>
10:16 pm - Tuesday August 16, 2022

በመንጋ እሳቤ የሚመሩ ሰዎች በደቦ ያብዳሉ!!! (አሳምነው ሀይለ ጊዮርጊስ)

በመንጋ እሳቤ የሚመሩ ሰዎች በደቦ ያብዳሉ!!!
አሳምነው ሀይለ ጊዮርጊስ
 
* የመንጋው ኢፍትሃዊ የሆነ ተግባር ከጎረቤታችን ኬኒያ እስከ ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ፣ ከማንዴላዋ ደቡብ አፍሪካ እስከ ፑቲኗ ራሻ ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች “የደቦ ጥቃቶች” ይፈጸማሉ፡፡ ይሁን እንጂ አገራቱ በዚህ ህገወጥ ድርጊት የተነሳ የደረሰውን በደል ከግምት በማስገባት ተቋማዊ መፍትሄ አስቀምጠውለታል
 
ጊዜው ይራቅም ይቅረብ፣ ቁጥሩ ይብዛም ይነስ፣ ድርጊቱ በስፋት ይዘገብ ወይም ይሸፋፈን፣ ድርጊቱ መነሻም ይኑረው በዘፈቀደ ይከወን ብቻ በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች ዘግናኝ የሆኑን ድርጊቶች መስማቱ ማባሪያ አልተገኘለትም። በተለይ የሻሸመኔው ሰቅጣጭ ድርጊት ብዙዎችን ያሳዘነ ሆኗል፡፡ በዚህ ክስተት ዙሪያ ብዙ እንደመነገሩ በሆነው ላይ ሳይሆን ከሻሸመኔው ክስተት በፊት ሆነ በኋላ ባሉት አጠቃላይ የመንጋ ኢፍትሃዊነት ድርጊቶች ዙሪያ የበኩሌን ሐሳብ መሰነዘሩን መርጬያለሁ፡፡ እንዲህ ያለው ክስተት በጊዜ ሁሉን አቀፍ ተቋማዊ የሆነ መፍትሄ ካልተበጀለት በቀር ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ መገመቱ ለማንም የሚያዳግት አይደለም፡፡ ከሰሞኑ እዚህም እዚያም እየተሰሙ ያሉ ዘገባዎች በጣም ሰቅጣጭ መሆናቸውን ተከትሎ አንዳንዶች እንዲህ አይነቱ ድርጊት መከወን የተጀመረው አንፃራዊው ነፃነት በአዲሱ አመራር አማካኝነት ከመጣ በኋላ እንደሆነ አድርገው ሲፁፉ ታዝቤያለሁ፡፡ ይሄ አይነቱ አጠቃላይ ድምዳሜ በፍጹም ምክንያታዊ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን አርቆ ማስተዋል የተጓደለበት (shortsighted) እና የተቻኮለ ድምዳሜ ነው፡፡ እዚህ ላይ የጠ/ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉዞ አባል የነበረው ዲ/ን ዳንኤል ሳይቀር ‹‹ነጻነት ሰውን አውሬ ካደረገው፡ ባርነት ለዘላለም ይኑር፡፡›› ማለቱን ብዙዎች ሲቀባበሉት በማየቴ በጣም አዝኛለሁ፡፡ አንደኛ አንድን ከሞራል የወጣ ኢሰብዓዊ ድርጊት በሌላ ኢሞራላዊ ድርጊት ማረም በጭራሽ የሚመከር አይደለም፡፡ ነፃነትም ቢሆን በበለፀጉት አገራት ሆነ እንደ ቦትስዋና ባሉ የአፍሪካ አገራት እንዳየነው የሰውን ልጅ ወደ ላቀ የሞራል ሆነ የስልጣኔ ደረጃ የሚያደርስ እንጂ አውሬ የሚያደርግ አይደለም፡፡ በዛ ላይ ባርነት የሰውን ልጅ እንደሸቀጥ እንዲቆጠር የሚያደርግ እና ባለቤቱ እንዳሸው እንዲሸጥ እንዲለውጠው የሚያደርገው በመሆኑ ይህ አይነቱ ዘግናኝ ድርጊት እንኳን ለዘላለም ቀርቶ ለሰኣታት በጭራሽ የሚመኙት አይደለም፡፡ ከዚህ ውጪም በቦታው ላይ የነበሩ ቁጥራቸው በርከት ይበል እንጂ መቶ ሚሊዮን ከሚሆነው አገራችን ህዝብ አንፃር እዚህ ግባ የማይባል ቁጥር ባላቸው ሰዎች የጅምላ ፍረጃ ላይ ለመድረስ መጣደፍ አንድን ድርጊት ተከትሎ በአገራችን በተለይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰነዘሩ ሐሳቦች ምን ያህል ከስሜታዊነት ያልራቁ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
