>

ይህ ከልክ ያለፈው ፈንጠዝያ  ምስጢር ምን ይሆን ?  (ዘመድኩን በቀለ)

ይህ ከልክ ያለፈው ፈንጠዝያ ምስጢር ምን ይሆን ? 
ዘመድኩን በቀለ
የዐረብ ፣ የኢሳይያስና የጠ/ሚዶኮ ፍቅር መጨረሻው ምን ይሆን ? 
~ አይተ ኢሳይያስ አፈወርቂ በህይወት ዘመኑ እንዲህ ጥርስ በጥርስ ሆኖ እንደህጻን ልጅ ሲቦርቅ ታይቶ የሚያውቅ አይመስለኝም
 
~  ኢሱም ሆነ ጠ/ሚ ዶኮም የተባበሩት ዐረብ ኤምሬት ድረስ በወር ውስጥ 3ጊዜ መመላለስ ያበዙትስ ለምን ይሆን? 
 
~ ዐማራ ግን መክት፣ ትግሬም ወደ ልብህ ተመለስ። ነግሬሃለሁ ተመለስ። ከፊት የሚመጣው መቅሰፍት አንዳችንንም አይምረንም። ኦርቶዶክሳውያን ንቁ። ተሰባሰቡ፣ ተደራጁ፣ ተጠንቅቃችሁ ራሳችሁንና ቤተክርስቲያናችሁን ጠብቁ። በኦሮሚያ የኢትዮጵያ ባንዲራ የተቀቡ አብያተክርስቲያናትን ለመቅጣት ያሰፈሰፈውን ኃይል እግዚአብሔር ያስታግሰው። ተናግረናል። አራት ነጥብ።
~ ሀገሬ አንድዬ ይጠብቅሽ እንጂ ሌላማ ምን ይባላል። ምንም። ምንም አይባልም።
~ አይተ ኢሳይያስ አፈወርቂ በህይወት ዘመኑ እንዲህ ጥርስ በጥርስ ሆኖ እንደህጻን ልጅ ሲቦርቅ ታይቶ የሚያውቅ አይመስለኝም። ከ30 ዓመት ጦርነት በኋላ ኤርትራን ከእናት ሀገሯ ገንጥሎ ሀገር ያደረጋት ጊዜ እንኳ እንደዚህ የፈነጠዘም አይመስለኝም።
~ አይተ ኢሳይያስ ጠሚዶኮ ምን ብሎ ቢፈርምለት ነው እንዲህ እንደ እምቦሳ ጥጃ የዘለለው? የፈነጠዘውም ብሎ መጠየቅ ጤናማ ጥያቄ ነው። ሰውየው እኮ በደስታ አቅሉን ነው የሳተው። የሚያደርገውንም ነው ያሳጣው።
~ በሌላ በኩል ደግሞ የጠሚዶኮ ዐቢይ እንዲህ ከፕሮቶኮል በታች ወርዶ ለኢሳይያስ መሽቆጥቆጥ፣ የኢሳያስን እጅ እንቅ አድርጎ #መሳም፣ እንደ ፍቅረኛ እጁን ደረቱ ላይ አድርጎ መሽኮርመም፣ ለእኔ ፈጽሞ የጤና አልመስልህ ብሎኛል። እንዲያው ስምምነቱ ምን ቢሆን ነው እንዲህ በደስታ የሰከሩት?
~ የሁለቱ መሪዎች ልፊያና መሽኮርመም ፍፁም ጤናማ ያልሆነና መስመሩን የሳተ መተቃቀፍ፣ መሳሳምና መቦረቅን ሳይ የስምምነቱን ምስጢር ለማወቅ እጓጓለሁ።
~ የተባበሩት ኤምሬትስ ብትሆን ከኢትዮጵያ በምላሹ ምን ብታገኝ ነው ይኽን ሁሉ ኢንቨስትመንት የምታፈስብን፣ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን የምትለቅብንስ ምን ብታገኝ፣ ምን ቃል ቢገባላትስ ነው?  በእውነት እጸድቅ እንደሁ ብላ ለነፍሷ ነው ብላ ነው አይባል ነገር። ወይስ ሌላ ነገር ምን አስባ ይሆን? መቼም ያለአንዳች መያዣ እንዲህ አይነት ደግነትማ ከቶውኑ አይታሰብም። ደግሞስ ኢሱም ሆነ ጠሚዶኮም የተባበሩት ዐረብ ኤምሬት ድረስ በወር ውስጥ 3ጊዜ መመላለስ ያበዙትስ ለምን ይሆን?
