>

አመፃ ይቁም! የአመፃ ፍትሕ የለም! (በፈቃዱ ዘ ሃይሉ)

አመፃ ይቁም! የአመፃ ፍትሕ የለም!

በፈቃዱ ዘ ሃይሉ

(< የሚታየው ምስል ዘግናኝ በመሆኑ አደብዝዤዋለሁ )

ሐዲስ ዓለማየሁን የሚያክል የሚያስደምመኝ የተዋጣላቸው ኢትዮጵያዊ አክቲቪስት እና ደራሲ አላውቅም። ድርሰቶቻቸው የአክቲቪዝም ዓላማ ነበራቸው። ‘የሠላማዊነት’ አቀንቃኝ ነበሩ። “የልምዣት” በተሰኘው የረዥም ልቦለድ ሥራቸው ላይ ባሻህ ዘለሌ የሚባል ሰው የሚመራ አንድ ኅቡዕ ድርጅት ነበር። የድርጅቱ ዓላማ የባለጉ ባለሥልጣናትን መቅጣት ነበር። የድርጅቱ አባላት የባለጉ ባለሥልጣናትን ይገሉና አስከሬናቸው ላይ የቅጣቱን መንስዔ ያሰፍሩበታል። መጽሐፉን ካነበብኩት በጣም ስለቆየሁ መልዕክቱን ረስቼዋለሁ። የሆነ ሆኖ ኅቡዕ ድርጅቱ “ከፍትሕ ሰጪ” አካልነት ወደ “ውንብድና ድርጅትነት” ይቀየራል። ባሻሕ ዘለሌም ራሱ የመሠረተውን ድርጅት መቆጣጠር ያቅተዋል።

ሁልግዜም የአመፃ ትግል ተቃዋሚ ነኝ። በርግጥ በኢትዮጵያ የነበሩትን የትጥቅ ትግሎች የሚደግፉ አካላት “የመንግሥትን አመፃ የመከላከል እርምጃ” ነው ብለው መከላከያቸውን ሲያቀርቡ ሰምቻለሁ። የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ሳታልፍ የሠላማዊ ሽግግር ዕድል ስላገኘች ተደስቻለሁ። ነገር ግን አሁን ያለንበት ሁኔታም በጣም አሳሳቢ ነው።

ሁሉንም ነገር በአፈና እና በኃይል በመጨፍለቅ ላይ የነበረው ኢሕአዴግ፥ በሕዝብ ትግል ተንበርክኮ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየታገለ ነው። ተቃዋሚዎችም ራሳቸውን ጥሩ አማራጭ አድርገው ለማደራጀት እየተፍጨረጨሩ ነው። ነገር ግን የትግሉ ባለቤት የሆኑት ወጣቶች እዚህም እዚያም “የእርምት እርምጃ” ሰጪ ለመሆን መሞከራቸው በጣም አደገኛ እና ዛሬ ነገ ሳይባል ሊቆም የሚገባው ገር ነው። በየቦታው “ይሔን ጥፋት ሊያጠፋ ተያዘ” የተባለን ሰው መደብደብ፣ ማሰቃየት አሳዛኝ እና ይቅር የማይባል የታሪካችን አካል እየሆኑ ነው። መኪናዎችን በግለሰቦች እያስቆሙ መፈተሽ፣ በእሳት ማጋየት እጅግ በጣም ኢፍትሓዊ እርምጃዎች ናቸው።

ፖሊስ እንኳን ተጠርጣሪን ሲይዝ፣ ሲመረምር፣ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሲዳኝ፣ ተጠርጣሪው ጥፋተኛ መሆኑ ሲረጋገጥና እርምት ሲቀበል የሰዎችን ሰብኣዊ መብቶች እና ክብር ሳይገፍፍ ነው (መሆን ያለበት)። ከዚህ ውጪ ያለው አሠራር በሙሉ ኢፍትሐዊ ነው። ኋላ ቀር ነው። ግፍ ነው። ይቅር የማይባል ነው።

ባለፈው ሰሞን ‘የአቶ በረከት ስምዖን መኪና ነው’ ተብሎ በእሳት ጋይቷል። የቁሱስ ይሁን እርሳቸው ቢገኙም ኖሮ በሕይወት አይተርፉም ነበር። ከዚህ አስደንጋጭ ክስተት ብዙም ሳንርቅ ዛሬ በሻሸመኔ የተከሰተው እጅግ ሰቅጣጭ ነው። አቶ ጃዋርን ለመቀበል እየተደረገ ባለው ድግስ መሐል “ቦንብ ይዟል” ተብሎ የተጠረጠረ መኪና በእሳት ሲለኮስ፣ ሹፌሩ ደግሞ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ ስቃይ ደርሶበታል። ይህ በጣም ዘግናኝ እና ከአራዊትነት የከፋ ተግባር ነው። የተጠረጠረ ቢኖር እንኳ ለፖሊስ ተላልፎ ተሰጥቶ፣ በሕግ አግባብ ራሱን የመከላከል ዕድል ተሰጥቶት፣ በፍርድ ቤት ነው ጉዳዩ ውሳኔ ማግኘት ያለበት። ስሜታዊ ሰዎች የመንጋ እርምጃ ሲወስዱ መንግሥት ጥቂቶችን የማስቆም ግዴታ አለበት። እንዲህ ዓይነቱ ስርዓት አልበኝነት ከአሁኑ ካልተገራ እያደር ባሕል መሆኑ አይቀርም።

የመንጋ ፍርድ ሰብኣዊነታችንን አደጋ ውስጥ ይከተዋል። አውሬ እንኳን በገዛ ዘሩ ላይ እንዲህ አይጨክንም። በክፉ ቀናችን ለትግል የመለመልናቸውን ወጣቶች (ልክ እንደ ሐዲስ ዓለማየው ልቦለዳዊ ኅቡዕ ድርጅት ወደ ውንብድና እንዳይገቡ) ስለፍትሕ አሰጣጥ፣ ስለሰብአዊነት፣ ስለስርዓት ባሉን ሚዲያዎች፣ በተገኘው ሁሉ ዕድል በማስተማር ማረጋጋት አለብን። የአመፃ ፍትሕ የለም። አመፃን እናውግዝ። ያለማቋረጥ። #StopMobJustice
#የመንጋ_ፍርድ_ይቁም

 

Filed in: Amharic