“ስም አልባው” አረመኔያዊ ድርጊት ከትላንት እስከዛሬ
በዋንኛነት ያልሰለጠኑ ሰዎች ድርጊት (Act of Barbarians) በሚል የሚገለፀው አሳፋሪው ንጽሀንኑ በደቦ ተጠያቂ በማድረግ መንጋው ራሱን ከሳሽ እና ፈራጅ በማድረግ ሌላውን ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሕይወቱን እንዲያጣ ወይም ለከፋ የአካል ጉዳት እንዲዳረግ የሚያደርግበት ሕገወጥ ተግባር በስፋት ከእንግሊዘኛው አቻ ቃል (Mob Justice) ትርጓሚ በቀጥታ የተወሰደው የመንጋ ፍትህ መጠሪያው ተደርጎ በስፋት ይወሳል፡፡ ይሁን እንጂ የድርጊቱ መጠሪያ በጭራሽ ክስተቱን የሚገልፅ አይደለም፡፡ በመንጋ የሚወሰድ አረመኒያዊ ድርጊት ፍትህ ብሎ ነገር አያውቅም፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያለው ድርጊት በቋንቋ ተቋማት ወይም በስነልሳን ምሁራን አግባብ ያው ስያሜ እስኪወጣለት ድረስ በግሌ የመንጋ ኢፍትሃዊነት የሚለውን ቃል መጠቀሙን እመርጣለሁ፡፡ የሆነው ሆኖ ይህ ስም አልባው አረመናዊ ድርጊት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እዚህም እዚያም መከሰቱ እሙን ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት እንዲህ ያለው ድርጊት በበርካታ ቦታዎች ተከናውነዋል፡፡ ለዚህ እንደማሳያ ቂሊንጦ ሳለሁ አብረውኝ የነበሩ ተከሳሾች ጥፋተኛ የተባሉበትን እና በጋምቤላ ክልል በማዣንግ ዞን ጎደሬ ወረዳ ሜጢ ከተማ ውስጥ የተፈጠረው የተደራጀው የመንጋ ኢፍትሃዊ ድርጊት አንዱ ነው፡፡ በዚህ ያልተገባ እና ሠላማዊ ዜጎች ላይ በተወሰደ ሕገወጥ እርምጃ 79 ሰዎች ሞት፣ ለ27 ሰዎች ከፍተኛና ዝቅተኛ የአካል መጉደል፣ ለ270 ለሚልቁ መኖሪያ ቤቶች መቃጠል፣ ከ13,000 በላይ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ መንስኤ ሆኗል፡፡
የዚህ አስነዋሪ ድርጊት ተሳታፊዎች በማዣንግ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በሕጋዊ መንገድ ለበርካታ ዓመታት ሲኖሩ የነበሩ የሌላ ብሔር ተወላጆችን እነሱ ‹ደገኞች› ብለው የሚጠሯቸውን፣ የተለያዩ ብሄር ተወላጆችን ‹‹መሬት አካፍሉን ወይም አገራችንን ጥላችሁ ውጡ፤›› በማለት ግድያ፣ የአካል ማጉደልና የንብረት ውድመት ማድረሳቸውን በጊዜው ከቀረበባቸው ክስ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በክሱ ላይ በግልፅ እንደሰፈረው ለማሰብ በሚዘገንን ሁኔታ የገዛ ወገናቸውን ከገደሉ በኋላ ሬሳውን በገጀራ እስከመቆራረጥ የደረሰ ግፍ ተፈፅሟል፡፡ በተለይ ግፉ ላይ ከተራው ማህበረሰብ በተጨማሪ ከፍተኛ ሃላፊነት ያላቸው ሰዎች ጭምር በዚህ ድርጊት ተሳትፈው መገኘታቸው ነው በተለይ ይህንን ክስተት ለመጥቀስ የመረጥኩት፡፡ አሳዛኙ ነገር ከ2006 ክረምት መግቢያው ላይ አንስቶ እስከ 2007 አዲስ ዓመት መስከረም በዘለቀው በዚህ ጥቃት ምንም ከማያውቁ ህፃናት እስከ አረጋውያን ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡ አሳዛኙ ድርጊት ግን ይህንኑ ክስተት በሚገባ በመዘገብ ሌሎች ቦታዎች እንዲህ አይነት ድርጊት እንዳይደገም ሰፊ ግንዛቤን የሚፈጥር ዘገባን በመስራት ፋንታ ጉዳዩን መሸፋፈን በመመረጡ ብዙዎች ስለዚህ አሳዛኝ ዕልቂት በተለይም የመንጋ ኢፍትሃዊነት ጥቃቱን ተከትሎ ወደለየለት እርስበርስ ጦርነት የተሸጋግረውን እና ከ12 ሺህ በላይ ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ያደረገውን ክስተት በሚገባ አንዳይረዱት ተደርጓል፡፡ በየጊዜው እዚህም እዚያም የሚከሰተውን ጉዳይ በሚገባ አጥንቶ፣ ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር ትንታኔ አቅርቦ የመፍትሄ ሐሳብ በጊዜ መወሰድ አለመቻሉ ዛሬ ለደረስንበት አስከፊ ደረጃ ዳርጎናል፡፡
የሰሞንኛ የመንጋ ኢፍትሃዊ እርምጃዎች
ከሶስት ዓመት በፊት ከተከሰተው ከዚህ ዘግናኝ ድርጊት የመንጋ ኢፍትሃዊ እርምጃ ሆነ ከሌሎች መሰል ድርጊቶች በመነሳት ሌሎች አገራት ችግሩን ለመፍታት የሞከሩበትን ብልሃት ለመረዳ በመጣር፣ በአገራችን ያለውን ይህንኑ ችግር ለመፍታት ሁሉን አቀፍ የሆነ መፍትሄ ባለመቅረቡ ለወትሮው በአገራችን ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ በሚያሳፍር ሁኔታ አንድን ድሃ የመስቀል፣ በሱማሌ ክልል ደግሞ 7 አብያተ ክርስቲያናትን የማቃጠል እንዲሁም ክፉ ሊናገሯዋቸው እንኳ ማሰብ የሚቸግረውን ሃይማኖት አባቶች (ካህናት) ያለ አንዳች ጥፋታቸው ተገድለው ጭራሽኑ አስከሬናቸው እንዲቃጠል ተደርጓል፡፡ በቅርቡም በሃዋሳ የወላይታ ተወላጆች ላይ የተወሰደው ያልተገባ ድርጊት ብዙዎችን ያሳዘነ እና ሴት ልጅ አስክሬን ለማቃጠል እሳት ስትለኩስ የሚያሳይ ምስል ሁሉ ይፋ የሆነበት ነበር፡፡ ከዚሁ ከደቡብ ክልል ሳንወጣም በወልቂጤ፣እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች በተፈጠሩ ግጭቶች የዜጎች ሕይወት መጥፋቱ ይታወሳል፡፡
በባሌ ዞን በጎባ ከተማም በተፈጠረ ግጭት የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ@ የበረሃዋ እንቁ በምትሰኘው ድሬዳዋም በተከሰተ ግጭት የ10 ሰዎች ህይወት አሳዛኝ በሆነ መልኩ ሲጠፋ@ በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን በቤንሻንጉል ክልል ካማሺ ዞን በመንጋ ኢፍትሃዊ ድርጊት ብዙዎች ለሞት እና ከቀዬ ቤታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል፡፡ ባህር ዳር እህል እየዘረፉ እንደ ትግል ስልት መወሳቱ ያሳዝናል፡፡ በምስራቅ ወለጋ ገጠር ቀበሌም የትግራይ ተወላጆች በቡድን በድንጋይ ተደብድበው መሞታቸው ተሰምቷል። እንዲሁም ሌሎችም በአዊ ዞን በጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት አቅራቢያ በምትገኘው ፈንድቃ ከተማ ጥቃት ደርሶባቸው የሞቱ ወገኖች መኖራቸው ሳይዘነጋ መሆኑ ነው፡፡
በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ ላይም የመንጋው ኢፍትሃዊ ድርጊት በቴፒ ከተማ መዳረሻውን አድርጎ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ሌላ አንድ ሰው መጎዳቱ ታውቋል፡፡ በጥቅሉ በአገሪቱ በአራቱም ማዕዘን ከጅግጅጋ እስከ ቤኒሻንጉሉዋ አሶሳ ፣ከሻሸመኔ እስከ ድሬ፣ ከባህርዳር እስከ አዲግራት የተሰሙት አሳዛኝ ዜናዎች ይህ አይነቱ ያልተገባ ድርጊት መቋጫ ሊበጅለት እንደሚገባ አይነተኛ ማሳያ ናቸው፡፡
በተለይ ከመንጋው ኢፍትሃዊ ድርጊት ባልተናነሰ መልኩ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ፖሊስ መካከል የሚደረገው ግጭት የበለጠ ለማገርሽቱ የባለፉት ሶስት ሳምንታት አሳዛኝ እልቂቶች ሁነኛ ማሳያ ናቸው፡፡ በተለይ የሻሸመኔው አሳዛኝ ክስተት በተፈፀመበት ወቅት የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ፈጽሞታል በተባለው ጥቃት በምስራቅ ሐረርጌም 37 ሰዎች ሲገደሉ 44 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በርግጥ ይህ ጥቃትን የበለጠ ከመንጋ ኢፍትሃዊነት እርምጃ አስከፊ የሚያደርገው ሠላማዊ ዜጎች ሊጠብቃቸው በተገባ ሃይል ሕይወታቸውን መነጠቃቸው ነው፡፡ አቶ ሞሃመድ ሲራጅ ‘’በቤት ውስጥ ተቀምጠን ባለንበት ወቅት የሶማሌ ልዩ ፖሊሶች በር ገንጠለው ገቡብን። ባለቤቴን፣ ልጄንና የሁለት ዓመት የጎረቤት ልጅ አጠገቤ ገደሉ’’ ሲሉ የደረሰባቸውን ጉዳት ለቢቢሲ የገለፁበት ሁኔታ የጥቃቱን ስፋት በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይም ሴቶች፣ ዓይነ ስውር አዛውንቶች እና ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ሳይቀር በጥቃቱ ተገድለዋል መባሉ የችግሩን አሳሳቢነት በስፋት የሚጠቁም ነው፡፡
ከዚህ ጥቃት በፊትም በሞያሌ የኦሮሚያ ፖሊስ በሶማሌዎች ላይ አድርሶታል በተባለው ጥቃት 50 ሠላማዊ ዜጎች ተገድለው በመቶዎች ወደ ኬኒያ ተሰደው፣ ከፍተኛ የሆነ ንብረት ሊወድም በቅቷል፡፡ አንድ እናት አራት ልጅዋን በአንድ ቀን ያጣችበት ይህ ዘግናኝ ክስተት በተገቢው መንገድ ባለመዘገቡ ከፍተኛ ቁጣን በኢትዮ ሶማሊ አራማጆች ዘንድ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ የዚህ አይነቱ ጥቃት ለጅግጅጋው የደቦ የጭካኔ እርምጃ እንደሁነኛ መቀስቀሻ በአብዲ ኢሌ ሃይሎች መዋሉ ይታወቃል፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ይህንን ሊጠብቁዋቸው በሚገባ ፖሊሶች ከሁለቱም ወገን እየደረሰ ያለውን ሕፃን አዛውንትን ያለየ ግድያ ለማስቆም ጠንካራ እርምጃ አለመወሰዱ ነው፡፡
