>
4:27 am - Friday February 3, 2023

ወይ ሞንጆሪኖ  ?!? (ካሳ አንበሳው)

ወይ ሞንጆሪኖ  ?!?
ካሳ አንበሳው
መቀሌ መሽጓል የሚባለውን ቡድን “ጸረ ለውጥ” ብለህ የምታስበው አንተ ነህ፤ 
እሱን ብትጠይቀው “ኢትዮጵያን ለማዳን ነው” ብሎ ነው የሚመልስልህ….
የጁልየስ ኔሬሬ ጦር ወደ ካምፓላ ሲገሰግስ ኢዲ አሚን ዳዳ (big daddy) እግሬ አውጭኝ ብሎ ወደ ሳውዲ ፈረጠጠ፤ ከወራቶች በኋላ ወደ ዩጋንዳ ካልተመልሰክ ብሎ ለያዥ ለገናዥ አስቸገረ፤ “ለምን?” ቢሉት ህዝቤ ድርሰልን፤ አሁን ከገባንበት አዘቅት አውጣን እያለ ነው” ሲል መለሰ፤ ይህን በሚልበት ወቅት ድፍን የዩጋንዳ ህዝብ ቂጡን በካልቾ እየጠለዘ ደስታውን በመግለጽ ላይ ነበር፤
የመካከለኛው አፍሪካ ሪፕብሊክ አንባገነን ቦካሳ ለስራ ጉብኝት እንደወጣ በመፈንቅለ መንግስት ተወገደ፤ ስልጣን ላይ የወጣው ቡድን ችሎት ዘርግቶ በሌለበት የሞት ፍርድ አከናነበው፤ ህዝቡ በደስታ ጮቤ ረገጠ፤ ቦካሳ ይህን ሁሉ እየሰማ በጥገኝነት ከሚኖርበት ፈረንሳይ ወደ ሀገሬ ካልተመለስኩ ብሎ አስቸገረ፤ ወዳጅ ዘመድ ከለከለው፤ አንድ ቀን እዚህ ሄድኩ ሳይል ተንስቶ አውሮፕላን ተሳፈረ፤ የአውሮፕላኑ መዳረሻ ባንጉኢ ነበርና ከአውሮፕላኑ እንደወረደ ካቴና ጠለቀለት፤ ቤተመንግስት ሊገባ የተመለሰው ቦካሳ ወደ እስር ቤት ተወረወረ፤
 “የሊቢያን ህዝብ ከጨረሳችው በኋላ ነው እኔን ይምታገኙት፤ ህዝቤ ለኔ ይሞታል” ይል ነበር ሙአመር ጋዳፊ ይሞትልኛል ባለው ህዝብ ተገደለ፤
የአንባገነኖች በባህሪ አንድ ናቸው፤ መጀመሪያ የራሳቸውን አለም ይፈጥራሉ፤ ከሌላው ህዝብ የተለየ ትንሽ አለም፤ የሚመላለሱት በዛች ትንሽ አለም ነው፤ ህዝቡን አያውቁትም፤ እውነት እኛ ጋር ነች ብለው ያምናሉ፤ ሰማይን እንደ ምሰሶ ደግፈው እንዳቆሙ ይሰማቸዋል፤ ስልጣን ከለቀቁ ሰማይ እንደሚደፋ ምድር እንደምትጠቀለል ያምናሉ፤ ሊያሳምኑም ይሞክራሉ፤ ህወሓት እያደረገ ያለው ከአንባገነን የማይጠበቅ አይደለም፤
——————————
ባለፈው ትግራይ ኦን፟-ላይን የኢትዮጵያ ህዝብ እና ጠ/ሚ አብይ አህመድ ሆድ እና ጀርባ ሁነዋል የሚል ጽሑፍ አስነብቦ ነበር፤ ምክንያቱን ሲዘረዝር (1) የታላቁን መሪ (መለስ ዜናዊ) ስም በንግግራቸው ውስጥ ባለመጠቀማቸው (2) “ብሔር ብሔረስብ” የሚለውን ሀረግ ጠርተውት ባለማወቃቸው (3) አሻባሪዎችን “አሸባሪ” ብለው ለመጥራት ባለመድፈራቸው (4) ስለ ህዳሴው ግድብ አለማንሳታቸው …….እያለ ይቀጥላል፤ ይህ ጽሑፍ ሌላ ድረ-ገጽ ላይ ወጥቶ ቢሆን እንደ ሽርደዳ (ሾርኔ) ተደርጎ ይወሰድ ነበር፤ ጽሑፉ ላንተ ፌዝ ቢመስልህም ለጻፈው ግን “እውነት” ነው፤
ኤሳዋን የሚባለው የአላሙዲን ፌደሬሽን የመጨረሻው ዝግጅት ላይ የVOA ጋዜጠኛ አንዱን ጺላ መጠይቅ አድርጎለት ነበር፤ “ምነው ሰው የለምሳ?” ብሎ ጠየቀው፤ “ባለኮከቡ ባንዲራ ባለመኖሩ ነው” ሲል በቁጭት መለሰለት፤ ከልቡ የሚያምነውን ተናገረ፤ ዛሬ ሞንጆሪኖ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተመልሶ ቦታውን ካልያዘ ሀገሪቷ ያበቃላታል አለች፤ ይህም ለሞንጆሪኖ እና ለሌሎች እውነት ነው፤ መቀሌ መሽጓል የሚባለውን ቡድን “ጸረ ለውጥ” ብለህ የምታስበው አንተ ነህ፤ እሱን ብትጠይቀው “ኢትዮጵያን ለማዳን ነው” ብሎ ነው የሚመልስልህ፤ የህወሓት ነውረኞች እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ያበቃላታል የሚለውን ትርክት ለኦባማ ጭምር ሳይነግሩት የቀረ አይመስለኝም፤ ኦባማ በአፍሪካ ህብረት ባደረገው ንግግር እንዲህ ብሎ ነበር”
sometimes you’ll hear leaders say, well, I’m the only person who can hold this nation together.  If that’s true, then that leader has failed to truly build their nation
እንደኔ እንደኔ ሰዎቹ ታስረው የማስላሰያ ጊዜ ቢያገኙ ጥሩ ነው፤
Filed in: Amharic