>
4:55 pm - Wednesday November 30, 2022

“ጄል” ኦጋዴን እና የጅግጅጋ ፖለቲካ (መስከረም አበራ)

መስከረም አበራ

የሃገራችን ፖለቲካዊ ከባቢ በተበድዬ ተረክ “የበለፀገ” የጎሳ ፍትጊያ የተንሰራፋበት ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካችን ንረት ፖለቲካ ማለት ጎሳ ማለት ብቻ እንደሆነ እርግጠኛ ሊሆን ይሞክረዋል፡፡ ይሄው አደገኛ አዝማሚያ የሚዘወረው ደግሞ የግል ደም-ፍላታቸውን በካሜራ ፊት ሲሆኑ እንኳን መቆጣጠር በማይችሉ፤ ደርሶ ቱግ ባይ የፖለቲካ ሊቅ ነን ባዮች ነው፡፡ ይህ ህወሓት ይዘውረው በነበረው መንግሥታዊ መሰላልም፣ ተቃዋሚ ነን በሚሉ ስብስቦችም ሆነ የጎሳችን አክቲቪስት ነን በሚሉት ዘንድ የሚስተዋል ልማድ ነው፡፡

በብዛት ንዴት የሚቀድማቸው የጎሳ ፖለቲካ ቀሳውስት ለሰንዓዊነት ቦታ የላቸውም፡፡ የራሳቸውን ጎሳ የተመለከ ጉዳይ ሲሆን ወደቀ የሚለውን ተሰበረ የሚሉት ደማቸው እየተንተከተከ ነው፡፡ ኢሬቻ ላይ ወረቀት የሚበትን ሄሊኮፕተር አይተው “ህዝብ ከሰማይ በሚወርድ ቦንብ ተደበደበ” ያሉ “ታዋቂ” አክቲቪስቶች እውነቱ ሲታወቅም ሃፍረት አልጎበኛቸውም፡፡ ወሰን ከልለው የሆነውንም ያልሆነውንም እየቀላቀሉ ደም ፍላታቸውን ወደ ጎሳ ተጋሪዎቻቸው የሚያጋባ የመሰላቸውን ነገር ሁሉ ያደርጋሉ፡፡በዚህ መልክ ስሜታዊነት ይዋለድ ይዟል፡፡ በስህተት ስለ ሌላው ጎሳ ጉዳት መናገር ትዝ አይላቸውም፡፡

እንዲህ ያለ ተንደቅዳቂ የጎሳ ፖለቲከኛ ወይ አክቲቪስት የሌላቸው የዓለምን ፍዳ የሚፈጁ ህዝቦች ደግሞ ሰማይ ሙሉ መከራቸው፣ ምድር ሙሉ ፍዳቸው ተለባብሶ መራራ እውነታቸው ተዳፍኖ ይቀራል፡፡ የኢትዮ-ሶማሌ ህዝቦች መከራቸው ተለባብሶ ከቀረባቸው ህዝቦች ዋነኞቹ ይመስሉኛል፡፡ እነዚህ ህዝቦች ጫፍ የረገጠው የጎሳ ፖለቲካችን ሁለት ሶስቴ የበደላቸው ሰዎች ናቸው፡፡

አንድ ቢሉ አብዲ ኢሌ የሚባል ምኑም ለአለቅነት የማይመጥን ሰውዬ ጎሳው ብቻ እውቀት፣ ምጥቀት፣ ብቃት ሆኖ ተቆጥሮለት እላያቸው ላይ ተጫነ፡፡ ሁለተኛ የሚደርስባቸውን መከራ እንኳን ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማሳወቅ እንዳይችሉ ትናጋቸው በዚሁ ሰውዬ ታፍኖ ኖሯል፡፡ የሕዝባቸው ነገር አሳስቧቸው በስደት ተቀምጠው እንኳን ስለህዝቡ ሥቃይ ሊናገሩ የሚሞክሩ የኢትዮ-ሶማሌ አክቲቪስቶች ሃገር ቤት ባሉ ዘመዶቻቸው ሕይወት መፍረድ አለባቸው፡ ፡የመጣው ይምጣ ብለው የሚናገሩቱም በጎሳቸው ላይ ብቻ አተኩረው የማያወሩ ኢትዮጵያዊነታቸው የሚጫናቸው ናቸውና አሁን እየተንበለበለ ካለው የጎሰኝነት ደመራ ጋር መሳ ሊሄዱ አልቻሉም፡፡

እውነትን ከውሸት እየደባለቀ ሃላፊነት በማይሰማው መንገድ የሚንተገተግ ብቻ ጆሮ የሚስብበት ብልሹ የፖለቲካ ልማዳችን የነዚህን ሰዎች ንግግር ነገሬ ሊል አልቻለም፡፡ወደቀ ሲባል ተሰበረ የሚል የኢትዮ-ሶማሌ የጎሳ አክቲቪስት በብዛት ባለመኖሩ የህዝቡ በደል ትኩረት አጥቶ ኖሯል፡፡ሌላው ኢትዮጵያዊ በደላቸውን እንዳይናገርላቸው ደግሞ ጠጠር መጣያ ሳያስቀር የተንሰራፋው የጎሳ ፖለቲካችን ከሰብዓዊነት አጉድሎናልና ከሰፈራችን ሰው ውጭ ያለ ዋይታ አይሰማንም፤ቢሰማንም የሠርግ ቤት ድለቃ የሚመስለው ይበዛል፡፡