~ ለማንኛውም ትውልደ ኢትዮጵያዊው የኤርትራው ፕሬዘዳንትን [ኢሱ] ከኢትዮጵያችን ጠሚዶኮ ዐቢይ ጋር እፍፍ ብትን ያለ ፍቅር ከጀመሩ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ደስታ ብዙ ዋይታ እየተሰማ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በተለይ ሁለቱም መሪዎች ግብጽ ደርሰው ለአልሲሲ በአሏህ ስም መሃላ ፈጽመው ቃል ገብተው ከመጡ በኋላ፦
፩ኛ፦ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ በቀን ብርሃን በጠራራ ፀሐይ በመስቀል አደባባይ ታርዶ ተገኝቷል። ስለሟችም ስለገዳዮቹም የጠሚዶኮ መንግሥት ጮጋ ተብሏል። ግብጽ ግን ጮቤዋን ረግጣለች።
፪ኛ፦ በግብጽ ፋይናንስ፣ በኤርትራ ቤዝ ኖሮት ይንቀሳቀስ የነበረው የእስላማዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ለመመሥረት የሚታገለው ኦነግ ኦሮሚያን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሯል። በጃዋር በኩል ሚዲያ ገንብቷል። ካርታ አሠርቶ የዓማራን መሬቶች በሙሉ በእጁ አስገብቶ ማስተዋወቅ ጀምሯል።
፫ኛ፦ የጎረቤት ሀገር የሶማሌው ፕሬዘዳንት ኤርትራን ጎብኝተው ወደ ሀገራቸው በተመለሱ ማግስት የሶማሊያን ባንዲራ በጅግጅጋ ያውለበለቡ የተደራጁ ኃይሎች ከ10 በላይ አብያተ ክርስቲያናትን በእሳት አውድመው ከ15 በላይ አገልጋይ ካህናትንና ዲያቆናትን እንዲሁም ከ30 በላይ እስከ አሁን ያልተቀበሩ ምእመናንንም ጭምር በሰይፍ አርደው በቤንዚል አቃጥለው ተልእኮዋቸውን ያለምንም ሳንካ ፈጽመዋል። [ በመሃል ጅጅጋ የሱማሌ ባንዲራ ሲውለበለብ ከርሟል]  ፎቶው አለኝ ።
~ ይኼ ሁሉ ሲሆን ሚሽኑን የወሰዱት አካላት ተልእኮዋቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ የሚመሩት የፌደራሉ መከላከያ ኃይል በጉዳዩ ጣልቃ እንዳይገባ በ12 ቁጥር ሚስማር ተጠርንቆ እንዳይንቀሳቀስ ተደርጓል።
~ “በአክሱም መስጊድ የማይሠራበት ምንም አይነት ምክንያት የለም” የሚለው የጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድን ውሳኔ የሰሙት የትግራይ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በድንጋጤ እነሱ በአክሱም ጽዮን ምህላ እያደረሱ በጅጅጋ ስለሚቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት፣ ስለሚታረዱት ካህናት፣ ዲያቆናትና ምእመናን ምንም ግድ ሳይሰጣቸውና አንዳችም ርኅራሄ ሳያሳዩ ለአራጁና ለአውዳሚው አካል ሲሟገቱ መታየታቸው በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከባድ ቅሬታን መፍጠራቸው ይታወቃል። የትግራይ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ከሚመጣው መከራ ይታደጋቸው ዘንድ ጀዋር መሀመድ እግር ስር መደፋት ጀምረዋል። ወይ ጊዜ ደጉ አንተ መቼም አታሳየን ጉድ የለ?
