>

የድምጻዊ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ትንቢቶች!!! (አሰፋ ሀይሉ)

የድምጻዊ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ትንቢቶች!!!
አሰፋ ሀይሉ
 
– ከ «ጃ ያስተሰርያል!» እስከ «ሆላን ይዞ!»
ድምጻዊ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ያኔ በምርጫ 97 ላይ የለቀቀውና በወቅታዊነቱ መቼውንም ያን ወቅት የሚጠቅስ ታሪክ ሊያልፈው የማይችል ዘመን አይሽሬ ዘፈን ለቅቆ እንደነበር ብዙዎቻችን እናስታውሳለን፡፡ ያም ዘፈን ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› የሚለው ነበር፡፡ በእውነቱ ባሳለፍነው የ50 ዓመታት ፖለቲካዊ-ኪናዊ የታሪክ ጉዞ ምናልባት ያ ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› የሚል ዘፈን ከበዓሉ ግርማ ‹‹ኦሮማይ›› በመቀጠል በአወዛጋቢነቱ ተስተካካይ የተገኘለት አይመስለኝም፡፡ ያ ዘፈን ብዙዎችን እንዳወዛገበ ሁልጊዜ የምንሰማው ነው፡፡ ከቅርቡ ብንጀምር በ2010 ዓ.ም. በባህርዳር በተካሄደው የቴዲ ኮንሰርት ላይ ይህንኑ አወዛጋቢ ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ክፈተው እና አትክፈተው በሚሉ የቴዲ ‹‹ፋኖች›› ብዙ መባሉን ሰምተናል፡፡ እርሱም ላለመዝፈን መምረጡን ጭምር፡፡ ይሄ እንግዲህ የቅርቡ ነው፡፡
የሩቁስ? የሩቁማ ፀሐይ የሞቀው ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ይህንን የቴዲ አፍሮን ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› የሚል ዘፈን አስመልክቶ ውስጣዊ የፖለቲካ አፊዳቪት እስከመበተን የደረሱ የሀገራችን የፖለቲካ ቡድኖች መኖራቸውን ጭምር ሁሉ ሰምተን ነበር በወሬ በወሬ፡፡ መነሻውም በዚያ ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ዘፈን ውስጥ የተጠቀሰው የቴዲ ስንኝ – ማለትም «ባ17 መርፌ በጠቀመው ቁምጣ» የሚለው ስንኝ ለለውጥ በተዋደቁ የአንድ ብሔር ሰማዕታት ደም ላይ የሚቀልድ ነው! የሚል ማኒፌስቶ እስከመሠራጨት ደርሶ ነበር – ይል ነበር በዛን ሰሞን በየጉራንጉሩ ይነፍስ ከነበረው ወሬ በጆሮአችን የነፈሰውን ወቅታዊ ትኩስ ነፋስ ጨለፍ ስናደርገው ሹክ የሚለን አነጋጋሪ ዜና፡፡
በእርግጥ እውነታው – መርፌ እየጠቀመ ቁምጣ የለበሰውና ለውጥ ያነገበው የአንድ ብሔር አባል ብቻ እንዳልሆነ ቢታወቅምና – ብዙዎችንም ለምንስ እንዲያ ብሎ ጣትን መቀሰርና ማግነን እንዳስፈለገ ምሥጢሩ ባይገለጥላቸውም – ግን በየተለያዩ መንገዶች ሕዝቡ ጋር በሚደርሱት የተለያዩ ጤናማ ያልሆኑ ‹‹መንግሥታዊ›› ወይም ‹‹ፓርቲያዊ›› አተያዮችና ተፅዕኖዎች የተነሣ – ብዙዎች – አርቲስቱን ለእስር ያበቃው ፈጸመ የተባለው ወንጀል ሳይሆን በዚሁ ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ዘፈኑ ገዢው የመንግሥት አካል ባደረበት ቂም የተነሳ ነው እስከማለት የደረሱበት ብዙዎች ነበሩ፡፡ አሁንም እነዚያ ብዙዎች በየጨዋታውም ሆነ ቁምነገሩ መች አልጠፉ?!!!