የኢትዮ-ሶማሌ ክልል ዋይታው የተዳፈነ፣ ለብሶቱ ጆሮ ዘንበል ያላለለት አሳዛኝ ክልል ነው፡፡ ኢህአዴግ ወደስልጣን ሲመጣ ሃገሪቱን ከመስቀለኛ መንገድ መለስኩ በሚልበት አካሄዱ የሽግግር መንግሥት ምሥረታው ታዳሚዎች ካደረጋቸው የጎሳ ፓርቲዎች አንዱ ዛሬ “ዓይንህን ላፈር”  የሚለው ኦብነግ እንደ ነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በመጀመሪያው የክልል ምክር ቤት ምርጫም ኦብነግ የክልሉን ምክርቤት  ስልሳ ፐርሰንት መቀመጫ አግኝቶ ነበር፡፡ በ1986 ዓ.ም ኦብነግ የክልል ፓርላማውን አብላጫነት ተጠቅሞ ክልሉን ለመገንጠል ህዝበ-ውሳኔ ለማድረግ በመንቀሳቀሱ ሳቢያ የአቶ መለስን መንግሥት በማስቆጣቱ የፌዴራሉ መንግሥት የክልሉን ፕሬዚደንት እና ምክትላቸውን አስሮ፣ ዋነኛ የክልሉን ባለስለጣናት ከሥራ ገበታቸው አስወገደ፡፡ እንዲህ ዋናውን ያጣው፣ ከመገንጠል ውጭ ዜማ የሌለው ኦብነግም ይህን ተከትሎ ነገር ዓለሙን ጥሎ ብረት አንግቶ ወደ ጫካ ነጎደ፡፡

ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ ውጅግራ አንግቶ ዱር ያደረው ኦብነግ 1999 ላይ “ኦቦሌ” በተባለው የነዳጅ ቁፋሮ ማእከል ላይ ወደ ሰባ የሚጠጉ የቻይና የቁፋሮ ሰራተኞችን እና ተጨማሪ የኢትዮጵያ ዜጎችን ማርኮ፣ የቀሩትን ባሰቃቂ ሁኔታ መግደሉ መኖሩን የሚያሳውቅ ብቻ ሳይሆን የአቶ መለስን መንግሥት ያስደነገጠም ያስቆጣም ጥቃት ነበር፡፡ከዛ ወዲህ የኢትዮጵያ መንግስት ኦብነግን ለመደምሰስ ቆርጦ ተንቀሳቀሰ፣ በርከት ያለ የመከላከያ ሰራዊት ወደቦታው ጎረፈ፡፡  በዚህ ጊዜ ነው የኢትዮ-ሶማሌ ህዝብ የመከራ ድፍድፍ የተደገሰው፣በመንታ ቢለዋ መታረድ የጀመረው፡፡

ኦብነግን አጠፋለሁ ብሎ ወደ ቦታው የተመመው የመከላከያ ሠራዊት “ኦብነግን ትደግፋላችሁ፣ሽፋን ትሰጣላችሁ” እያለ ህዝቡን ቁም ስቅል ያሳያል፣ ያፈናቅላል፣ ሴቶችን ይደፍራል፣ ኦብነግን ደግፏል ብሎ ያሰበውን ሰው እንደሙሴ ዘመን በህዝብ ፊት አቁሞ ይረሽናል፣ ሴት ወንድ ሳይል ወደ እስር ቤት አግዞ መከራ ያሳያል፡፡ ኦብነግን ለማጥቃት ንፁኃን የኢትዮ-ሶማሌ ሲቪል ሰዎችን በጅምላ ይቀጣል፡፡ኦብነግ በበኩሉ ተመሳሳዩን ያደርጋል፡፡ ከሁለት ያጣው ሲቪል ህዝብ በመንታ ምጣድ ተጥዶ ይቆላል!

ገለልተኛ ወገን ገብቶ ጉዳዩን እንዲያጣራ ቢጠየቅ ሥራውን የሚያውቀው የአቶ መለስ መንግስት በጄ ሳይል ኖሯል፡፡ በኢትዮጵያ በሁሉም ቦታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የዕለት ተዕለት የኑሮ አካል ቢሆንም የኢትዮ-ሶማሌ ክልል ባስ የሚልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ጋዜጠኞች፣ የሰብኣዊ መብት ተቆርቋሪዎች፣ ዲፕሎማቶች በክልሉ መንቀሳቀስ አይፈቀድላቸውም፡፡ሲንቀሳቀሱ ከተገኙ የስዊድን ጋዜጠኞችን ያገኘ ያገኛቸዋል፡፡ በክልሉ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ተንቀሳቅሶ የሚሰራ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም፡፡