~ እልቂቱና ጥፋቱ ድሬደዋ ደርሶም ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ የዶሮ ነፍስ የጠፋ እንኳ ሳይመስላቸው በዝምታ ተውጠዋል። በጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ ፍቅር ነፍስያቸው የተሰለበባቸው አካላት ደግሞ የፈለገ ጥፋት በኢትዮጵያ ቢፈጸም አጥፊዎቹ ” የቀን ጅቦቹ ናቸው ” በሚል የጦስ ዶሮ ስላገኙ ዐቢይን መውቀስ እንደሚያስቀስፍ ሲሰብኩ ይታያሉ።
~ ዳያስፖራው ማኖ ስለነካ ሳይለንት ሙድ ላይ ስለተደረገ ጮጋ ብሏል። ቫይብሬት እንኳን እንዳያደርግ ነው የተደረገው። ኢሳት የግፉአን ድምጽ እንዳልነበር አሁን ኢቲቪን ተክቶ ዝም ጭጭ ብሏል። እነ ታማኝ በየነ ምን አፍ አለን በሚል አፋቸውን ዘግተው እንዲቀመጡ ተደርገዋል። ኦርቶዶክሱ ሁለቱ ሲኖዶሶችን አስታርቀውልናል በማለት አቅሉንስቶ ስለጨፈረ አሁን በአንድ ክልል የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናቱ በእሳት ሲወድሙ፣ ካህናቱ ሲቃጠሉ ዝም ጭጭ ብሏል። ብቻ ሁሉም ማኖ ስለነካ አንገቱን አቀርቅሮ የሚሆነውን ከማየት ውጪ ሌላ ውልፍት ለማለት አልቻለም።
~ ኢሳይያስ ግን ኢትዮጵያን የማፍረስ የልጅነት ህልሙን ሳይሞት በፊት በአይኑ እንዲያይ እየጸለየ ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል። ትውልደ ትግራዋዩን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩን አቶ ገበየሁ ወርቅነህንና የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ኦቦ ለማ መገርሳን ከኦነጎቹ ጋር በአስመራ አደራድረውና አስታርቀው መርቀው ሸኝተዋል። ኦነግ በሰጠው መግለጫም “ዕርቁ” የኦነግን እስከመገንጠል ድረስ የሚለውን ዓላማውን ይዞ ኢትዮጵያ ገብቶ መታገልን እንደሚፈቅድለት ስምምነታቸውን አስመልክተው ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
~ ህውሓት የትግራይን ህዝብ ከወንድሙ ከዐማራ ጋር እሳትና ጭድ አድርጋ አድፍጣ መቐለ ከትማለች። እየመጣ ያለው መቅሰፍት ግን የትግራይን ኦርቶዶክሶች፣ የዐማራን ኦርቶዶክስና እስልምና፣ የኦሮሞን ኦርቶዶክሳውያን፣ የአንድነት አቀንቃኙን የጉራጌ፣ የደቡብና የኮንሶ ህዝብ ሊበላ አሰፍስፏል። አንዳቸው ለአንዳቸው እንዳይተጋገዙ እንኳ በመሃላቸው ህውሓት ደንቃራ አስቀምጣ አንዱ የአንዱን ውድቀት እንዲጠባበቅ አድርጋ አስቀምጣዋለች።
~ እነ ጃዋር በደንብ ስለነቁ አዲስ ጨዋታ ጀምረዋል። በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ትግሬ እንዲጠላ አድርገው ሲያበቁ፣ ትግራዋዩን ከሥልጣን አስወግደው መቐለ እንዲመሽግ ካደረጉት በኋላ አሁን ትግሬው ከዐማራ ጋር ከታረቀ ሊፈጠር የሚችለው አደጋ ስለታያቸው ትግሬውን በድጋሚ አባብለው ወደ አዲስአበባ በማምጣት ከኦሮሞ ጋር እናስታርቅህ፣ ከዐብይ ጋር እናስማማህ በማለት ላይ ይገኛሉ። ጃዋር ለዚሁ ሥራ መቐለ እንደሚሄድ ከዶር ደብረጽዮንም ጋር እንደመከረ ለአውራአምባው ዳዊት ከበደ በሰጠው ቃለምልልስ ላይ ተናግሯል።
~ ሁለቱ ህዝቦች በተለይም ዐማራውና ትግራዋዩ ይኽን ሴራ በጥሰው በአንድነት ከቆሙ ግን ጨዋታው ፍጻሜውን ያገኛል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በድኑ ብአዴን ቀድሞ ለህውሓት አሁን ደግሞ ለኦህዴድ የአሽከርነት ተግባሩን በመፈጸም ላይ ይገኛል። ዣንጥላ ይዞ ዐብይን ይከተላል። ቤተ መንግሥቱን በዘበኝነት ይጠብቃል። ምፅ ሲያሳዝን !
