>
5:16 pm - Sunday May 24, 4798

በሲሳይ አጌና አዘንሁ በያሬድ ጥበቡ አፈርሁ (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

በሲሳይ አጌና አዘንሁ በያሬድ ጥበቡ አፈርሁ

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

(ኮተቤ  ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ)

ሲሳይ አጌና በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱ የተባለ ታላቅ ሰው ነው፡፡ የመረጃ ጥልቀቱ፣ የአጠያየቅ ዘዬው፣ ማስተዋሉ እና ግንዛቤው አጀብ ነው፡፡ ሲሳይ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ‹‹ኢንሳይክሎፔዲያ›› ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ያሬድ ጥበቡም በፖለቲካው ዓለም ያሳለፈው ህይወት ረጅም  እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ እነዚህን ታላላቅ ሰዎች አንቱ ከማለት አንተ ማለቴ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቼን ከማቅረብ እንደሆነ እንዲሰመርበት እፈልጋለሁ፡፡

ሲሳይ አጌና ከአቶ ያሬድ ጥበቡ ጋር ነሀሴ 04/2010 ዓ.ም ያደረገውን ቃለ-ምልልስ አዳምጬ ታላቁ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ረብ በሌለው ጉዳይ ላይ ጊዜውን በማጥፋቱ አዘንኩ፤ በአቶ ያሬድ ጥበቡ መልስና አስተሳሰብ ደግሞ አፈርኩ፡፡

ከአፈርኩባቸዉ ጉዳዮች በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸዉ፡፡ ነገርን ከስሩ ውሀን ከጥሩ እንዲሉ ከመሰረቱ ልጀምር፡፡ በ1960ዎቹ የተጀመረው የተማሪዎች ንቅናቄና የገበሬዎች አመጽ ዋናው ጥያቄ የመደብ ትግል እንጂ የብሔር ትግል አልነበረም፡፡ ይህን በተመለከተ አላን (2002) በ20ኛ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የታየው የተማሪዎች ንቅናቄ መንስኤ የመደብ ግጭት እንጂ በብሔሮች መካከል የሚታይ ግጭት እንዳልነበረ አትታለች፡፡ በቀድሞ በአፄ ኃ/ስላሴ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምሩ የነበሩ በርካታ ምሁራን እንደተናገሩት የተማሪዎችም ሆነ የህዝቡ ጥያቄ የመደብ እንጂ የብሔር አልነበረም (ያንግ፣ 2006)፡፡ በተመሳሳይ፣ ዶ/ር ገብሩ በዶክትሬት ጽሁፋቸው ላይ እንዳተቱት የገበሬዎች አመጽ ዋናው ምክንያት የመደብ ጭቆና እንጂ በሸዋ አማራ ስልጣን በመያዙ አልነበረም (ገብሩ፣ 1977)፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም (2012) በተመሳሳይ ሁኔታ በ1960ዎቹ የነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ የመደብ እንጂ የብሔር ይዘት እንዳልነበረው ገልጸዋል፡፡ አብዛኛው የተማሪዎች ጥያቄ የብሔር ሳይሆን የመደብ ጭቆና ቢሆንም ጥቂት የኤርትራ ነጻነት ግንባርና የሕወኃት የፖለቲካ ልሂቃን  የብሔር ጥያቄዎችን ሲያራግቡ እንደነበር ተዘግቧል(ያንግ፣ 2006)፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ብሔርተኞች የአማራ የበላይነት ለኢትዮጵያ ዋነኛ ችግር አድርገው ይረዱት ስለነበረ ነው (አላን፣ 2002)፡፡