ይበልጥ የሚገርመው ይህን የሚያዙት አቶ መለስ አፈር እስኪገቡ ድረስ ደርግ ህወሓትን ለማጥፋት የትግራይን ህዝብ በጅምላ ደበደበ፣ አሰረ፣ ገደለ እያሉ ሲያብጠለጥሉ የኖሩ መሆኑ ነው፡፡ ሞኛሞኙ ደርግ “አሳውን ለማጥፋት ውቂያኖሱን ማድረቅ ያስፈልጋል” ያለውን እያነሳሳ የሚያላዝነው ህወሃት ዋና የሆኑት አቶ መለስ ተመሳሳዩን በሌላ ህዝብ ላይ ሲያደርጉ ልክ እንደሆነ የሚነግራቸው እስከ ሞት የተከተላቸው ክፉ ዘረኝነት ብቻ ነው፡፡

የልዩ ሃይል ውልደት

በ1999 ዓ.ም. ኦብነግ በነዳጅ ቁፋሮ ሰራተኞች ላይ ያደረገውን እስር እና ግድያ ተከትሎ አካባቢውን የወረረው የሃገር መከላከያ ሰራዊት በሚያደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በስብዕና ላይ ወንጀል በመስራት ሲያስከስሰው ኖሯል፡፡ ህዝቡም ከሆነበት ነገር የተነሳ መከላከያ ሰራዊትን መጥላት ጀመረ፡፡ራሱም የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን የሚያጧጡፈው ኦብነግም የሃገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርሰውን የሰብአዊ መብት ረገጣ እያነሳሳ ነገሩ ሌላው ኢትዮጵያዊ በኢትዮ-ሱማሌ ህዝብ ላይ የሚያደርሰው በደል እንደሆነ ፕሮፖጋንዳ እየሰራ የመገንጠል አጀንዳውን ትክክለኝነት መስበክ ጀመረ፡፡ ጦርነቱም በሌሎች ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮ-ሶማሌ ህዝብ መሃከል የሚደረግ አድርጎ ማቅረቡን ተያያዘው፡፡ይህን ያስተዋሉት ነገርን ከብዙ አቅጣጫ የማያዩት አቶ መለስ የኦብነግን የመገንጠል ፕሮፖጋንዳ ያረክስልኛ ያሉትን ግን እጅግ አደገኛ ነገር አመጡ፡፡

ይህ አደገኛ መፍትሄ የኢትዮ-ሶማሌ ልዩ ኃይልን ማቋቋም ነው፡፡ ልዩ ሃይሉ የሃገር መከላከያ ሰራዊትን ተክቶ ህዝቡን አሳር መከራ እንዲያሳይ የተፈቀደለት ወንጀለኛ ሆኖ አረፈው፡፡ አቶ መለስ ልዩ ኃይል ፖሊስን በ2001 ሲያቋቁሙ አባላቱ ባጠቃላይ በሚባል መልኩ ከዛው ከኢትዮ-ሶማሌ ክልል በተለይ ደግሞ ከገናናው የኦጋዴን ጎሳ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ በሃገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያሉ የኢትዮ-ሶማሌ ክልል ተወላጆች ከመከላከያ ሰራዊት ወጥተው ልዩ ኃይሉን እንዲቀላቀሉ ሆነ፡፡

አቶ መለስ ልዩ ኃይሉን ከኢትዮ-ሶማሌ ተወላጆች በተውጣጡ አባላት የሞሉበት ምክንያት ጦርነቱ በሌላው ኢትዮጵያዊ እና የኢትዮ-ሶማሌ ህዝብ ተወካይ ነኝ በሚለው ኦብነግ መሃከል ነው የሚለውን የኦብነግ ፕሮፖጋንዳ ለማርከስ እና የመገንጠል አጀንዳውን ለማዋደቅ ሲሉ ነበር፡፡ ነገሩ በከፊል በጎ ነገር ቢኖረውም ትልቁ ጥፋት ግን ልዩ ሃይሉ የህዝቡን ሰብአዊ መብት ማክበር ግዴታው እንደሆነ በውል ሳይነገረው ጭራሽ የሰላማዊ ሰዎችን ሰብአዊ መብት የመረጋገጥ ስልጣንም አብሮ መሰጠቱ ነው፡፡ የልዩ ሃይሉ ስራ እና ሃላፊነት ያልተወሰነ መሆኑ፣የቁጥሩ ብዛት፣የትጥቁ ከባድነት ደገሞ ሌላው ጥፋት ነው፡፡

እንደ “Human Rights Watch” ዘገባ በክልሉ ህዝብ ዘንድ ልዩ ሃይሉ እንደ አጋንንት ሰራዊት ይፈራል፣ እንደ አባት ገዳይ ይጠላል፣ እንደ እርኩስ ይታያል፡፡ ልዩ ሃይሉ ስራ ከጀመረበት ከ2001 ጀምሮ ጄል ኦጋዴን የተባለው የማሰቃያ ስፍራ በልዩ ሃይሉ ሰዎች ቁጥጥር ስር ወድቋል፡፡ልዩ ሃይሉ ተጠሪነቱ ለክልሉ ፀጥታ እና ደህንነት ቢሮ ሲሆን ይሄው ቢሮ ደግሞ በአብዲ ኢሌ ይዘወራል፡፡ልዩ ሃይሉ ከአብዲ ኢሌ ውጭ የሚሰማው አካል የለም፡፡ እሱ ያለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡አብዲ ኢሌ ደግሞ በክልሉ በሰፈረው የምስራቅ ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት መኳንንት እየታገዘ የህዝብ መከራ ያከብዳል፡፡በልዩ ሃይል ክንድ የሃገር መከላከያ ሰራዊት መኳንንት የክልሉን ህዝብ ይገርፋሉ፡፡