ለማንኛውም ኢትዮጵያን የፈጠራት አምላኳ ያውቅላታል። ከቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ ከአበው በሰማነው ቃል መሰረት ኢትዮጵያችን ምንም አትሆንምም። ዐማራው ግን ከዐማራ ብሔርተኝነትህ ውጪ ምንም መዳኛ እንደሌለህ አውቀህ በመደራጀትህ ቀጥል። ዛሬ ትመክታለህ። ነገ የከፋ ነገር ከመጣ ታነክታለህ። ለሁሉም ግን መዘጋጀቱ መልካም ነው። አያያዝህ ደስ ይላል። ማንንም ሳትነካ፣ ሳትተናኮስ፣ የራስህን ህልውና ለማስጠበቅ ጠንክረህ ታገል። ግፋ፣ ቀጥል፣ በርታ።
#ዐብን ከተመሠረተ በኋላ ዐማራው የተስፋ ጭላንጭል ማየት ጀምሯል። እየታረደም፣ እየተቃጠለም፣ እየተፈናቀለም ቢሆን ዐማራው አሁን በተስፋ ድልን እያሰበ ችግሩን ህመሙን ዋጥ እየደረገ መደራጀቱ ላይ አተኩሯል።  ዐማራው በድፍረት በአደባባይ ቆሞ እኔ ዐማራ ነኝ ማለት ጀምሯል። ዐማራው ባህሉን፣ ማንነቱን፣ በአደባባይ መመስከርም፣ ማሳየትም ጀምሯል። ዐማራው ዐማራነቱ ሲፋቅ ኢትዮጵያዊ መሆኑ የታወቀ፣ የተረዳ ነገር ነው። እናም የዐማራው በዐማራነቱ መደራጀት በኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣው አንዳችም አይነት ስጋት የለም።
ከሌሎች በብሔር ከተደራጁ ፓርቲዎች ጋር በጥምር ሲሠሩ ትንፍሽ የማይሉት የአንድነት ኃይል ነን ባዮቹ የዐማራው መደራጀት ለምን ነስር በነስር እንደሚያደርጋቸው መድኃኔዓለም ይወቅ። ለማንኛውም ዐማራ ከእንግዲህ ወደኋላ ይላል ብሎ ማሰብ የማይሞከር ነው። እነ ጃዋር ወሎን፣ ሸዋንና ጎጃምን በካርታቸው ሠርተው ለፀብ እየፈለጉት ይቅርና እንዲሁም መከራው ከፊቱ የተዘፈዘፈበት ህዝብ ስለሆነ መደራጀቱ ወሳኝ ነጥብ ነው።
~ ለአንድነት ኃይሉ የኢኮኖሚ ምንጭ የነበረው ዐማራው አሁን ገንዘቡንም እውቀቱንም ወደ #ዐብን ማዞሩ ብዙዎችን ሲያስከፋ እያየን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው። በጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው አማካኝነት የተሞከረው የገቢ ማሰባሰብ በጥቂት ቀናት ከተጠበቀው በላይ ማስመዝገብ ሀገር ምድሩን አስደንግጧል። ዐማራውን ግን አስፈንድቋል። እናም ይኼ ነገር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
