>
4:38 pm - Monday December 3, 5792

የፌደራል መንግሥት በምን ምክንያትና እንዴት ወደ ክልል ይገባል? (ውብሸት ሙላት)

የፌደራል መንግሥት በምን ምክንያትና እንዴት ወደ ክልል ይገባል?
ውብሸት ሙላት
ሰሞኑን ሕዝባዊ አጀንዳ ከሆኑ ጉዳዮች ዋናው በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣በተለይም ጅግጅጋ ከተማ ላይ የተፈጠረው ቀውስና ያስከተለው ጣጣ ነው፡፡ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ቤተክርስቲያናት ተቃጥለዋል፡፡ የግለሰቦችና የመንግሥት ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ይህንን ሁኔታ ማስቆም አልቻለም፤ወይም አልፈለገም፡፡
ይህንን ቀውስ ተከትሎም የክልሉ መንግሥት በ30/10/2010 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊቱ እንዲገባ እና ፀጥታ የማስፈን ሥራ እንዲሠራ የፌደራል መንግሥቱን እንደጠየቀ የመንግሥት ጉዳዮች የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ፣ አቶ አህመድ ሺዴ፣ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል፡፡
ሚኒስትሩ፣ በክልሉ የተፈጠረውን ቀውስ እና የተወሰኑ የክልሉ አመራሮች ቀውሱን በመፍጠር ረገድ የነበራቸውን ድርሻም በጥቅሉ ገልጸዋል፡፡ በዚሁ ሳቢያም የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡ መከላከያ ሠራዊቱም በክልሉ ፀጥታ የማስከበር ተግባር ላይ ተሰማርቷል፡፡
ይህ በመሆኑም የተለያዩ ሰዎችም፣የሕገ መንግሥት ባለሙያዎችም የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል የገባበት ሁኔታን በሚመለከት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ጨምሮ በሌሎችም የተለያዩ፣ አንዳንዶቹም የሚጋጩ፣ አስተያየቶችን በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው በፌደራል ሥርዓት የክልሎችና የፌደራሉ መንግሥት በሕገ መንግሥት ተለይቶ የሚቀመጥ ሥልጣንና ኃላፊነት አላቸው፡፡ የሕገ መንግሥት መኖርም ዋና ጥቅሙ የዜጎችን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ የመንግሥት ተግባርና ኃላፊነት በመወሰን ሥልጣኑን መገደብ ነው፡፡
መንግሥታት የዜጎችን መብት እንዳይጥሱ የመቆጣጠሪያ ልጓም የማበጀት ሚናም ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ተግባርና ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ በመቅረት ወይም በራሳቸው ሕገ መንግሥቱንና ሌሎች ሕጎችን በመጣስ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ መከላከያ ዘዴ፣ ካደረሱም ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር ማስፈን በአገራት ዘንድ የተለመደ ነው፡፡
በፌደራል ሥርዓት የዜጎችን መብት የሚጥሱት ውስጥ የወረዳ፣የዞን፣የክልል፣የፌደራል መንግሥታት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአንዱ እርከን ላይ የሚገኘው መንግሥት በእንደዚህ ዓይነት ድርጊት የተሳተፉ ባለሥልጣን ወይም ሠራተኞች በሚኖሩበት ጊዜ በራሱ ተጠያቂ ማድረግ አለበት፡፡ ካለሆነ ደግሞ ከፍ ያለ እርከን ላይ የሚገኙ መንግሥታት ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ የዜጎች መብት እንዲጠበቅ አጥፊዎች ለፍትሕ አካል እንዲያቀርቡ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አገራችን የፌደራል ሥርዓት መከተል ከጀመረች በኋላም የክልል መንግሥታት በአግባቡ የዜጎችን መብት ሳያስጠብቁም ሳያከብሩም የቀሩባቸው ጊዜያት እንደነበሩ የሚታወቅ ነው፡፡ በክልል ውስጥ የሰብኣዊ መብት ጥሰት እየደረሰ ክልሉ ካላስቆመ የፌደራል መንግሥቱ ሚና ምንድን ነው? በምን ምክንያናትና  አኳኋን የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል በመግባት የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ሊያስጠብቅ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንም ከአደጋ ሊታደግ ይችላል? የሚሉት ጉዳዮች የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ፣የፌደራሉ መንግሥት ወደ ክልል በመግባት የክልል መንግሥትን ሥራ ሊሠራ የሚችልባቸውን ምክንያቶች እና አገባቡንም በሚመለከት በሕገ መንግሥቱ ላይ ሠፍሮ እናገኘዋለን፡፡ በመሆኑም በአራት አኳኋን ወደ ክልል ሊገባ እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡
