>
4:34 pm - Saturday October 16, 0004

የአጤ ቴዎድሮስ ጠባይ እና  — የጳውሎስ ኞኞ መልዕክት (አሰፋ ሀይሉ)

የአጤ ቴዎድሮስ ጠባይ — እና  — የጳውሎስ ኞኞ መልዕክት
አሰፋ ሀይሉ
 
፩ ፠ ጥቂት ስለ ጳውሎስ ኞኞ
ጳውሎስ ኞኞ ት/ቤት ገብቶ መደበኛ ትምህርት የተማረው እስከ 3ኛ ክፍል ብቻ ነው፡፡ ሶስተኛ ክፍል ብቻ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ የ3ኛ ክፍል ሽፍታ ነው፡፡ ጳውሎስ ኞኞ በራሱ በንባብ፤ በጥናትና ምርምር፤ በህይወት ተሞክሮ፤ እና ከምንም በላይ ደግሞ በሠላ አዕምሮው ጥልቅ ግንዛቤ ራሱን በራሱ ያስተማረበት የትምህርት ደረጃ ሲታይ ደግሞ – ጳውሎስ የ3ኛ ክፍል ተማሪ አልነበረም – የ33ኛ ክፍል የህይወት ዘመን ተማሪ ነው – ተማሪ ማለት እስከ ህይወቱ ፍጻሜ ሌላም ነገር ለመማር፣ ለመጨመር፣ ለማወቅ፣ ለመዳሰስ የሚተጋ – ወደር የሌለው የዕድሜልክ ተማሪ ማለቴ ነው – እና በቃ.. ይገርመኛል – ብቻ ሳይሆን ግርርርርርርም ይለኛል – ታላቁ ኢትዮጵያዊ ምሁር ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ – ሰው ማለት እንደእሱ!!!!
ጳውሎስ ኞኞ ይህን ‹‹አጤ ቴዎድሮስ›› የሚል መጽሐፉን የሚጀምረው እንዲህ በሚል የመቅድም ርዕስ ነው፡-
‹‹ይድረስ ለመጽሐፌ አንባቢዎች
የተላከ ከጳውሎስ ኞኞ
2ኛ ተሰሎንቄ 3፡17››
ከዚያ ጉጉት አደረብኝ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ በመጽሐፉ መግቢያ ርዕስ ላይ ስለምን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማስቀመጥ አስፈለገው? ጥቅሱስ ምን ይል ይሆን? እያልኩ ሳላየው በመሃል ዘንግቼው ተውኩት፡፡ ምናልባት ከ6 ዓመታት በኋላ ይመስለኛል መጽሐፉን በድጋሜ ያገኘሁት፡፡ ሳየው አሁንም ያ ‹‹2ኛ ተሰሎንቄ 3፡17›› የሚል የጳውሎስ ኞኞ የመቅድም ርዕስ አሁንም በዓይኖቼ ላይ ዋለ፡፡ ትዝ አለኝ፡፡ በቸልተኝነቴ ራሴን ወቀስኩ፡፡ ከዚያ አይ ጳውሎስ በህልፈተ-ሕይወትህም ወደቅዱስ መንገድ ትመራኛለህ! እያልኩ እየተገረምኩም.. መጽሐፍ ቅዱሱን መዘዝኩ፡፡ 2ኛ ተሰሎንቄ 3፡17 የሚለውንም ገልጬ ሳነበው እንዲህ ይላል፡-
‹‹በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው፤
የመልእክቴ ሁሉ ማስረጃ ይህ ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ።››
፪ ፠ አሁንም ጥቂት ስለ ጳውሎስ ኞኞ
ጳውሎስ ኞኞ ስለ አፄ ቴዎድሮስ በታሪክ የሚታወቁ የጀግንነት ውሎዎች ብቻ አይደለም የጻፈው፡፡ ስለ አነሣሥ፤ ንግሥና ውድቀታቸው ብቻም አይደለም፡፡ በውጭም ሆነ በኛ ፀሐፊያን ስለ ቴዎድሮስ በተጻፉ ደብዳቤዎችና አስረጅ መዛግብት ላይ ብቻ የሰፈረውንም ብቻ አይደለም ጳውሎስ ኞኞ የጻፈው፡፡