“ጄል” ኦጋዴን- የሲኦል ቅርንጫፍ

በኦብነግ እና በማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግስት መሃከል ባለው ነፍጥ ያማዘዘ ውዝግብ ውስጥ ኦብነግን በመርዳት በኩል አንዳች አስተዋፅኦ አድርገዋል የተባሉ የኢትዮ-ሶማሌ ክልል ሰላማዊ ሰዎች ወደ “ጄል” ኦጋዴን ይጋዛሉ፡፡ከጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ አምስት ደቂቃ ያህል ብቻ ሚያስኬደው ይህ እስር ቤት የአዲስ አበባውን ማዕከላዊ የሚመስል ነው፡፡የሰው ልጅ ችሎ ያስተናግደዋል፤ ሰው የሆነ ሰውም በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ያደርገዋል ተብሎ የማይታሰብ አረመኔያዊ ድርጊት ይደረግበታል፡፡ የዚህ ሁሉ እኩይ ድርጊት አስመድራኪ ኢህዴግ ሲሆን የድርጊቱ ፈፃሚ ደግሞ ልዩ ሃይል የተባለው አረመኔያዊ ቡድን ነው፡፡

በ”ገመና ከታቹ” ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አንጥፎ የተኛበተን፣በጄል ኦጋዴን የሚደረግ ሰቅጣጭ ነውር “Human Rights Watch” የተባለው የባዕዳን ድርጅት አይገቡ ገብቶ መርምሮ አጋልጧል፡፡ይህ ድርጅት ከ 2003-2010 በጄል ኦጋዴን በተለይ ሲደረግ የኖረውን “እግዚኦ” የሚያስብል የሰብአዊ መብት ረገጣ “WE are Like the Dead” በሚል ርዕስ በባለ 88 ገፅ ሪፖርት ሃምሌ 2010 ላይ ይፋ አድርጓል፡፡ ሰው የሆነ ሁሉ ሙሉ ሪፖርቱን ቢያነበው እላለሁ፡፡ሪፖርቱ በአጠቃላይ ወደ 98 የሚጠጉ ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ አድርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ 70ዎቹ የቀድሞ ታሳሪዎች ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ 32ቱ ሴት የቀድሞ እስረኞች ናቸው፡፡ቀሪዎቹ የታሳሪ ቤተሰቦች፣የመንግስት ባለስልጣናት፣የቀድሞ ልዩ ሃይል አባላት ፣የክልሉ የፀጥታ እና ደህንነት ሰራተኞች ናቸው፡፡

በሪፖርቱ እያንዳንዱ መስመር ሲታለፍ ለሃገር አለማዘን አይቻልም፡፡ምልባትም “እንዲህ ባለ ሃገር ለምን ተፈጠርኩ?” ሊያሰኝም ይችላል፡፡ምንም አይነት የሰው ልጅ ጥፋት እንዲህ ያለ ቅጣት አይገባውም፡፡የቅጣቱ ሁሉ መንስኤ ያልተረጋገጠው ኦብነግን የመደገፍ ጥርጣሬ መሆኑ ደግሞ እጅግ ያሳዝናል፡፡”ቀለል” ካለው ቅጣት ቢጀመር የእስረኛው ብዛት ያመጣው መተፋፈግ እንቅልፍ ለመተኛት ወረፋ ያስጠብቃል፡፡ ወረፋ ደርሶት የተኛ እስረኛ በተኛበት መገላበጥ ካሰኘው ጎረቤቱን ቀስቅሶ አስቁሞ ነው መገላበጥ የሚችለው፡፡

በዚህ መተፋፈግ ውስጥ ሲደበደብ የቆስለው፣ደሙን እያዘራ የመጣ ትኩስ ተደብዳቢ ሁሉ ከቁስሉ የሚወጣውን ፈሳሽ እየተጋራ ይተኛል፡፡በዚህ ሳቢያ የሚመጣውን የጤና ጠንቅ ለማሰብ ዛሬን ስለማደር እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡በዚሁ መተፋፈግ እና የውሃ እጥረት ሳቢያ በእስርቤቱ ውስጥ ተላላፊ በሽታ ይነሳልና ሰው ይሞታል፡፡ሰው እንደሞተ ሪፖርት ተደርጎም ወዲያው ሬሳ የሚያነሳ ባለመኖሩ በዛ በተፋፈገ ሁኔታ  ከሞተ ሬሳ ጋር ቀናትን ማሳለፋቸውን፣ በሞተው በድን ሽታ መሰቃየታቸውን  የሪፖርቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡በህመም፣በበዛ ቶርቼር ወይም በርሃብ የሞተ ሰው አስከሬን “ምልክት እንኳን በሌለው ቦታ እዛው እስርቤቱ ጓሮ ይቀበራል አለያም በጅጅጋ ከተማ ዳርቻ ተጥሎ በጅብ እና በጥንብ አንሳ ይበላል” ሲል የቀድሞ ልዩ ሃይል አባል የነበረ ሰው ለ”Human Rights Watch” ተናግሯል፡፡