እና ግን ያኔ – ቴዲ አፍሮ ‹‹ጃ ያስተሰርያል››ን ለፖለቲከኞቻችን ሲያንጎራጉር – ፓርቲዎቹ ደግሞ ድብልቅልቅ ያለ እንደ አሁነኛው ሰሞኖቹ ‹‹ሰበር ዜናዎች›› የሰዉን ቀልብ ‹‹ምን ያሰማን ይሆን?›› በሚል ገዝተው የነበሩትን የቴሌቪዥን ክርክሮች ሲያጧጡፉ – እኔንና እኜን የመሰልን ብዙዎቻችን ግን – በየጥጋጥጉ፣ በየእነክሽ-እነካው፣ በየወዳጅ-ዘመድ ጉባዔው ሁሉ ያንኑ የፈረደበትን ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› እያነሳን ሞቅ ያለ ክርክር እናደርግ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ በእርግጥ መነሻዬ ላይ ከኦሮማይ ቀጥሎ አወዛጋቢ የሆነ የጥበብ ሥራ እንደ ‹‹ጃ ያስተሰርያል››  አላየንም ብዬ ነበር፡፡ እውነትም ነው፡፡ የታሰረው በዚያ ሰበብ ነው ለሚሉት ብዙ ኢትዮጵያውያን ያኔም የምለው ነገር ቢኖር – ግምታቸው እውን ከሆነ – ምናልባት ቴዲ  አፍሮ ዕድለኛ ነበር ነው የምላቸው፡፡ ምክንያቱም ያኔ በበዓሉ ግርማ ‹‹ትርስ የነከሱበት›› ባለሥልጣናት (የመንግሥት አካሎች) በመኖራቸው የተነሳ – ወደማይመለስበት ወደዚያኛው ዓለም ተሸጋግሮ ነዋ እንደወጣ እልም ያለው፡፡ የዛሬ 13 ዓመቱ ቴዲ አፍሮ ግን – ትንሽ ወደ በዓሉ መንገድ ሄደት ብሎ – ቶሎ መለስ ነው ያለው ማለት ነዋ እንግዲህ!!
/በበኩሌ ግን ‹‹መናፍቅ›› ቢያሰኘኝም… የነበረኝ (እና ያለኝ) አስተያየት – «የሰውን የክስና የፍርድ መዝገብ ሳላይ እንዴት አስተያየት መስጠት እችላለሁ?» የሚል ጥያቄ ብቻ ነበር፡፡ ወንድሜ ሰው እሣት ውስጥ ገባ እየተባልክ፣ እንዴት ድምዳሜ ትሰጣለህ? በጥያቄ ማስቀመጡ አይሻልም?! Lol! አማኝ ‹‹ለምን?›› ብሎ አይጠይቅ ይሆናል፣ ቶማሳዊው እኔ ግን እጠይቃለሁ – ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም! አሁን ወደጀመርኩት ‹‹ጃ ያስተሰርያል››  ጨዋታዬ!/
እና ያኔ ከ97ቱ ክርክር ጋር – ያ የቴዲ አፍሮ ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ዘፈን ትዝ እንደሚለኝ – ምንም ያን ያህል አሁን የሚባልለትንም ያህል የድጋፍ ቲፎዞም ሆነ ያኔ የሚባልለትን የውግዘት ማኒፌስቶ የሚያሰጠው ግነትን የተላበሰ የጥበብ ሥራ አልነበረም ባይ ነኝ፡፡ ማለትም የሆነው ሁሉ – ወይ ሆነ ተብሎ – ወይ ደግሞ በማያውቁ ጨዋዎች አማካይነት – መሆን ከሚገባው ሥፍራና ክብደት በላይ ተሰጥቶት – እጅግ እጅግ ተጋንኗል፡፡ ያኔም ሆነ አሁን እንደማምነው – ያ የቴዲ አፍሮ ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ዘፈን – ማንም ላይ በተለየ ጣቱን የቀሰረ ዘፈን አልነበረም! አይደለምም! ወደፊትም 1 ሚሊየን ጊዜ ቢሰማም እንደዚያ የሚል ትርጉም የሚሰጥ አይመስለኝም – ጆሮ እንደሰሚው፣ ህልም እንደፈቺው ቢሆንም!!!