ከክልል መንግሥታት የመቆጣጠር አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መድፍረስ ሲያጋጥም በክልል መስተዳድር  ጠያቂነት በጠቅላይ ሚኒስትር ትእዛዝ፤
በክልል ውስጥ በሚፈጸም የሰብኣዊ መብት ጥሰት ሲያጋጥም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አነሳሽነት በፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በመሆን ለፌደራል መንግሥቱ እና ለክልሉ ምክር ቤት በሚሰጥ መመሪያ፤
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በክልል ውስጥ ሲከሠት በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ፤
ክልሎች በሚያስተዳድሯቸው ወሰን ውስጥ በፌደራል መንግሥት ማለትም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል ሊገባ ይችላል፡፡
ከላይ የአንድ እስከ አራት በተቀመጠው መሠረት የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል የሚገባባቸውን ሁኔታዎች በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡
ፀጥታ ሲደፍረስ በክልሉ ጥያቄ
በፌደራል ሥርዓት የማእከላዊው መንግሥትም  የክልል መንግሥታትም ሕገ መንግሥት ላይ ተለይቶ የሚቀመጥ ሥልጣን፣ ኃላፊነት እና ተግባር ይኖራቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም በአንቀጽ 51 የፌደራሉ፣ በአንቀጽ 52 ላይ የተገለጹትና ለፌደራሉ መንግሥት ወይም ለፌደራልና ለክልል መንግሥታት በጋራ ሥልጣንነት ያልተሰጡት በሙሉ የክልል እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
 ምናልባት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ቢኖሩና ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ ሕግ ያወጡበት ዘንድ የተፈቀደው ለክልሎች ከሆነ በፌደሬሽን ምክር ቤት  ዉሳኔ ለፌደራል ሊመለስ ይችላል፡፡ በዚህ መሠረት ፌደራልም ክልልም ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንዴ ክልሎች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት እንዳይወጡ መሰናክል የሚሆኑ የሰላም አለመኖር፣የፀጥታ ሁኔታው መበላሸት ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታው በመበላሸቱ ምክንያት የሕዝብ ደኅንነትና ዋስትና አደጋ ውስጥ ሊገባ፣የክልሉ መንግሥትም በራሱ የፖሊስና ሌሎች የፀጥታ ሠራተኞች አማካይነት የሕግ ማስከበር አቅም ካነሰው የፌደራል መንግሥቱ ዕርዳታ እንዲያደርግለት ሊጠይቅ ይችላል፡፡
ይህ ዓይነቱ ቸግር ሊያጋጥም እንደሚችል ሕገ መንግሥቱ አስቀድሞ በመገመት ክልሎች ከፌደራል መንግሥት እርዳታ መጠየቅ የሚችሉበትን አሠራር በአንቀጽ 51(14) አስቀምጧል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት ወደ ክልሉ እንዲገባ የተገለጸው የመከላከያ ሠራዊቱ ነው፡፡
እንደሚታወቀው የመከላከያ ሠራዊት ዐቢይ ተልእኮ አገርን ከውጭ ወራሪና ጠላት መጠበቅ ሉዓላዊነቷን ማስከበር ነው፡፡ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ በአገር ውስጥ የተፈጠረው ሁኔታ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያናጋ፣የሰብኣዊ መብት ክፉኛ ሲጣስ፣ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ሲወደቅ የፀጥታና ሰላም ማስከበር ተግባር ላይ ሊሰማራ ይችላል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ በክልል ላይ የተፈጠረን ችግር ለመቆጣጠር በራሱ በክልሉ መስተዳድር በመጠየቁ ምክንያት የፌደራሉ መንግሥት ትእዛዝ ሲሰጥ ነው፡፡
ከሕገ መንግሥቱ በተጨማሪ በአዋጅ ቁጥር 359/1995፣ ከአንቀጽ ሦስት እስከ ስድስት ድረስ  በክልል ጥያቄ የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል የሚገባበትን ሁኔታ ዘርዘር ባለ መንገድ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች የምናገኛቸውን ቁምነገሮች በአጭሩ እንመልከታቸው፡፡ የፀጥታ መድፈረስ ተከስቷል ለማለት በክልሉ የተፈጠረው ድርጊት የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት የሚያውክ ብሎም በክልሉ ሕግ አስከባሪና የዳኝነት አካላት ሁኔታውን መቅረፍ ሳይችሉ ሲቀሩ ነው፡፡
በራሱ ኃይል ሊቋቋመው የማይችለው የፀጥታ መደፍረስ ያጋጠመው ክልል በሕግ አውጭ ምክር ቤቱ ወይም በከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚው በኩል ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር እርዳታ እና እገዛ ይጠይቃል፡፡ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትርም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳውቃል፡፡
 በየክልል ሕግጋተ መንግሥታቱ ላይ እንደተገለጸው ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ወይም የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ናቸው፡፡
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የሚባለው በርእሰ መስተዳድሩ የሚዋቀር የቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎችም አባላት የሚኖሩት የፌደራሉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አምሳያ ነው፡፡ ከሁለት በአንድኛው በኩል የክልልን የፀጥታ መደፍረስና ከአቅም በላይ መሆኑን ለፌደራል መንግሥት ሊያሳውቁ ይችላሉ፡፡
የክልሉ ርእሰ መስተዳድር በሁኔታው የፌደራል መንግሥትን እገዛ ባይፈልግ እንኳን ካቢኔው ተሰብስቦ በድምጽ ብልጫ ሊወስን ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭም  የክልሉ ምክር ቤትም የመወሰን ሥልጣን እንዳለው አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡
ከክልል ጥያቄው የደረሰው ጠቅላይ ሚኒስትርም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነቱን በመጠቀም የመከላከያ ሠራዊቱን ወደ ጠያቂው ክልል ገብቶ የደፈረሰውን ፀጥታ መልሶ እንዲጠራና እንዲስተካከል የማድረግ ሥልጣን አለው፡፡ እዚህ ላይ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51(14) ላይ ወደ ክልል እንደሚገባ የተገለጸው መከላከያ ሠራዊቱ እንጂ፣የፖሊስ ስም አልተነሳም፡፡ የክልሉን ጥያቄም የሚያቀርበው የክልሉ መስተዳድር (state administration) እንጂ የክልሉ ምክር ቤት አይደልም፡፡
ወደ ክልሉ የገባውን መከላከያም ሆነ ፖሊስ ችግሩን ለመቅረፍ ብቻ ተመጣጣኝ ኃይል ይጠቀማል፡፡ የክልሉ  መንግሥትም አሰፈላጊውን መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ የሚሰማራው ፖሊስም ሆነ መከላከያ ሠራዊት ችግሩን በመፍጠር የተሳተፉ ሰዎችን ለፍትሕ አካላት ለማቅረብ እንዲቻል ሁኔታዎችን የማመቻቸት ኃላፊነትም ተጥሎበታል፡፡
ወደ ክልል የገባው የፌደራል መንግሥት (መከላከያና ፖሊስ) ከክልሉ የሚወጣው አንድም የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ሥር ሲውል፣ካልሆነም  በክልሉ ምክር ቤት ወይም ከፍተኛው የሕግ አስፈጻሚ አካል ተልእኮው እንዲያበቃ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲጠይቁ ነው፡፡
መከላከያ ሠራዊት ወይም የፌደራል ፖሊስ ከላይ በተገለጸው አኳኋን ወደ ክልል ገብቶ ስለነበረውና ስላደረገው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡
እንግዲህ በዚህ መንገድ የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል የሚገባው ክልሉ ከጠየቀ ብቻ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ካልጠየቀ ግን የተፈጠረው የፀጥታ ችግር የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ በመጣል የሰብኣዊ መብት ጥሰት ቢያጋጥም ሌላ ዘዴ መጠቀም ይጠይቃል፡፡