ረሃብ ሌለው “ቀለል” ያለ ቅጣት ነው፡፡መፈጠርን በሚያስረግም ድብደባ የሚሰቃዩት በቀን አንድ ዳቦ ወይም አንድ እንጀራ ለአራት በልተው ነው፡፡ከነአካቴው ምግብ የማይገኝበትም ሁኔታ አለ፡፡ አስርቦ መደብደቡ ድብደባውን ይበልጥ አስከፊ ለማድረግ ነው፡፡እየተደበደቡ ባሉበት የሞቱ እስረኞችን እንዳዩ የሪፖሪቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡መጥቀስ ይኑርብኝ አይኑርብኝ ከራሴ ጋር ሙግት ብገጥምም አስከፊነቱ ስላሸነፈኝ የምጠቅሰው ነገር ከርሃቡ ጥናት የተነሳ በህመም ምክንያት የወደላይ ያለው እስረኛ ያወጣውን ምግብ አንስቶ የበላ ሰው እንዳዩ የዓይን ምስክሮች መናገራቸውን ነው፡፡ይህን ሳነብ ዞሮብኛል! ሃገሬን ልጠላ ሞክሮኛል፡፡

በጣም የሚገርመው እስረኞቹ እንዲህ ባለ ርሃብ የሚሰቃዩት ቤተሰቦቻቸው ምግብ እያመላለሱ መሆኑ ነው፡፡ ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ ጄል ኦጋዴን የገባ እስረኛ በቤተሰብ አይጠየቅም፤ቤተሰብ ምግብ ለጠባቂዎች አስረክቦ ወደቤቱ ይሄዳል፡፡የእስርቤቱ ጠባቂዎች ታዲያ የእስረኞቹ ቤተሰቦች የሚያመጡትን ምግብ ለራሳቸው እየተመገቡ፤የእስረኛ ቤተሰቦች ደግሞ ምግቡ ለታሳሪ ዘመዶቻቸው የሚደርስ እየመሰላቸው ሲያመላልሱ ኖረዋል፡፡ይሄ ተራ ወራዳ ነገር የሚደረገው በመንግስታዊ አካል ያውም ከህግ አስከባሪው ክንፍ መሆኑ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡

ሴት ልጅ የምታስተናግደው ውርደት፣ የሚደርስባት አረመኔያዊ ድርጊት እጅግ ዘግናኝ ነው፡፡ባለ ትዳር ሴት እስር ቤት ገብታ በልዩ ሃይል ተደፍራ የማታውቀውን አረመኔ አባት ልጅ ትታቀፋለች፡፡ እዛው እስር ቤት የሚወልዱ ሴቶች ያለ ህክምና ባለሙያ ድጋፍ፣ንፅህና በማይታሰብበበት በታሰሩበት ክፍል ወለል ላይ ይወልዳሉ፡፡ ለወሊድ እያማጡ የሚያልፉ፣ከወለዱ በኋላ ቅፅበት ሳይቆዩ ከነልጆቻቸው የሚሞቱም እንዳሉ ሪፖርቱ የአይን ምስክሮችን ጠቅሶ ያትታል፡፡በፈጣሪ ተአምር እና በእስርቤት ጓዶቻቸው እርዳታ አምጦ መውለዱ የሰመረላቸው ደግሞ የልጃቸውን እትብት የሚቆረጥበት ምላጭ እንኳን አያገኙና የእስርቤት ጓዶቻቸው ከሆነ ስርቻ የብረት ቁራጭ መሳይ ፈልገው ያትቡላቸዋል፡፡ በዚህ መልክ ወልደው የሚያጠቡ ሴቶች ተጨማሪ ምግብ ማግኘታቸው የሚታሰብ አይደለም፤ጭራሽ በረሃብ ሊሞቱም ይችላሉ፡፡

ሴት እስረኞች ጣራ ላይ በታሰረ ገመድ ላይ ራቁታቸውን ተሰቅለው ከስር በኤሌክትሪክ ገመድ ይገረፋሉ፣ ባለ ፍም ትኩስ አመድ ላይ ከነልብሳቸው ይንከባለላሉ፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ትርኳሽ እሳት ባለው ፍልጥ ይደበደባሉ፡፡ አንዷ ተሳታፊ እንደውም “አመድ ላይ የተንከባለልኩበትን ቀሚሴን አብዲ ኢሌ ሲከሰስ ማስረጃ ለማድረግ ከነቀዳዳው አስቀምጨዋለሁ” ስልትል ለ”Human Rights Watch” ተናግራለች፡፡ በፈለጉት ሰዓት የእስርቤቱ ሰራተኞች ወስደው ሴት ልጅን ይደፍራሉ፡፡  በእስርቤቱ መደፈር እምብዛም የማያስደንቅ የተለመደ ነገር ነው፡፡”በየጥጋጥጉ የሚደፈሩ ሴቶች ሲቃ መስማት የተለመደ ነው” ይላል ሌላው ተሳታፊ፡፡ ከጄል ኦጋዴን ውጭ መሆንም ላለመደፈር መድህን አይደለም፡፡ በአብዲ ኢሌ ግዛት በቀን በብርሃን ሃገር ሰላም ብላ የምትንቀሳቀስ ሴት በጋጠ-ወጥ ወታደር ትደፈራለች፡፡

