>

ግፈኞቹን ፋሺስታውያን ተጠርጣሪዎችን እሹሩሩ የምንለው  እስከመቼ ነው???  (አሰፋ ሀይሉ)

ግፈኞቹን ፋሺስታውያን ተጠርጣሪዎችን እሹሩሩ የምንለው  እስከመቼ ነው???
 አሰፋ ሀይሉ
 * በየዜናው – ይህን ያህል መቶዎች ተገደሉ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቀሉ – የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም – ለመርዳት… ምናምን እያልን ባየር ላይ እየለፈለፍን ለወንጀለኞቹ ሽፋን እየሰጠን የምንጓዘው የእውር ድንብር ጉዞ ይብቃ!
ክቡር አብዲ ኢሌ . . . እና በዓይናችን ሥር ያለፉት ክብረ-ነክ ኩነቶች ! ! !
ብዙ ጊዜ – ራሴን ጨምሮ – ብዙ ሰዎች – ወደገደለው ጨዋታ – በቀጥታ ያለመግባት ከባድ ችግር አለብን፡፡ አምኜያለሁ፡፡ አለብኝ፡፡ አሁን ግን ታርሜያለሁ፡፡ ይኸው በቀጥታ ወደ ዋናው ነጥቤ ! !
/ወደ ገደለው ከመሄዴ በፊት ግን – እዚህ ላይ- … በፅሑፌ ያሰፈርኳቸው ግላዊ ሃሳቦች የሉም እንጂ – ካሉ – የራሴ የግሌ አስተያየት፣ መረጃዎቹም የምንጮቹና የዜናዎቹ፣ ድርጊቶቹ ደግሞ ባለፉት ወራት በዓይናችን ሥር ስንሰማቸውና በመስታይት ስናስተናግዳቸው የከረምናቸው መሆኑን በቅድሚያ ማስመር እወዳለሁ፡፡/
አሁን ወደ ገደለው ፡፡ በእኔ አመለካከት – እኚህ የተከበሩ ሰው – ወይም ከይቅርታ ጋር ይህ ሰው – በሰው ዘር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ክስ ጉዳይ ለሚከታተለው ዓለማቀፉ ችሎት ክስ ሊመሠረትበትና ተላልፎ ሊሰጥ ይገባል እላለሁ፡፡ ይፈረድበት አይደለም፡፡ ግን አደረጋቸው ወይም አስደረጋቸው ለሚባሉት ዓለማቀፍ ሰብዓዊ ወንጀሎች ሚዛናዊ በሆነ ዓለማቀፍ ችሎት ቀርቦ ይጠየቅ፡፡ እንዲህ የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡
ተመድ በሶማሊያ ክልል አጎራባች ወረዳዎች የደረሰውን የኢትዮጵያውያን ዜጎች በተመለከተ ያወጣውን አሃዝ እንመልከተው፡፡ ቁጥሩ ይዘገንናል፡፡ በዓለማቀፉ ማኅበረሰብ፣ በተመድ በአሁን ወቅት በዓለማቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት ካገኘው የማያንማር ሮሂንጊያ አናሳ ሙስሊሞች ቁጥርም የበለጠ ነው ይኸው የኛ ጉድ፡፡
በ140 በሚደርሱ ዋና ዋና የሶማሊ-ኦሮሞ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎች ብዛት ከ700 ሺህ እስከ 1 ሚሊየን ይደርሳል፡፡ ከዚያ ውስጥ ከ637 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ 400 በሚጠጉ ቦታዎች ተጠልለው የሚገኙ ናቸው፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ ከ68ሺህዎቹ የሶማሌ ተወላጅ ተፈናቃዮች ውጭ ሌሎቹ አብዛኞቹ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ዜጎቻችን