ጳውሎስ ኞኞ አጼ ቴዎድሮስ የተጓዙባቸውን ቦታዎች ሁሉ አስሷል፤ የጦርነት ውሏቸውን ብቻ ሳይሆን በያንዳንዱ ጉዟቸው ባላገር ምን እንዳለ፤ ምን እንደተሰማው ፤ ምን እንደደረሰበት ፤ አዝማሪው ምን ብሎ እንደገጠመ ፤ ተጻራሪዎቻቸው ምን ሁኔታ ላይ እንደነበሩ፤ የወቅቱ የአካባቢው ፖለቲካና የአውሮፓውያን ነገስታትና መልዕክተኞች ምን ያስቡ፤ ምን ያደርጉ፤ እና ምን ይጻጻፉስ እንደነበር፤ የእያንዳንዷን ወንዝና ፈፋ ሳይቀር.. የእያንዳንዷን ሠፈርና መንደርተኛ ሁኔታ ሳይቀር… እንደታሪክ ጸሐፊ ብቻ ሳይሆን.. ልክ እንደ ዘመናዊ የማህበረሰብ ጥናት ተመራማሪ (ሶሺዮሎጂ ሪሰርቸር) ከመቶ ሃምሣ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ሃገራችን – ከመሃል ሃገር እስከ ቀይ ባህር – የነበረውን እያንዳንዱን በጎም ሆነ አስከፊ ሁኔታ በዝርዝር… በሠላ ብዕርና.. በወቅቱ በነበረው አንደበት.. ያሳየናል፤ ያስጎበኘናል፡፡
 የአጤ ቴዎድሮስን ጭካኔ በስጋችን ዘልቆ እንዲሰማን ያሳየናል፤ የአጼ ቴዎድሮስን ደግነት በነፍሳችን ዘልቆ እንዲያረሰርሰን ያደርገናል፤ የአጼ ቴዎድሮስ የሃገር ፍቅርና አርቆ አስተዋይነት በሁለመናችን እንዲሰርጽ ያደርገናል.. ያውም በሚገርም ለዛ!!!  የጳውሎስ ኞኞ የተባ ብዕርና የሰላ አዕምሮ ለወገኑ ያለው ፍቅር ለሰው ልጆች ያለው ጥልቅ መረዳት ሁሉ አስገራሚ ሆኖብኛል፡፡ ይገርመኛል፡፡ በመቅድሙ ላይ ጳውሎስ ስለአጼ ቴዎድሮስ ታላቅ ተግባር የተገነዘበውን መቅድሙን ሲደመድምም እንዲህ በማለት ይጽፋል፡-
‹‹ቴዎድሮስ ብዙ ጊዜ የቀረቡልን ጨካኝና ክፉ ሰው ሆው ነው፡፡ ይህ ባህርያቸው ቢኖርም ቴዎድሮስ ጨካኝ ብቻ ሳይሆኑ ደግና ሩህሩህም ነበሩ ፡፡ አጋጣሚ ክፉ ያደርጋቸዋል ፡፡ አጋጣሚም ደግ ያደርጋቸዋል ፡፡ እነኚህንም ተለዋዋጭ ባህሬአቸውን ለመግለጥ ሞክሬአለሁ ፡፡››
፫ ፠ ተለዋዋጩ የአፄ ቴዎድሮስ ጠባይ
‹‹[…] አጤ ቴዎድሮስ ጠባያቸው ተለዋዋጭ ነበር፡፡ በማያስቆጣ ነገር ይቆጣሉ ፥ ይበሳጫሉ ፥ ይቀጣሉ ፡፡ በሚያስቆጣው ነገር ደግሞ ይስቃሉ ፥ ይምራሉ ፥ ወይም ዝም ይላሉ ፡፡ አለቃ ተክለ ኢየሱስም፡- ‹‹… የአጤ ቴዎድሮስ ነገር ያስቸገረ ነበረ ፡፡ ለምሕረት የተባለው ለመዓት ፥ ለመዓት የተባለው ለምሕረት ይሆን ነበረ›› ብለው ይጽፉና ይህንኑ ሲያብራሩት፡-
 ‹‹አንዱ ያልታሰበ መዓት በመቅደላ የነበረውን እስረኛ ገደል ሲጥል ፥ ክርስቶስ የፈረደበት አንድ መነኩሴ አላገደደው መጥቶ ይህን ታሪክ አይቼ ልሂድ ብሎ በንጉሱ ትይዩ ቆመ ፥ እርሱ ሊመክር አስቦ ነበረ ፡፡ ንጉሱ ግን ተቋጭቷልና እርሱንም አብረህ ጣልልኝ አሉ ፡፡ ደግሞ የተበደለ ሰው ቢጮህለት ፍርድ አዛብቶ ባፉ አረደው ፡፡ የዚህ ጊዜ ሚስቱ ስታለቅስ፡-
