>
5:16 pm - Wednesday May 23, 7460

የብሄር ብሄረሰብ ምሽግ ፈርሶ ግልጽ አደባባይ ይገንባ!! . (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ) 

የብሄር ብሄረሰብ ምሽግ ፈርሶ ግልጽ አደባባይ ይገንባ!!
በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) 
.
‹‹ብሔር-ብሔረሰብ›› የተባለው ምሽግ ተፈጠረ። 
ይህ ምሽግ ጥይት አይበሳውም፤ 
ኒውክለር አይደረምሰውም፤
 የፍትህ ጨረር አይደርስበትም፤
 ሰብአዊና ሀይማኖታዊ ስነምግባር አያናውጠውም፤
 የብሔር-ብሔረሰብ ምሽግ፣ ጥቂቶች ቢሆኑ እንኳ በስሙ ለሚፈጽሙት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ከለላና ሽፋን ይሆናቸዋል፡፡
       ***
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ፣ በምንኖርበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ስልጣኔ ታሪክ ውስጥ የሚፃፍበት ገጽ ከማይገኝላቸው ጥቂት እንስሳዊ ተግባራት አንዱ ነው፡፡ በሊባኖስ ለስልጣንና ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት፣ እናቶችና ህፃናት ሳይቀሩ በህንፃ ፍርስራሽ ውስጥ ከእነ ህይወታቸው ይቀበራሉ፡፡ በናይናማራ ሙስሊሞች እርቃናቸውን እንደ ድንጋይ ተነጥፈው ተሽከርካሪ ይነዳባቸዋል፤ አካላቸው ይቆራረጣል፤ በረሀብ ይቀጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ ዜጎች ከመንገድ ተይዘው ይቃጠላሉ፤ ተዘቅዝቀው ይሰቀላሉ፤ ኮበሌዎች በቢላ ይቆራረጣሉ፤ ሚሊየኖች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ከኖሩበት አካባቢ፣ ንብረታቸው እየተዘረፈ፣ ቤታቸው እየተቃጠለ፣ አካላቸው እየጎደለ ይሰደዳሉ፡፡
የኢትዮጵያውያን ግፍና ኢ-ሰብአዊ ተግባር ከሌሎች በዓለማችን ከሚደረጉት ተመሳሳይ ድርጊቶች የሚለየው ሀገራቱ በአምባገነን መሪዎች የሚመሩና መሪዎቻቸው የድርጊቱ አስፈፃሚዎች ወይም ተባባሪዎች መሆናቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስለ ፍቅርና መደመር የሚዘምር፣ ስለ ዲሞክራሲና ፍትህ መከበር ሙሉ ጊዜውን የሚሰራ፣ ሀገሪቱን ከተዘፈቀችበት የጥፋት መቀመቅ ለማውጣት ቆርጦ የተነሳ መሪ ያላት፣ ግን ደግሞ ያለ መሪ ብቻ ሳይሆን፣ ያለ ህሊና በደመነፍስ ብቻ በዱር የሚኖሩ እንስሶች በዝርያዎቻቸው ላይ የማይፈጽሙት በደል የሚፈጸምባት ሀገር እየሆነች ነው፡፡
.
ይህቺ በሁለት እግር የሚራመዱ ፍጡራን፣ ከእንስሳዊ ደመነፍስ ሚዛን የወረደ ግፍና ጭካኔ የሚፈጽሙባት ኢትዮጵያ፣ ያለፈው ግማሽ ምእተዓመት የደርግ አምባገነንነትና የኢህአዴግ የጎሳ ፖለቲካ ውጤት ናት፡፡ እነዚህ ሁለት አምባገነን መንግስታት ገድለው ይጥሉ – አስረው ያሰቃዩ ነበር። ህዝቡ ደግሞ ሲደፍር ያምጻል፤ ሲፈራ ተደብቆ ያለቅሳል፡፡  በተለይ የሃያ ሰባት ዓመት የኢህአዴግ አምባገነን አገዛዝ፣ ኢትዮጵያውያንን በጎሳ ሸንሽኖ ተፋቅረው እንዳይኖሩ፣ በጥላቻ የክልል ዋሻ ውስጥ ከትቷቸዋል፡፡ ኢህአዴግ የደርግን አምባገነን መሪ በጣለበት ጠመንጃ፣ እኩልነትን፣ የፍትህ ተቋማትን፣ ተጠያቂነትን፣ ሰብአዊነትን፣ ሀይማኖታዊ ስነምግባርን፣ . . .  ሀያ ሰባት ዓመት ጨፍጭፎ፣ በዘመኑ የተወለዱ ወጣቶችን፣ የጎሰኝነት መርዝ ፕሮፓጋንዳ እየጋተ ይህቺን ኢትዮጵያ ፈጥሯል፡፡
.