ናቸው፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ የቀረበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት የሚለው ለእነዚህ ከ700ሺህ በላይ ለሆኑ ንፁሀን ዜጎች መፈናቀል በዋንኛነት በመጀመሪያ አብዲ ኢሌ የሶማሊያ ፀጥታ ኃይል ኃላፊ በነበረበት ሰዓት ጀምሮ ያደራጃቸው የሶማሊ ልዩ ኃይሎች በምክንያትነት መጠቀሳቸውን – የብዙ ተፈናቃዮችን ቃል ያጣቅሳል፡፡
 ብዙዎች የኦጋዴን ከርቸሌ እየተባለ በሚጠራው – እና የጂጂጋ ማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ – ብዙ ንፁሀን ኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያ ዜጎች – ከድብደባ እስከ ግድያ፣ ከአስገድዶ መድፈር እስከ አካል ማጉደል እና ህሊናቸውን የሚያዋርድ፣ ሰብዓዊነታቸውን የሚያጎድፍ የኃይል ተግባር ተፈጽሞባቸዋል በማለት – ቁጥራቸው ከ100 በላይ የሆኑ የቀድሞ ታሳሪዎችን ቃል በሪከርድነት ቀርጾና በጽሑፍ አደራጅቶ ያወጣውን ዳታ ስናየው – በእውነት ይህ እዚህ እኛ ሀገር ነው ወይስ የት? ማሰኘቱ አይቀርም፡፡
በአጠቃላይ በተደጋጋሚ በሀገራችን ላይ በወጡ ተከታታይ ቀጠናዊ እና ብሔራዊ የአደጋ ተጋላጭነት ሪፖርቶች እና ዓለማቀፍ ዜና ምንጮች ጭምር – በመረጃ ተደግፈው የሚቀርቡት አሃዞች – ዝም ብለው አሃዞች እኮ አይደሉም፡፡ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አቅመ ቢስ ንፁሐን ሰዎች ላይ የተፈጸመባቸውን አሰቃቂ ግፍ የሚናገሩ ናቸው፡፡
መሰረታዊ ጤና መከልከል፣ መሰቃየት፣ ከቤተሰብ እንዳይገናኙ ማድረግ፣ ማፈናቀል፣ እና የሚዘገንን ቁጥር ያላቸው ንፁሀን ኢትዮጵያውያን ህልፈተ ህይወት (ወደፊት በማስረጃ መረጋገጡ እንዳለ ሆኖ እስከ 10ሺህ ሰው ሳይሞት እንዳልቀረ… ሲባል ግን የምር ጤነኛ ህሊናን፣ ሰብዓዊ ሰውነትን ውርርር አያደርግም?)፣ ለህይወታቸው ዋስትና አጥተው ከመኖሪያቸው መፈናቀል፣ ሠላማዊ አካባቢያቸው ለተከታታይ ግጭትና ሁከት መጋለጥ፣ ቤተሰቦች መበተን፣ መኖሪያቸው ሀብት ንብረታቸው መዘረፍ፣ መውደም፣ መጎሳቆል፣ ሆነ ተብሎ የደህንነት ስጋት እንዲያድርባቸው ማድረግ፣ የልዩ ኃይሉ ህግአልበኝነት የሞላባቸው የኃይል ተግባራት፣ ወዘተ ወዘተ… ተዘርዝረው አያልቁም – ነው የሚሉን እነዚህ ሁሉ የአውሮፓ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የቀጠናዊ፣ የተመድ፣ እንዲሁም የዓለማቀፍ የዜና ዘጋቢዎች መግለጫዎችና ዳታዎች፡፡
እንዴ? መንግሥት ባለበት ሀገር፣ ህግ በሰፈነበት ሀገር፣ የሌላን የጎረቤት ሀገር ሠላም የሚያስጠብቅ ሠራዊት ባለበት ሀገር፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ ፌዴራል መንግሥት ባለበት ሀገር – እንዴት አንድ ክልል – ወይም አንድ ሰው – ወይም አንድ ኃይል – ይህን ሁሉ ግፍ ሲፈጽም ወይም ፈጸም እየተባለ – ተፈናቃዮች አንድ ሚሊየን ደረሱ እየተባለ – እንዴት ነው ግን ዝም የሚባለው? የተፈናቀሉት እኮ ከብቶች አይደሉም፡፡ ቢሆኑ እንኳ የሀገር ሀብት ናቸው ተብሎ እኮ አድራጊዎቹ አይታለፉም፡፡