በበኩሌ ያ የቴዲ አፍሮ ዘፈን ከሌሎችም አርቲስቱ ከሚዘፍናቸው ዜማ-ስንኞች ጋር አብሮ የሚፈስስ – እና ፍጹም ለሀገር ሲባል አንድ ሁኑ – እያለ የሀገሪቱን ፖለቲከኞችና ጎራ ለይተው ለውጥ እናመጣለን ብለው ሲጋደሉ የኖሩትን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያትን ሁሉ – ባንድነት – ያውም በአብዮቱ ጊዜ የጋራ መቃብር እየተቆፈረ የክቡር ዜጎቻችን አስከሬኖች ሲወረወሩበትና ሲቀበሩበት ከሚያሳይ የቪዲዮ አልበም ጋር – ተዉ ይሄንን ታሪክ አንድገመው! እያለ በዚያች ቅጽበት ደጋፊዎቻቸውን በየጎራው አሰልፈው በቴሌቪዥን እሰጥ-አገባ ላይ ለተጠመዱት ፖለቲከኞች ሀገራዊ፣ አባታዊ፣ ወገናዊ መልዕክቱን – በዚያች በትክክለኛዋ ቀውጢ ሰዓት ማስተላለፉ – ምንድነበር ኃጢያቱ?? እያልኩ እንድጠይቅ ነው የሚያደርጉኝ – ዘፈኑ ከተለቀቀበት ከ97 ጀምሮ እስካሁን ላለፉት 13 ዓመታት – በ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ላይ የተለያዩ አስገራሚ ጎራ የለዩ አስተያየቶችን፣ እንዲሁም የከረሩ ቲፎዞዎችንና የመረሩ ተቃውሞዎችን – በየሄድኩበትና ዘፈኑ በተሰማበት ሁሉ ስሰማና ሳስተናግድ፡፡
እንዴ?!! ደግሞም እኮ ያ የአርቲስቱ ምክር ባለመሥራቱ የተነሣ እኮ – ያ እርሱ የፈራው ትንቢት ደረሰ፣ ተደገመ እኮ – አይደለምእንዴ?!
አርቲስቱ የተናገረው ለእኔ እነዚህን ነው፡- ድሮም በ66 ለውጥ ለውጥ ተብሎ ስንቱ ነፍስ ጠፍቶ እምብዛም የተለወጠ ነገር አላየንም፣ የተማሪ ሬሳ መዓት ብቻ ነበር፤ ልክ እንደዚያው 17 ዓመት ሙሉ ለውጥን አንግቦ የታገለውም በዙፋኑ ላይ ሲመጣ የሕዝባችን ኑሮ ሲለወጥ አላየሁም – በዙፋን ላይ መተካካት ብቻ ሆነ የኛ ነገር – እስቲ ‹‹ሀገሬን ሕዝቤን›› ካላችሁ – እናንት ፖለቲከኞች – እርስ በርስ መናቆሩን ትታችሁ – የዛሬ 3ሺህ ዓመት በነበረ ቴክኖሎጂ የተቀለሰ ያዘመመ የደሃ ጎጆ የሚኖሩትን ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያንን ሕይወትና ኑሮ ለውጡ ነው!