ጎረቤቱ፣ አብሮ አደጉ ላይ እሳት የሚጭሩ ወጣትና እሳቱን የሚሞቅ ጎልማሳ ተፈጠረ፤ ዜጋን ዘቅዝቆ በአደባባይ የሚሰቅል፣ ሰቅሎ የሚፎክር ወጣት ተፈጠረ፡፡ ‹‹አትገድሉም›› ሳይሆን፣ ‹‹ሬሳውን በመኪና አትጎትቱም›› ብሎ የሚተኩስ ፖሊስ ተፈጠረ፡፡
‹‹ብሔር-ብሔረሰብ›› የተባለው ምሽግ ተፈጠረ። ይህ ምሽግ ጥይት አይበሳውም፤ ኒውክለር አይደረምሰውም፡፡ የፍትህ ጨረር አይደርስበትም፤ ሰብአዊና ሀይማኖታዊ ስነምግባር አያናውጠውም። የብሔር-ብሔረሰብ ምሽግ፣ ጥቂቶች ቢሆኑ እንኳ በስሙ ለሚፈጽሙት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ከለላ ይሆናቸዋል፡፡
.
በቤኒሻንጉል አንድ የ14 ዓመት ልጅ፣ ብልቱ ተቆርጦ፣ ተመትሮ ተገኘ፡፡ መንግስት አሳከመው እንጂ አራጆቹን ለፍትህ አላቀረበም፤ ምክንያቱም ገዳይና ሟች ሰዎች አይደሉም፤ ብሄር ብሔረሰብ ናቸው። ከሱማሌ ኦሮሞዎች ተፈናቀሉ፤ በአዋሳ ወጣቶች – ወጣቶችን በእሳት አነደዱ፤ ጂጂጋ ሱቆች ተቃጠሉ፤ ቤተ ክርስቲያን ከእነ አገልጋዮቿ ተቃጠለች፤ አዳማ . . . ሀረርጌ ፤ ሁሉም የተደረጉት በሰዎች አይደለም፤ ያጠቁትም የተጠቁትም – ሁሉም ሰዎች አይደሉም፤ ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰብ ከሆንክ፣ ህግ አይሰራም፤ ዳኝነት የለም። ዋናው ብሔር ብሔረሰብ መሆን ነው። ብሔር ብሔረሰብ ስትሆን ቀድመህ ከገደልክ፣ ከዘረፍክና ካቃጠልክ፣ የብሄር ብሄረሰብ ምሽግህ ከህግ ይከልልሀል፤ ከተቀደምክና ከተገደልክ፣ ከተዘረፍክ፣ ከተቃጠልክ መንግስት ሁኔታውን ያጠናልሀል፡፡
ኢትዮጵያ ከሶስት ወራት በፊት በአምባገነኑ የኢህአዴግ የአልሞትም መንፈራገጥ ወቅት የነበረችበት አስፈሪ ሁኔታ፣ ዛሬ ካለችበት የተሻለ ነበር፡፡ ያኔ አምባገነኖችን ከስልጣን ለመጣል፣ ያመፀ ህዝብ በአንድ በኩል፣ ስልጣንን የሙጥኝ ያለ፣ ህግን ለስልጣኑ ማራዘሚያ በጭካኔ የሚጠቀም አምባገነን መንግስት በሌላ በኩል ተሰልፈው ነበር፡፡ ዛሬ ህዝባዊው አመጽ፣ አውሬያዊ ጭካኔ በተሞሉ ቡድኖች ተተክቷል፤ አምባገነኑን መሪ የተካው አዲሱ መሪ ደግሞ ህገ መንግስታዊ ጥርሱን፣ እንደ መቶ ዓመት ሽማግሌ፣ ሰው ሰራሽ ጥርስ አውልቆ፣ ስልጣኔና እውቀት ያልገራውን፣ በጎሰኝነት አቅሉን የሳተ አውሬ ሊማርክ ይታገላል። ይህ ሊሆን አይችልም፡፡ መንግስት የህግ ጥርሱን ማሳየት አለበት፤ ያለዚያ እንፈርሳለን፡፡
.
ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ  . . . በደልና የዲሞክራሲ እጦት የወለዳቸው ህዝባዊ አመጾች እንጂ ቡድናዊ ነውጦች (ሞብ) አይደሉም፡፡
 አንባገነንነትን ያንበረከኩትና ፍቅርና መደመርም ያመጡት፣ የህዝብን ጥያቄ ይዘው በየመንገዱ እየተሰዉ፣ በየእስር ቤቱ እየተሰቃዩ እንጂ፣ ዜጎችን እያቃጠሉና እየሰቀሉ አይደለም፡፡ ቄሮ በጠራው ሰላማዊ የቤት መቀመጥ አመጽና የመንገድ መዝጋት ነው አምባገነንነትን ድል ያደረገው፤ የተኛበት በግፍ ተገድሏል፤ ለዚያ እንኳን በበቀል ስሜት አልገደለም – አላቃጠለም – አልሰቀለም፡፡ ታዲያ የትግሉን – የመስዋእትነቱ የመጀመሪያ ፍሬ – ‹‹የቲም ለማን›› የፍቅርና የመደመር መንገድ ላይ የቆመ ቄሮ – ፋኖ – ዘርማ – እንዴት በእድሜያችን ያላየነውን ጭካኔ ይፈጽማል!? አይፈጽምም፤ አልፈጸመምም፡፡ ወንድሙ  ለፍትህና ዲሞክራሲ መስዋእት ሆኖ ከጎኑ ሲወድቅ በቁጭት እየቀበረ ለድል የበቃ ወጣት፣ ወንድሙን ዘቅዝቆ ሊሰቅል – በእሳት ለኩሶ ሊያቃጥል አይችልም፤ ይህን ካደረገ ደግሞ ወንድሙ የተሰዋለትን፣ እሱ የታገለለትን አላማ አያውቅም ማለት ነው፤ ድርጊቱ እየተፈጸመ ያለው የእነሱን ህዝባዊነት እንደ በግ ለምድ ባጠለቁ፣ አውሬያዊ ስብእና ያላቸው ግለሰቦች ባደራጁት ነውጥ (ሞብ) ነው፡፡ የምናያቸው ችግሮች እየተፈጸሙ ያሉት በቄሮ፣ ፋኖና ዘርማ . . . አይደለም፤ እነዚህ የህዝባዊው አመጽ ጠንካራ ክንዶች ናቸው፡፡
.
አሁን ሀገራችን የምትገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ለህዝባዊ አመጽ የሚጋብዙ ምቹ ሁኔታዎች የሉም፤ በአንጻሩ ደግሞ ለነውጥ (ሞብ) ሁሉም ተሟልተው የሚገኙበት፣ እጅግ ምቹ ሁኔታ አለ። አብዛኛው ማህበረሰብ አሁን ባለው የ‹‹ቲም ለማ›› የተሀድሶና የለውጥ አመራር ደስተኛ ነው፤ ይህ በየድጋፍ ሰልፉ ታይቷል፤ ባለፈው ግማሽ ምእተአመት፣ ይህን ያህል ህዝባዊ ተቀባይነት ያለው መሪ አልታየም፡፡ በመሆኑም አሁን የሚታየው ነውጥ፣ ህዝባዊ አመጽ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ አሁን ሀገራችን የምትገኝበት ሁኔታ ቀጥሎ በተዘረዘሩት ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች (ቢያንስ በእኔ ማሰላሰል ነው፤ ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ) የተነሳ ለቡድን ነውጥ ምቹ ነው፡፡
.