የሰብኣዊ መብት ሲጣስ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አነሳሽነት
ከላይ በክልል መንግሥት ጥያቄ በፌደራል መንግሥቱ የሕግ አስፈጻሚ በኩል የፌደራል መንግሥት የፀጥታ አካላት ወደ ክልል የሚገቡበትን ተመልክተናል፡፡ ይሁን እንጂ በክልሎች ውሥጥ ከፍተኛ የሰብኣዊ መብት ጥሰት ቢፈጸም፣በተለይም የክልሉ መንግሥት ተሳታፊ ከሆነ የፌደራሉ መንግሥት እንዲገባ የመጠየቅ አጋጣሚው አነስተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ የክልል መንግሥት ባይጠይቅም የፌደራል መንግሥት ወደ ክልሎች በመዝለቅ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን የማስቆም፣ለዜጎች ጥበቃ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
ሕገመንግቱ አንቀጽ 13(1) የፌደራሉ መንግሥት የሰብኣዊ መብትን የማክበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ይገልጻል፡፡ የፌደራል መንግሥት በቀጥታ የሚያስተዳድረው ግዛት ስለሌለው፣አዲስ አበባና ድሬዳዋም ቢሆኑ ራሳቸውን የማስተዳደር ሥልጣን ስላላቸው፣የማስከበር ኃላፊነቱ በጥቅሉ በአገሪቱ ላይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ይህንን የሰብኣዊ መብት የማስከበር ኃላፊነትም ቢሆን በሕግ በታወቀ አሠራር ብቻ የሚፈጸም እንጂ የፌደራሉ መንግሥት እንዳሰኘው ክልል ውስጥ መግባት አይችልም፡፡
በክልሎች ውስጥ የሰብኣዊ መብት ጥሰት ከተፈጸመ የፌደራል መንግሥት በቀጥታ ጥሰቱን ማስቆም ከሚችልበት አካሔድ አንዱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 (16) ላይ የተቀመጠው ነው፡፡
በዚህ አንቀጽ መሠረትም በክልል ውስጥ የሰብኣዊ መብት እየተጣሰ ክልሉ ማስቆም ካልቻለ የክልሉ ይሁንታና ፈቃድ ሳያስፈልግ የፌደራል መንግሥቱ በመግባት የማስቆም ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ የአገባቡን ሁኔታም ስንመለከትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ችግሩን እንደተረዳ የፌደሬሽን ምክር ቤትን ለጋራ ስብሰባ በመጥራት  የሰብኣዊ መብት ጥሰቱን ለማስቆም አስፈላጊውን ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ በውሳኔው መሠረት ችግሩ ለተፈጠረበት ክልል ምክር ቤት መመሪያ በመስጠት ሁኔታውን እንዲያስተካክሉ ያደርጋል ፡፡
ይህንን የሕገ መንግሥት አንቀጽ ሥራ ላይ ለማዋል ዘርዘር ያሉ ድንጋጌዎችን ከላይ በጠቀስነው አዋጅ ከአንቀጽ ሰባት እስከ አስራ አንድ ድረስ እናገኛለን፡፡ በእዚህ አዋጅ ከተብራሩት ጉዳዮች አንዱ የፌደራል መንግሥትን ጣልቃ መግባት የሚጠይቅ የሰብኣዊ ጥሰት ተፈጽሟል የሚባለው መቼ ነው የሚለው ነጥብ ነው፡፡ የተጣሱት መብቶች በሕገ መንግሥቱ ወይም በሌሎች ሕግጋት ዕውቅና የተሰጣቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የሚጥሰውም የክልሉ መንግሥት ወይም ሌላ ቡድን ሊሆን ይችላል፡፡ ቁምነገሩ፣በክልሉ ሕግ አስከባሪ እና የዳኝነት አካላት አማካይነት የሰብኣዊ መብት ጥሰቱ ሊገታ ወይም ሊቆም ያለመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት የሰብኣዊ መብት ጥሰቱን ካላስቆመ የፌደራል መንግሥት ወደ ክልሉ በመግባት የማስቆም ኃላፊነት ሊጣልበት ይችላል ማለት ነው፡፡
የሰብኣዊ መብት ጥሰቱን በሚመለከት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰብኣዊ መብት ኮሚሽን፣ ከሕግ አስፈጻሚው ወይም ከሌላ አካል መረጃ እንደደረሰው ወደ ክልሉ በራሱ ያቋቋመውን ቡድን በመላክ መረጃ ማሰባሰብ እንደሚጠበቅበት አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡
አጣሪ ቡድኑ በክልሉ በመገኘት መረጃ አሰባስቦ፣ የችግሩን ምክንያት፣ ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎችን፣ ክልሉ ማሰቆም መቻሉን ወይም አለመቻሉን ክልሉ ችግሩን ለማስቆም ያደረገውን ጥረት ጭምር በማካተት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ በዘገባውም መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደሬሽን ምክር ቤትን ለስብሰባ ጠርቶ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡
የምክር ቤቶቹ ውሳኔና ሊያስተላልፍ የሚችለው መመሪያ ይዘት ለምክር ቤቶቹ የተተወ ሥልጣን ሆኖ የሰብኣዊ መብት ጥሰቱ መቆም እንዳለበት እና ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎች ለፍርድ መቅረብ ያለባቸው መሆኑ የሚቀር አይደለም፡፡ ከዚህ ባለፈ ምክር ቤቶቹ ችግሩን ለማቃለልም ሆነ በዘላቂነት ለመፍታት አስፈላጊ እንደሆነ ያመኑበትን ውሳኔዎች ማሳለፍ ይችላሉ፡፡ የተላለፉት ውሳኔዎች ይፈጸሙ ዘንድ ለፌደራል መንግሥቱ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው ምክር ቤትም መመሪያ ይደርሰዋል ማለት ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ፣ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች እንዲቀጥሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ችግሮችን በሕግ ብቻ ከመፍታት ይልቅ ውስብስብ ወደ ሆኖ የፖለቲካ ሽኩቻና አማራጮች አገሪቱን እንድትገባም የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና በሌሎች ለምሳሌ፣ኦሮሚያ፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝና አማራ ክልልም ላይ የተፈጸሙ የማፈኛቀል ድርጊቶችን በዚህ መልኩ መፍትሔ ለመሥጠት አልሞከረም፡፡ ምክር ቤቱ ራሱ ያወጣውን ሕግ ራሱ አቃልሎታል፡፡
ይህን ባለማድረጉም የክልሉ ሁኔታ ከሰብኣዊ መብት ጥሰት አልፎም የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት እንዲሆኑ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ለችግሮቹ መከሠት የራሱ አስተዋጽኦም ነበረው ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ መንገድ የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል በመዝለቅ የሰብኣዊ መብት ጥሰቱን ለማስቆም የተወሰኑ ጊዜያት (ሳምንታት እና ምናልባትም ወርም) ሊፈጅ ይችላል፡፡ መረጃ ከተሰባሰበ ወይም ከደረሰው በኋላ፣ አጣሪ ኮሚቴ ወደ ቦታው በመላክ መረጃ አሰባስቦ፣ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አድርጎ ከዚያም የፌደሬሽን ምክር ቤት በመጥራት የጋራ ስብሰባ በማድረግ ውሳኔ ለማሳለፍ በሚወስደው ጊዜ መካከል የሰብኣዊ መብት ጥሰቱ ካልቆመ በዚህ አኳኋን በቅርቡ ጅግጅጋ ላይ የተፈጠረው ችግር ዓይነት በፍጥነት ለማስቆም አይችልም፡፡ ስለዚህ ሌላ አማራጭ ዘዴ ያስፈልጋል፡፡
  ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ በፌ/ም/ቤት
ከላይ በተገለጹት ከሁለቱ ምክንያቶች ሌላ የፌደራል መንግሥቱ ወደ ክልል የሚገባበት መንገድም አለ፡፡ እንደውም በዚህ መንገድ ለመግባት በክልሉ የተፈጸመው ወይም በመፈጸም ላይ ያለው ድርጊት ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው ውጭ የሚፈጸሙ ተግባራት በመኖራቸው ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠውን ሥርዓት አደጋ ላይ የጣሉ ሲሆኑ ነው፡፡
ክልላዊ መንግሥታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ከጣሉ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝች በጋራ የሚሳተፉበት ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከመማፍረስ ለመታደግ የፌደራል መንግሥት ወደ ክልሉ በመግባት ሁኔታዎችን እንዲያስተካክል ሊወሰን ይችላል፡፡ ይሄ ዓይነቱን አሠራር ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 62 (9) ላይ በመፍትሔነት አስቀምጦታል፡፡
ከሕገ መንግሥቱ ባለፈም የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው፣ከላይ በገለጽነው፣በአዋጅ ቁጥር 359/1995 ከአንቀጽ አስራ ሁለት ጀምሮ እስከ አስራ ሰባት ድረስ የሚዘልቁ ዝርዝር ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በእነዚህ አንቀጾች የተካተቱት ነጥቦች በርከት ያሉ ስለሆኑ አንኳር አንኳር የሆኑትን ብቻ እንመለከት፡፡
የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ለመግባት ክልሉ በራሱ ተሳትፎ ወይም በሚያውቀው ድርጊት ሕገ መንግሥቱን ባለማክበር በትጥቅ የተደገፈ አመጽ እየተደረገ ከሆነ፣ክልሉ ከሌሎች ብሔሮች ወይም ክልሎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ ሰላማዊ መፍትሔ ካላገኘ፣የፌደራሉን መንግሥት ሰላምና ፀጥታ የሚያናጋ ድርጊት ውስጥ ከተሰማራ ወይም ደግሞ የሰብኣዊ መብት ጥሰት በመፈጸሙ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት የሰጡትን መመሪየ እያከበረ ካልሆነ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ እንደጣለ ይቆጠራል፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን አደጋ ላይ የጣሉትን ሁኔታዎች መከሠታቸውን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች (ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ከሚኒስትሮች ምከር ቤት ወዘተ..) ሊሰበስብ  እንደሚችል  በሕጉ ተገልጿል፡፡
በተለይ ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ፋንታ ችግር የተፈጠረበትን ክልል ሁኔታ ለፌደሬሽን ምክር ቤት በማቅረብ አስወስኖ ጣልቃ በመግባት የአገሪቱ ኅልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመታደግ ሊገባ ይችላል፡፡ ማለትም፣የፌደሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን መርመሮ፣አውጥቶ አውርዶ የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል እንዲገባ ሊያዝ ይችላል፡፡
የፌደራል መንግሥቱ ችግሩ ወደ ተፈጠረበት ክልል በመግባት የተፈጠረውን አደጋ የማስወገድ ተግባር ያከናውናል፡፡ ይህንን ለማድረግም የፌደሬሽን ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ለፌደራል መንግሥቱ ሥልጣን ሊሰጥ፣ክልሉንም ሊነፍግ ይችላል፡፡
 የፌደሬሽን ምክር ቤት የመከላከያ ሠራዊት እና/ወይም የፌደራል ፖሊስ ወደ ክልሉ በመግባት የተፈጠረውን ችግር እንዲያስቆሙ ሊያዝ ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈም፣የክልሉን ሕግ አውጪም ይሁን ሕግ አስፈጻሚ እንዲበተን ወይም እንዲታገድ  የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
ችግር ፈጣሪዎችን ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ ማቅረብ፣ሕጋዊ አሠራር ድጋሚ እንዲሰፍን ማድረግ ተግባርም ይወጣ ዘንድ ግዴታ ሊጣልበት ይችላል፡፡ የፌደራል መንግሥቱም የክልሉን አስተዳደር አፍርሶት ከሆነ ከእንደገና ምርጫ እስኪከናወን ድረስ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር ያደርጋል፡፡ የክልሉ ከፍተኛው የሕግ አስፈጻሚ ተቋም ሊያደርግ የሚችለውን ሁሉ የማከናወን ሥልጣን አለው፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤትም ይህንን ለማከናወን ሁለት ዓመት ጊዜ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማከናወን ይችል ዘንድ ጣልቃ ለገባው ለፌደራል  መንግሥቱ፣ ለስድስት ወራት ያህል ለማራዘም ፌደሬሽን ምክር ቤት ይችላል፡፡
ስለክልሉ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየሦስት ወሩ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ሪፖርት ያቀርባል፡፡ የክልሉን ሕዝብ ጨምሮ ለሌላው መረጃ በየጊዜው የመሥጠት ኃላፊነት በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ተጥሎበታል፡፡
በዚህ መልኩ ወደ ክልል በመግባት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመታደግ የሚፈጀውም ጊዜ እንዲሁ ሊረዝም ይችላል፡፡ በዚህ መካከል ዜጎች ላይ የማይተካ ጉዳት ሊደርስ ይችላል፡፡ የእርስ በርስ ጦርነትም ሊያስከትል ይችላል፡፡ ስለሆነም ይሄም ቢሆን በሌላ አማራጭ ካልታገዘ በስተቀር በፍጥነት ችግር ለመቅረፍ አይመችም፡፡
