>

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን የዉሸት ወሬዎች እና የማወናበጃ መረጃዎችን በመዋጋት እናግዛቸው! (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን የዉሸት ወሬዎች እና የማወናበጃ መረጃዎችን በመዋጋት እናግዛቸው!
ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
 
ትርጉም በ ነጻነትለሀገሬ 
የጸሀፊው ማስታወሻ፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ቅንነት የሌላቸው እና የተዛቡ ወሬዎች በሶማሊ ክልል ሰብአዊ ቀውስ ላይ ነዳጅ ይጨምራሉ፡፡“
ትላንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ በማለት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን መክረዋል፣ “ቅንነት የሌላቸውን እና የተዛቡ ወሬዎችን በመቀበል አታሰራጩ፡፡ ቅንነት የሌላቸውን እና የተዛቡ ወሬዎችን በፍጹም አናሰራጭ ምክንያቱም በዚሁ ሰበብ በርካታ ሰዎች እየተጎዱ ነው፡፡ የመረጃ እና የወሬ ምንጮችን አስተማማኝነት በሰከነ እና ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ ማገናዘብ አለብን፡፡ ቅንነት የሌላቸውን እና የተዛቡ ወሬዎችን ተቀብሎ እንዳያሰራጭ እያንዳንዱ ሰው ጥንቁቅ እና ንቁ በመሆን የዕለት ከዕለት ህይወቱን እንዲመራ እጠይቃለሁ፡፡“
በጦርነት ጊዜ እውነት የመጀመሪያው የጉዳት ሰለባ ነው፡፡ ይህም እውነት ከሳይበር የመረጃ ጦርነቶች የበለጠ በየትኛውም ቦታ የጉዳት ሰለባ ሊሆን አይችልም፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በተቃራኒው ጎራ በመቆም በኢትዮጵያ ላይ እየመጣ ያለውን ሰላማዊ የለውጥ ማዕበላችንን ለማደናቀፍ እና ወደ ዱሮው የጭቆና፣ የአፈና እና የጨለማ አገዛዛቸው ለመመለስ ሲሉ የማህበራዊ መገናኛዎችን/ሜዲያዎችን በመሳሪያነት፣ በመከፋፈያነት፣ በግድየለሽነት፣ በጎሰኝነት እና በአናሳነት በመጠቀም የሳይበር (ኢንተርኔት) የመረጃ ጦርነቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ የማህበራዊ መገናኛ/ሜዲያ ተዋጊዎች በሙሉ የዉሸት ወሬዎች፣ የተዛቡ የሀሰት መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን ሁሉ በማጋለጥ እና በመዋጋት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጎን በጽናት በመቆም እና በማገዝ ውድ ሀገራችሁን እንድትታደጉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን መንግስት ለመጉዳት፣ ሕጋዊነቱን ለማሳጣት እና በሀገሪቱ ውስጥ ያልተረጋጋ ሁኔታን ለመፍጠር ሲሉ ቅንነት የሌላቸውን ወሬዎች፣ የተዛቡ የሀሰት መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን በመሳሪያነት መጠቀምን ምርጫቸው በማድረግ የስነ ልቦና እና የመረጃ ማዛባትን እኩይ ተግባራት(ጦርነት) እውን ለማድረግ ሌት ከቀን በመዋተት ላይ ይገኛሉ፡፡
ቅንነት የሌላቸውን ወሬዎች የማሰራጨት ዓላማቸው ቀላል እና ግልጽ ነው፡፡ እንዲህ በሚለው የዱሮ አባባል ላይ የተመሰረተ ነው፣ “ውሸት ተደጋግሞ ሲነገር እውነት ይሆናል“ ወይም ደግሞ ማኦ ዜዱንግ በአንድ ወቅት እንዳሉት “አንድ መቶ ጊዜ የተነገረ ውሸት እውነት ይሆናል” እንደማለት ነው፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሳይበር ጦርነት (ማህበራዊ መገናኛ/ሜዲያ) ቋንቋ የዉሸት ወሬዎች “ስሌታዊ ፕሮፓጋንዳ” በመባል ይጠራሉ፡፡
በኢትዮጵያ እና በዲያስፖራው ውስጥ ያሉ የጨለማው ጎን ኃይሎች በትንሹ እንኳ ሲታሰብ የሚያሰራጩት መረጃ ለምንም የማይውል ቆሻሻ መሆኑ ቢታወቅም ነገሮች ሁሉ የበለጠ ታማኝነት ያላቸው በማስመሰል በርካታ የሆኑ መሰረተ ቢስ እና እርባና ቢስ መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡
የጨለማው ጎን ኃይሎች የሀሰት የማወናበጃ መረጃዎችን የማሰራጨት ዘመቻዎችን እያካሄዱ እንዳሉ ቀደም ሲል ጽፊያለሁ፡፡