እነዚህ እኮ በህገመንግሥት በህይወት የመኖር፣ የመዘዋወር፣ የአካል ደህንነት፣ የነፃ ዳኝነት፣ ንብረት የማፍራት፣ ልጆቻቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ ሰላማዊ አካባቢ የማሳደግ፣ ቋንቋቸውን ባህላቸውን ያለማንም ጣልቃገብነት የማበልፀግ፣ የማራመድ፣ ህጋዊ – ህጋዊ ብቻ ሳይሆን – ህገመንግሥታዊ መብትን የተጎናፀፉ ሰብዓዊ ፍጡራን፣ ሰብዓዊ ዜጎች፣ ከማንኛችንም የማያንስ ህጋዊ እና ህጋዊ መቶ ፐርሰንት መብት ያላቸው ንፁሀን ኢትዮጵያውያን ዜጎች እኮ ናቸው፡፡
እና እንዴት ነው – በየዜናው – ይህን ያህል መቶ ሺህ ሰዎች ተፈናቀሉ – የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም – ለመርዳት – ለመረዳዳት – ለመበላላት – ለመበ**ት – ወዘተ ወዘተ እያልን ባየር ላይ እየለፈለፍን – ግፈኞቹን ፋሺስታውያን ተጠርጣሪዎች – ዝም ብለን አፋችንን ከፍተን የምንለመከተው??
በዓለማቀፉ ችሎት የሚዳኙ በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ኢሰብዓዊ ወንጀሎች እና የሰው ዘር ማፅዳት ወንጀሎችስ ከዚህ በተደጋጋሚ ከተጠቀሱት ድርጊቶች የተለዩ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ናቸውን? እነዚህስ በተደጋጋሚ የተጠቀሱት የኦሮሞዎችም ይሁን፣ የሮሂንጊያም ይሁን፣ የፊጂም ይሁን ጂጂጋ፣ ወይ ፈረንጅም ይሁን ማዳጋስካራዊ… እንዴ! እነዚህ እኮ በተደጋጋሚ ሪፖርት የቀረቡት ውንጀላዎች፣ እና በዓይናችን በብረቱ በየሚዲያው ያየናቸው ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሁሉ – እነዚህ ሁሉ እኮ – ከሰማይ የወረዱ መቅሰፍቶች አይደሉም፡፡ ልክ “ቪክቲም ታርጌት” እንዳላቸው ሁሉ – ፈጻሚም አድራጊም አላቸው፡፡
እነዚህ ሁሉ ሲፈጸሙ ‹‹ልዩ ሀይል የሚባለውን አደራጅቶ በበላይነት ይመራ የነበረው፣ ክልሉን ሲያስተዳድር የነበረው፣ እና በብዙዎች ዋነኛ ተዋናይ ተደርጎ የሚቆጠረው – ከአይሁዳውያን 2 ሚሊየን ተፈናቃዮች ቀጥሎ – በ20ኛው ክፍለዘመን ትልቁን የ1ሚሊየን ሰላማዊ ሰዎች – ጦርነት በሌለበት ሀገር በማፈናቀል – ወይም መፈናቀላቸውን በበላይነት በመምራት – ወይም ደግሞ በቸልተኝነት በማለፍ – ወይም ደግሞ አይቶ እንዳላየ በማለፍ – ወይም ደግሞ በመካድና በመሸሸግ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለድርጊቶቹ መፈጸም አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደረገ – ወይም የተባበረ – ወይም ይሁን ብሎ በህሊናው የተስማማው – ወይም በእነዚህ ሁሉ የተጠረጠረው – የዘመናችን ተጠርጣሪ-ኤክማን – ክቡር አብዲ ኢሌ – በተደጋጋሚ በቀረቡ የዓለማቀፍና የሀገር ውስጥ ሰብዓዊ ሪፖርቶች በተጠረጠረባቸው የሰው ልጅ ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን የመፈጸም ዓለማቀፍ ወንጀሎች – ሊከሰስ ይገባዋል – እላለሁ፡፡ ሊከሰስ ይገባዋል፡፡ ራሱን ይከላከል፡፡ ፍርዱን ለዓለማቀፍ ችሎትና ለእግዜሩ ትተንለት፡፡
