>
10:02 pm - Tuesday August 16, 2022

የንግግር ጥሪ!  (ደረጄ ደስታ)

የንግግር ጥሪ! 
ደረጄ ደስታ
አንዳንዶችን ከንግግር የሚያግዳቸው የአቋም ጥያቄና ኮተት ነው። አዎ እውነት ነው አቋም ለፍቅር ነው፤ አቋም ለሚዛን ነው ፤ አቋም ለፍትሕ ነው፤  አቋም ለነጻነት ነው። አቋም ተቃዋሚ ወይም ደጋፊ ሰፈር ውስጥ ጸንቶ መቆም አይደለም። አቋም የመንግሥት ደጋፊ ነቃፊ የመሆን አይደለም። ከሁለቱም የሚነቀፍም የሚደገፍም ነገር አለ!!!
የሰው ልጅ ስለመናገር ነጻነት ለምን ይናገራል? ዝምብሎ ለምን አይናገርም? አትናገር እየተባለ ነዋ!
ግን መናገርን ያልተከለከው ወይም ለመናገር የደፈረው ሲናገርስ ምን እየተናገረ ነው? ደግሞስ መናገርን የተከለክልን ሰዎች የመናገር ነጻነት የተገኘ ቀን ምን እንናገርበታለን? መናገር ያልቻልን ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ አፋችንን ስንከፍት ከአፋችን እሚወጣው ቃል ምን ይሆናል? የመናገር ነጻነት በመናገር ብቻ ይመጣል? ወይስ በመናገር ሳይሆን በመነጋገር ነው እሚመጣው? ዛሬስ እየተናገርን ነው ወይስ እየተነጋገርን?
አዋቂዎች መልሱን እስኪነግሩን ድረስ እኛ እምናውቃትን እየተካፈልን መቆየት የግድ ነው። ወዳጄ ስለተናገርክ ነጻ አልወጣህም። ስላልተናገርክ አልታፈንክም። የመናገርና የመነጋገር ልዩነቱ ገብቶህ ሊሆን ይችላል። አዎ መነጋገር ባንዲት ጀምበር አይመጣም። ሂደቱን ግን በትንሽ በትንሹ መጀመር ይገባል። ሂደትና እድገትም አለው። መነጋገር ሲያስፈልግ ርዕስ ይመረጣል። በሚያግባቡን ነገሮች ላይ ብቻ መነጋገር እንችላለን። በሚያሳስቁን ነገሮች ላይ አብረን መሳቅ ካልቻልን በሚያገዳድሉን ነገሮች ላይ መነጋገር አይታሰብም።
አንዳንዶችን ከንግግር የሚያግዳቸው የአቋም ጥያቄና ኮተት ነው። አዎ እውነት ነው አቋም ለፍቅር ነው፤ አቋም ለሚዛን ነው ፤ አቋም ለፍትሕ ነው፤  አቋም ለነጻነት ነው። አቋም ተቃዋሚ ወይም ደጋፊ ሰፈር ውስጥ ጸንቶ መቆም አይደለም። አቋም የመንግሥት ደጋፊ ነቃፊ የመሆን አይደለም። ከሁለቱም የሚነቀፍም የሚደገፍም ነገር አለ። ወያኔ ጠላት ነው ተቃዋሚ ፍቅር ነው ማለት አቋም አይደለም። ወይም ወያኔን የጠላ ሁሉ የትግራይ ህዝብ ጠላት ኦነግን የጠላ ሁሉ የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ነው ተብሎ እንደሚያዝ የድርጅቶቹና የደጋፊዎቻቸው