ይህ አልበቃ ብሎ የክልሉ ባለስልጣናት ሴት እስረኞችን ቆንጠር አድርገው እንዲያመጡላቸው ያዛሉ፡፡ የእስርቤቱ ጠባቂዎች ከእስርቤቱ ውጭ ራቅ ወዳለ ቦታ ሴቶቹን እየነዱ ለባለስልጣናቱ ይወስዱላቸዋል፡፡ “የት ነው የምሄደው? ብሎ መጠየቅ አይቻልም፡፡ ከጠየቅን እንደፈለግን የምናደርጋችሁ አህዮቻችን ናችሁ፤ ፈጣሪም ቢሆን ከእኛ እጅ አያድናችሁም ይሉናል፡፡ስለዚህ የሚወስዱን ቦታ ዝም ብሎ ከመወሰድ፤ የሚያደርጉትን ዝም ብሎ ከመቀበል ውጭ አማራጭ የለም” ትላለች አንድ የሪፖርቱ ተሳታፊ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ነገር ከእነዚህ ሴቶች ውስጥ ግፉ ከተፈፀመባቸው በኋላ እንኳን ወደ እስር ቤቱ የማይመለሱት የሚበዙ መሆኑ ነው፡፡

የሚመለሱት ትቂቶች ደግሞ ማታ ተወስደው በማግስቱ ማታ ልብሳቸው እላያቸው ላይ ተበጣጥሶ እያለቀሱ እና እየተንቀጠቀጡ ይመለሳሉ፡፡  በዚህ መንገድ ሴት ልጅ ላይ ግፍ የሚፈፀሙ የክልሉ ባለስልጣናት ያደረጉትን ካደረጉ በኋላ “ድርጊቱን የፈፀምኩት ለራስሽ ብየ አዝኜልሽ ነው” ሲሉ እንደሚያፌዙ እማኞቹ ይናገራሉ፡፡ በዚህ መልክ የተመለሱ ሴቶችን ያዩ ሌሎች ሴቶች ደግሞ “የእኔ ተራ ደግሞ መቸ ይሆን?” በሚል ስጋት ይረበሻሉ፡፡

ሴት እስረኞችን አስገድዶ መድፈሩ ከእስርቤት ሰራተኞች እና የክልሉ ባስልጣናት በተጨማሪ በወንድ እስረኞችም እንዲፈፀም ይገደዳሉ፡፡ ሴቶችን በማታ ከክፍላቸው አውጥቶ ወስዶ ጨለማውስጥ አቁሞ ወንድ እስረኛንም እንዲሁ ከክፍሉ አውጥቶ አፉ ውስጥ ሽጉጥ ደግነው “ኦብነግ እያለህ ስታደርግ እንደነበረው ይህችን ሴት ድፈር” ተብሎ ታዞ እንደሚያውቅ አንድ ምስክር ይናገራል፡፡ “ይህን አላደርግም በማለቴ ራሴን እስክስት በፌሮ ደብድበው፣ በወደቅኩብ በላየ ላይ ተረማምደው ሄዱብኝ” ይላል፡፡

ወንድ እና ሴት እስረኞችን በረድፍ አሰልፎ፣ልብሳቸውን አስወልቆ እርስ በርስ እንዲተያዩ፣ወንድ እስረኞች ብልት ላይ አሸዋ የተሞላበት ሁለት ሌትር የውሃ ጠርሙስ ተንጠልጥሎ በሴቶቹ ፊት በክፍሉ ውስጥ እንዲራመዱ ማስገደድ፣ሴት እስረኞች እርቃናቸውን በክፍሉ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ አድርጎ እየተከተሉ መደብደብን ጨምሮ እጅግ ዘግናኝ እና አዋራጅ ቃላትን መሰንዘር የሰው ልጅ በረከሰበት ጄል ኦጋዴን የዕለት ተዕለት ልማድ ነው፡፡

ፆታ ባልለየ መልኩ በቡድን ከሚደረገው አሰቃቂ እና አዋራጅ ድርጊት በተጨማሪ ለብቻ በባዶ ቤት ውስጥ በፌሮ ብረት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ፣በፍልጥ እንጨት መደብደብም አለ፤ በድብደባ ብዛት ተጥሎ በሚደበደብበት መሬት ላይ ሞቶ የሚቀረው ብዙ ነው፡፡  በድብደባው ሰዓት ስቃዩን ለማባባስ ቀዝቃዛ ውሃ ገላ ላይ ይደፋል፡፡የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ በኤሌክትሪክ ገመድ ይጠበሳል፡፡ በብልት ላይ በሚደረግ ቶርቼር ሳቢያ ሽንታቸውን መቆጣጠር የማይችሉ፣ በማያባራ ህመም የሚሰቃዩ እንዳሉ ሪፖርቱ ዘግቧል፡፡ መቀመጠም መተኛትም በማይቻልበት፣ ቁምሳጥን መሰል በተለምዶ ስምንት እና ሶስት ቁጥር በመባል በሚታወቀው ጨለማ ክፍል ለብቻ መታሰርም ሌላው አሰቃቂ ቶርቸር ነው፡፡  በዚህ ክፍል የሚታሰሩ እስረኞች ከጨለማው ክብደት የተነሳ ቀን ይሁን ማታ አያውቁም፡፡