የፍትህ ተቋማት አቅመ ቢስነት፤ የኢትዮጵያ የፍትህ ተቋማት፣ በተለይ ፖሊስና ፍርድ ቤት ባለፉት 27 አመታት በደረሰባቸው ጠንካራ የኢህአዴግ አሉታዊ ተጽእኖ የተነሳ፣ አሁን ሙሉ ለሙሉ ‹‹የሉም›› ከሚባልበት ደረጃ ደርሰዋል። የሲቪክ ማህበራት በነጻነት እንዳይሰሩ ተደርጓል። ፖሊስም ሆነ ፍርድ ቤቶች የመንግስት ስልጣንና ጥቅም ማስጠበቂያ መሳሪያዎች በመሆናቸው፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ካድሬዎች፣ የባለስልጣናት ዘመዶች ካልሆኑ በቀር፣ ዜጎች ‹‹ፖሊስ ይጠብቀናል፣ ፍርድ ቤት ፍትህ ያስጠብቅልናል›› ብለው አይተማመኑም። ላለመሰረቅ ሌባን በፖሊስ ማስያዝ ሳይሆን፣ ሌባን ጓደኛ ማድረግን፣ መበደልንና ግፍን በፍርድ ቤቶች ከመዋጋት ይልቅ ተለማምጦና ተሽቆጥቁጦ መኖርን መርጧል። ማህበረሰቡ የፍትህ ተቋማት እንደማይጠብቁት፣ ነውጠኛውም፤ ተቋማቱ መንግስትን እንጂ ህዝብን እንደማይከላከሉ ያውቃል፡፡ በመሆኑም ፖሊስ ከእነ ትጥቁ በቆመበት ዜጎች አሰቃቂ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ይህ የፍትህ ተቋማት አለመኖር፣ በየሰዉ ነፍስ ያለው የአውሬነት ባህርይ ያለ ልጓም  እንዲፈነጭና ከሰብአዊነት እንዲርቅ አድርጎታል፡፡
.
የብሄርብሄረስብ ምሽግ፤ በደርግ ዘመን፣ (እንደ ዘመነ ኢህአዴግ በሰፋና በተንሰራፋ መጠን ባይሆንም) ኢሰፓአኮና ኢሰፓ የግፈኞች ምሽግ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ኢህአዴግ የብሄር ብሄረሰቦች ‹‹ምሽግ›› ከፍትሀዊ ተጠያቂነት የሚያስጥል ምሽግ የለም። በዘመነ ደርግ በኢሰፓአኮና ኢሰፓ ምሽግ ውስጥ ተጠልለው ከፍትህ ለማምለጥ የሚችሉት ጥቂት የፓርቲው አባላትና የአብዮቱ ልጆች ብቻ ነበሩ፡፡ የኢህአዴጉ የብሄር ብሄረሰብ ምሽግ ግን፣ ግፈኝነትን፣ ህገወጥነትንና ኢ-ሰብአዊነትን ያልተጸየፈ ዜጋ ሁሉ ይጠለልበታል። የደርግ ምሽግ ለራሱ ለደርግ መጠለያ የተሰራ ሲሆን፣ የኢህአዴግ ምሽግ ግን ለሌሎች – ግፈኝነትን፣ ህገ-ወጥነትንና ኢ-ሰብአዊነትን ላልተጸየፉ ዜጎች የተሰራ ነው፡፡ ኢህአዴግ ምሽግ አያስፈልገውም፤ የፍትህ ተቋማቱ ይጠብቁታል፡፡ ምሽጉ የተሰራው ዜጎች በስማቸው በተሰራላቸው ምሽግ ገብተው እንዲታኮሱበት ነው፡፡
.