ከግብታዊነት ወደ ለውጥ አራማጅነት
በመንጋ እሳቤ የሚከሰትን ግድያ ሆነ ሌላ ክፍ ክስተት ሲሰማ ሆነ ሲታይ በግብታዊነት ምሬትን ብቻ መሰንዘሩ ዋጋ የለውም፡፡ ከዚህ ይልቅ እንደ ክስተቱ ሁኔታ የአጭር እና የረዥም ጊዜ መፍትሄን ለመሻት መረባረቡ እና የሚመለከተውን አካል መጠየቁ የላቀ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከዚህ ውጪ አንድን ክስተት ብቻ ነጥሎ በተለየ ሁኔታ ማራገቡ ወደ መፍትሔ አያደርስም፡፡ እውነቱን ለመናገር በደቦ ዜጎችን የመግደሉ፣ የማሳደዱ ተግባር ድርጊቱን የሚገልፅ ስያሜ እንኳ የለውም፡፡ ለምሳሌ ሌብነት በህግ ድርጊቱ ጥፋት መሆኑ ታውቆ ማንም ቢሆን ከዚህ አይነቱ ድርጊት እንዲርቅ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ተገቢው ቅጣት ተቀምጦለት ይገኛል፡፡ ይህ የደቦ አረመኔያዊ ተግባር ግን የሰውን ሕይወት የሚነጥቅ ዘግናኝ ተግባር ቢሆንም በድንገት የሚፈጠረውን እንዲህ ያለውን ወንጀል ለመግታት እስካሁን ድረስ ምንም የተወሰደ ተቋማዊ እርምጃ የለም፡፡ የመንጋው ኢፍትሃዊ የሆነ ተግባር ከጎረቤታችን ኬኒያ እስከ ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ፣ ከማንዴላዋ ደቡብ አፍሪካ እስከ ፑቲኗ ራሻ ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች “የደቦ ጥቃቶች” ይፈጸማሉ፡፡ ይሁን እንጂ አገራቱ በዚህ ህገወጥ ድርጊት የተነሳ የደረሰውን በደል ከግምት በማስገባት ተቋማዊ መፍትሄ አስቀምጠውለታል፡፡ በመሆኑም ድርጊቱ ልክ በወንጀል ሕግ እንደተቀመጡ ማናቸውም ጥፋቶች ተለይቶ የታወቀ በመሆኑ እንዲሁም በዚህ ያልተገባ ድርጊት ላይ ሰፊ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ፕሮግራሞች ሆነ የቅስቀሳ ሥራዎች በመከናወናቸው እንዲህ ያለውን ዘግናኝ ተግባር ለመቀነስ በቅተዋል፡፡ ኬኒያ እንኳ እንዲህ አይነቱን ድርጊት በየዓመቱ ለመቆጣጠር በከፍተኛ ደረጃ ከመንቀሳቀሷ ባሻገር የዚህን አይነት የደቦ ጥቃት ትመዘግባለች፡፡
የእኛው አገር ዋንኛ ችግርም ለክስተቱ ተቋማዊ መፍትሄ ለመስጠት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን በስፋት በማውገዝ እና ግንዛቤ በሚፈጥር መልኩ ለሕዝቡ በማቅረብ ፋንታ እከሌን አይወክልም በሚል ሽፋን ጥፋቱ አላግባብ ተሸፋፍኖ ይቀራል፡፡ እርቃኑን ያለግብሩ የተሰቀለው የወንድማችን ማንነት፣ የእናቱ ሃዘን፣ የቤተሰቡ ምሬት ምን አልባትም የትዳር አጋሩ ወይም የልጆቹ ሁኔታ ቢቀርብ ይህንን አረመኔያዊ ድርጊት የፈፀሙትን ከማሳፈር ባለፈ ሌሎች ወገኖችም በዚህ አይነቱ የመንጋ አረመኔያዊ ተግባር ላለመሳተፍ ቆም ብለው እንዲያስቡ መንገድ በከፈተ ነበር፡፡ በተለይም ድርጊቱን የፈፀሙ ሰዎች ለህግ መቅረብ ተከታትሎ መዘገብ እና የሚተላለፍባቸውን ውሳኔ ማሳወቅ ሌላኛው የዚህን አይነቱን ድርጊት መግቻ መንገድ ነው፡፡ ይሁንና ከዚህ በተቃራኒው ሰዎቹ ተይዘዋል ወይም በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተከናወነ ነው የሚል ጎዶሎ ሐሳብ ከመሰንዘር ባለፈ በተከታታይ ሂደቱን ተከታትሎ ውጤቱን ለህዝቡ ይፋ የማድረግ ባህል አለመኖሩ ድርጊቱን በየጊዜው እዚህም እዚያም ከመከሰት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ዋጋ ቢስ አድርጎታል፡፡
