመሸጋገር መንገድ የጀመረውን ኢህአዴግን አይዞህ እያሉ በማበረታታት፣ የ27 አመታቱ የጥፋት ዘመን እንዳይደገም ብቻ ሳይሆን ፣ አሁን ያለው ትውልድ በስርዓት እንዲመራ፣ መጪው ትውልድ ደግሞ የተሻለ አገር እንዲረከብ  መስራት ሲገባ፣ ወደ ነበርንበት ይጥፋት እሽክርክሪት እንድንመለስ በስሜት እየተወራጩ  የልዩነት ዘር መዝራት አደገኛ ነው። ኢህአዴግ ከሰራው በተሻለ መስራት የምንችለው ከኢህአዴግ ጥፋት ተምረን ሌላ የተሻለ መንገድ መቀየስ ስንችል ነው። ኢህአዴግ ራሱ “መንገዴ ትክክል አልነበረምና አትከተሉት” እያለ እየመከረን፣  በዚያው መንገድ ለመጓዝ የምንፍጨረጨር ሰዎች ውስጣችንን በደንብ መመርመር አለብን። ይሄ ደግሞ እገሌ ከእገሌ ሳይባል በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙ፣ ካለፈው የኢህአዴግ ስህተት ባለመማር ያንኑ ስህተት ለመድገም የሚሯሯጡትን ሁሉ እኩል ይመለከታልና ከስሜት ወጥተን ነገሮችን በሰከነ መንገድ ብናስኬዳቸው እኛም መጪው ትውልድም የተሻለ አገር እንዲኖረው ማድረግ እንችላለን።
Filed in: Amharic