የኢትዮጵያ ህዝቦች ከደርግ ቀድመው በነበሩት ስርአቶች በማንነታቸው ሲያፍሩና ሲሸማቀቁ መኖራቸው ስላንገበገባቸው፤ በ1983 ኢህአዴግ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት ሲያውጅ እያንዳንዱ ብሄረሰብ በየአደባባዩ ወጣ፡፡ ቀስ በቀስ . . ከ27 አመታት በኋላ . . . ዛሬ ያ አደባባይ የግፈኞች መሸሸጊያ ምሽግ ሆነ፡፡ ኢህአዴግ የብሄረሰቦችን መብትና ነጻነት፣ የክልሎችን እድገት ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ማደላደል እንዴት ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ላይ ሳይሆን፣ ‹‹የብሄር ብሄረሰቦችን ፖለቲካ እንዴት አድርጌ በስልጣን ላይ እቆይበታለሁ?›› የሚለው ጥያቄ ላይ አተኩሮ በመስራቱ፣ ለተቃወሙት ጋት፣ ለደገፉት በክንድ እየሰጠ፣ ያንን የብሄር ብሄረሰቦች የእኩልነት አደባባይ፣ የግፈኛ ነውጠኞች ምሽግ አደረገው፡፡ እዚህ ላይ ከአስር አመታት በፊት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሀላፊነት ላይ ስሰራ ያጋጠመኝን አንድ ገጠመኝ ልግለጽ፤ ነጥቤን ያጎላልኛል፡፡
አንድ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ፣ የተማሪዎች ሻይ ቤት የምትሰራ ወጣትን በአይኑ አፈቀራትና ቀርቦ ጠየቃት። ‹‹እኔ አልወድህም›› አለችው፤ ፍቅሩ ባሰበት፤ ደግሞ ጠየቃት፡፡ ‹‹እምቢ›› ብላ ድርቅ አለች፡፡ አንድ ቀን ማታ ካፊቴሪያ ድረስ ሄዶ ደበደባት፡፡ ‹‹ወንጀል ፈጽመሀል፤ ደንብ ጥሰሀል›› ተብሎ፣ በግቢው ፖሊሶች ሲያዝ፣ ዘሎ የብሄር ብሄረሰብ ምሽጉ ውስጥ ገባ፡፡ ‹‹በብሄረሰቤ ጠርታ አንቋሻ ሰድባኛለች፤ እኔስ እሺ ብሄር ብሄረሰቤ ምን በወጣው አለ››፡፡ ፖሊሶች ከምሽጉ በር ተመለሱ፤ የተማሪው ብሄረሰብ አባል የሆኑ ተማሪዎች ግቢው አልበቃቸው አለ፡፡ በተፈጠረው ረብሻ ተማሪዎች በጩቤ ቆሰሉ፤ ትምህርት ለሳምንታት ቆመ። ዩኒቨርሲቲው በዚህ ረብሻ የተሳተፉና የተለያዩ ብረታብረቶችና ጩቤዎች የተገኘባቸውን ተማሪዎችን ለዲስፕሊን ኮሚቴ አቅርቦ፣ በደንቡ መሰረት ለአንድ አመት ከትምህርታቸው አገዳቸው፤ ይህንን የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ካጸደቀው በኋላ፣ የክልሉ አስተዳደር፣ በዩኒቨርሲቲው ቦርድ ውስጥ ባስቀመጠው ሰው አማካይነት፣ ውሳኔው ተግባራዊ እንዳይሆን አገደ፡፡ የቀረበው ምክንያት፣ ‹‹ከሁለቱ በስተቀር ወደ 29 የሚጠጉት የአንድ ብሄረሰብ አባል በመሆናቸው፣ በብሄረሰቡ ላይ የተወሰደ ጥቃት ይመስላል›› የሚል ነበር፡፡ ያ ተንኮለኛ አፍቃሪ የተሸሸገበትን የብሄር ምሽግ፣ የክልሉ መንግስት አጠናከረው፡፡ እና በዛሬዋ ኢትዮጵያ፤ ብቻህንም ሰራህ በቡድን ተደራጅተህ፣ የብሄር ብሄረሰብ ምሽግህ ውስጥ ከገባህ ጠያቂ የለብህም፡፡
.
ሀገራዊ የስነምግባር ዝቅጠት፤ የእሳት ዳር ተረት እንደ ስነምግባር ማስተማሪያነት ጊዜው አልፎበታል፤ የስነዜጋ ትምህርቱ እንጨት እንጨት የሚሉ የልማታዊ ፕሮፖጋንዳ ታጭቆባቸዋል፤ ቲቪው የሚንቀሳቀስ ቶምና ጄሪ፣ ራዲዮው የሚናገር ቶምና ጄሪ፣ የህጻናት መጻህፍቱ የሚነበብ ቶምና ጄሪ! . . . ልጆቻችን በየት በኩል ስነምግባር ይማራሉ! ትምህርት ቤቶች ክፍል የሚቆጠርባቸው፣ ዩኒቨርሲቲዎች ዲግሪ የሚሰጥባቸው ቦታዎች ሆነዋል። ሀገራችን ታታሪዎች ሳይሆኑ  እራስ ወዳዶች፣ ሙሰኞች ተከብረው የሚኖሩባት ሀገር ሆናለች። በደርግ ዘመን ፊናንስ ፖሊስ የሚባል ነበር፤ ኬላ ጠባቂ፣ ኮንትሮባንድ ነጣቂ ፖሊስ፡፡ ደሞዛቸው 100 ብር አይዘልም ነበር፡፡ ግን እዚያ ለመቀጠር የነበረው መዋደቅ አይጣል ነበር፤ ‹‹ለምን?