ዘግናኝ የሆነውን የደቦ ጥቃት ተከትሎም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከሚሰጠው ስሜታዊ አስተያየት ባለፈ “ይህ ጉዳይ እዚህ ላይ መገታት ይኖርበታል” የሚል ተነሳሽነትን በመውሰድ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ እና ተቋማዊ የሆነን መፍሄ እንዲያመጣ ያለመ መንግስታዊ ያልሆነን ተቋም ወይም መደበኛ ያልሆነን የዜጎች የውይይት መድረክ መፈጠር አለመቻሉ መፍትሄውን እውን ለማድረግ የሚከድበትን ርቀት ጠቋሚ ነው፡፡ በተለይ ሚዲያው ሊጫወት የሚችለውን ሚና በሚገባ እንዳይጫወት መሸበቡ የራሱ የሆነ ሰፊ አሉታዊ ተፅዕኖን መጫወቱ አልቀረም፡፡
በመንጋ ሚመሩ – “ሰዎች በጎች፣ ቴሌቪዥን እረኛቸው ነው”
ታዋቂዋ ደራሲ ጄሲ ስኮት በመንጋ የሚመሩ እና የማያገናዝቡ ሰዎችን በተመለከተ “People are sheep. TV is the shepherd.” (ሰዎች በጎች፣ ቴሌቪዥን እረኛ ነው፡፡) የሚልን መከራከሪያ ያወሳቸው የተነገራቸውን (ከቲቪ ይሁን ከሌላ ግለሰብ) በማድመጥ ብቻ ለደቦ ፍርድ የሚጣደፉትን ወገኖች ለመግለፅ ነበር፡፡ ይህ አይነቱ የመንጋ ኢፍትሃዊ እርምጃ ለዘገባ ለድሬደዋ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ጋዜጠኞችን እና ሹፌሮችን ጨምሮ የብዙዎችን ጓዳ እየዳሰሰ ነው፡፡ እንግሊዛዊው ፈላስፋ፣ የስነ አምክንዮ ሊቁ እና ሃያሲው በርትራንድ ረስል የጋርዮሽ ፍርሃት የመንጋዊ ስሜትን ይቀሰቅሳል፡፡ የመንጋው አባል ያልሆኑ ወገኖች ላይም ጭካኔዊ ድርጊት እንዲፈጠርባቸው ያደርጋል የሚል ሐሳብን ያንጸባረቀ ቢሆን በአገራችን አንዳንድ ቦታዎች የተወሰዱት የደቦ የድንጋይ ውርጅብኖች ተጠቂዎቹ የመንጋው ወይም የጥቃቱ አድራሾችን ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆኑም እንኳ ‹‹ተከፍሏዋችሁ ለስለላ ነው የመጣችሁት›› በሚል በጭራሽ ያልተጨበጠ ፍረጃ የከፋ ጥቃት እንደደረሰባቸው ሲታወስ ምን ያህል መንጋዊ እርምጃው ፈሩን እንደሳተ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ቻርልስ ማኬይ Memoirs of Extraordinary Popular Delusions” በተሰኘው ሥራው በመንጋ እሳቤ (Herd Mentality) የሚመሩ ሰዎች በደቦ ያብዳሉ የሚሰሩትን አያውቅም ወደ ትክክለኛ ማንነታቸው የሚመለሱትም ከመንጋው ተነጥለው ብቻቸውን የተከሰተውን ነገር ሲያስቡ ብቻ ነው ሲል የደቦ እብደቱ መቆሚያን ይጠቁማል፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን የደቦ ዕብደቱ ከሰኣታት በኋላ ቢያበቃም መተኪያ የሌለው ሕይወት መቀጠፉ ነው፡፡ ለዚህ ፁሁፍ ግብዓት ይውል ዘንድ በደቦ ፍርድ (Mob