‹‹አንተ እየተሟገትህ ዳኛው እያደላ ፥
ባፋረዱህ እንጂ እኔ ምን ልበላ›› አለች ፡፡ […]
[…] አለቃ ወልደ ማርያም ይህንኑ የቴዎድሮስ የጠባይ መለዋወጥ ባጭር ቃል ጽፈው ሲያስረዱ ‹‹… ሰውም ከሰው ተጣልቶ ከቴዎድሮስ መዓት ይጣልህ እያለ ሲረግም ፥ ሲመርቅም ከቴዎድሮስ በረከት ይክፈልህ ይል ነበር…›› ብለዋል ፡፡››
፬ ፠ ሎሌውን የሚታገሰው አጼ ቴዎድሮስ
[…] አለቃ ወልደ ማርያም ስለዚሁ ስለቴዎድሮስ ጠባይ ሲገልጡ ‹‹… በጉዞ ሲሄዱ በጭንቅ ሥፍራ ከመንገድ ላይ ወታደር ከባልደረቦቹ ብቻውን ተለይቶ አንድ ፈረስ ሁለት አህያ ሲነዳ ፈረስ ለብቻ ወደቀ ፡፡ አህያ ጭነቱን ጣለ ፡፡ ይህን ጊዜ ወታደር ለማናቸው ይሁን? ተቸግሮ ጨንቆት ፈጣሪውን ሲያማርር ንጉሱ በኋላው ደርሰው ቢሰሙት፡-
‹‹ለምን ፈጣሪህን ታማርረዋለህ ፡፡ ይህን ንጉስ ግደልልኝ እንዳርፍ ብለህ ለምነው እንጂ!›› አሉት፡፡ እርሱም ሲመልስ፡-
‹‹ጃንሆይ ፥ አልሰማም አለኝ እንጂ እኔስ ሁልጊዜ ለመንሁት›› አለ፡፡ ቴዎድሮስም ‹እውነትህን ነው› ብለው ዝም ብለውት ሔዱ ፡፡….›› በማለት ጽፈዋል፡፡
፭ ፠ ለየዋሁ የዋህ፤ ለምላጩ አቅላጭ 
ስለ ቴዎድሮስ ርህራሄ (ደግነት) ወዳጃቸው የነበረው ዎልድሜየር ሲጽፍ ‹‹[…] አንድ ቀን ከንጉሱ ጋር በጋማ ከብት ተቀምጠን በአገር ውስጥ እንዘዋወር ነበር ፡፡ አንድ ሰው ከመንገዳችን ላይ ቆመና፡- ‹‹ጃንሆይ ጃንሆይ›› እያለ ጮኸ ፡፡ ንጉሱም ‹‹ምን ሆነሃል ተናገር›› አሉት፡፡ ሰውየውም-
 ‹‹ከመንገድ ላይ ሃያ ብር አገኘሁ ፡፡ ይህ ገንዘብ የማን እንደሆነ እኔ አላውቅም ፡፡ በዚህ ምክንያት ገንዘቡን ወደ ጃንሆይ አመጣሁት›› አላቸው ፡፡
ንጉሱም፡- ‹‹ይሄ ያንተ የዋህነት ነው ፡፡ አሁንም ገንዘብ የጠፋው ሰው እስቲገኝ ድረስ ገንዘቡን አንተጋ አስቀምጠው ፡፡ ስላንተ ታማኝነት ግን እኔ ሌላ ሃያ ብር እሰጥሃለሁ›› ብለው ሰጡት፡፡ ሰውየውም እየተደሰተ ሔደ፡፡
ይህን ወሬ አንድ ሌላ ሰው ሰምቶ እንዲህ በቀላሉ ገንዘብ የሚገኝ ከሆነ የቀበርኩትን አርባ ብር አውጥቼ ለንጉሱ ላቅርብ ብሎ ይዞ መጣና፡-
 ‹‹ጃንሆይ ፥ ይሄንን ገንዘብ ከመሬት አገኘሁት ፡፡ የማን ገንዘብ እንደሆነ ስለማላውቅ ወደ እርስዎ አመጣሁት›› አላቸው ፡፡
ንጉሱም የሰውየው አታላይነት ገብቷቸው ‹‹ገንዘቡን ወስደህ ለኔ ገንዘብ ያዥ ስጥ›› አሉት፡፡ ሰውዬውም እያዘነ ገንዘቡን ለንጉሱ ገንዘብ ያዥ አስረክቦ ወደ ቤቱ ሔደ…›› በማለት ጽፏል ፡፡
፮ ፠ ድህነቱን የማይረሳ፤ ለድሃም ክብሩን የሚያስነካ ንጉሥ