~ ዐማራው መጀመሪያ እራሱን ማዳን አለበት። በውጪ ሀገር ያለው ዐማራ ገንዘብ አለው፣ እውቀት አለው፣ እናም አስተባባሪ ካገኘ ተአምር መሥራት እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው።
አሁን ሁለት ነገር ልጠቁም።
፩ኛ፦ ዐማራው በአስቸኳይ አንድ ትልቅ ግዙፍ የሚዲያ ተቋም በአስቸኳይ ይመስርት። ይኼ ጊዜ የማይሰጠው ነው። እስከአሁን በድሮዋ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ ውስጥ ተቀምጦ ለእርድ እንደተዘጋጀ በግ የመታረጃ ቀኑን የሚጠብቅ ዐማራ ስላለ እሱን ማንቃት የሚቻለው በሚዲያ ነው። የዐማራ ቴሌቭዥን ህውሓት ለማስደንገጥ ብሎ ቀነጫጭቦ ያቀረበው የዐማራ እስረኞች ግፍ እንኳ ምን አይነት መነቃቃት እንደፈጠረ ሁላችንም እናውቃለን። እናም ዐማራው ሚዲያ ይመስርት። ፍጠኑ ።
፪ኛ፦ ልክ እንደ ኦሮሞዎቹና እንደትግሬዎቹ ዓለም አቀፍ የዐማራ ልማትና በጎ አድራጎት ማኅበር በአስቸኳይ መመሥረት። በጎንደር፣ በጎጃም፣ በወሎና በሸዋ ሳይሆን በአንድ ዐማራ ስም ይመሥረት። ያ ማለት አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈናቀለውን ዐማራ መንግሥትም፣ የውጭ እርዳታ ድርጅቶችም እንደማይረዱት የታወቀ ነው። ዐማራው በጠኔ ድፍት ይላታል እንጂ የሚረዳው እንደማይኖር የታወቀ ነው። ትግሬ ተፈናቀለ ተብሎ ክልሎች ከዓመታዊ በጀታቸው ላይ እንደሚሠጡት፣ ኦሮሞው ተፈናቀለ ተብሎ ሀገር ምድሩ እንዲረባረብ እንደሚገደደው ዐማራው ሲፈናቀል፣ ሲራብ ዞር ብሎ የሚያየው እንደሌለ የታወቀ ነውና በአስቸኳይ ዓለም አቀፍ የዐማራ ልማትና የበጎአድራጎት ማኅበር መመሥረት የግድ ይላል። የጅጅጋው ትምህርት ይሁናችሁ።
በትግራዩ የቀለሚኖ ትምህርት ቤት አይናችሁ ሲቀላ ከመዋል በዐማራው ክልል 100 የቀለሚኖ ዓይነት ትምህርት ቤት ማቋቋም የሚችል አቅም እንዳላችሁ ማሳየት አለባችሁ። በዳስ ውስጥ እየተማሩ ዓለምን የሚያስደምም ውጤት የሚያመጡ ባለ ብሩህ አዕምሮ ልጆች ባለቤት ያላችሁ መሆኑ ታይቷል። እናም ከዳስ ውስጥ አውጥታችሁ በተረጋጋ ሁኔታ የሚማሩ ተማሪዎችን ብታፈሩማ ሀገር ምድሩን በችግር ፈቺ ምሁራን ባጥለቀለቃችሁ ነበር። እናም በአስቸኳይ አስቡበት።
ሻሎም ! ሰላም !
ነሐሴ3/2010 ዓም
ከራየን ወንዝ አጠገብ።
Filed in: Amharic