›› ቢባል፣ ገንዘብ ተቀብለህ ታሳልፋለህ፤ የያዝከውን ኮንትሮባንድ ለራህ ትወስዳለህ፡፡ ዛሬ ከ40 አመት በኋላ፣ የክልል ፕሬዚዳንቶችና የጦር መሪዎች ናቸው ይህን ስራ የሚሰሩት፡፡ የኮርፖሬሽን ሀላፊ ሆኖ፣ ኮርፖሬሽኑን አክስሮ ያዘጋ ሚኒስትር ይሆናል፤ ሚኒስትርነቱ ሲያቅተው ትንሽ ዘርፎ አምባሳደር ወይም የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ይሆናል፡፡ ልጆቻችን በተረቱና በትምህርቱ ያጡትን፣ በየመስሪያ ቤቱ፣ በመንግስት መዋቅር አሰራር . . .  ከህይወት ለመማር እንኳን እድል የላቸውም፡፡
እና መንግስት እየሰረቀ አትስረቁ ይላል፤ ዜጎችን እየገደለ፣ በየእስር ቤቱ እያሰቃየ ተከባበሩ – ተፋቀሩ ይላል፡፡ እያሸበረ አታሸብሩ ይላል፡፡ ማን ይሰማዋል?! ስርአተ አልበኝነት ነገሰ፡፡
ምን ይደረግ!
.
የመጀመሪያው አጣዳፊ ተግባር መንግስት ላይ ይወድቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እጅግ በፍጥነት የፍትህ ተቋማትን በአዲስ መልክ አደራጅተው፣ ማህበረሰቡን ባሳተፈ ቁርጠኝነት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ አለባቸው፡፡ ኢህአዴግ የገነባው የብሄር ብሄረሰብ ምሽግ ፈርሶ፣ ግልጽ አደባባይ መሰራት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስፈልገው አንዱ ብሄረሰብ ሌላውን በድሎ የሚደበቅበት ምሽግ ሳይሆን፣ አንዱ ከሌላው ተቃቅፎ የሚታይበት- የሚኖርበት አደባባይ ነው። የአንድ ብሄረሰብ መብት የሚከበረው፣ ልማቱ የሚደራጅለት እሱ በብሄር ተደራጅቶ፣ ‹‹መብቴ ይከበር›› ብሎ ሲነሳ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች በሙሉ፣ ‹‹መብቱ ይከበር›› ብለው ሲነሱ ብቻ ነው፤
ሁሉም ለአንዱ – አንዱ ለሁሉም ሊነሳ ይገባል፡፡
.
አገራዊ የስነምግባር ዝቅጠት በአጭር ጊዜ የሚቀረፍ ችግር አይደለም፤ ፍንጩን ለማየት እንኳን ቢያንስ የአንድ ትውልድ ግማሽ እድሜ ይፈልጋል፡፡ ይህ ችግር በአብዛኛው ከቤተሰብ ባህልና ከትምህርት ስርአት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ረዥምና ተከታታይ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስራ ይፈልጋል፡፡ የብዙኃን መገናኛም በቤተሰብና በማህበረሰብ ባህልና አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስለሚያደርግ፣ በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ መደረግ አለበት፡፡
በአጠቃላይ አሁን ያለውን ቀውስ ለመግታት መንግስት ሀላፊነትንና ተጠያቂነትን በብሄር ብሄረሰብ ላይ ሳይሆን፣ በዜጎች – እንደ አንድ ሰብአዊ ፍጡር የሚያደላድል ስርአት መገንባት አለበት፡፡ ለዚያ ግን ቀዳሚው የእያንዳንዱን ዜጋ ሀላፊነትና ተጠያቂነት የሚያረጋግጡ ተቋማትን ማደራጀት ነው፡፡ ይህ ሲሆን እንደ ግለሰብ ሀላፊነታቸውን የሚያውቁና የሚወጡ ዜጎች ልንቀርጽ እንችላለን። ሀላፊነቱን የሚያውቅና የሚወጣ ግለሰብ ስናፈራ ብቻ ነው እንደ ማህበረሰብ መኖር መቀጠል የምንችለው፡፡
Filed in: Amharic