ዱፍተን ስለ ቴዎድሮስ አዛኝነት ሲጽፍ ‹‹…. ድሆችን ራሳቸው እየተቆጣጠሩ ይጠብቃሉ ፡፡ ድንኳናቸው በተተከለበት ቦታ ሁሉ የድሆችን አቤቱታ መስማት ይወዳሉ ፡፡ ሁልጊዜ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የድሆችን ጉዳይ ይሰማሉ ፡፡ በጉዞም ላይ በሳምንት በሺህዎች የሚቆጠር ብር ለድሆች ይሰጣሉ ፡፡ ይህንንም ስጦታ በሚሰጡበት ጊዜ ‹‹ድሆችን ባረዳ ለእግዚአብሔር ያሳጡኛል ፡፡ እኔም እራሴ ድሃ ነበርኩ ይላሉ ፡፡ …. ›› ብሏል ፡፡ […]
ይሄው ዎልድሜየር ሲጽፍ ‹‹አንድ ቀን ከንጉሥ ቴዎድሮስ ጋር ስንዘዋወር አንዲት ድሃ ሴት አጋጠመችን ፡፡ ሴትዮዋ ምንም ልብስ ያለበሰች ፈፅማ ራቁትዋን ነበረች ፡፡ ንጉሱ ከበቅሎአቸው ወረዱና የለበሱትን ሸማ ከላያቸው ላይ አንስተው ሴትዮዋን አለበሷት ፡፡ ከዚያም በኋላ ገንዘብ ሊሰጧት ፈልገው ገንዘብ አጡ ፡፡ ወደኔም ዞር ብለው እስቲ ብር እንዳለህ አበድረኝ አሉኝ ፡፡ እኔም ‹እሺ ጃንሆይ ፥ አሁን ለግዜው አምስት ብር አለኝ ፡፡ እሱን ስስጦት› ብዬ ሰጠኋቸው ፡፡ እሳቸውም ገንዘቡን ከኔ ወስደው ለደሃይቱ ሴትዮ ሰጧት ፡፡ ሴትዮዋም ደስ ብሏት ሄደች ፡፡ ማታ በሠፈር ንጉሱ አንድ መቶ ብር ሰጡኝ ፡፡ እኔም ‹ጃንሆይ እኔ የሰጠሆት አምስት ብር ነው ለምን 95 ብር አስበልጠው ይሰጡኛል?› አልኋቸው ፡፡ እሳቸውም ‹የመለስሁልህና የሰጠሁህ እንደ ንጉሥነቴ ነው ፡፡› አሉኝ ፡፡ አመስግኜም እኔም እየተደሰትኩ ወደ ቤቴ ሄድሁ….›› ብሏል ፡፡ […]
፯ ፠ የአበራሽ የብሶት ግጥም — እና — የቴዎድሮስ ቁጣና ምህረት
[…] ደግሞ ያልታሰበ ምሕረት እናት አባትዋ እት ወንድሟ በእሳት ተቃጥለውባት የቆጫት የነደዳት አበራሽ የምትባል ሴት ስታለቅስ፡-
‹‹ሺ ፈረስ በኋላው ፥ ሺ ፈረስ በፊቱ ፥
ሺ ነፍጥ በኋላው ፥ ሺ ነፍጥ በፊቱ ፥
ይህን ሣታይ ሞተች ፥ ኮሶ ሻጭ እናቱ ፡፡
በሸዋ በትግሬ የተቀመጣችሁ ፥
በጎጃም በላስታ የተቀመጣችሁ ፥
አንድ ዛላ በርበሬ ፥ መንቀል ቸግሮአችሁ ፥
በሉ እንዲህ ቆጥቁጦ ፥ ለብልቦ ይፍጃችሁ ፡፡›› ብላ ተሳደበች ፡፡
ይህን ስድብ ንጉሱ በሰማ ጊዜ ፈከረ ፡፡ ካሣ አንድ የናቱ ፡፡ የሀበሻ ባል የኢየሩሳሌም ውሽማ አለና አስመጣት ፡፡ እርስዋም ተጨነቀች ፡፡ ተንቀጠቀጠች ፡፡ ሰዉም ልትቀጣ ነው ብሎ ቁርጥ አወቀ ፡፡ እርስዋ ግን፡-
‹‹አይሰማም ብዬ ፥ እንዴት በጉድ ወጣሁ ፥
መንጠልጠያ ባገኝ ፥ ከሰማይ በወጣሁ ፥
መውረጃውን ባገኝ ፥ ከምድር በገባሁ ፡፡››
እያለች አለቀሰች ፡፡ ምሕረት የታዘዘበት ቀን ሆኖ [ንጉሱ ቴዎድሮስ] ማራት ፡፡ ወዲያው ሸለማት ፡፡ ብርም ባርያም ሰጣት ፡፡ …. በማለት ጽፈዋል ፡፡
፰ ፠ የፕላውዴን ምስክርነት — ስለአፄ ቴዎድሮስ ጠባይ
[…] [የእንግሊዙ ቆንሲል] ፕላውዲን ጁን 25 ቀን 1855 ወደ አገሩ ባስተላለፈው ሪፖርት፡-
