>

ግንቦት ሰባቶች ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ነው!! - ከ10 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ገብተዋል

ግንቦት ሰባቶች ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ነው!!

ከ10 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ገብተዋል

አለማየሁ አምበሴ

  *  የ“አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ” ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ 100 ያህል አመራሮችና አባላትን ይዘው ወደ ሃገር ቤት እንደሚገቡ የታወቀ ሲሆን ንቅናቄው በሃገር ውስጥ በአዲስ አደረጃጀትና ቅርፅ እንደሚዋቀር ተገልጿል፡፡ 


ላለፉት 10 ዓመታት ያህል የትጥቅ እንቅስቃሴን ጨምሮ ዋና መቀመጫውን ኤርትራ በማድረግ ሁለገብ ትግል ሲያከናውን የቆየው “አርበኞች ግንቦት 7”፤ በቅርቡ በሃገር ውስጥ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታና መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሰረት፣ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ፣ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ መወሰኑ ይታወቃል፡፡
የንቅናቄው ሊቀ መንበርና ከፍተኛ አመራሮች በመጀመሪያው ዙር ከሰሞኑ ወደ ሃገር ቤት እንደሚመለሱ አቀባበል ለማድረግ የተዋቀረው ኮሚቴ የገለፀ ሲሆን በቀጣይም በኤርትራ ያሉ የሰራዊት አባላትና ሌሎች አመራሮች በተመሳሳይ ወደ ሃገር ውስጥ የሚመለሱበት ሁኔታ ይመቻቻል ብሏል፡፡
አመራሮቹ ወደ ሃገር ቤት በሚመጡበት ወቅትም ደጋፊዎቻቸው ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው የጠቆመው ኮሚቴው፤ ወደፊት አመራሮቹ ከህዝቡ ጋር በሰፊው የሚገናኙባቸው መድረኮች ይፋ ይደረጋሉ ብሏል፡፡
በሀገር ውስጥ በህቡዕ፣ በውጪ ሃገራት፣ በይፋ ሁለገብ የትግል እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል የተባለው “አርበኞች ግንቦት 7” በቀጣይ ራሱን ከንቅናቄ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ቀይሮና በህጋዊነት ተመዝግቦ በዜግነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስልት በመከተል ለምርጫ ውድድር እንደሚቀርብ ተገልጿል፡፡
ከሊቀመንበሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ከሚመለሱት አመራሮች መካከል አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ዶ/ር ታደሰ ብሩ፣ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ ዶ/ር አዚዝ መሐመድ እና አቶ ነአምን ዘለቀ ይገኙበታል፡፡
በሀገሪቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ከተደረገ በኋላ ከተወሰዱ የፖለቲካ ማሻሻያዎች አንዱ በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶችን ፍረጃ በማንሳት ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ የተደረገው ጥሪ ሲሆን በዚህ መሰረት እስካሁን ከ10 ያላነሱ ተፅዕኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሃገር ውስጥ ተመልሰዋል፤ 25 ያህሉም ለመመለስ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ወደ ሃገር ውስጥ ከተመለሱት መካከል የአፋር ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር፣ የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የአማራ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ህብረት፣ የኦሮሞ ዲሞክራሲዊ ግንባር (ኦዴግ) እንዲሁም የኦጋኤን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ይገኙበታል፡፡ 

Filed in: Amharic