አቋምም ያለ ዓይነት አተረጋጎምም አይደለም። አድማጭና ተናጋሪ የበሰሉበት ዘመን ሲመጣ ኦሮሞው ወያኔዎቹን ሲተች የትግራይ ህዝብ ያጨበጭባል ወይም ትግሬው ኦነግን ሲተች የኦሮሞው ህዝብ ያጨበጭባል። ወይም በተቃራኒው አንድ ኦሮሞ ስለ ወያኔዎቹ ወይም አንድ የትግራይ ልጅ ስለ ኦነግ ጥሩና ጠንካራ ጎን ቢናገር ባንዳ ከሀዲ ተብሎ አይሰደብም። ኦሮሞ የሆነ ሰው ስለኦሮሞ ጥቅም ማውራት የለበትም ትግራይም አማራም ስለህዝባቸው ጥቅም ቢናገሩ ጠባቦች ናቸው ተብሎ መደምደሙም ይቀራል። ሰዎች ጎሰኛ እባላለሁ ብለው ሳይሰጉ የራሳቸውን ህዝብ ጥቅም እሚያወሩበት ባንዳ እባላለሁ ብለው ሳይሰጉ የራሳቸውን ህዝብ አጠንክረው እሚገስጹበት ዘመን የተባረከ ነው። የነጻነት ብቻ ሳይሆን የብስለትም ዘመን አብሮ ሲመጣ ወልቃይት የትግራይ ነው ብሎ እሚከራከር የአማራ ልጅ ወይም የለም ወልቃይትስ የአማራው ነው ብሎ እሚከራከር የትግራይ ልጅ እስከመስማት ያስኬዳል። ሰዎች እውነትን ከማንነታቸው ሲያስበልጡ ከጨቀዩበት የጎሳና የመንጋ ፖለቲካቸው ነጻ ይወጣሉ።
ግን ይህን ሁሉ ለይቶ ለማውራትና ለመነጋገር ጊዜው ገና ይሆናል። ሀሳቦች በጊዜያቸው ይፈጥናሉ። የሰው ፍላጎት እልፍ ነው። በመሆኑም ወቅቱ የየትኛውን ንግግር እንደሚያስተናግድ አያስታውቅም። ምናልባት መጠበቅ የግድ ነው። ካልሆነ ግን መናገር መብቴ ነው ተብሎ አፍ እንዳመጣ የተከፈተ እንደሁ አደጋና ጦስ አለው። ጦሱን አሁን እያየነው ነው። አንድ የብሔረሰብ ተወካይ ስለሌላው ብሔረሰብ ቢናገር ….ሁሉም እንዳለውና እንደሚስማማበት ተደርጎ ሊታይ ይችላል። አንድ የተረገመ ወፈፌ ከኢንተርኔት ጀርባ ተደብቆ አንድ ነገር ቢል ሌላኛው ወፈፌ ቸኮሎ መልስ ይሰጣል። ሁለቱ ሁለት ግራና ቀኝ ይወልዳሉ። ከዚያም ይቀጥላል። የጥቂት ግራና ቀኝ ወፈፌዎች ሀሳብ የህዝብ ተደርጎ ህዝብን ከህዝብ ሊያጋጭ የሚችል ነገር ይወለዳል። በዚህ የሚጠቀሙ የፖለቲካ ድርጅቶችና መንግሥትም ያተርፋሉ። እሚጯጯኸው መንጋ ግን ይከስራል። በዚህ መካከል እረ ባካችሁ እንነጋገር ማለት እንዲሁ ጮኾ መቅረት ነው። ገና ለገና ሲተያዩ ሊተናነቁ እሚፈላለጉ ሰዎችን እንዲነጋገሩ መጥራት ከነገሮች ሁሉ የከበደ ነው። ቢሆንም እጅና አፍን አጣጥፎ መቀመጥ ግን መፍትሔ አይሆንም። ነገር ሁሉ ለበጎ ነው እንዲሉ አንዳንዴ ቶሎ ለመነጋገር መጣደፍና ሰዎችም እንዲነጋገሩ ማጣደፍ እማይመረጥ ሊሆን ይችላል። እንዲሁ ተነጋገሩ አንድ ሁኑ ተደማመጡ ስለተባለ ብቻ ሰዎች ብድግ ብለው “ነፍሴ እንዴት ነሽ!” አይባባሉም።
