>

ያሬድ ጥበቡ፣ የአራዳ ልጅ ሸገር ላይ ማኪያቶ ሊጠጣ ነው! (ግዛው ለገሰ)

ያሬድ ጥበቡ፣ የአራዳ ልጅ ሸገር ላይ ማኪያቶ ሊጠጣ ነው!
ግዛው ለገሰ
የሀገር፣ የሕዝብ፣ እና የጓደኛ ፍቅርን እንደሱ መግለፅ የሚችል ያለ አይመስለኝም፡፡ ወጥቼ አልወጣሁም መጽሐፉን ማሳተሙ ለትውልድ የሚጠቅም ነው፤ ደግ ነው ያደረገው፡፡ እኛም ያሬድን በብዙ አውዶች ተመልክተነዋል – በመጽሐፉ ምክንያት፡፡
«ቡክ ሪቪው» እጽፋለሁ ብዬ ሦስት አራት ገጽ ማስታወሻ ይዤ እንደቃሌ መሆን አቃተኝ፡፡ ከጊዜ ማጣት ብቻ አይደለም፤ ከቃላት ማጠር ጭምር ነው፡፡ መጣጥፎቹን እያነበብኩ ብዙ ጊዜ አዝኛለሁ፤ አንድ ጊዜ ግን እምባ አውጥቼ አልቅሻለሁ፡፡ ያሬድ ጥበቡ (Yared Tibebu) ለትግል ጓዶቹ ያለው ፍቅር የተለየ ነው፤ እንዴት እንደሚገልፃቸው!
መጽሐፉ ላይ የተካተቱት መጣጥፎች በተለያየ ጊዜ የተከተቡ በመሆናቸው የሀገራችንን የፖለቲካ ሂደት ብቻ ሳይሆን የእርሱንም የምልከታ እና የድምደማ ለውጦች ለማስተዋል ችለናል፡፡ መለስን ሲያደንቀውም ሲያወግዘውም ታነቡታላችሁ፡፡ ህወሓትንም እንዲሁ፡፡ የዚያን ትውልድ ትጋት ነግሮን ሲያበቃ፣ ለዚች ሀገር እንቅፋት ሆኖ እንደነበርም አይደብቅም፡፡ ጥርስ የነቀለበትን ትግል ጥሎ ስለመሄዱ አሳማኝ ምክንያቶችን ከየመጣጥፉ ነቅሰን ሳናበቃ፣ የሆነውን ሆኖ እስከመጨረሻው በውስጥ ቢፋለም ይሻለው እንደነበር አምርሮ ሲቆጭ እናየዋለን፡፡ ፍቅሩ ከሀገር ብቻ ሳይሆን ከጓደኞቹም ጭምር እንደሆነ እንመለከታለን፤ የነሱ መንገድ መሳት እንደራሱ ሀጥያት ያንገበግበዋል፡፡
ሰውየው (Yared Tibebu) ቀና ልብ ከልዩ የፅሁፍ ችሎታ ጋር ስለሰጠው እንዲሁ በፅሁፉ ውስጥ ‘አለቀስኩኝ’ ሲል ያስለቅሳል፡፡ በረከት እና አዲሱ እንዴት በልቡ ነግሰው ነበር? ምን ዓይነት ህይወት፣ ምን ዓይነት ስቃይ ይሆን አብረው ያሳለፉት? ያን ሁሉ ፍቅሩን ስናነብ አሁን ያሉትን ሰዎች አይመስለንም፤ ለነገሩ እሱም የሞታቸውን መርዶ ለራሱም ለኛም ነግሮን በቁም ይቀብራቸዋል፡፡ ምን ተሰምቷቸው ይሆን – እሱን ያነበቡ ለታ?
እኔን የሚገርመኝ በዝች ሀገር ያለው ተስፋ ነው! የትኛውም ፅሁፉ ላይ ተስፋ ሳያጭርብን አያጠናቅቅም፡፡ ተስፋው ከራዕይ የመነጭ ይመስላል፡፡ ይህን ለማለት የሚያበቃን ደግሞ ትንቢተኛነቱ ነው፡፡ በዓለማዊ አገላላፅ፣ በሳል ፖለቲከኛነቱን የሚያመላክት የነገሮችን መሆን አስቀድሞ የሚተነትንበት ልዩ ብቃት አለው፡፡ መጽሐፉን ያነበባችሁ አሁን በሀገራችን እየሆነ ያለው ሁሉ እንዴት እንደተገለፀ አይታችኋል፤ ውስጣዊ ለውጥ፣ የኦነግ መመለስ፣ የሕዝብ እምቢተኝነት፣ የኦሕዴድ እና ብአዴን መንቃት፣ ሌሎችም ክስተቶች በያሬድ ‘ሲመላመቱ’ የቆዩ ናቸው፤ አይቀሬነታቸውን ቀድሞ ተናግሯል፡፡
እናም ዛሬ ከመሸ ወዳጄ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን (Wossen Ayehu) ደውሎ ያሬድ ቅዳሜ ይገባል ሲለኝ ደስ አለኝ፡፡ ለሥልጣንም ሆነ ለፖለቲካው እንደስጋት ስለማይታይ በየድጋፍ ሰልፉ ስሙ አልተነሳ ይሆናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም አሜሪካን ሀገር ሲሄድ እንደያሬድ ጥበቡ ያለ ሰው ቀዳሚ ዒላማው አልነበረም፤ ምክንያቱም እንደሱ ያሉቱ የተደመሩ ቅስቀሳ አያስፈልጋቸውም፡፡ (እኔ ግን በሦስቱም መድረክ ላይ ያሬድን ባለማየቴ ወይም ስሙ ሲጠራ ባለመስማት ከፍቶኝ ነበር፡፡)
ያም ሆነ ይህ፣ ያሬድ የአራዳ ልጅ ሸገር ላይ ማኪያቶ ሊጠጣ ነው፤ ኧረ የምን ማኪያቶ የናፈቀውን የጀበና ቡና ፒያሳ አፋፉ ላይ ቁጭ ብሎ ይጠጣል! ደስታውን ጽፎ እስክናነብ እንጓጓለን፡፡ «ቅዳሜ ጠዋት እሱን ለመቀበል ባይመችህም፣ ቤቱ ድረስ ሄደን እናገኘዋለን» አለኝ ወሰኑ፤ እግዜር ይባርከው!
Filed in: Amharic