ስለሆነም፣ ሕወኃት በ1968 ዓ.ም ባወጡት ማኔፌስቶ ላይ የትግራይ ህዝብ ለረጅም  ዘመን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቱ ተነፍጎ ሲጠላና ሲናቅ እንዲሁም አድልዎ ሲደረግበት መቆየቱን ገልጸዋል፡ ይህን በደል ጨቋኝዋ የአማራ ብሔር ሆን ብላ እንደመንግስት  መመሪያ አድርጋ ስትሰራበት ቆይታለች(የሕወኃት ማንፌስቶ፣1968)፡፡ ምንም እንኳን የሕወኃት ማኔፌስቶ እንዲህ ቢልም ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቱ የተነፈገው የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ እንጂ የትግራይ ሕዝብ ብቻ አልነበረም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ጭቆናና በደልንም ያደረሰዉ የአማራ ብሔር ሳይሆን የሁሉም ብሔር ገዢ መደቦች ናቸው፡፡የኢትዮጵያን ታሪክ በትክክል ለተረዳ ግለሰብ ሰዎች በብሄር ማንነታቸው አድሎዎ የተደረገባቸው በሕወኃት መራሹ ስርዓት እንጂ ከዚህ በፊት በነበሩት ስርዓቶች አልነበረም፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩት ስርዓቶች የመደብ ጭቆና እንጂ የብሔር ጭቆና እንዳልነበር በርካታ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ((ገብሩ 1977፣ አላን 2002፣ ያንግ 2006፣ ቲዉዶር 1999)፡፡ እውነታው ይሀ ሆኖ እያለ የሕወኃት የፖለቲካን ሊሂቃን በተሳሳተ የታሪክ ግንዛቤ የአማራውን ህዝብ በጥላትነት ፈርጀው የብሔር ድርጅት አቋቋሙ፤ ይህን አስተሳሰባቸውን በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ አሰረጹትና የኢትዮጵያን የመሪዎች  ችግር የብሔር ችግር አድርገው ያቀርቡት ጀመር፡፡ በሂደቱም አማራዉን የጥቃት ኢላማ አድርገውት ኖሩ፡፡

የኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች የቂምን ግንብ ገንብተው፣ በቋንቋ ሀገሪቱን ከፋፍለው፣ አንድነታችንን በትነው በውሸትና በፈጠራ ወሬ በህዝባችን መካከል አለመተማመንን ዘርተው ሀገሪቱን የቁልቁለት ጉዞ ይዘዋት እንደነጎዱ በርካታ ምሁራን  እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ገልጸዋል (አምንስቲ ኢንተርናሽናል 2013/2014፣ ሂውማን ራይትስ ዎች 2013/14/15/16/፣ ትራንስፓራንሲ ኢንተርናሽናል 2014፣ አላን 2002፣ ሙሉቀን 2015፣ በቃሉ 2017፣ አቢንክ 2006 ፣ ቲዉዶር 1999 እና ሌሎችም)፡፡

አቶ ያሬድ ግን ከዚህ እውነታ ባፈነገጠ መልኩ፣ ሕወኃቶች በብልጠትና  በመሰሪነት የጀመሩት ጥያቄ አድጎ ዛሬ አገሪቱን በጎሳ ፖለቲካ ከፋፍሎ እርሰ በእርሳችን እንድንጠራጠር፣ እንዳንተማመን፣ በጎሪጥ እንድንተያይ ሲያደርገን እያየህ አንተ ግን የኢትዮጵያን ቀጣይነት የተረጋገጠው  በሕወኃት መምጣት ነው ብለህ በሚድያ ስትናገር ሰማሁህና አፈርኩብህ ፡፡

የህወኃት መምጣት ሀገሪቱን አፈራረሳት እንጂ አንድ አላደረጋትም፡፡ ህወኃት በጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያን እያፈራረሰ ልትበተን የደረሰችን ሀገር ደረስንላት እያለ የሚያስተጋባውን ወሬ አንተ የእነሱ ልሳን ሆነክ ስትናገር ሰማሁና አፈርሁ፡፡ህወኃት ኢትዮጵያን እያፈረሰ የኢትዮጵያ ባለሟል ለመምሰል የሚደርገውን ጥረት አጋዥ ሆነህ በመገኘትህ አዘንሁ፡፡ አቶ ያሬድ ጥበቡ በፖለቲካው ዓለም በቆየበት ዘመን መጠን የበሰለ አልመሰለኝም፡፡ ይህ ግለሰብ የእኔን እድሜ ያህል በኢትዮጵያ ፖለተካ  ላይ ቆይቷል፤ ዳሩ ግን የሚያስተጋባው የፖለቲካ ዲስኩር የራሱን ሳይሆን የገዢ ጨቋኞቻችንን የሕወኃትን አስተሳሰብ ነው፡፡በዚህ እድሜ ሰው እራሱን መሆን አለመቻሉን ተረዳሁና ገረመኝሁ፡፡ኢትዮጵያ አንተና የህወኃት ጀሌዎች በምታስቡት መጠን የምትፈርስ የእንቧይ ካብ አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ታላቅ ሚስጥር ናቸው ሆኖም ግን አንተ በዚሁ አሁን ባነገብከው አስተሳሰብህ ልትረዳው እንደማትችል አወቅሁ እና  በእውነት አዘንኩኝ፡፡