ሰዎች ተለባብሰው ከከባባድ ዓለማቀፋዊ ኢሰብዓዊ ወንጀሎች ነፃ እንዲሆኑ፣ እንዲያመልጡ፣ እንዲጠለሉ፣ እንዲቀባቡና እንዲታለፉ የሚያደርግ ኢ-ፍትሃዊ የ‹‹ኢምፕዩኒቲ›› አካሄድ – ዛሬ ላይ በ1ሚሊዮን ነው፣ ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ – ከዚህ ብዙ ብዙ እጥፍ የሆነ ታላቅ ሰብዓዊ ቀውስን እንደማያበረታታብን ምንም ማረጋገጫ የለንም፡፡
በሌሎች ሀገራት – ይህ የኢምፒዩኒቲ – ተጠርጣሪዎችን እንደ ጲላጦስ እጃችሁን ታጠቡ በንፁህ ውሃ ብሎ አፎ የማለት – ኢፍትሃዊ አካሄድ – ብዙ ብዙ ዘግናኝ የማያባሩ የእርስ በርስ ጥፋቶችን አበረታቷል፡፡እኛም ጋር አያበረታታም ማለት – በእዝጌር ቸርነት ብቻ – ህገመንግስታዊ መብቶችን ለማስከበር የመሞከር – ለታላላቅ ወንጀለኞች አመቺ ዕድልን የሚፈጥር – የየዋሀን ምኞት ብቻ ይሆናል፡፡
 በሌላው የደረሰው በእኔም ይደርሳል እንበል፡፡ ሰብዓዊነት ይሰማን፡፡ በአደባባይ ሚሊየን ሰው አፈናቅሎ – ባደባባይ በነፃ እንዲመላለስ አንፍቀድ፡፡
ማንም ቢሆን፡፡ ሁሉም ከህግ በታች ነው፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ ሁሉም ሰው የሰብዓዊ መብቶች ባለቤት ነው፡፡
ሰብዓዊነት ይለምልም፡፡
ተጠርጣሪዎች ለሚገባቸው ተገቢ ችሎት ለፍርድ ይቅረቡ፡፡
ኡ ቡ ን ቱ ! ! !
በጽሑፉ ለተጠቀሱት የተለያዩ መረጃዎች ቤሲክ ማጣቀሻዎች፡-
5ኛ/ የዓለማቀፉ የወንጀል ችሎት መመሥረቻ ስምምነት፣ ዘ ሮም ስታትዩትስ ኦፍ ዘ ኢንተርናሽናል ክሪሚናል ኮርት፡፡
አምላክ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በያሉበት በረገጡበት ሥፍራ ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፣ ከክፋት ሥራ ሁሉ ይጠብቅ፡፡ የብዙሃን እናት ኢትዮጵያ ሀገራችን በፍቅር – በኅብረት – በወገናዊ መተሳሰብ ፀንታ – ለዘለዓለም ትኑር፡፡
‹‹ማለባበስ ይቅር፤ ማግለል ነው አደጋ
ማለባበስ ይቅር፤ እውቱን እናውራ››
እያልኩ አበቃሁ፡፡ መልካም ብሩህ ዘመን ለሁላችን፡፡
ማስታወሻ፡- 
ይበልጥ ዝርዝር መረጃዎችንና ኢንተርናሽናል አርካይቭስና ሪፖርቶችን ለማገላበጥ ፍላጎት ያደረባቸው አንባብያን ቢኖሩ.. በጉዳዩ ዙሪያ በዓለማቀፍ ሰብዓውያን ድርጅቶች ድረገጾች ወይም ከመረጃ መረብ ላይ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ በራሳቸው ፍለጋ (‹‹ሠርች›› አድርገው) ሊያነቧቸው ይቻላቸዋል፡፡
Filed in: Amharic