>
5:14 pm - Wednesday April 20, 9031

ሺንድለርን አሰብኩት !!! (ሳምሶን ሚሀይሎቪች)

ሺንድለርን አሰብኩት !!!
ሳምሶን ሚሀይሎቪች
ከመንገኝነት ወጣ ብለው የሚያስቡ ክፉ ቀን የመጣ እንደሆነ ምንዱባንን የሚያስጠጉ ይኖሩን ይሆን ብለን ማሰቡ ሟርት መጥራት አይሆንም ! 
 
ማህበራዊ ሚዲያችን በጥላቻና ቁጣ ወሬ ተሞልቷል። ትናንት በደል ሲደርስባቸው የነበሩ ወገኖች ዛሬ ሂሳብ ካላወራረድን እያሉ ይመስላል። ‘ጸጉረ ልውጦችን’ ስማቸውን እየመዘገባችሁ በውስጥ መስመር ላኩልን የሚሉ የጥሪ ጽሁፎችም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። አንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ከትራፊክ ፓሊሶች ባሻገር ህግና ስርዐትን የሚያስከብሩ የፓሊስ አባላት እንደሌሉ ቢኖሩም ጥርስ እንደሌላቸው እየተነገረ ነው። የሰፈር አለቆች የጉልበት ህግ እየገነነ እንደሆነ እየተሰማም ነው። እንደ ስጋቴ አይሁን እንጂ እነዚህ የመንደር ክፉዎች ወደ ‘ጎሳ ሚሊሻ’ ሊቀየሩም ይችሉ ይሆናል። expect the unexpected ነው ነገሩ !
እንደዚህ አይነቱ ‘ጸጉረ ለውጦችን’ የማደን ክፉ ተግባር የተጀመረ እንደሆን ቀን የሚከዳቸውን በጎዶሎ ቀን አጉል ቦታ ( in the wrong place at the wrong time እንዲል ፈረንጅ )ሊገኙ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ሰቆቃ ሳስብ ነው ኦስካር ሺንድለር ወደ አዕምሮዬ የመጣልኝ። ሺንድለርን ያወቅሁት The Scindler List በተሰኘው ፊልም ነው። ሺንድለር የናዚ ፓርቲ አባልና ደጋፊ የነበረ ቢሆንም ወደ ኃላ ከ1200 በላይ አይሁዶችን በፋብሪካው አስጠልሎ ከኦሽዊትዝ የፍጅት መጋዘኖች ህይወታቸውን የታደገ ጀርመናዊ ነው ። ሺንድለር የአይሁዶቹን ህይወት ለመታደግ ዘወትር ይከፍለው በነበረው ጉቦ ሳቢያ ፋብሪካው እስከመክሰር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ሂትለር በተባበሩት ሀይሎች ጦር እስኪሸነፍ በስሩ የነበሩትን ይሁዲዎች ከፍጅት ታድጓቸዋል ። ሺንድለር ለዚህ በጎ ተግባሩ የጀርመንን ትልቁን የሰብዐዊነት ሜዳል የተሸለመ ሲሆን ከፍጅት ያተረፋቸው ይሁዲዎች በቀሩት ዘመናት ይወድቅ ይነሱ የነበሩትን የንግድ ተቋሞቹን እየደጎሙ ማምሻ ዕድሜውን የተረጋጋ እንዲሆን አድርገዋል። የአና ፍራንክ ማስታወሻን ያነበበ Anne Frank እና ቤተሰቦቿን እመስሪያ ቤቷ ቆጥ ላይ ለ 3 ዓመታት ከናዚዎች የደበቀችውን Miep Gies ማስታወሱም አይቀርም። (የእኛይቱ ዓለም ብዙ ደጋጎች እንዳሏት ልብ ይባል )
ለነገሩ አንጽፍ አንመዘግበውም እንጂ እኛም ሀገር በክፉ ቀን ሰብዐዊነታቸው በፈተና ያስመሰከሩ ብዙ ወገኖች ነበሩን። በ5ቱ አመት የጣሊያን ወረራ የራሳቸውን ህይወት አደጋ ላይ ጥለው አርበኞችን የሸሸጉ ፣ ያከሙና ያስጠለሉ በርካታ ስመ ጥሩዎች ነበሩን። ደርግ ፊውዳል ፣ ጸረ አብዮት ወዘተ ሲል የፈረጃቸውን ባሳደደ ሰዐትም እንዲሁ ብዙ አስደናቂ የሰብዐዊነት ስራ ተስርቷል። በዘመነ ወያኔም ብዙዎች የመንደር ጆሮ ጠቢ ሳያሰጋቸው ህወሃት የሚያሳድዳቸውን አስጠልለው ክፉ ቀን ተገፍቷል አልያም የፈለጉትን ወደ ሶስተኛ ሀገር እንዲሸሹ እረድተዋል።
የሺንድለርን ታሪክ ሳነሳ አንተ ደግሞ አጋነንከው የእኛ ፓለቲካና ዘመነ ናዚን ምን አገናኘው የሚሉኝ ይኖራሉ። ትክክል ነው የናዚና ሩዋንዳውን አይነት ዘር ማጥፋት እኛ ሀገር አይፈጸም ይሆናል። ነገር ግን በየጥጋ ጥጉ ብሄርን መሰረት ያደረገ ጥቃት የደረሰ እንደሆነ ለተጠቂዎች ከመንጋው ተለይተው ከለላ የሚሰጡ እንደ ሺንድለር ያሉ ሰዎችን ከወዲሁ ማዘጋጀት ግድ ይላል። አሁን እንደምንታዘበው ‘ተማሩ’ የምንላቸው ሳይቀር ለመንገኛው ህሳቤ ምርኮ ሆነዋል። ሙግታችን የሀሳብ መሆኑ ቀርቶ በብሄርና የተቧደነ ሆኗል። የእኔ ብሄር ያለው የማይመረመር ጥያቄ የማይቀርብበት የእግዜያብሄር ቃል ነው መባል ከተጀመረ ሰነበትን። እናም ከመንገኝነት ወጣ ብለው የሚያስቡ ክፉ ቀን የመጣ እንደሆነ ምንዱባንን የሚያስጠጉ ይኖሩን ይሆን ብለን ማሰቡ ሟርት መጥራት አይሆንም !
Filed in: Amharic