እነዚህ የዘር ልክፍት ያለባቸው ሰዎች በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሱማሊያ፣ በቤንሻንጉል እና በሌሎችም የአገሪቱ ክልሎች በዜጎች ደም የጨቀዩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአርባ ጉጉ፣ በሀረርጌ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በቤንሻንጉል፣ በወልቃይት፣ በጅጅጋ፣ በሻሸመኔ እና በአብዛኛው የአገሪቱ ክልሎች ላይ በዘር ጥላቻ ከአውሬ በባሰ ጭካኔ የኢትዮጵያዊያንን ደም ያፈሰሱና ያሰደዱ መሆናቸው በበርካታ ተመራማሪዎች ተገል (በቃሉ፣2018፤ ሙሉቀን፣2015፣ ቲዉዶር፣1999)፡፡ ይህ እየታወቀ የነዚህ ሰዎች የጓደኝነት እና የአሲንባ ፍቅራቸው እንዴት ይናፍቃል?  የእነሱ ጨዋታና ፈገግታ ለአንተ ሲናፍቅህ በእነርሱ ትእዛዝ በእነርሱ ሴራና ተንኮል ልጆቻቸው፣ ወላጆቻቸው ቤተሰቦቻቸው በግፍ የተገደሉባቸው ወገኖቻችን ምን ይሰማቸዋል? ለሀያ ሰባት ዓመታት ለተከፈለው መስዋእትነት፣ ለተኖረው የሰቆቃ ህይወት ምክንያት የሆነው የእነዚህ ግለሰቦች ፈገግታ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ልብ እንደሚሰብር ለምን መረዳት ተሳነህ?  ከወንጀለኞች ጋር መተባበር፣ ህብረት መፍጠር ወንጀል እንደሆነ ለመረዳት ምነው አቅም አጣህ? የዜጎቻችን ህመም እና ቁስል፣ ረሀብና ስደት፣ ሀዘንና ሰቆቃ መጋራት አለመቻልህ ከሰውነት ተራ ሊያወጣህ እንደሚችል በዚህ እድሜህ ለመረዳት ምነው ዳገት ሆነብህ?

ሕወኃት ሀገሪቱን እንድትበተን አስቦ በጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ሲከፋፍላት የለውጥ ቡድኑ (ዶ/ር አብይ አህመድ፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አቶ ደመቀ መኮንን እና የለውጡ ቡድን) ልትበተን የተቃረበችውን ሀገር አንድ ሊያደርጓት ሲታትሩ እያየህ አንተ ግን ‹‹ኢትዮጵያን በትነው እንዳይሄዱ ማድረግ የምንችልበትን ሁኔታ ፈጥረናል›› ብለህ ስትናገር ሰማሁህና  ኢትዮጵያን ስለማወቅህ ተጠራጠርሁ፡፡ ለሀያ ሰባት ዓመታት የተዘራውን የመለያየት ዘር ወደ አንድነት ያመጡት እና ጠብን ወደ ፍቅር እየቀየሩት ያሉት እነ ለማ መገርሳ ፣ ዶ/ር አብይ አህመድ እና የለውጡ ቡድን እንጂ ፈገግታቸው የናፈቁህ ወዳጆችህ አይደሉም፡፡ ዳሩ ግን የመንፈሳዊ አስተሳሰብ ብስለት እና የአእምሮ ልእቀት አንደበታችንን ካልገራው ንግግራችን ሰዎችን የሚያሳዝን እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡

በያሬድ ጥበቡ ያዘንኩባቸውን ቅሬታዎቼ  ብዙ ቢሆኑም በዚህ አጭር ጽሁፍ ሁሉን መዘርዘር አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ይህን ቅሬታዬን ስገልፅ ግን የአቶ ያሬድ ጥበቡን ዲሞክራሲያዊ የመናገር መብቱን እየተጋፋሁ አይደለም፡፡ አቶ ያሬድ … መፈለግም መናፈቅም መብቱ ነው፡፡ ሆኖም ግን የአንድን ኢትዮጵያዊ መብት ስንጠብቅ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቁስል፣ ህመም እና ሰቆቃ ልንጠነቀቅለት ይገባል፡፡ ሰው የመሆን ሚስጥሩ የወገንን ስሜት፣ ደህንነት ፣ ችግር እና ህመም መጋራት ነውና፡፡ አቶ ያሬድ ጥበቡ ግዜ ካልውና በጉዳዩ ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ከፈለገ የሚከተሉትን የምርምር ጽሁፎች ማንበብ ይችላል፡፡

References

Aalen Lovise (2002). Ethnic Federation in a Dominant Party State: The Ethiopian Experience 1991-2000

Abbink J(2006). Ethnicity and Conflict Generation in Ethiopia. Journal of Contemporary African Studies

Alemante, G. Selassie 2003. Ethnic federalism: Its promise and pitfalls for Africa. The Yale Journal of International Law, 28 (51), pp. 51–107.

Alemayehu, G. Mariam 2014. Demonizing Ethiopian history. Ethiomedia News, 13 January. Available from: <http://www.ethiomedia.com/index.html> (An African-American news and views website)

Amnesty International 2014/15. The state of the world’s human rights report. Amnesty International Report 2014/15. Available from: <http://www.amnesty.org> [Accessed  12 June 2016].

Assefa, Fiseha 2006. Theory versus practice in the implementation of Ethiopia’s ethnic federalism. In: Turton, David ed. Ethnic federalism: The Ethiopian experience in comparative perspective. Oxford, James Currey. pp. 131–164.

Bahru, Zewde 2002. A history of modern Ethiopia: 1855–1991. Addis Ababa, Addis Ababa University Press. Berman, Bruce 2010. Ethnicity and democracy in Africa. Tokyo, Japan International Cooperation Agency Research Institute.

Bekalu Atnafu Taye (2018). Ethnic Cleansing in Ethiopia: The Canadian Journal of Peace and Conflict     

           Studies. Volume 50, Number 1 (2018): 77-104

Bekalu Atnafu Taye (2017). Ethnic federalism and conflict in Ethiopia. African Journal of Conflict  

           Resolution Volume 17, Number 2, 2017: 41-66

Dickovick, Tyler  2014. Federalism in Africa: Origins, operation and (in)significance. Journal of African Affairs,  24 (5), pp. 553–570.

Ethiopian Human Rights Council 2015b. Stop ethnic cleansing in Ethiopia. Press Release,  16 November, p 4. Freedom on the Net 2013.

Gebru, Tareke 1977. Rural protest in Ethiopia, 1941–1970: A study of three rebellions. Ph.D. dissertation, Syracuse University.

Human Rights from 1992–2015. Addis Ababa, HRC. Ethiopian Human Rights Council 2015a. The situation of Human Rights and Human Rights defenders in Ethiopia. Press Release, 30 June, p 7.

Legesse, Tigabu  2015. Ethnic federalism and conflict in Ethiopia: What lessons can other jurisdictions draw? Africa Journal of International and Comparative Law, 23 (3),  pp. 462–475.

Muluken Tesfaw, “Time of Destruction: Ethnic Cleansing Executed on Amhara People from 1991-2015,”  

           [Amharic Version].

Oakland Institute 2014. Engineering ethnic conflict: The toll of Ethiopia’s Plantation Development on the Suri people. Available from: <http://oaklandinstitute.org info@ oaklandinstitute.org> [Accessed 16 July 2015].

Turton, David 2006. Introduction. In: Turton, David ed. Ethnic federalism: The Ethiopian experience in comparative perspective. Oxford, James Currey. pp. 1–31.

Valfort, Marie-Anne 2007. Containing ethnic conflicts through ethical voting? Evidence from Ethiopia. Available from: <www.hicn.org> [Accessed 10 March 2008].

Vestal, Theodore 1999. Ethiopia: A post-cold war African State. Westport, Greenwood Publishing Group. Watts, Ronald 2008. Comparing federal systems. London, McGill-Queen’s University Press.

Young, John 2006. Peasant revolution in Ethiopia. Cambridge, Cambridge University Press.

Filed in: Amharic