የሀሰት የማወናበጃ መረጃ ሆን ተብሎ ታስቦበት እና ታቅዶ የሚሰራጭ የውሸት ወይም ደግሞ ትክክለኛ ያልሆነ የተዛባ መረጃ ነው፡፡
የሀሰት የማወናበጃ መረጃ የማሰራጨት ዋና ዓላማው የለየላቸውን ቅጥፈቶች እና ተራ ውሸቶች እውነት እንደሆኑ አድርጎ በማቅረብ ሌሎችን ሰዎች ለማሳመን ነው፡፡ ዓላማውም በሕዝቡ ውስጥ ስጋት፣ ፍርሀት እና  ጭንቀት ለመፍጠር ነው፡፡
የሸፍጥ ህልወት/conspiracy theory በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል በሚል ከንቱ ተስፋ እውነትነት የሌለው ወይም ደግሞ ያልተለመደ እና ልዩ የሆነ በተከታታይነት የሚደረግ ግምታዊ ትንበያ ነው፡፡
ለተጠናከረ የስነ ልቦና እና የሀሰት የማወናበጃ መረጃ ጦርነት ስርጭት ዋና ዒላማዎች እና ሰለባዎች የሚሆኑት ደግሞ ከቴክኖሎጂ ጋር ቅርርብ የሌላቸው ወይሞ ደግሞ የበርካታ መረጃዎች ምንጮች ተደራሽነት የሌላቸው እና መልካም ሀሳብ ያላቸው ተራ ኢትዮጵያውያን እና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደጋፊዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም በእነዚህ ከኢንተርኔት ጋር ግንኙነት የሌላቸውን፣ ከበርካታ የመረጃ ምንጮች ጋር ተደራሽነታቸው በጣም ትንሽ የሆኑ እና በማህበራዊ መገናኛ እና በመረብ ግንኙነት በሚተላለፉ ቆሻሻ ዜናዎች እና እውነትን መሰረት ባደረጉ በጣም ወሳኝ ዘገባዎች መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ያልቻሉትን ወገኖች ዒላማ በማድረግ ቅንነት የሌላቸውን እና የተዛቡ ወሬዎችን፣ የሀሰት የማወናበጃ መረጃዎችን እና የሸፍጥ ህልወቶችን በማሰራጨት እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ይጠቀማሉ፡፡
የኢንተርኔት ጅቦች የሆኑት የጨለማው ጎን ኃይሎች ስለአብይ ደህንነት እና ሰላምነት ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ ሕዝብ በእርሳቸው ላይ ያለውን ከፍተኛ ፍቅር ለማስለወጥ እና ከፍተኛ ከሆነ ስሜታዊነት ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ሌት ከቀን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት ስለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ደህንነት፣ ከእይታ መጥፋት፣ ጤንነት፣ የት እንዳሉ፣ ወዘተ በርካታ ሰዎች እየተገናኙ ጠይቀውኛል፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዩኤስ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ በይፋ አልታዩም፣ እናም ሁሉም የሚጠይቁኝ ሰዎች “የሆነ መጥፎ ነገር አጋጥሟቸዋል” ይላሉ፡፡
ጥቂቶች ደግሞ እንባ አውጥተው አልቅሰዋል፡፡
በእርግጥ እኔ አውነታውን ብቻ ልነግራቸው ችያለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፍጹም በሆነ ደህንነት በጤና በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ወደ አሜሪካ ካደረጉት ፈጣን ጉዞ በኋላ የሚገባቸውን ረፍት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ዕለት በዕለት ይፋ የመንግስት የቢሮ ስራቸውን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ ለመፍታት በመስራት ላይ ናቸው፡፡ እርሳቸው ደህና ናቸው፡፡ አመሰግናለሁ!
 በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በኢትዮጵያ ላይ በየዕለቱ የሚካሄዱትን ቅንነት የሌላቸውን ወሬዎች፣ የሀሰት የማወናበጃ መረጃዎች እና የሸፍጥ ህልወቶች በመዋጋት መልዕክቶችን በማሰራጨት በሚደረገው ዘመቻ እንድትቀላቀሉኝ ሁሉንም የሳይበር ጓደኞቼን፣ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼን ሁሉ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡**
Filed in: Amharic