>

የእብድ ተጫዋች በዝቷል! ሁሉም ተቆጪ፣ ሁሉም ቀጪ ሆኗል!!!!  (መሳይ መኮንን)

የእብድ ተጫዋች በዝቷል! ሁሉም ተቆጪ፣ ሁሉም ቀጪ ሆኗል!!!!
 መሳይ መኮንን
 
* ስለፍትህ ስትጮሁ እድሜአችሁን የጨረሳችሁ ዛሬ በፍትህ ዘመን ፍትህን አትጨፍልቋት። ሰከን እንበል። ስሜታችንን እንቆጣጠረው። የእብድ ገላጋይ አንሁን። ኢትዮጵያ ሽግግር ላይ ናት። ሂደቱን ባናግዘው እንኳን አናደናቅፈው!!!!!
 
 ጥሩ አይደለም። የእብድ ተጫዋች በዝቷል። ሁሉም ተቆጪ፡ ሁሉም ቀጪ ሆኗል። ህገወጥነትን ሲታገል የነበረው ሁሉ ህገወጥ ተግባር በመፈጸም አሳፋሪ ታሪክ እየጻፈ ነው። እዚህም እዚያም ጉልበተኛው ግልገል መንግስት በኪሱ ወሽቆ ማስተዳደር ጀምራል። መንደር ለመንደር የአለቃ ብዛቱ ያስደነግጣል። ያለፍርድ ቤት ውሳኔ የሚቀጣ፡ ያለማስረጃ የሚፈርድ፡ ትላንት ሲያወግዘው የነበረውን ኢሰብዓዊ ተግባር ዛሬ በነጻነት ስም ኢሰብዓዊነትን የሚያራግብ ትውልድ የሀገሪቱን ህልውና እየተፈታተነ ነው።
ስርዓት አልበኝነት የወቅቱ ብርቱ ፈተና ሆኖ ተደቅኗል። የኢትዮጵያ ህዝብ ስርዓት ማፍረስ እንጂ ስርዓት መገንባት አይችልም የሚለው አባባል ምልክቱ እየታየ ነው። በአንዳንድ የሀገሪቱ አከባቢዎች በህዝቡ እየተወሰዱ ያሉት ህገወጥ ተግባራት አደገኛ አዝማሚያ እየተከተልን ለመሆናችን ማሳያ ናቸው። በቶሎ መስመር ካልያዘ ለውጡን የመቀልበስ አቅም ያለው መጥፎ ተግባር ነው። ስሜታዊነት ሀገርን ለአደጋ አጋልጧል። በየመንደሩ የተፈለፈለው የጎበዝ አለቃ አንቀጽ 39ኝን ጠቅሶ ለመገንጠል እየዳዳው ነው። የመንደር ንጉስ በየቦታው አቆጥቁጧል። ፈላጭ ቆራጭ፡ አዛዥ ናዛዡ፡ እንደአሸን ፈልቷል። ወዴት እያመራን ነው?
የሻሸመኔው የዛሬ እርምጃ በጽኑ ሊወገዝ ይገባዋል። ህግና ስርዓት ባለበት ሀገር ራሳቸው መርማሪ፡ ራሳቸው ፈራጅ፡ ራሳቸው ቀጪ የሆኑበት አሰቃቂ ተግባር ተፈጽሟል። በምንም ሚዛን ላይ ቢቀመጥ አሳማኝ እርምጃ አይደለም። የባህርዳሩ የጤፍ እገታም የስርዓት አልበኝነት መገለጫ እንጂ ሌላ ስም የለውም። የሰከነ አካሄድ በሚጠይቅበት ወቅት በስሜት የሚጋልቡ፡ ባልተጣራ መረጃ የሚፈርዱ፡ በግብታዊነት የሰውን ህይወት የሚቀጥፉ ሰዎችን ከጥፋት መስመራቸው እንዲመለሱ መደረግ አለበት። ትላንት ተበድለናል፡ ተገርፈናል ተገድለናል የሚል መፈከር እየያዙ ስርዓት አልበኝነትን ማስፋፋት ለማንም አይበጅም። ከምንም በላይ ሀገር ያጠፋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በእርጋታና በጥሞና የሚመራ የለውጥ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ቤተመንግስት የተቀመጠው አዲሱ አመራር የህዝብ ለመሆኑ ባለፉት አራት ወራት በወሰዳቸው አስደናቂ እርምጃዎች አስመስክሯል። የሚያዳምጥ ስርዓት መጥቷል። ከአፉ ይልቅ ጆሮውን የሚሰጥ አስተዳደር ስልጣን ይዟል። በሁለት እግሩ እስኪቆም መንገዳገዱ አይቀርም። ሀገርና ትውልድ አጥፊ የሆነው የህወሀት አገዛዝ የተከላቸውን መርዛማ ችግኞች ነቅሎ ለማስወገድ የሰከነ አመራር ያስፈልጋል። የዶ/ር አብይ አስተዳደር የመጀመሪያውን ምዕራፍ በድል እያጠናቀቀ ነው። ህወሀት የሚባልን ክፉ አገዛዝ መሰባበርና ከጨዋታ ውጪ ማድረግ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሆኖ እየተሰራበት ነው። ጥሩ መስመር ይዟል። ይህን ተስፋ ሰጪ አስተዳደር ቢያንስ ራስን ከስርዓት አልበኝነት በመቆጠብ ልናግዘው አይገባምን?
ይህ እድል ሊያመልጠን አይገባም። ኢትዮጵያ ለዘመናት ያለመችውን፡ ያማጠችውን ልታየውና ልትገላገለው በዋዜማው ላይ ደርሳለች። መቶ ሺዎች የተሰዉለት፡ ሚሊዮኖች ሀገር ጥለው የተሰደዱበት፡ ከአንድ ክፍለዘመን በላይ የወሰደው እልህ አስጨራሽ ትግል ፍሬ በሚያፈራበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ይህ ሽግግር ፍጹም ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ስሜት ሳይሆን እውቀትና ብልሃት የሚጠይቅ ነው። ይህ እድል ከተጨናገፈ መልሰን ልናገኘው ሌላ አንድ ክፍለዘመን እንደሚወስድብን ጥርጥር የለውም።
እናም ወገን ኳስ በመሬት ይሁን። ዱላ ያነሳችሁ ሁሉ አስቀምጡት። ስለፍትህ ስትጮሁ እድሜአችሁን የጨረሳችሁ ዛሬ በፍትህ ዘመን ፍትህን አትጨፍልቋት። ሰከን እንበል። ስሜታችንን እንቆጣጠረው። የእብድ ገላጋይ አንሁን። ኢትዮጵያ ሽግግር ላይ ናት። ባናግዘው እንኳን አናደናቅፈው!!!!!
Filed in: Amharic