አርቲስቱ ያውም ትክክለኛ ሰዓቷን ጠብቆ በ‹‹ጃ ያስተሰርያል››  ያስተላለፈው መልዕክት – እስቲ እናንት ፖለቲከኞች፣ ምንደኞች፣ የዚህ ዓለም ገዢ ሥልጣናትና የጦርዕቃ የለበሳችሁ ያገር ልጆች ሁሉ – እስቲ መበላላቱን ትታችሁ – ዓለም ከተፈጠረ እስካሁን በባዶ እግራቸው በየገረጋንቲውና ቆንጥሩ ላይ የሚረማመዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን እስቲ ጫማ አልብሱ፣ እስቲ መወጋጋቱንና መጫረሱን ተዉትና በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ከድሮ እስከ ዘንድሮ ረሃብ ጓዳቸውን እየጎበኘ በዓለም ፊት በውርደት የሚለመንላቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ረሃብ እስቲ ባንድ ላይ ተነስታችሁ ሆ ብላችሁ አስታግሱላቸው ነው የሚለው!
አርቲስቱ ያለው – እስቲ ጎራ አሰልፋችሁ ለዳግም፣ ለሣልስት ጥፋት ከመነሳሳት ይልቅ – እስቲ እርስበርሳችሁ ይቅር ተባባሉና – እስቲ ኋላ የቀረውን ያገራችሁን ሕዝብ አኗኗር፣ የኑሮ አቅም፣ ሕይወት፣ ጤና፣ ዲሞክራሲ፣ ምርጫውን፣ ጉርሻውን፣….. –  እስቲ አበልፅጉለት – እስቲ አስፉለት ወፍራም እንጀራውን በጋራ፣ – አውጡለት አንጡረ-ሃብቱን – እጅለእጅ ተያይዛችሁ፣ እስቲ የዜጎቻችሁን ነፍስ ማጥፋትና ወደስቃይ መግፋት ይቅርባችሁና – እስቲ እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ የኢትዮጵያ ሀገራችሁን ትንሣዔ አብስሩላት!!!!!! – ነው የሚለው የቴዲ አፍሮ ‹‹ጃ ያስተሰርያል››  መልእክት!!!!
እና እንዴት እንዴት ቀናነት ቢጎድለን ቢጎድለን ይሆን ግን?፣ አሊያ ምን ያለው የፊውዳል ‹‹ዘራፍ! አትንኩኝ›› የሚል ትምክተኛ መንፈስ ቢያድርብን ይሆን ግን?፣ ወይስ እንዴት እንዴት እያሰብን ወይ እያላሰብን ይሆን ግን ጃል? – እንዲያ ዓይነት ወርቃማ ምክርን ‹‹ተነሣ ተራመድ ክንድህን አበርታ›› ሳይል – በረቀቀ የጥበብ መንገድ አላብሶ – ሁላችንን ፖለቲከኞችን ሁሉ እርስ በርስ ሲከራከሩ የሚታዩበትን ምስል እያሳየ – ጥበብንና ምክርን በፍቅር የሚለግሰንን ያን የአርቲስቱን ወቅታዊ የነበረ የጥበብ-እንጀራ ግን – እንዴት ብለን ይሆን ግን ትርጉሙን አጣጥሞ ከመቋደስና ከመታነፅ ይልቅ – እንዲያ እጅ-እጅ እንዲለን ያደረገን አንዳች ነገር??!! ምን ይሆን??!!
‹‹ጃ ያስተሰርያል››  እኮ ሌላ ሳይሆን ይኼ ነው፡-
«ባ17 መርፌ በጠቀመው ቁምጣ
ለለውጥ ያጎፈረው ዙፋን ላይ ሲወጣ
እንደአምናው በበቀል ያምናውን ከቀጣ  [If!]
አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ?
ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ
ምህረት አስተምረን አንድ አድርገን መልሰህ!
ጃ ያስተሰርያል!