Justice) ዙሪያ ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረጉ ጥናቶች ባፈላልግም ከሰፊ ዘገባዎች እና መጣጥፎች ባሻገር የመነሻ ጥናት እንኳ ለማግኘት አልቻልኩም፡፡ በመሆኑም Impacts of Mob [In]Justice on the Rule of Law in Ghana የተሰኘውን በጋና በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ የተከናወነ ጥናት የማየት ዕድል ገጥሞኛል፡፡ በዚሁ ጥናት መሰረት ለመንጋ ኢፍትሃዊ ተግባር የሚያነሳሱ ነገሮች ያልተጠበቀ ውድቀት፣ የህዝቦች በመንግስት የፍትሕ እና የህግ ተቋማት መተማመን ማጣት፣ የመንጋው ሃይል ጉልበት ማግኘት ዋንኛቹ ስለመሆኑ ያወሳል፡፡ ይህ ድምዳሜ በተወሰነ ደረጃም በአገራችን ለሚስተዋለው የመንጋ ፍትህ መነሻ ሊሆን ቢችልም አገራችን የተለየ ገፅታ ያላት እንደመሆኑ ይህንኑ ልዩ ገፅታ ከግንዛቤ ያስገባ ሰፊ ጥናት ማከናወን የመፍትሄ ሐሳቦችን ለማመንጨት የሚመለከታቸው አካላት ትልቁ የቤት ሥራ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡
የሁኔታውን አሳሳቢነት ከግንዛቤ በማስገባት በተለይ ድርጊቱ እየሰፋ እንጂ እየቀነሰ ባለመሄዱ ይህንን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርኣት የመሸጋገሪያ ወቅት ወዳላስፈላጊ እልቂት ከማምራት ለመታደግ እና ከምንም በላይ የንፁሃንን ሕይወት ለመታደግ በተለይም የማንነት (የብሄር) ፖለቲካውን እንዲጦዝ በማድረግ መንጋውን መሾፈሩ ቀላል ስለሚያደርገው ቢያንስ ዜጎችን በየትኛውም ክልል ተዘዋውረው የመኖር መብታቸውን በላቀ ደረጃ የሚያስከብር እና እዚህም እዚያም የሚታየውን የደቦ ጭፍጨፋ ለማስታገስ አማራጭ የህግ ማዕቀፍ እውን መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህም የህግ ማዕቀፍ ዋና ትኩረቱ ተጠያቂነትን በግልፅ ለማስፈን እንጂ ከቦታ ቦታ መዘዋወሩ ሕገ መንግስቱ ላይ መስፈሩ ጥፍቶኝ አይደለም፡፡ በተለይ በሕግ ብቻ ይህንን ድርጊት መግታቱ አዳጋች እንደመሆኑ መጠን በተለይ የእምነት ተቋማት አባቶች ሆነ ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በዚህ አስጸያፊ ከሰውነት በወጣ አረመኔያዊ ድርጊት ዙሪያ ከወጣቱ ጋ መምከር ይጠበቅባቸዋል፡፡
የዜጎችን ደህንነት አለማስከበር ወደለየለት ሁከት እና ብጥብጥ ዜጎች ያመሩ ዘንድ የሚጋብዝ በመሆኑ በተለይም በሠላም ውሎ ቤት መግባቱ ቀዳሚው የሰው ልጅ ፍላጎት እንደመሆኑ የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ ማሻሻያ ግቡን እንዲመታ እና አገሪቷን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ዜጎች ከመንጋ ፍርድ ተጠብቀው ኑሮዋቸውን በአግባቡ እንዲገፉ ማድረጉ ለነገ ቀጠሮ ሊሰጠው የማይገባ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ተረድቶ ለተግባራዊነቱ ከወዲሁ ተግቶ መስራትን ይጠይቃል፡፡
Filed in: Amharic