እንዲህ በጄል ኦጋዴን ከተሰቃዩ እስረኞች ውስጥ ለልዩ ሃይል አባልነት የመልመል እድል እንደሚሰጣቸው አንድ እማኝ ለ”Human Rights Watch” ተናግረዋል፡፡ ብዙ አሳር ያዩ እስረኞች ከመከራቸው ለመገላገል የቀረበላቸውን የልዩ ሃይሉ አባልነት ዕድል በደስታ ይቀበላሉ፡፡  ከእስረኝነት ቀጥታ የልዩ ሃይል አባል ሲደረጉ የአንድ ቀን ስልጠና እንኳን ሳያገኙ “ስትደበደብ እንደነበርከው አድርገህ ትደበድባለህ” ተብሎ ተነግሯቸው ብቻ ወደ “ሥራው” ይገባሉ:: ከተጨከነባቸው በላይ ጨክነው እስረኞችን ያሰቃያሉ፡፡

አብዲ ኢሌን ጨምሮ የክልሉ ባለስልጣናት ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ በእስርቤቱ ይገኛሉ፡፡ቁምስቅሉ ለአንድ አፍታ እንዳይስተጓጎል ኮስተር ያለ ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ከአረመኔነቱ ያጓደለ የእስር ቤቱ ሰራተኛ በእስረኞች እግር ገብቶ አበሳ እንዲያይ ያዛሉ፡፡ ሁሉም ራሱን ለማዳን ሲል በአረመኔነቱ ይብሳል፡፡ብበሳምንት ሁለት ቀን የእስረኞች ጉባኤ አለ፡፡ አብዲ ኢሌ፣ የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አብዱረህማን ላባጎ እና ሌሎች ጓዶቻቸው ብዙ ጊዜ በጉባኤው ይገኛሉ፡፡ ጉባኤው ሁለት ጥቅም አለው፡፡ አንደኛ የአብዲ ኢሌ መንግስት እንዴት ደግ እንደ ሆነና ኦብነግ ደግሞ እንዴት ክፉ እንደሆነ ይሰበካል፡፡

ሁለተኛ በከፋ ሁኔታ ጥርስ የተነከሰባቸው እስረኞች በመላው እስረኛ ፊት ወጥተው ይደበደባሉ፣ ይዋረዳሉ፡፡አንድ የሪፖርቱ ተሳፊ እንደተናገረው “አንድ ቀን አንድ እስረኛን ሌሎችን እስረኞሎች አነሳስተሃል ብለው ከመሃላችን አውጥተው ጥለው ሲደበድቡት፣ ድብደባውን መቋቋም አቅቶት ሲሞት ሃያ ሜትር ርቀት ላይ ነበር የተቀመጥኩት፤ ሲሞት ዝም ብዬ ከማየት በቀር የምረዳው ነገር አልነበረም” ይላል፡፡

በእስረኞች የጉባኤ ቶርቼር የሁለቱም ፆታ እስረኞች ይሳተፋሉ፡፡ ሌሎች እስረኞች እንዲፈሩ በሚል ጠንካራ የሚባሉ እስረኞችን ነጥለው አወጥተው ይደበድባሉ፣ ዓይናቸውን ከፍተው አመድ የሚጨምሩባቸው ጊዜም አለ፡፡ በልዩ ሁኔታ ለቅጣት የሚፈለጉ ወንዶች ተመርጠው ይወጡና “ከዚህ ውስጥ ኦብነግ እያለህ የደፈርካትን ሴት ጠቁም” ይባላል፡፡  ከድብደባ ለመዳን ከዚህ በፊት አይቷት እንኳን የማያውቃትን ሴት ይጠቁማል፡፡ የተጠቆመችው ሴት በህዝብ ፊት ትሸማቀቃለች፡፡ በዚህ ግን አያበቃም ኦብነግ እያለህ ከግመል እና ከፍየል ጋር የግብረስጋ ግንኙነት አድርጌያለሁ በል ይባላል ይሄን ከማለት እና በድብደባ ከመሞት ምርጫው የባለቤቱ ነው፡፡ ድብደባ የትም ቦታ በማንኛውም ሰዓት ይፈፀማል፡፡ “በቀን፣ በማታ፣ ለሽንት ተሰልፈህ፣ ለስብሰባ በተጠራህበት፣በማደሪያ ክፍልህ ውስጥ ይደበድቡሃል፤ ሁልጊዜ ድብደባ አለ” ይላል አንድ የሪፖሪቱ ምስክር፡፡

በውሃ ላይ መድፈቅ ሌላው የጄል ኦጋዴን አረመኔያዊ ትዕይንት ነው፡፡የጄል ኦጋዴን የውሃ ላይ ደፈቃ በስፋት እንደሚታወቀው በባልዲ ወይም በበርሚል በተሞላ ውሃ ሳይሆን ወደ አስር የሚጠጉ ሰዎችን በአንዴ በሚያስተናግድ የውሃ ገንዳ ውስጥ ሰዎቹን አቆራኝቶ አስሮ ከወገባቸው በላይ ውሃው ውስጥ በመድፈቅ የሚከናወን ነው፡፡በዚህ የውሃ ደፈቃ ውስጥ ተቆራኝተው ከታሰሩት ውስጥ የተወሰኑት ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ የሞተ ሰው ሰውነት ደግሞ የተቀሩትን ወደውሃው የመጎተት ባህሪ ስላለው መውጣት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ላይ ለቅፅበት ከውሃው አናትን ቀና ለማድረግ መሞከር ሞትን የሚያመጣ ድብደባ ያስከትላል፡፡ በዚህ መልክ ቅጣት ከተደረገባቸው በኋላ የጠጡት ውሃ ከሆዳቸው ወጥቶ የሚተርፉት ትቂቶች ናቸው፡፡

አብዲ ኢሌ ጥብቅና የሚቆምለት ሰው ነው?

በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ይሄን ሁሉ መከራ የሚያወርደውን ስርዓት የሚያጋፍረው የክልሉ ፕሬዚደንት አብዲ ኢሌ ሲሆን የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ወታደራዊ መኮንኖች ደግሞ አብዲ የሚሰራውን አሳዛኝ ድራማ የሚያቀናብሩ ናቸው፡፡በተጨማሪም አብዲ ኢሌ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን ያፈናቀለ፣የክልል አስተዳዳሪነት ቀርቶ የቤተሰብ አስተዳዳሪነት የሚጠጥረው፣ ሃላፊነት የማይሰማው ሰው ነው፡፡ ይህን ሁሉ ያደረውን ሰውየ አዲሱ ጠ/ሚ አብይ አህመድ በትዕግስት ይዘውት ሰንብተዋል፡፡ ስልጣን ላይ በወጡ ማግስት ያቀኑትም ወደዚሁ መከረኛ ክልል ነበር፡፡

አብይ አብዲን ለመክሰስ እና ከሃላፊነቱ ለማንሳት ከበቂ በላይ ምክንያት እና የህዝብ ድጋፍ አላቸው፡፡ከሁሉም በላይ የቆምኩለትን የኦሮሞ ህዝብ አፈናቀልክ ብለው ስልጣን በያዙ ማግስት ከአብዲ ጋር አምባጓሮ መግጠም ይችሉ ነበር፡፡ ሲቀጥልም አብዲ ኢሌ በጄል ኦጋዴን በራሱ ህዝብ ላይ የሚሰራውን ግፍ አብይ የማያውቁ ሆነው ወይም እንደመለስ ዜናዊ በሰዎች ዋይታ የሚደንሱ ሰው ስለሆኑ አብዲን አበጀህ እያሉ አይመስለኝም፡፡ ይህ የሆነው አብይ ዘረኛ እና ችኩል ባለመሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ሰውየ ላይ አብይ ያሳዩት ትዕግስት ሳያስወቅሳቸውም አልቀረም፡፡

በጣም በሚገርም ሁኔታ አብይ የሚወቀሱበትን ትዕግስት ከቁብ ሳይቆጥሩ ወንጀለኝነቱ ሳይበቃው ወጥ ሊረግጥ ያማረውን አብዲ ኢሌን፤ ሃገር ልገንጥል እያለ ጭምር  ለምን አብይ ዝም አላሉትም ብለው የሚተቹ አክቲቪስቶች እየተሰሙ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የእነሱ ሰፈር ሰው አዲስ አበባ ላይ በቋንቋው ሲያወራ አንዳንድ ሰዎች ሊገላምጡት ያሰቡ ይመስለናል ብለው እንደ ተልባ የሚንጫጩ ዘረኞች ናቸው፡፡አብዲ ኢሌን በአይናችሁ አትዩት የሚሉትም ከነጋጠ-ወጥነቱ ስልጣን ላይ ያስቀመጠው መለስ ዜናዊ የእነሱ ሰፈር ሰው ስለሆነ ነው፡፡ ጄል ኦጋዴን ላይ ጥብቅና በሚቆሙለት አብዲ ኢሌ ትዕዛዝ በፌሮ ከሚተለተለው ሰው ቁስል ይልቅ የእነሱ ሰፈር ሰዎች ገና ለገና፣ እንዴው ምናልባት መገላመጥ ከብዶ ይታያቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች እድል ቢያገኙ ጄል ኦጋዴን ወርደው ሰው ጣራ ላይ ሰቅለው በፌሮ እንደማይደበድቡ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

እነዚህን ሰዎች አጥብቆ የሚያሳስባቸው የአብዲን ወንበር ተተግነው ንግዱንም፣ዘረፋውንም ፣ ወንጀሉንም የሚያሳልጡ የሰፈራቸው ሰዎችም ተገናቸውን ስላጡ እንጅ በጄል ኦጋዴን ውስጥም ሆነ ውጭ  የሚንገላታው የኢትዮ-ሶማሌ ክልል ህዝብ ችግር አይደለም፡፡ ዘረኝነት እንዲህ ነው! ራስን ብቻ እንቁ ህዝብ አድርጎ ያሳያል፣ለራስ ጎሳ ብቻ ከልክ ባለፈ ጥንቃቄ ያሰቃያል እንጅ ስለሌላ ህዝብ ከልክ ያለፈ በደል ለማስተዋል ፋታ አይሰጥም፡፡ዘረኝነት ከሰው ተርታ የሚያወርድ ይሉኝታ ቢስነት ነው፡፡

Filed in: Amharic