«እማማ ኢትዮጵያ
እማማ አቢሲንያ
እማማ ኢትዮጵያዬ
«ዘፀአት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ
ባህሩን የሚያሻግረ አንድ ሙሴ ይዞ
ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሳኤ
ባንድነት ከገባን የፍቅር ሱባኤ!
ጃ ያስተሰርያል!
«ፍቅር አጥተን እንጂ በረሀብ የተቀጣን
ዐፈሩ ገራገር ምድሩ መች አሳጣን
ኦሲሳ ኦሲሳ ኦሲሳ ማንዴላ
ይቅር አባብሎ እንዳስጣለ ቢላ
በተስፋዋ መሬት እዲፈፀም ቃሉ
ሞፈሩን ያዙና ይቅር ተባባሉ!
«ጃ
ጃ ያስተሰርያል!
እማማ ኢትዮጵያ!
እማማ አቢሲንያ!
እማማ ኢትዮጵያዬ !
«እማማ እረ አይነጋም ወይ?
እማማ አይነጋም ወይ፣ አይነጋም ወይ ሌቱ ኢትዮጵያዬ?
እማማ እማማዬ!!»
እና ግን በመጨረሻ ፅሑፌን ልደመድም የምንፈልገው በአርቲስቱ (በቴዲ አፍሮ) ተከታታይነት ያላቸው – ጠብን እንድናርቅ፣ ቂምን እንዳናረግዝ፣ እርቅን በመካከላችን እንድናሰፍን፣ መጠላላትን ትተን እንድ ላይ እጅ ለእጃችን ተያይዘን የወደፊቱን ብሩህ መንገድ አብረን እንድንጓዝ የሚያሳስብባቸው መንገዶች – እና ጽኑ አቋሙ ሁልጊዜም ያስገርመኛል፡፡ አሁን እንግዲህ እስቲ ቴዲ አፍሮ በቅርቡ ካወጣው «ኢትዮጵያ» አልበሙ ውስጥ የተካተተው ‹‹ስምበሬ›› የሚል ዘፈን መልዕክት፤ ከዚያኛው ከ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ዘፈኑ መልዕክት ጋር የሚለየው ምን ይሆን? ያን ብዙ ያነጋገረውን የአርቲስቱን ‹‹እንደአምናው በበቀል ያምናውን ከቀጣ፤ አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ?›› ከሚለው ‹‹ጃ ያስተሰርያል›› ስንኞቹ መልዕክት ጋር እነዚህን የአዱሱን አልበሙን «ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ፤ ቦታ ቢለዋወጥ ወጥ ላያጥም ጉልቻ» ስንኞች ምን ይለያቸዋል??
«ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ………….ጉራ ብቻ!
ቦታ ቢለዋወጥ ወጥ ላያጥም ጉልቻ…………ጉራ ብቻ!
ልቤ ዛሬም ወደህ ልትሆን መተረቻ……………..ጉራ ብቻ!
ታዲያ ምን አመጣው ያንን ሁሉ ዛቻ …………ጉራ ነው ከአካሌ!
ከአካሌ ሳይጠፋ ስምበሬ!
ከአካሌ ሳይጠፋ ስምበሬ!»
በበኩሌ የሚለያቸው የለም ነው የምለው፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ፣ ወይም ወደፊት፣ በዚህች ሀገር ታሪክ – ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ በፍቅር ለአንዲት የጋራ ሀገርና ሕዝብ ብሎ የወደፊቱን የብልጽግና ተራራ በህብረት በተስፋ በቀናነት ሊጓዝ እስካልቻለ ድረስ – አንዱ ባንዱ ቦታ ከመተካት ውጭ የሚያመጣው ፋይዳ አልነበረም፣ የለም፣ ወደፊትም አይኖርም!!! እና እንደዚህ ትንቢታዊ ባለራዕይ አርቲስት – ቴዲ አፍሮ እንዳለው – እርስበርስ ጣት መጠነቋቆላችንንና ጎራ ለጎራ መሠላለፋቸንን ትተን – እስከዛሬ የመጣንበት መንገድ ምንድን ነበረ? ብለን ራሳችንን በሀቅ እንጠይቅ፣ ራሳችንን እንፈትሽ፡-
«ስለ ፍቅር ሲባል ስለ ፀብ ካወራን ተሳስተናል
አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል
አተናል እውነት ነው ተቸግረን ብዙ አይተናል
የመጣነው መንገድ ያሳዝናል!