ከዚህ ባለፈም ለአንዳንድ ክልሎች ይህ አካሔድ መፍትሔ የማያመጣበት አጋጣሚም ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህ በተለይ ለደቡብ ሲሆን አስቸጋሪ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ፡፡ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ብሔረሰቦች  መብዛት የተነሳ በምክር ቤቱ ወደ ግማሽ የሚሆኑት አባላት ከዚህ ክልል የሚመጡ ስለሆነ የፌደራሉ መንግሥት ወደዚህ ክልል ጣልቃ መግባቱን ከተቃወሙ በዚህ መንገድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ መታደግ የማይቻልበት ዕድል ሊኖር ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ለዚህኛውም ቢሆን ሌላ አማራጭ ያስፈልጋል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲወስን
የውጭ ወራሪ ሲያጋጥም፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ እና ሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሠት በአንቀጽ 77(10) እና 93 መሠረት የማወጅ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
ከዚህ ጽሑፍ ጋር በቀጥታ የሚገናኘው ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሲፈጸምና በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት የሚስተካከል በማይሆንበት ጊዜ የፌደራል መንግሥት  ቦታውንና ጊዜውን ወስኖ ወደ ክልል ሊገባ ይችላል፡፡ እንዲገባ መጀመሪያ ላይ የሚወስነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲሆን ውሳኔውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጽደቅ ይጠበቅበታል፡፡
 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራ ላይ ከሆነ በአርባ ሥምንት ሰዓት፣ እረፍት ላይ ከሆነ ግን በአስራ አምስት ቀናት ማጽደቅ ይጠበቅበታል፡፡ ካላጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅነቱ ይቀራል ማለት ነው፡፡
ከእነዚህ ከአራቱ በአንዱ አማካይነት የፌደራል መንግሥት ወደ ክልል ለመግባት የሚችልበት ሕገ መንግሥታዊ ድጋፎች አሉት፡፡ እንደሁኔታው ከአራቱ አንዱ ሊመርጥ ይችላል፡፡ በተለይም የመጀመሪያዎቹ ሦስቱን ለመጠቀም ካልተቻለ ለሁሉም አማራጭ የሚሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው፡፡
ክልሉ የፌደራል መንግሥቱ እንዲገባ ካልጠየቀ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አነሳሽነት የሚወሰነው ጊዜ የሚወስድና የሰብኣዊ መብት ጥሰቱ ከቀጠለ፣ ወይም በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ማሳለፍ የሚያስቸግር ከሆነ አማራጩ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ ነው፡፡
 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው ችግር የተፈጠረበት አካባቢ እንዲሁም ችግሩ እስኪወገድ ድረስ ነው፡፡ ችግር ያልተፈጠረበት አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የአስቸኳይ ጊዜ ሕግን መርሕ ይጥሳል፡፡
በአገሪቱ የሚፈጠሩ የፀጥታ መደፍረስና የሰላም መታጣት፣የሰብኣዊ መብት ጥሰት እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮ ሲፈጠሩ የክልል መንግሥታት፣የሕዝብ ተወካዮች፣የፌደሬሽን እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፡፡
አንዱ አካል መወሰድ የሚገባውን እርምጃ በወቅቱ ባለመውሰዱ ችግሩ እየተባባሰና ሌላ ችግር እያስከተለ የሰብኣዊ መብት ጥሰቱ ይጨምራል፡፡ ግጭት ይፈጠራል፡፡ የአገሪቱ ኅልውና ላይም አደጋ ያንዣብባል፡፡ አቶ አህመድ ሺዴ የዘረዘሯቸው በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈጠሩት ችግሮችም መንስኤያቸውና ያባባሱት ምክንያቶች ምንም ይሁኑ ምን መዘዙ ግን ዜጎችንም አገርንም ጎድቷል፡
Filed in: Amharic