ንግግርን ያለርዕሰ ጉዳዩ በራሱ ዝምብሎ መውደድና ማጋነንም ቢሆን መመጻደቅም ነው። ንግግሩ ገልቦ የሚያሳየውንም ገመና ወደራስ ቀልብሶ የሚያሳየውንም የሞራል ጭቅቅት ለማየት መዘጋጀትን ይጠይቃል። እንዲሁ ዝምብሎ በግልጽ እንነጋገር ማለት ሲባል የሚጣፍጥ እንጂ የትም አገር ቀላል ሆኖ ያልታየ ነገር ነው። እርግጥ ነው የንግግር ነጻነቱ ደረጃ ሊለያይ ይችላል። እንዲሁ መበረጋገዱ ግን እያመጣ ያለውን ጦስ የሞከሩት ያውቁታል። ሰዎች እንደቋጥኝ ተሸክመው የኖሩትን እምነት የምትንድ አንዲት ትንሽዬ ሐቅም ሆነ ጥያቄ ብቅ ያለች እንደሁ የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሳ ሊመስላቸው ይችላል። እውነት ተገልጦልኛልና ላንተም ይገለጥልህ ተብሎ የሰው ልጅ ድንገት ልብሱን ከላዩ አይገለጥም። ታሪክ የለበሰ እምነት የተከናነበ በተስፋ የጋለበ ስንት አለ። ሁሉ ነገር ተረት እና የከንቱ ከንቱ ነውና ስለዚህ ሁሉንም ባንዴ እንግፈፍህ አይባልም።
ንግግር ሲታሰብ የሚናገሩት ነገር ጠቃሚነት፣ ወቅታዊነት፣ ቀዳሚነት ብሎም አንገብጋቢነት አብሮ ይታሰባል። የንግግሩ ሁኔታ የአነጋገሩ ድምፀት(ቶን) አውድ (ኮንቴክስት) ሥልጡንነት ቁጥብነት ጥንቁቅነት እኩል ተሰሚነት….አብሮ እየታሰበ ነው። ለዚህ ነው አንዳንዶች ዝም የሚሉት። ከባለጌዎቹ ጋር አብሮ እንባልግ የማይባለው፣ከአፍ ከፋቾች ጋር አብሮ አፍ የማይከፈተው፣ እውነት ስለጎደለ አንደበት ስለተሳሰረ አይደለም። ለባለጌዎቹ ሌሎቹ ባለጌዎቹ እኩዮቻቸው ፈጥነው መልስ ስለሚሰጡም ብቻ አይደለም። ብዙዎቹ የሚናገሩትን ቢሰሙት ምንኛ ሊያሳፍራቸው እንደሚችል ስለማያስቡትም አይደለም። ሰዎች ስለማይቆጡ ስሜታቸው ስለማይነካ ወይም ፍርሃት ሰለገባቸውም አይደለም። ግን አፋቸው ውስጥ ያለውን የመረረ መልስ ያስቡታል። አጸፋቸው ምን ድረስ ሊሄድ እንድሚችል ያውቁታል። የራሳቸውን የነደደ ቁጣ እያሰቡ፣ ራሳቸውን ፈርተው አደብ ገዝተው፣ አካፋን አካፋ ሊሉት እየቃጡ አርፈው የተቀመጡ ብዙ ናቸው። ዝም ማለት ስቃይ ሆኖባቸው ውርጋጦች የሚፈነጩበትን በየመድረኩ የሚወረገረጉበትን ደናቁርት ለደናቁርት የሚደናነቁበትን ፈሪ አጭበርባሪና ቀጣፊዎች የሚጀጋገኑበትን የፖለቲካ ዓለም እያዩ ዳር ሆነው የሚታዘቡ በቁጭት የሚያነቡ አሉ። አለሁ- አለህ- አለሽ- አላችሁ- አለን- ተነሱ!
Filed in: Amharic