እግር ይዞ እንዴት አይሔድም?
ሰው ወደፊት አይራመድም?
አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ
ለምን ይሆን የራበው ሆዴ?››
እና – እንደ በጥበብ ራሳችንን እንደጠየቅን – የጎደለንን ነቅሰን – የስህተትን ጎዳናዎች ዳግም ላለመድገም – ራሳችንን በፍቅርና በኅብረት እናንፅ፣ ጥላቻና ቂማችንን እንግራ፣ እልሃችንንና ስሜታችንን ለመጪ ትውልድ ስንል እንዋጥ – እንደ መሪ፣ እንደ ተመሪ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ – ሁሉም – ምራቁን ይዋጥ!!!! እና ሁሉም ተፈጥሮ የቸረችውን የፍቅር ልብ ይዞ – ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ አምላክ ፈጣሪን ይዞ – ሁሉም – ወደማይቀረው ሀበሻዊ የብልፅግና ከነዓናችን – በፍቅር፣ በህብረት፣ በአንድነት፣ በንፁህ ወገናዊ መቆርቆር፣ በ‹‹ንጹ ፍቅር›› – ወ ደ ፊ ት ! ወ ደ ፊ ት !!!
«ይህንን አውቃለሁ፤
ወደ ፍቅር ልሂድ
ምን እጠብቃለሁ?
ሆላ እንደ ሲዳማ
መገኖ ካልን ጌታ፤
ይሰማናል ከላይ
የታረቅን ለታ!
«ኦላን ይዤ አላፍርም
ይህንን አውቃለሁ፤
ወደ ፍቅር ልሂድ
ምን እጠብቃለው?
ቂም ይዞ ማዝገሙ
ላቃታት ሕይወቴ፤
ሰተት ብለህ ግባ
ንጹ ፍቅር ቤቴ!
ሰት ሰተት …!!
«ወደ ፍቅር ጉዞ ……..ተያይዞ!
ቂምን ከሆድ ሽሮ ……… ኦላን ይዞ!
ኦላን ይዞ!
ኦላን ይዞ!»
በመጨረሻም ለታላቁ አርቲስት ቴዲ አፍሮ እና ለአስገራሚ ትንቢተኛ ዜማ ስንኞቹ ያለኝን አክብሮትና አድናቆት ገልጬ – አሁንም ወቅታዊ ነው የምለውን የአርቲስቱን የፍቅር መልዕክት እንደደብተራ ደግሜ-ደጋግሜ – መስተፋቅሩ ለሀገር ለወገን ሁሉ ይዳረስ ዘንድ በውስጤ ያሳደርኩትን ጥልቅ ምኞት ገልጬ – ለአርቲስቱና ለቤተሰቡ አንድዬ የኢትዮጵያ አምላክ የበዛ ዕድሜውን፣ ጤናውንና በረከቱን ሁሉ እንዲሰጥልኝ መርቄ – እነሆ ተሰናበትኩ!!!
አምላክ የጥበብ አውድማውን ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ አምላክ የቃልኪዳን ለጆቹን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ አብዝቶ ይባርክ፡፡ የብዙኀን እናት – እምዬ ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም ትኑር፡፡ የማያልቅ የፈጣሪ ፍቅር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ ‹‹ጃ ያስተሰርያል!›› – ‹‹ፍቅር ያሸንፋል!›› – አ ሜ ን ! ! !
Filed in: Amharic