‹‹…. ንጉሥ ቴዎድሮስ በዕድሜ ወጣት ናቸው ፡፡ …. ትሁትና ደስተኛ ናቸው ፡፡ የባርያ ንግድን አጥብቀው የሚቃወሙ ናቸው ፡፡ የተሸጡትን ባርያዎች እሳቸው እንደገና የተገዙበትን ዋጋ እየከፈሉ በማስለቀቅ ነፃ ያወጡዋቸዋል ፡፡ …. ወታደሩም ከሚከፈለውና እየሠራ ከሚያገኘው ገቢ በስተቀር ከገበሬው ዘንድ እንዳይደርስ ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥተዋል ፡፡….››
በማለት ለሕዝቡ ያላቸውን ርህራሄ ገልጿል ፡፡
**************
፱ ፠ የዎልድሜየር ምስክርነት — ስለአፄ ቴዎድሮስ
[…] ዎልድ ሜየር ስለ ባርያዎች ጉዳይ በጻፈው በጎንደር አካባቢ ነጋዴዎች የሚወስዷቸውን አስጥለው በብዙ መቶ የሚቆጠሩትን በነፃ ከለቀቁ በኋላ ጥቂቶቹን ለዎልድሜየር ሲልኳቸው በጻፉት ደብዳቤ፡-
‹‹…. እነኚህን ወጣት ልጆች ጥበብና ሃይማኖቶች እንድታስተምራቸው ይሁን ፡፡ እንደእነኚህ ያሉትንም ያልታደሉ ፍጥረቶች ባገኘሁ ጊዜ ሁሉ እልክልሃለሁ ፡፡ ደስ እንዲላቸው ፡፡ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ የምችለው እኔ ነኝ….›› ብለውታል፡፡››
***************
፲ ፠ የጋሼ ጳውሎስ ኞኞ መቅድም የመጨረሻ ቃሎች፡-
‹‹ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ ታሪኩን ሳጠረቃቅም አራት ዓመት ያህል ፈጅቶብኛል ፡፡ ከሚስቴ ከወይዘሮ አዳነች በስተቀር ማንም የረዳኝ ስለሌለ በዚች ቦታ ላይ የማመሰግነው ሰው የለኝም ፡፡›› ካለ በኋላ እንዲህ ብሎ ይሰናበታል፡- ‹‹ደህና እንሁን ብቻ››!!
********************
እኔም ከልቤ ከማከብረው ከጋሼ ጳውሎስ ኞኞ የአራት ዓመታት ጥናት በጣም በጥቂቱ ለፌ(ጦ)ቡክ እንዲሆን መራርጬ ያብኩትን ጥፈት (ወይም ጥፋት) በዚሁ አበቃሁ፡፡ ሳበቃም… ቀደም ሲል ጋሽ ጳውሎስ ኞኞ ከጠቀሰው ከ2ኛ ተሰሎንቄ ምዕራፍ 3፤ ቁጥር 17 ቀጥሎ ባለው ቁጥር 18 ላይ ከቅዱስ መጽሐፉ ባገኘሁት የምዕራፉ መደምደሚያ ጥቅስ ብሰናበትስ? ምናልባትም ጳውሎስ ኞኞ ቁ. 17ን ጠቅሶ… ይህቺኛይቱን የቁ. 18 ጥቅስ በመግቢያው ላይ ያላሰፈራት.. እርሱ የጠቀሰውን የገለጠ ሰው ብቻ ይህቺኛይቱንም በረከት እንደምርቃት ይቋደሣት ብሎ ይሆን?? ነው እንጂ!!! በዚሁ ምርቃት በድጋሚ ተሰናበትኩ፡-
‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፡፡›› (2ኛ ተሰሎንቄ 3፡18)
/ምንጭ ከከበረ ምሥጋና ጋር፡- ጳውሎስ ኞኞ፤ አጤ ቴዎድሮስ፤ ገጽ 128-137፤ የመጀመሪያ እትም በግንቦት ወር 1985 ዓ.ም. ታተመ በአዲስ አበባ፡፡/
Filed in: Amharic